Wednesday, August 13, 2014

አገር እና መኪና

ሰላም ለሁላችሁ ይሁንና አገር መኪና ናት ብለው አንድ ሽማግሌ ያጫወቱኝን ጨዋታ ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡ ሽማግሌው እውቀት የዘለቃቸው ዕድሜም የራቀባቸው አይነት ናቸው፡፡ ጸጉራቸው ባለሙያ ሴት ያባዘተችውን ጥጥ ይመስላል፡፡ ሲያዩዋቸው የደስደስ አለባቸው፡፡ ሲያወሩህም እንደ እግር ኳስ ደጋፊ ዓይንህን አፍጠህ ጥርስህን አግጠህ የምትመለከታቸው ናቸው፡፡ ሽማግሌው መኪና ውስጥ ከአጠገቤ ተቀምጠው ረጅሙን ጉዞ እየተጓዝን ሳለ ጉሮሯቸውን ሞረድ ሞረድ አደረጉና ለዛ ባለው አንደበታቸው “ልጄ አገርና መኪናን አነጻጽረሃቸው ታውቃለህ?” አሉኝ በመገረም አይነት ንግግር፡፡ “ኧረ በፍጹም!” አልኳቸው፡፡ “ልጄ ይህ መኪና ስንት ወንበሮች ናቸው ያሉት?” አሉኝ፡፡ ፈጠን አልኩና “አባቴ ይህ እኮ የሚታይ ነገር ነው፡፡ ለሹፌሩ አንድ ወንበር አለው ለተሳፋሪው ደግሞ ስድሳ ወንበሮች አሏቸው፡፡ በአጠቃላይ ስድሳ አንድ መሆኑ ነው” አልኳቸው፡፡ ሽማግሌው ቀጠሉ “እሽ ስንት ሰው ተቀጧል? ስንት ሰውስ ቆሟል?” አሉኝ፡፡ “የተቀመጥነው ስድሳ አንድ የቆሙት ደግሞ ሰላሳ አካባቢ ናቸው” አልኳቸው ዞር ብየ የቆሙትን በዓይኔ እየቃኘሁ፡፡ “አየህ ልጄ አገርና መኪና አንድ ሲሆኑ! እዚህ መኪና ውስጥ ተመችቶት የተቀመጠ፤ ሳይመቸው የተቀመጠ፤ ተመችቶት የቆመና ሳይመቸው የቆመ አለ፡፡ አንዳንዶች በመቆማቸው ብዙ ሲቸገሩ አታይም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ሊዝናኑ ይቆማሉ የተወሰኑትም መቀመጫው ላይ የሚያንቀላፉ አሉ፡፡ ታዲያ አገር ውስጥስ አንዱ በምቾት ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ሌሎችን ሳይመቻቸው ያስቆማቸው የለም እንዴ? ወንበሩ እኮ ለሁሉም እኩል ነበር ነገር ግን ቀድሞ የተቀመጠ ይወስደዋል፡፡ እኔና አንት ስለተቀመጥን የቆሙት የተመቻቸው ይመስለናል፡፡ በጣም ስህተት ነው! አገር ውስጥ አንዱ ጠግቦ ሲያድር ሌላውም የጠገበ የሚመስለው ለሌላው የማያስብ አለ” አሉኝ፡፡ “አባቴ ጥሩ እይታ አለዎት፡፡ ልክ ነዎት ጠቢቡ ሰሎሞን በተመቸ አስተዳደግ በማደጉ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ የተራበ ደሃ ሲለምነው ምን ሆኖ ነው ብሎ ጠየቀ፡፡ ተርቦ ነው ብለው መለሱለት ረሃብ ደግሞ ምንድን ነው? አለ፡፡ በኋላ እርሱም ሲቀምሳት ረሃብን አወቃት ይላሉ፡፡ አሁን ትዝ አለኝ ይህን ሲሉኝ” አልኳቸው፡፡ “እንዳልከው ረሃብን የማያውቅ ሰው የተራበ ሰው ያለ አይመስለውም፡፡ እንደእኔና እንደአንተ ማለት እኮ ነው፡፡ እኛ ስለተቀመጥን የቆሙትን ከምንም አልቆጠርናቸውም፡፡ አገር አንዱ ሲደሰትባት ሌላው ይከፋባታል፤ አገር አንዱ ሲሞላቀቅባት ሌላው ይሸማቀቅባታል፤ አገር አንዱ ሲቀመጥባት ሌላው ይቆምባታል፤ አገር አንዱ ሲፈነጭባት ሌላው ይታሰርባታል፤ አገር አንዱ ሲበላባት ሌላው ይራብባታል፤ አገር አንዱ በሄክታር የሚሰፈር መሬት ሲሰጥ ሌላው የሚቀበርበት ቦታ ያጣባታል፡፡ እሽ ይህ መኪና ስንት በሮች አሉት?” አሉኝ፡፡ በሮቹን ቆጠርኩና “ሦስት ነዋ!” አልኳቸው፡፡ “አየህ አይደል! ሹፌሩ ስንት ነው? አንድ አይደለምን?” አሉኝ፡፡ ለአንድ መኪና ስንት ሹፌር ሊኖረው ይችላል ብየ አሰብኩና “አንድ ነው፡፡ ተሳፋሪዎች ደግሞ ስድሳ የተቀመጡ ሰላሳ የቆሙ በአጠቃላይ ዘጠና መሆናችን ነው” አልኳቸው፡፡ “በጣም ጥሩ! አገርና መኪና አንድ ናቸው የምልህ እኮ ለዚህ ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ በር ተዝናንቶ ይገባል ይወጣል፡፡ ዘጠና ሰዎች ግን በሁለት በሮች እየተጋፋን እንገባለን እንወጣለን፡፡ አስተውለኸው አታውቅም? በአንድ በር አንድ ሹፌር በሁለት በሮች ዘጠና ተሳፋሪዎች ሲገቡ ሲወጡ፡፡ አገርም እንዲሁ ናት ባለስልጣኑ ከአገር ውጭ እየሄደ ይማራል ይዝናናል፡፡ እንደእኔና እንደአንተ ያለው ተራ ግን ውጭ ሄዶ ለመማርና ለመዝናናት ቀርቶ ውጭ የሚባለውን በቴሌቪዥንም መከታተል አንችልም፡፡ የባለስልጣናት ወገኖች በተለያዩ መናፈሻዎች ሲዘንጡ እኔና አንተ ግን ደመወዛችን ወር አላደርሰን ብላ ተሸማቅቀን እንኖራለን፡፡ አንድ ባለስልጣን ፎቅ የሚገነባበት መሬት ቆርሶ ይወስዳል እኔና አንተ ግን ተደራጅተንም ማግኘት አይቻለንም፡፡ አሁንስ አገርና መኪና አንድ መሆናቸው አልገባህም” አሉኝ፡፡ “አሁን ገብቶኛል ነገር ግን እስከአሁን ድረስ ምንም አገናዝቤው አላውቅም ነበር፡፡” አልኳቸው፡፡ “አገር ሰፊ መሆኗ እንጅ ከመኪና ምን ትለያለች? በግልጥ በተግባር እያየኸው! አንዱ የሚቀመጥባት ሌላው የሚቆምባት ናት እኮ ብቻ ተወው ተከድኖ ይብሰል አሉ አበው፡፡ ብዙ እናወራ ነበር ግን እዚህ ስለምወርድ የሰላም መንገድ ያድርግላችሁ” ብለው ከአንድ አነስተኛ ከተማ ወረዱ፡፡ እኔም የሽማግሌውን ንግግር እያደነቅሁ ጉዞየን ቀጠልኩ፡፡

No comments:

Post a Comment