የሁሉም አስገኝ እግዚአብሔር
ለሥራው ሁሉ ጊዜ አለውና ፍጥረታትን መፍጠር የጀመረ እሁድ ሲሆን ሥራውን አርብ ፈጽሞ ቅዳሜ ከሥራው ሁሉ አርፏል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ
አክሲማሮስ በሚባል መጽሐፉ በእነዚህ ዕለታት የተፈጠሩ ፍጥረታት በቁጥር ብዙውን አንድ በማለት ሃያ ሁለት ናቸው በማለት ይናገራል፡፡
መዝ118፥126፣ ዘፍ 1፥1-25፣ መክ3፥1 ፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ
መቼ ምን ተፈጠረ ቢሉ፡-
በስድስቱ ዕለታት የተፈጠሩት
ሃያ ሁለት ፍጥረታት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.
እሁድ ፡- ስምንት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v እሳት፣ውኃ፣ ነፋስ፣ ጨለማ፣ ብርሃን፣
መሬት፣ ሰባቱ ሰማያትና መላእክት፡፡
2.
ሰኞ ፡- አንድ ፍጡር ተፈጥሯል፡፡
v በሦስት የተከፈለው ውኃ ከምድር በታች ውቅያኖስ፣ ከጠፈር በላይ ሐኖስ የተባለውና ከአየር በላይ ጸንቶ ጠፈር የሆነው
ውኃ፡፡
3.
ማክሰኞ ፡-ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v ዕፅዋት፣ አዝርእትና አትክልት፡፡
4.
ረቡዕ ፡- ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት
5.
ሐሙስ ፡-አራት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v በልብ የሚሳቡ፣በእግር የሚሽከረከሩ፣ በክንፍ የሚበሩና በደመ ነፍስ ህያዋን ሆነው የሚኖሩ በባሕር የተፈጠሩ፡፡
6.
አርብ ፡-አራት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡
v ሰው፣ በየብስ የሚገኙ
በደመ ነፍስ ህያዋን የሆኑ እንስሳት፣ አራዊትና አዕዋፍ
እነዚህን ፍጥረታት ካስተዋልናቸውና
ከተረዳናቸው እጅግ በጣም አስተማሪዎች ናቸው፡፡ በተሰጠን ከሁሉም በሚበልጥ አእምሮ ፍጥረታትን ማስተዋል ከቻልን ብዙ የምንገበያቸው
ቁም ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙ አስተማሪ ፍጥረታት መካከል ጥቂቶችን ለመማሪያ ያህል እነሆ!
Ø
ፀሐይ ፡- ለዓለም ሁሉ የምታበራ ጊዜዋን ጠብቃ በምሥራቅ የምትወጣና በምዕራብ የምትገባ ፍጡር ናት፡፡ መዝ103፥19፡፡ ከዚች ፍጡር ሁለት ነገር እንማራለን፡፡ የመጀመሪያው
ብርሃን መሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ነው፡፡ ፀሐይ ለዓለም ሁሉ ብርሃን እንደሆነች ሁሉ እኛም በሥራችን
፣ በኑሯችን ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ብርሃን መሆን እንደሚገባን መማር እንችላለን፡፡ ብርሃን መሆን ማለት አስተማሪ የሆነ አኗኗር
መኖር ማለት ነው፡፡ በቤተሰብ አመራር፣ በልጅ አስተዳደግ፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ ለሰው በመራራት፣ ክርስትና ሕይወትን በተግባር መኖርን
ወዘተ… ያካትታል፡፡ ሌላው ከፀሐይ የምንማረው ነገር ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ነው፡፡ ፀሐይ ጊዜዋን ጠብቃ እንደምትወጣና እንደምትገባ
ሁሉ እኛም ጊዜያችንን ጠብቀን ቤተክርስቲያን ለጸሎት ለስግደት ለአገልግሎት መሄድ እንዲገባን እንማራለን፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን
ከዚህ በመለየቱ ጊዜውን ጠብቆ ባለመግባቱና ባለመውጣቱ ወጣቱ ሽማግሌው በአልባሌ ቦታ ወድቆ የበሽታ ሰለባ የወንጀል ተቋዳሽ ለመሆን
ተገዷል፡፡ ስለዚህ ከፀሐይ በመማር ጊዜያችንን በትክክል ለሚፈለገው ተግባር ብቻ ማዋል አርአያነታችንን ለዓለም ሁሉ እንዲያበራ ማድረግ
ይጠበቅብናል፡፡
Ø ዕፅዋት፡- ከቦታ ቦታ የማይንቀሳቀሱ ለሰው ልጅ ኑሮ ተስማሚ የሆነውን ንጹህ አየር የሚለግሱ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ሊጠቀምባቸው ፈልጎ
በምሳር በመጋዝ ቢቆርጣቸው እንኳ ለምልመው አቆጥቁጠው ይወጣሉ እንጅ ፈጽመው አይጠፉም ጥቂት ከሚባሉ ዕፅዋት በስተቀር፡፡ዕፅዋት
ከተተከሉበት ቦታ የማይንንቀሳቀሱ እንደሆኑ ሁሉ እኛም ከሥላሴ ልጅነት ከተተከልንባት ቅድስት ቤተክርስቲያን ካደግንባት ኦርቶዶክስ
ተዋህዶ እምነት ውጭ ልንንቀሳቀስ እንደማይገባ እንማራለን፡፡ ከጥቂት ዕፅዋት በቀር ሲቆረጡ እንደሚለመልሙ እንደሚያቆጠቁጡ ሁሉ እኛም
ሰይጣን በተለያየ ዘዴ በኃጢአት ቢቆርጠን በመማርና በንስሓ መለምለም ማቆጥቆጥ እንዳለብን እንማራለን፡፡ስለዚህ ከዕፅዋት ተምረን
በእምነታችን ጸንተን ከቤተክርስቲያን ተተክለን በንስሓ ለምልመን መኖር ይጠበቅብናል፡፡
Ø
በሬ፡- ትልቅ እንስሳ ሆኖ ሳለ ሕጻናት ሳይቀሩ በፈለጉት አቅጣጫ ይነዱታል፡፡ ምንም እንኳ ክረምት ከበጋ ለሰው ልጅ የሚደክም
ቢሆንም የድካሙ ክፍያ ፍሬ ሳይሆን ገለባ ጭድ ነው፡፡ በትሕትና ዝቅ ብሎ የቀረበለትን ገለባ ጭድ ይመገባል፤ ገለባ ጭድ ካላቀረቡለት
ጎንበስ ብሎ ሣር ይግጣል፡፡ ይህን ተመግቦ የሚጥለው እበት ለቤት ማስጌጫነትና ለማገዶነት ይውላል፡፡ አስተዋላችሁ ወገኖቼ! እኛም ከበሬ በመማር ለራሳችን ትልቆች ስንሆን የታናናሾችን
ምክርና ተግሳጽ ያለመናቅ በማክበርና በማስተዋል መቀበል ይገባናል፡፡ ትሕትና መማር አለብን ማለት ነው፡፡ በሬ በትልቅነቱ ተመክቶ
ሕጻናት ሲነዱት በሕጻናት ላይ አመጸኛ እንዳይደለ እኛም ሕጻናትን አይጠቅሙም በማለት ከቤተክርስቲያን እንዲወጡና ከማመስገን ዝም
እንዲሉ ልናምጽባቸው አይገባም፡፡ ማቴ 19፥14፣ማቴ21፥16 የበሬ የድካም ክፍያ ገለባ ጭድ ቢሆንም በዚህ ተበሳጭቶ ሥራውን እንደማያቆም
ሁሉ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ስንሳተፍ ደመወዙ ዝቅተኛ ቢሆንብን ወይም ባይከፈለን በዚያ ተበሳጭተን ኪዳን ከማድረስ፣ ቅዳሴ ከመቀደስ፣
ሰዓታት ከመቆም፣ ወንጌል ከማስተማር ወዘተ… ልንርቅ አይገባንም፡፡ ሌላው አስተማሪ ነገር በኩራት ፈረስ የምንጋልብ ራሳችንን ከፍ
ከፍ ማድረግ የሁልጊዜ ተግባራችን የሆነ እኛ ያማረ መብልና መጠጥ መርጠን ተመግበን የሚወጣን አሰር ሽታ ለራሳችን ሳይቀር አያስቀርብም፡፡
ስለዚህ ከበሬ በመማር ኩራትንና ራስን ከፍከፍ ማድረግን በማራቅ በትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን በፈሪሐ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን
ልንኖር ይገባናል፡፡
Ø
ርግብ፡- የመንፈስ ቅዱስ
(ማቴ 3፥16) ፤ የእመቤታችን (ዘፍ 8፥8-11) ምሳሌ ሆና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጽፋ
እናገኛለን፡፡ ርግብ በአንድ ባል ጸንታ የምትኖር ባሏ የሞተ እንደሆነም ምላሷን ሰንጥቃ በብቸኝነት ትኖራለች፡፡ ሌላ ወንድ የመጣባት
እንደሆነ የተሰነጠቀ ምላሷን በማሳየት ትመልሰዋለች፡፡ በርግቦች ዘንድ ድጋሜ ሌላ ወንድ ማግባት ነውር ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ያለን
እኛስ? አስቡት እንኳን የትዳር አጋራችን ሞቶብን ቀርቶ በሕይወት እያሉ በላያቸው ላይ የምንነግድባቸው ቀላል ነን እንዴ? ርግብን
ማስተዋል ከቻልን በሥጋና ደሙ ጋብቻችንን መሥርተን በአንድ ጸንተን በመተሳሰብ፣ በመረዳዳትና በመፈቃቀር የምንኖር እንሆናለን፡፡
ምናልባት በሞት የምንለያይ ከሆነና ብቻን ለመኖር አስቸጋሪ ሆኖ ከተገኘ በድጋሜ በሥጋና ደሙ ማግባት ይቻላል፡፡ ይህ ሥርዓት የሚፈጸመው
ለምዕመናን ሦስት ጊዜ ለካህን ሁለት ጊዜ (ክሕነቱ ፈርሶ) ከዚህ የዘለለ ጋብቻ ግን ከዝሙት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ከርግብ በመማር
ለትዳራችን ታማኝ በመሆን እግዚአብሔርን በመፍራት ልንኖር ይገባናል፡፡
Ø
ጉንዳን፡- በመጠን በጣም ትንሽ
ፍጡር ብትሆንም በትጋት የክረምት ምግቧን በበጋ ትሰበስባለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመተባበርና በመረዳዳት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ፍጡር
ናት፡፡ በጣም ከባድና አስቸጋሪ የሆነን ነገር ሳይቀር በመተባበር ከቦታቦታ የማንቀሳቀስ ችሎታ አላት፡፡ ከዚች ፍጡር መማር የተሳነው
የሰው ልጅ የሰማይ ምግቡን በምድር መሰብሰብ አልቻለም፡፡ የሰማይ ምግባችንን ክረምት ሳይቀርብ መንቀሳቀስ በምንችልበት ወቅት ልንሰበስብ
ይገባናል፡፡ እንደ ጉንዳን በመረዳዳትና በመተባበር ለሀገራችን፣ ለወገናችንና
ለቤተ ክርስቲያናችን አስቸጋሪ የሆነን ፈተና ማንከባለልና ማስወገድ ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ከጉንዳን በመማር በፍቅር መተባበርን፣
ለሰማይ ምግባችን ስብሰባ መትጋትን የሁልጊዜ ተግባራችን ልናደርግ ይገባናል፡፡
Ø አውራ ዶሮ፡-ከጥንት ጀምሮ ዶሮ ሲጮኽ ሌሊቱ እንደነጋ ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት …” የሚባለው፡፡ ሰዓቱን ጠብቆና አክብሮ በመጮኽ የሚታወቅ እንስሳ ነው ዶሮ፡፡
ከዚህ በመማር እኛም ጊዜውን ጠብቀን በጸሎት በስግደት በጾም ወደ እግዚአብሔር ልንጮኽ ያስፈልጋል፡፡ ዳዊት በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፡፡
መዝ118፥164 እንዳለ በሰዓቱ ምስጋና ገንዘቡ የሆነውን እግዚአብሔር በማመስገን መጮኽ
አለብን፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን እጅግ ጥቂት ፍጥረታትን ለመግለጽ ሞከርን እንጅ ተፈጥሮን ካስተዋልን ተራ የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ
አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድን ለዚያ ሁሉ ክብርና ቅድስና ያበቃው ተራ ከምንለው ትል መማሩ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን በመረዳትና
በማስተዋል ልንማር ያስፈልጋል፡፡ ሰባኪ መምህር፣ ዘማሪ ወይም መጽሐፍ ባናገኝ እንኳ በአካባቢያችን ከምናያቸው
ፍጥረታት መማር ያስፈልገናል፡፡ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡ አሜን፡፡ መድረሻ እሳቱ የማይጠፋ ትሉ የማያንቀላፋ የኩነኔ ቦታ በመሆኑ፡፡
የመንግሥተ ሰማያት መድረሻ ሀዲድ እጅግ ጠባብ ብትሆንም ፍጻሜዋ ተድላ ደስታ የሞላባት የጽድቅ ቦታ በመሆኗ ወደዚች በሚወስደው ሀዲድ
ላይ መሽከርከር አለብን፡፡ ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች እንሆን ዘንድ የጽድቅ ሥራ እየሠራን እንድንኖር ሁልጊዜ በጸሎት መትጋት
ይገባናል፡፡ የዲያብሎስ ባቡሮች ከመሆን ተቆጥበን ራሳችንን ለፈጠረን
እግዚአብሔር በማስገዛት ለመኖር በቸርነቱ ይርዳን፡፡