Tuesday, August 12, 2014

የስድብ ሱስ


አጋንንት የሰውን ልጅ ከሕጻንነቱ ጀምረው በመቆራኜት ጠላትነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ የሚቆራኙባቸው መንገዶች በጣም ብዙ በመሆናቸው በዚህ ርእስ ውስጥ አንዱን ብቻ እንመለከታለን፡፡በዚህ ዘመን ሕጻናት አፍ የሚፈቱት በስድብ ነው፡፡ ወላጆቻቸውም ያንኑ በማስተማር ያሳድጓቸዋል፡፡ ከሕጻንነታቸው ጀምሮ የተቆራኜ የስድብ ጋኔን ከፍ ቢሉም ጾምና ጸሎት የማያበዙ ከሆነ ስለማይወጣ ያገኙትን ሁሉ በስድብ መዝለፋቸው አይቀርም፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ስለሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ “እግዚአብሔር ይገስጽህ” ከማለት ውጭ ሌላ የስድብ ቃል እንዳልተናገረ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፡፡ይሁ9 ዓይናቸውን የታወሩ ሰነፎች ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስን ያልሰደበው ስለፈራው ወይም ከዲያብሎስ ስለሚያንስ ይመስላቸዋል፡፡እንደዚህ አይምሰላችሁ ምስጋና ምግባቸው፣ ምግባቸው ምስጋና የሆኑ መላእክት የሚሳደቡበት አንደበት ስለሌላቸው እንጅ ከቅዱስ ሚካኤል የገነነ ቅዱስ መልአክ ከዲያብሎስም ያነሰ ርኩስ መንፈስ የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስድብን የትልቅነትና የማሸነፍ ምልክት የሚያደርግ የዲያብሎስ ልጅ እንጅ የእግዚአብሔር ልጅ መገለጫ አይደለም፡፡  ምክንያቱም ስድብ የትዕቢተኛው ምስጋና የማያውቀው አእምሮ የተለየው የውሸት አባት ለሆነው ዲያብሎስ ስለሆነ፡፡ ዛሬ ግን እኛ የሚያንሱንንም የሚልቁንንም በስድብ ማዕበል እንገፋቸዋለን፡፡ በእርግጥ ዲያብሎስ በስድብ የተቆራኘው ሰው የስድብ ሱስ ስለሚይዘው ለመስደብ አፉን ያፈጥናል፡፡ ታዲያ ይህ ተሳዳቢ ሰው ቅዱስ ሚካኤልን ይበልጠዋልን? የሚሰድበውስ የከበረ የሰው  ልጅ ከወደቀው ዲያብሎስ ያንሳልን? እንደዚህስ አይደለም፡፡ ተሳዳቢው በስድብ ሱስ ስለተያዘ ግብሩ ከዲያብሎስ ያነሰ ያደርገዋል እንጅ፡፡ የስድብ ሱስ ያለበት ሰው ሲሰድብ መሳደቡን እንጅ የሚሰድበው ማን እንደሆነ አያውቅም፡፡ ሲሰርቅ ያገኘውን “የሌባ ልጅ”፣ ሲዋሽ ያገኘውን “የውሸታም ልጅ” ወዘተ… በማለት የስድብ ሱሱን ያረካል፡፡ በውኑ ችግሩ ያለባቸው ወላጆች ናቸው እንዴ? ሲሰርቁ፣ ሲዋሹ ወዘተ…  የተገኙ ልጆች ናቸው ታዲያ የወላጆች መሰደብ ምኑ ላይ ነው? እኔ የሚመስለኝ ይህ የስድብ ጋኔን የተቆራኘው ሰው ችግር ያለባቸውን ልጆች የሰደብኩ መስሎት “የእንዲህ ልጅ” በማለት ሱሱን ለማርካት የወሰደው ሰይጣናዊ ርምጃ ነው፡፡ የስድብ ሱስ ከባድ ነው፡፡ የሚሰድቡት ሰው ቢጠፋ እንኳ ድንጋዩን ያሰድባል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ፈጣሪውንና ማደሪያውን አስከመስደብ ያደርሳል፡፡ አንድ የስድብ ሱስ ያለበት አባት በትምህርት የደከመ ልጁን “የአህያ ልጅ” ብሎ ይሰድበዋል፡፡ እስኪ ፍረዱ በዚህ ስድብ ውስጥ አህያው ማነው? ራሱ ተሳዳቢው አይደለምን? ልጁ ይህን ስድብ ይቀበል ስለነበር “አባዬ የአህያ ልጅ ስትል እኮ እኔ ውርንጭላ አንተ ደግሞ እናት አህያ ነን ማለትህ ነው” በማለት አባቱን አስተማረው፡፡ ወንድሜ ሆይ በእውነት ክርስቲያን ከሆንክ ስድብን ከአንተ አርቃት ገንዘብህ አይደለችምና፡፡ አንተ ከመልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል አትበልጥም የምትሰድበው የሰው ልጅም ከረከሰው ዲያብሎስ አያንስም፡፡ ተሳዳቢ በመሆንህ ትልቅነት አይሰማህ በጣም ትንሽ ከሚባሉት አንዱ ሆነሃልና፡፡ ያገኘኸውን ሁሉ በስድብ የምትዘልፍ አንተ በሱስ እንዳበድክ በመረዳት ከእብደትህ ልትመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጭ ዛፍ ቅጠሉን፣ ወፍ አራዊቱን፣ ድንጋይ አፈሩን፣ ሰማይ ምድሩን፣ አየር ነፋሱን፣ ትንሽ ትልቁን፣ የሰው ልጆችን ሁሉ በመስደብ “ተሳዳቢ”  የሚል መታወቂያ እስኪሰጥህ ድረስ መጠበቅ የለብህም፡፡ የስድብ ሱስ አልለቅ ካለህ ራስህን ስደብ፡፡ ራስህን ከሰደብክ ማንነትህን ስለምትረዳ በጽድቅ ለመነሣት ጊዜ አይወስድብህም፡፡ ስለዚህ የስድብ አጋንንትን በጾም፣ በጸሎት ድል በማድረግ ከስድብ ሱስ ልንላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ከሕጻንነታቸው ጀምረው ስድብ እንዳይለምዱ መቆጣጠር አለባቸው፡፡ ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ሸኝቶ ሲመለስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ  ኢያሪኮ በደረሰ ጊዜ ራሱ ጸጉር ስላልነበረው “እርግ በራህ! እርግ በራህ!” ብለው የሰደቡትን 42 ሕጻናት በ2 ድቦች እንዳስፈጃቸው እኛም መቅሰፍት እንዳይመጣብን ስድብን ገንዘብ ልናደርጋት አይገባንም፡፡“መራራነትና ንዴት ቁጣም፣ጩኸትም፣ መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ፡፡”ኤፌ4፥31

No comments:

Post a Comment