Monday, August 4, 2014

የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ መኃ 1፥6

ሰሎሞን ከምስጋናው ሁሉ በሚበለጥ ምስጋናው የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ አለ፡፡ ጥል በተለያየ መንገድ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በገንዘብ፣ በቦታ፣ በሥራ ጉዳይ ወዘተ… ፡፡ ነገር ግን ወንድምና እህቶቻችን እናትና አባቶቻችን የሚጣሉን ምክንያት አልባ በሆነ ነገር ሊሆን ይችላል ልክ እንደ ሰሎሞን ማለት ነው፡፡ አንተ በማታውቀው ነገር ሌሎች ጉዳዩን ጨርሰውት በፍቅር ያዩ የነበሩ ዓይኖች ሁሉ ወደ ጥላቻ ተለውጠው ልትመለከት ትችላለህ፡፡ በአንተ ላይ በመቅናት ፊቱን የሚያዞርብህም አይታጣም ልክ እንደ ዮሴፍ ወንድሞች ማለት ነው፡፡ የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው ዮሴፍ ከእኛ በላይ ይሆንብናል ብለው ተመቅኝተው በገንዘብ ለማያውቁት አሳልፈው ሸጠውታል፡፡ የእናቱ ልጆች ዮሴፍን በማያውቀው ድብቅ ምሥጢራቸው ተጣሉት፡፡ አንዳንዶች የሚጣሉበት ምክንያት በራሱ በውል አይገባቸውም፡፡ ሰው እነርሱን ሊያግዛቸው ከተጠጋ ጥቅማቸውን የሚጋራ ይመስላቸዋል፡፡ ምክር ሊመክራቸው የሚሞክር ካለም ስድብ ይመልሱለታል፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ከባዱ ጉዳይ የዚህ አይነቱ ነው፡፡ ለሌላው በማዘንና በመራራት አንድን በሸክም ብዛት የደከመ ሰው ወንድሜ ደከመህ ሸክምህን ትንሽ ላሳርፍህ ስትለው የግል ክብሩ የተገፈፈ፣ ጥቅሙ የተነካ ያህል ያንሰፈስፈዋል፡፡ በእርግጥ ከተሸከመው ሸክም ባሻገር እንዳይታወቅበት የሚፈልገው ድብቅ ምሥጢር ቋጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ የሥራ ኃላፊህን ሥራ በዝቶበት ብታገኘውና ሰብአዊነት ተሰምቶህ ላግዝህ ብትለው ያንተን እገዛ አይሻም ሌሊት ከቀን ብሎ አእምሮውን ወጥሮ፣ ተጨንቆና ተጠብቦ ይሠራዋል እንጅ፡፡ ለምን? ለምንማ ዛሬ አንተ ካገዝከው ነገ ወንበሩን የምትገለብጠው ስለሚመስለው ወይም የግል ጉዳዩን የሚያረካበትን ሽርፍራፊ ነገር እንድታውቅበት ስለማይፈልግ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የዓለማውያኑ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን አሁን ወደ ቤታችን ጎራ ማለት ጀምሯል፡፡ በአገልግሎት ውስጥ የሚታየው ከባዱ ፈተና የዚህ አይነቱ ጉዳይ ነው፡፡ የአገልግሎትን ጥቅም ያልተረዳ ትውልድ ሊነጥቀን ጦሩን የሰበቀበት ዘመን ላይ ነን አሁን፡፡ የምእመናንን ጥያቄ ከምንም ባለመቁጠር የግል ጥቅማቸውን የሚያካብቱ አንዳንዶች ከግል ደመወዛቸው ሠርተው ካገኙት ጥሪታቸው በመክፈል የበረከት ሥራ እየሠሩ ባሉ ግለሰቦችና ማኅበራት ላይ ዓይናቸው ደም ይለብሳል፡፡ ለምን? ለምንማ ነገ የውስጥ ማንነቱን ሊገልጥበት እንደሚችል ስለሚፈራና ያ በሕገ ወጥ መንገድ ያካበተው ሀብትና ንብረቱን የሚወርሰው መስሎ ስለሚታየው ነው፡፡ እውቅና የሌለው እውቅና ያለውን ይወነጅላል፡፡ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን ለመሥራት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት፣ አሕዛብን በማስተማር ወደ እናት ቤተክርስቲያን ለመመለስ፣ ገዳማት ራሳቸውን የሚችሉበትን የሥራ መስክ ለመፍጠር ከጎናቸው በመቆም የሚደግፋቸውን ግለሰብ ወይም ማኅበር የሚያብጠለጥሉ አንዳንድ የአድባራትና የገዳማት መሪ ወይም አስተዳዳሪ ነን ባዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ በእርግጥ ለኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል ግንባር ቀደም ተዋንያኖች የአይሁድ ካህናት እንደ ነበሩ ስለምናውቅ ይህ ብዙም ላይደንቀንም ላይገርመንም ይችላል፡፡ ዓለም ክርስቶስን እንደጠላችው በስሙ የሚያምኑት ሁሉ በዓለም ዘንድ የተጠሉ ይሆናሉ፡፡ እኔ በጣም ደስ የሚለኝ ነገር አለ ይኸውም ዓለም ስትጠላን ወንድሞቻችን ሲጣሉን ክርስቶስን የማመናችን ብሎም የማምለካችን ውጤት መሆኑ ሲሰማኝ ነው፡፡ ከአብያተ ክርስቲያናት ተጠግተው መኪና የገዙ፣ ቪላ ቤት ያስገነቡ እነዚህ ወንበዴዎች የማይጠግቡ ስልቾች ናቸው፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ብሎ እግዚአብሔር በመዓቱ ጅራፍ ገርፎ የሚያስወጣበት ቀን ቅርብ እንዲሆን ጸሎታችን ነው፡፡ ግራ ተጋባን እኮ ቆዩ እስኪ ግን! አገልጋይ የሚባለው የቱ ነው? አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘጋ ወይስ የሚከፍት? አሥራት በኩራት የሚያወጣ ወይስ ምእመናን ያስገቡትን አሥራት በኩራት ወደማይሞላ ኪሱ የሚያስገባ? ወደ ሙዳየ ምጽዋት ሳንቲም የሚጥል ወይስ ውዳየ ምጽዋትን የሚገለብጥ? ምእመናንን የሚያስተምር ወይስ ምእመናን ለአመጽ የሚገፋፋ? እንጃ በጣም አስፈሪ ዘመን ነው፡፡ “አቤቱ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ከማለት ውጭ ምን እንላለን? ለመንጋው የማያስቡ እረኞች ይመጣሉ የተባለው ትንቢት ይኸው ዛሬ ተፈጸመ፡፡ መንጋው ሲጠፋ የማይገዳቸው እረኛ መሳይ ፖለቲከኞች እንደ አሸን መፍላት ጀመሩ፡፡ ምእመኑ የካህኑን፤ ካህኑም የምእመኑን ሥራ መሥራት ጀመሩ፡፡ በጎች እረኛቸውን መጠበቅ ጀመሩ፡፡ ሥርዓት ተጣሰብን ቀኖና ፈረሰብን የሚሉ ለእምነታቸው የተቆረቆሩ ምእመናን ሲነሡ ከመንግሥት ፖለቲካ ጋር በማያያዝ “አሸባሪ ናቸው” በማለት በጎቻቸውን ለጅብ አሳልፈው የሚሰጡ እረኞች በእርግጥ የሥርዓተ ቤተክርስቲያንና የቀኖናው ጉዳይ ተዘንግቷቸው አልያም ጉዳያቸው አልሆን ብሎ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽና ቁጥር የመንግሥትንም አዋጅ የሚያንሰላስሉ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ የተቸገርነው ሕገ መንግሥቱን የሚያስተምረን አጥተን አይደለም ወንጌሉን፣ ሥርዓቱን እንጅ፡፡ ለሕገ መንግሥቱ ለራሱ የተወከለ ሰው አለው የእናንተ ሥራ ሊሆን የሚችለው ወንጌሉን በማስተማር፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማሳዎቅ ለሀገሩ ልማት የሚተጋ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ለአገር እድገት ከመንግሥት ጋር ዓላማን ሳይዘነጉ መሥራት እጅግ በጣም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ምእመናንን በማስፈራራትና በመዛት እንዲሁም ያለምንም ጥያቄና አቤቱታ ወደምመራችሁ ሁሉ ተከተሉኝ በማለት ሊሆን አይችልም፡፡ አገልጋይ ነን ባዮች ሆይ የተመረጣችሁ ለወንጌል አገልግሎት እንጅ ለፓርላማ አባልነት አይደለም፡፡ እናንተ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ልታከብሩና ልታስከብሩ እንጅ የፖለቲካ ሕግ አስፈጻሚ አካላት አይደላችሁም፡፡ ሰው የሚፈልገውን አይነት አመለካከት፣ እምነት፣ ፖለቲካ ፓርቲ መደገፍ አባል መሆን መቃወም ይችላል ይህ ነጻነት ከሰማያዊው ንጉሥ ተሰጥቶናልና ማንም ሊነጥቀን አይችልም፡፡ ነገር ግን በቦታውና በጊዜው ልናደርገው ያስፈልጋል፡፡ አውደ ምሕረት ላይ የቆመ ሰው እንዲያስተምረን የምንፈልገው ወንጌል እንጅ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ዘመኑ ተገለባበጠ መሰለኝ፡፡ እረኞች ገደል ሲገቡ የሚመለከቱት በጎች ናቸው፡፡ በጎች ተሰብስበው እረኛቸውን ገደል እንዳይገባ ቢመክሩትም በጎቹን ስለሚንቃቸው ከምንም አይቆጥራቸውም፡፡ እረኞች ሆይ! እናንተ የምትጠብቁን በመስቀል እንጅ በሽጉጥ አይደለም፣ በቃለ ወንጌል እንጅ በሕገ መንግሥት አንቀጽና ቁጥር አይደለም፣ በምክር በተግሳጽ እንጅ በመወንጀል በማስፈራራት አይደለም፡፡ እረኛ በበጎቹ ላይ ቢኮራባቸው በጎቹ ጥለውት ይሄዳሉ ወይም ወግተው ይገድሉታል የሚገባውንም የእረኝነት ክብር ይነፍጉታል፡፡ እኔ የማዝነው አክብሮ የያዛችሁ ምእመን ከልቡ አውጥቶ ፊቱን አዙሮ ይሰጣችሁ የነበረውን የአባትነት ክብር ነፍጎ ዓለም ቀጥቅጦ ሲጥላችሁ የሳምራዊውን እንክብካቤ ማድረጉን ሲያቆም ያን ጊዜ የምትተማመኑበት ሲሸሻችሁ ብቻችሁን ቀርታችሁ የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ስትሆኑ ነው፡፡ የተሳለ ጦርን መርገጥ የሚብሰው በረጋጩ እንጅ በተረጋጩ አይምሰላቸችሁ፡፡ የእረኞች ክብር በበጎች ላይ ነው፡፡ አሁንም ደግሜ እላለሁ የእረኞች ክብር በበጎች ላይ ነው፡፡ እኛስ “የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ” የሚለውን ምስጋና በማመስገን ቤተ መቅደሱ ከእናንተ ደባ የሚጸዳበትን ቀን እንጠብቃለን እናንተ ግን “የእናቴን ልጆች ልጣላቸው” እያላችሁ ስትመክሩ እስከመቼ ትኖራላችሁ? እኛ አሁንም አምላክ ልብ ይስጣችሁ ብለን እንመርቃችኋለን፡፡ እየሄዳችሁ ካላችሁበት መጥፎ ጎዳና ተመለሱ የእኛ የልጅነት ምክራችን ይህ ነው፡፡ ፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠

No comments:

Post a Comment