Sunday, August 10, 2014

ማንነቱ ያልገባው ትውልድ


ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ?
እንዴት ከረማችሁ እንዴትስ ዋላችሁ?
እንዴት አደራችሁ እንደምን አላችሁ?
ለነገሩለእናንተ የማቀርበው ሰላምታ፣
ሆኖባችሁ ጨዋታ አለን ነው የምትሉኝ በእርጋታ፡፡
ለመሆኑ ማን አኖረህ?
እስካሁንስ ማን አቆየህ?
በኃይልህ ነው እንዴ የምትኖረው?
ወይስ በምግብ ብቻ ነው ያለኸው?
በእርግጥአንተ ከበላህ ከጠጣህ ከተነፈስህ፣
በቃ! አለሁ!” ትላለህ እንደፈለግህ፡፡
ኧረ ስማ ወገኔ! ይህ ነው ወይ መኖር ይህ ነው ወይ ማለት?
አለሁ!”  የምትል በድፍረት፡፡
በዝናብ አብቅሎ በነፋስ አሳድጎ በፀሐይ አብስሎ ይመግብሃል፣
ሲበርድህም ያሞቅሃል፣
ሙቀት እንዳይጎዳህ ቀዝቃዛ አየራትን ለግሶሃል፡፡
ስትበድለውም ይምርሃል፣
ይባስ ብሎ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ይወድሃል፣
ለመሆኑ ላንተ ምንድን ነው ያጎደለው?
አለሁ!” ብቻ የምትለው፡፡
አንተ ተራ! አንተ ከንቱ!
አመስግን እግዚአብሔርን ስለቸርነቱ፡፡
እንደምን ዋልክ፣እንዴት አደርክ፣እንዴት ከረምክ ሲሉህ አለሁ!” አትበል፣
እግዚአብሔር ይመስገን በል፡፡
ቆይ እስኪ…! በቸርነቱ ያኖረህን ብታመሰግነው፣
ኃፍረቱ ምኑ ጋር ነው?
ሁሉን ሲሰጠን ሲያደርግልን፣
እኛ ሁልጊዜ አለን!” ብቻ ለምን እንላለን?
እግዚአብሔር ይመስገን እንዳንል ማነው አዚም የጣለብን?
ለነገሩ…! ዝሙት ርኩሰት መዳራት፣
ጣዖት ማምለክ ምዋርተኝነት፣
ጥል ክርክር ቅንዓት፣
ቁጣ አድመኛነት፣
መለያየት መግደል መናፍቅነት፣
ምቀኝነት ስካር ዘፋኝነት፣
ይህን የመሰለ ነው ግብርህ፣
የሁልጊዜ ተግባርህ፣
ታዲያ! የትኛው አንደበትህ፣
እግዚአብሔር ይመስገን ይበልልህ፡፡
አንተ ከንቱ! ዕድሜህ እንደ አበባ ታይቶ የሚጠፋ፣
ምግባርህ እጅጉን መራራ የከፋ፣
መሆኑን ብታውቀው፣
ፈጣሪህን ባወቅኸው፡፡
አንተ እኮ! ማን ፈጠረህ ሲሉህ እናትና አባቴ፣
ማን አኖረህ ሲሉህ ጽድቅ ደግነቴ፡፡
የሚለው ነው መልስህ፣
ማንም ሲጠይቅህ፡፡
ግሩም ነው…! በጣም የሚገርም፣
የሚያስደንቅ የሚያስደምም፡፡
ታችህ ጣዖት፣
ላይህ ታቦት፡፡
አፍህ ቅቤ፣
ልብህ ጩቤ፡፡
በብርሃን ቤተክርስቲያን፣
በምሽት ከጠንቅ ዋይ ቤት፡፡
በጨለማ ቤት ሰርሳሪ፣
ሲነጋጋ ሥራ ሠሪ፡፡
ብቻያንተ ነገር! የተደባለቀ የተጨማለቀ፣
የተመሳቀለ የተቀላቀለ፡፡
ኧረ ሰው ጠፋ! ደግ ሰው አለቀ፣
ለጠንቅ ዋይ ተገዛ ለጣዖት ሰገደ፡፡
የአጋንንትን ጽዋዕ ከእግዚአብሔር ጋር ቀላቀለ፡፡
በውኑ! እግዚአብሔር ማዳን አልችል አለን?
ከጠንቅ ዋይ ከአጉሪ ከመተተኛ ዘንድ መሄዳችን፣
ገና! የሕመም ምልክቱ ሲታየን የሕመም ስሜቱ ሲሰማን፡፡
ኧረ! ሌላም አለ! ምቀኝነት ጎለቶብን፣
እገሌን ግደልልኝ እገሊትን ድሃ አድርግልኝ፣
እገሌን አሳብደው እገሌን ጨርቅ አስጥለው
እያልን ለጠንቅ ዋይ የምንሰግደው ለምንድን ነው?
የእኛስ ጥቅም ምኑ ጋር ነው?
አንተ ጠንቅ ዋይ መተተኛ በዚህ ደባ፣
ወዮልህ ወዴት ይሆን የምትገባ?
አምላክ በግርማው ሲመጣ፣
ከየት ይሆን ያንተስ ዕጣ?
አልሰማህም እንዴ? የጠንቅ ዋዩን የመጥቁልን ታሪክ፣
ድንግል ማርያምን በስረዩ አጠፋለሁ ብሎ ሲደፍር፣
የደረሰበትን የመከራ ክምር፡፡
የአጋንንት ሥልጣን ስለማይበልጥ ከእግዚአብሔር፣
መጥቁል ተዋጠ በዚች ምድር፡፡
ይህን ባወቅህ ጠንቅ ዋይ ባልሆንህ፣
ማንነትህን በተረዳህ፡፡
ነገሩማ! ትዕቢትህስ መቼ ያልቃል?
አእምሮህስ መቼ ያስተውላል?
ልብህስ መቼ ያስባል?
ታዲያ! ካሰብክ ፈርዖንን አስበው ናቡከደነጾርን ልብ በለው፡፡
ትዕቢታቸው ወዴት ገባ እነርሱስ የት ደረሱ?
እሽ! እንቀጥል ይህ ነው መልሱ፣
ፈርዖን በትዕቢት ልቡ ቢደነድን፣
አልለቃቸውም ቢል እስራኤላውያንን፣
አልተሻገራትም ባሕረ ኤርትራን፡፡
ሰጥሞ ነው የቀረው ከነሠራዊቱ ፈርዖን በትዕቢቱ፡፡
ሌላስ! ናቡከደነጾር ቢነሣ በትዕቢት፣
ቢሰግድ ቢንበረከክ ለሰው ሠራሽ ጣዖት፣
ሣር ጋጠ እኮ እንደ ከብት ለሰባት ዓመታት፡፡
ታዲያ! የእኛ ትዕቢት በባሕር ሰጥሞ ለመቅረት፣
ወይስ ሣር ለመጋጥ እንደ ከብት?
እባክህ ወገኔ! አድምጠኝ እባክህ፣
ጥንቆላው ይቅርብህ፡፡
ሥር መማሱ ቅጠል መበጠሱ አያጓጓህ፣
ትዕቢት ድፍረት አይሰማህ፣
ትሕትና ነው የሚያዋጣህ፡፡
ኧረ ስማኝ ወገኔ! ላስተምርህ፣
ለነገሩ…! ከኔ በላይ ማን አለ?
እንደእኔ አዋቂ እንደእኔ ጠቢብ የት ይገኛል?
ነው የምትል፡፡ ለመሆኑ…!
ፊደል ቆጥረሃል? ዳዊትን ደግመሃል?
መጻሕፍትን አንብበሃል?
ውሸት! ኧረ ባዶ ደንቆሮ ነን፣
ባዶ ሆነን ሁሉ ያለን የሚመስለን፡፡
ታዲያ…! ዛሬ ኢትዮጵያዊ መለያ ፊደላችንን ሊቀንሱ፣
አላዋቂዎች ሲነሱ፣
ፊደላችን በዝቷል! አንዱ ይብቃን ሲሉህ፣
አዎ ትላለህ አብረህ ልዩነታቸው ስላልገባህ፣
ትርጉማቸውን ስላላወቅህ፡፡
ታዲያ…! የቱ ነው ትምህርቱ?
አውቄያለሁ ነቅቻለሁ ማለቱ፡፡
ኧረ ተነሣ ወገኔ! ግዕዝ ሞተልህ!
ሀገራዊ ትልቅ ሀብትህ፡፡
በባዕድ ቋንቋ ከንፈርህን ስታጣምም፣
የአንተ የሆነውን ንጹሕ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ቀበርከው፣
ዳግም እንዳይነሣ ልታደርገው፡፡
አቤት ኃፍረት! አቤት ውርደት!
ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርን፣
ለግዕዝ ቋንቋ ባዕድ መሆን፡፡
! ያማረው የተዋበው የቅኔ መፍለቂያ፣
የመጻሕፍት መጻፊያ የአዳም ቋንቋ መግባቢያ፣
ሞተ ሲባል በይፋ ዛሬም አለሁ!” እያልክ ልትደነፋ?
በባዶው ሳናውቅ አወቅን እያልን፣
አስጠፋነው ግዕዝ ሐብታችንን፡፡
አንተ በውኑ ኢትዮጵያዊ ነህ፣
ወይስደግሞ የሌላ ነህ?
ለግዕዝ ቋንቋ ባዕድ የሆንህ፡፡
ለፊደላችን የሌለህ ፍቅር ሲቀነሱ ያላለህ ቅር፡፡
የራስህን ወዲያ ጥለህ በሌሎቹ ተገንዘህ፣
አእምሮህን መርዘህ በከንቱነት ትኖራለህ፣
የእናት የአባትህን አደራ ዘንግተህ፡፡
በዓለማዊ ፍልስፍና በሥጋዊ ብልጽግና፣
ገነት መግባት ከተቻለ እስክንድርን ጠይቀው፣
ማን እንዳባረረው?
በእውነት አሁን…! የእኛ ሥጋዊ ፍልስፍና፣
ዕድሜ ያስጨምራል ወይስ ጤና?
ከንቱ! ብቻ ሁሉም ከንቱ!
ኧረ ተማር ወገኔ! አላወቅህም!
አዋቂ ብትሆንማ ኢትዮጵያን ባወቅህ፣
የምትኖርባትን አገር ታሪኳን በመረመርህ፣
እንደእንስሳት ስትመስል አለባበስህ ሲከፋ፣
ዕርቃነ ሥጋህ ሲታይ በይፋ፣
የለበስክ የሚመስልህ አውቃለሁ!” አትበለኝ አላዋቂ ነህ፣
አንተ ራስህ አላዋቂነትህን ታውቃለህ፣
ልትቀልድ ነው አውቃለሁ!”  ማለትህ፡፡
አንቺ የሔዋን ልጅ! ስሚኝ እህቴ፣
አድምጭኝ ዛሬን ብቻ በሞቴ፣
ልብስሽ አጠረች ተቀደደች፡፡
አለባበስሽ ተቀየረ ወደ ባዕድ አገር ተሻገረ፡፡
ፀሐይ አይምታው አይቃጠል ሰውነትሽ፣
አልብሽው ሞልቷል ጥሩ አልባሽ፣
አንቺ መልበሻ ካጣሽ፡፡
ያንቺ ሱሪ ያንቺ ቁምጣ፣
ኧረ እህቴ ከየት መጣ?
ያን ረዥም ቀሚስ ወዴት ጣልሽው?
የት ቀበርሽው የት ደበቅሽው?
አንቺ ጉደኛ በይ ስሚኛ!
መልሽልኝ ዝም አትበይኝ!
እሽ በቃ…!
ሱሪ ወይስ ቁምጣ ወይስ ቀሚስ ያሳየችሽ?
ያቺ  ምስኪን ደግ እናትሽ፡፡
ታዲያ…! ከየት አመጣሽው ይህን ቆራጣ ቁምጣሽን፣
ያጋለጠ ዕርቃነ ሥጋሽን፡፡
ኧረ አስተውይ ተመለሽ!
የእናትሽን ልብስ ልበሽ፣
ስለሆነ ውብ ባሕልሽ ስትለብሽውም የሚያምርብሽ፡፡
ነገሩ እኮ በጣም ያሳዝናል! ያስለቅሳል ያበሳጫል፣
ማንነታችን ጠፍቶብናል፣
አኲሱምን ቀርጾ ያቆመውን፣
ፍልፍል ዋሻ ላሊበላ ያነጸውን፣
አጠፋነው ከአእምሯችን፣
ያንን ጀግና ያን ገናና ያኮራንን፣
ክብር ሞገስ ያደለንን፡፡
በጸሎቱ በእምነቱ በብርታቱ በትዕግስቱ፣
ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት፣
አድርጎ ኢትዮጵያን የጠበቃት ጀግና ሕዝብ!
ልጅ መስለነው ለእኛ ቢሰጥ፣
ከፋፈልናት በቋንቋ በሰፈር በጎጥ፡፡
በውኑ አንተ አገርህን ትወዳለህ?
ሕዝቦቿንስ ታከብራለህ ለባሕሏስ ትገዛለህ?
በቋንቋዋስ ታወራለህ?
እስኪ ስማ! የአባቶች ደም ዕዳ አለብን፣
የማንጨርሰው ሁሌም ከፍለን፣
ለባዕድ አገር ባሕል እንዳትገዛ ቢገዝቷት፣
አቡነ ጴጥሮስ ተገደሉ በፋሽስት ጥይት
ደማቸውም ፈሰሰ ከመሬት፡፡
ታዲያ! እርሳቸውን ብርቅዬ አባት ለገደለ እጅ ትሰጣለህ?
ተላላ፣ ሞኝ! ቂል እንዴት ትሆናለህ?
ልጅ ሲያደርጉህ እንዴት ባርነትን ትመርጣለህ?
ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንዴት ሊለውጠው ቻለ?
ኢትዮጵያዊስ በባዕድ መርዝ ባሕል እንዴት ተታለለ?
አንተ! የእመ ብርሃንን የአሥራት አገር አስደፈርካት፣
አንተ ደካማ ግዴለሽ ከንቱ ፍጥረት፡፡
ሳይወጉህ ተሸንፈህ ሳይማርኩህ ተማርከህ፣
ለባዕድ ባሕል ባሪያ ሆነህ መኖር መስሎህ ትኖራለህ፡፡
አቡነ ተክለሐይማኖት ዞረው የባረኳት፣
ገነትን የሚያጠጣ የግዮን ባለቤት፣
በረከትን ያልነፈጋት ፈጣሪ አምላክ የጠበቃት፣
ኢትዮጵያ እኮ ድንቅ አገር ናት፡፡
እኛ ግን! ድንበሮቿን አፍርሰን ባሕላችንን ቀይረን፣
ሥማችን ኢትዮጵያዊ ሥራችን አውሮፓዊ፣
ፊታችን ሀገራዊ ልቡናችን ባዕዳዊ፣
የሆነብን አእምሯችን የዞረብን፣
እጅግ በጣም ብዙዎች ነን፡፡
አይ እማማ…! የወላድ መካን አደረግንሽ፣
ተደፈረ ! የባሕል የእምነት ድንበርሽ፣
ጠብቁኝ ልጆቼ አደራ” እያልሽ፣
ድንግል ማርያምን በእንግድነት ተቀብለሽ፣
ያለሽን አሰናድተሸ ድግስሽን ደግሰሽ፣
በረከትን ተቀብለሽ ስትኖሪ እኛን ወለደ ማኅፀንሽ፣
አሳልፈንም ሰጠንሽ፡፡
መቼም…! ላናብስ እንባሽን፣
ያንችን ሥራ ዘንግተን፡፡
አስለቀስንሽ አሳዘንሽ፣
ንፉጋን ልጆች ሆነንብሽ፣
እንግዳ መቀበልን ጠልተንብሽ፣
አንቺ ግን አሁንም እንዲህ እያልሽ ትመክሪያለሽ፣
ሎጥ እንግዳ መቀበልን ልማድ ቢያደርግ፣
መላእክትን መቀበሉን ልብ እናድርግ፣
አብርሃም ለእንግዶቹ ክብር መስጠቱ፣
ሥላሴን ተቀበለ በቤቱ፡፡
ታዲያ…! ምን ተጎዱ እነ ሎጥ እነ አብርሃም እንግዳ መቀበልን የጠላነው?
ከቅዱሳኑ ያልተማርነው?
ለነገሩ…! ታሪክህን ስለማታውቅ ማን ይፈርዳል?
ማንስ ምን ብሎ ይወቅስሃል?
ኧረ ንቃ እባክህ!
ዛሬ የመኝታ ጊዜ አይደለም ተደፍረሃል ተወርረሃል፣
የማንነትህ አሻራ ጠፍቶብሃል፡፡
አይ አንቺ ምድር!
ስንቱን መከራ ተቀበልሽ ስንቱን ሰቆቃ አየሽ፣
ስንቱን ክፉና ደግ በላሽ ስንቱን መጥፎና ጥሩ ቀበርሽ፡፡
አብርሃምን የዋጠ አፍሽ ይሁዳን ዋጠ፣
የናቡቴን ደም የጠጣ አፍሽ የኤልዛቤልን ደም ጠጣ፡፡
ስንቱ ይዘረዘራል መዘርዘርስ ማን ይችላል?
ኧረ ስማኝ! አንተ ጠማማ የማታስተውል ያንቀላፋህ፣
የማን ልጅ ነኝ ትላለህ?
የሚኒልክ ነኝ አትለኝ አገርህን አስደፍረሃል፣
በባዕድ እጅ ተማርከሃል፣
የአቡነ ጴጥሮስም ልጅ ነኝ አትል፣
እርሳቸው የገዘቷትን አንተ ፈትተሃታል፣
ለባዕድ ባሕል እንዳትገዛ ቢሞቱላት፣
አንተ ለአውሮፓውያን ተገዝተህ ሙት ሆንክባት፡፡
የአቡነ ተክለሐይማኖት ልጅ እንዳልልህ፣
የት አለ ቅድስናህ በረከት ማግኘት ማስገኘትህ?
ብኩርና እምነትህን በምሥር ወጥ በድቃቂ ሳንቲም የምትለውጥ፣
ተረፈ ኤሳው እምነትህን ከምንም የማትቆጥረው፡፡
የቅዱሳን መገኛ ኢትዮጵያን የኃጥአን መፈንጫ፣
የባዕዳን መሮጫ የሰይጣን ማላገጫ፣
አደረግሃት! አንተ ከንቱ ፍጥረት፡፡
ታዲያ…! የማን ልጅ ነህ ኧረ ንገረኝ ልጠይቅህ?
አባቱን የገደለው እናቱን ያገባው፣
አምላኩን የሸጠው የዚያ! የይሁዳ ልጅ ነህን?
ወይስ! እምነት ብኩርናውን የሸጠው የኤሳው?
ልክ ነው! ይህ ያስማማል! አንተስ እናትህን ገድለህ አባትህን ሰልበህ፣
ሚስትህን ቆራርጠህ አሰቃቂ ድርጊት ፈጽመህ፣
ወንድምህን ለአውሬ ጥለህ አምላክህን በገንዘብ ለውጠህ፣
ወልደ ማርያም የተባለ ሥምህን መሐመድ” አላስባልክም?
አመተ ማርያም የተባልሽ እህቴስ ከድጃ አላስባልሽም?
የጆሮ ያለህ! ኧረ ስሙኝ! ከጊዜያችሁ ትንሽ ስጡኝ፣
ለነገሩ! ጊዜ ለእናንተ ወርቅ ነው፡፡
የፊልም ማየቻ የአረቄ የጠላ መጠጫ፣
የኳስ መጫወቻ፣
ዓይንህን አፍጥጠህ ጆሮህን አውሰህ፣
አፍህን ከፍተህ ልቡናህን ሰቅለህ፣
የምታየው የአውሮፓውያንን እርግጫ፣
የዐረባውያንን ሩጫ ነው፡፡
የእግር ኳስ ክለቦችን ሁሉ! ከነተጫዋቾች ሥም ሸምድደህ ትይዛለህ፣
ፊልም ሠሪዎችንም አንድ በአንድ ታውቃለህ፣
ስለ አንተ ግን ብጠይቅህ መልስ አለህ?
ክርስትና ሥምህን ታውቀዋለህ?
አላውቅም ነው መቼም መልስህ፡፡
ታዲያ! ራስህን ሳታውቅ ሌላ ለማወቅ ምን ያባክንሃል?
መጀመሪያ ራስህን ማወቅ ይሻልሃል ይበጅሃል፡፡
ከተራ ፍልስፍና ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይጠቅማሃል፡፡
የዘፋኝ ሥም ከመሸምደድ የዜማውን አባት አንድ ያሬድን ብታውቅ ይሻልሃል፡፡
ወደ ጠላ ቤት ከምትሮጥ ቤተክርስቲያን መገስገስ ያተርፍሃል፡፡
ለጊዜዬ ዋጋ እሰጣለሁ ትላለህ ተሰብስበህ ታወራለህ፡፡
ስትስቅ ስትቀለድ ትውላለህ፣
ታዲያ…! የምትቀልድበት ጊዜ አይደለም?
መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቢያ ጊዜ ያጣህ፣
ቤተክርስቲያን ለመሄድ የደከመህ፣
ለመጸለይ ያንቀላፋህ፡፡
ይመሻል ይነጋል፤ ይነጋል ይመሻል፣
አንተ ግን ዛሬም ተኝተሃል፡፡
ኧረ ንቃ እባክህ ይበቃሃል!
ጊዜህን በአግባቡ ተጠቀመው መቀለጃ አታድርገው፡፡
በሳቅ በጨዋታ አትጨርሰው፣
ሞት እንዳይጠራህ ማንነትህን ሳትረዳው፣
አንተነትህን ሳታውቀው፡፡
ስካር ይብቃህ ዝሙት ይቅርብህ፣
በበሽታ ትቀጣለህ በዘላለም መከራ ትወድቃለህ፣
የሲዖል እራት ትሆናለህ፡፡
ኧረ ቆይ እንጅ! ገንዘብህንስ ምን አደረግኸው?
አሥራት በኩራቱን ከፈልከው፣
ወይስ በጠላ በሲጋራ ጨረስከው?
ለቤተክርስቲያን እርዳታ ሲጠይቁህ የተራቡት ሲለምኑህ፣
ለአምስት ሣንቲም ዕቅድ አለኝ ትላለህ፣
ይባስ ብሎም ስድብ ትቀላቅላለህ፣
ነገር ግን ከጠላ ቤት ለሰከረው ሳይቀር ትከፍላለህ፣
አንተም ሰክረህ ትወድቅበታለህ፣
ለዝሙትም ትከፍላለህ፣
ታዲያ …! ዕቅድህ ተዘነጋህ፣
ለአምስት ሣንቲም ዕቅድ አለኝ ስትል መቶ፣ ሽህ ብር ማጥፋትህ፡፡
ኧረ ስማኝ ! የአዳም ልጅ ምንድኑ ነው ያስጨነቀህ?
የምትበላው የምትጠጣው ወይስ የምትለብሰው?
የሰማይ ወፎችን አታይም?
የምድር አበቦችን ልብ አትልም?
የወፎች እርሻ የወፎች ቁፋሮ አለ እንዴ?
ጠግበው ከዛፍ ዛፍ የሚበሩት በሰላም የሚኖሩት፡፡
ማን አለበሳቸው ማንስ መገባቸው?
ታዲያ ! አንተ የምትጨነቀው ፈጣሪ አይመግበኝም ብለህ ነው?
ከነፍስና ከምግብ የሚበልጥ ማነው?
ነፍስ የሰጠን ምግብ መስጠት ይሳነዋልን?
ለምግብህ ስትጨነቅ የምትውለው የምታድረው፡፡
ኧረ ተፈጥሮው በቂ ነው አስተውል፣
ያስተምራል ይመክርሃል፡፡
ተመራምረህ ድረስበት አእምሮህን ከንቱ ነገር አትሙላበት፣
ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣
እርሱም ይደግፍሃል ይላል ! ያላነበብከው መጽሐፍ፡፡
ኧረ ማነህ! ማንነትህ ተሸፍኖ፣
ኢትዮጵያዊነትህ ተከድኖ፣
በአውሮፓ ባሕል ትዋኛለህ ማንነትህ ተዘንግቶህ፡፡
ለንስሓ እንብቃ እባካችሁ ያለፈው ጊዜ ይብቃችሁ፡፡
ዛሬን ለሰጠን ፈጣሪያችን ምስጋና እናቅርብ ከልባችን፡፡
ለንስሓ ነው የጨመራት ይችን ጊዜ በእውነት፣
የእኛ ጓደኞች የት አሉ?
አልሞቱም እንዴ ምድር አልገቡም እንዴ?
ኧረ ይብቃን እባካችሁ ይች ምድር ሳትውጣችሁ፡፡
ከንፈር መምጠጡ አያዋጣም ገነትን አያወርስም፡፡
ንስሓ ነው መፍትሔያችን የገነት መክፈቻ ቁልፋችን፡፡
የታደሉት! በንስሓ ነጽተው በቅተው ሥጋና ደሙን ተቀብለው፣
የዘላለም ሕይወት አግኝተው ይኖራሉ፣
አንተ ደግሞ ዳልቻ ዶሮ ጥቁር ፍየል ..
እያልህ ጊዜህን በከንቱ ታጠፋለህ በምክረ ከይሲ ተታልለህ፡፡
የክርስቶስ አማናዊ ሥጋና ደም ተዘጋጅቶ፣
አልበላም አልጠጣም አልህ ኃጢአትህ እጅግ በዝቶ፡፡
ኧረ እባክህ ተመለስ! ጹም ጸልይ ስገድ አልቅስ፣
ንስሓ ነው መድኃኒቱ፣ ገነት መግቢያ ብልሐቱ፡፡  
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

No comments:

Post a Comment