Thursday, February 28, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 22


                ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
                  ******
፳፡ ወእንዘ ዘንተ ይሔሊ ናሁ አስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር ለዮሴፍ በሕልም።
                  ******
                  ******
ታሪክ። እመቤታችን የብፅዓት ልጅ ናት። ሦስት ዓመት ሲሆናት አባት እናቷ ወስደው ለካህናት ሰጡ። ክህናትም ተቀብለው አክብረው ከቤተ መቅደስ ያኖሯታል። አሥራ ሁለት ዓመት ትኖራለች ከዚያ ሶስት ከዚያ አሥራ ሁለት አሥራ አምስት ዓመት ይሆናል ። አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ይህች ብላቴና መጠነ አንስት አይረሰች ቤተ መቅደሳችንን ታሳድፍብናለች ትውጣልን አሉት። ዘካርያስ ሂዶ እንደምን ትሆኝ አላት። ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ አለችው። ቢያመለክት ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን በትር ሰብስበሀ ከቤተ መቅደስ አግብተህ አውጣው ምልክት አሳይልሃለሁ አለው። ቢሰበስብ ሽህ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ አምስት ለሁለት ሽህ አሥራ አምስት የጎደለው ማለት ነው። ያን አግብቶ ቢያወጣው ከዮሴፍ በትር ኦ ዮሴፍ ዕቀባ ለማርያም የሚል ተገኘ። ዕጣም ቢያወጡ ለሱ ወጣ። ርግብም መጥታ በራሱ ላይ አረፈች። እንደ ሦስት ምስክር ያም ሆነ ያም ሆነ ከእግዚአብሔር አግኝተን የሰጠንህን ከእግዚአብሔር አግኝተን እስክናሰናብትህ ወስደህ ጠብቅ አትንካ ብለው ሰጡት። ይዟት ሄደ።
ጊዜው ዓፀባ ነበርና ንግድ ሂዶ ሦስት ወር ኑሮ ቢመለስ ዮሐንስ የሚባል ፈላስፋ ወዳጅ ነበረው ሊጠይቀው መጣ። ተጨዋውተው ሲሄድ ሊሸኘው ወጣ። ይህች ብላቴና ፀንሳለች ከአንተን ነው ከሌላ አለው። እኔስ እንኳን ነቢብ ገቢር ሐልዮም አላውቅባት አለው። እንኪያስ ፀንሳለች ገብተህ ጠይቃት አለው። በምን አውቆ ቢሉ ፈላስፋ ነውና በመልኳ ገብቶ ኦ ወለተ እስራኤል መኑ ቀረጸ አክናፈ ድንግልናኪ ወእምኀበ መኑ ፀነስኪ ብሎ ጠየቃት። እመንፈስ ቅዱስ አለችው። ነገሩ ቢረቅበት ከደጁ ወድቆ የሚኖር ደረቅ ግንድ ነበርና ተክላ አለምልማ አሳይታዋለች። በዚያውስ ላይ አዕዋፍን ከባሕርያቸው እንዲራቡ አዕዋምን እንዲያፈሩ የሚያደርግ ማን ይመስልሃል አለችው ነገሩን ተረዳው።
ከዚህ በኋላ ለበዓል የሚወጡበት ጊዜ ደረሰ። ትቻት ብወጣ ያደረገችውን ታስታውቅ ከደረቷ ትታጠቅ እንዲሉ ያደረገውን አውቆ ትቷት መጣ ይሉኛል፤ ይዣት ብወጣ ሴሰነች ብለው በደንጊያ ወግረው ይገሉብኛል እያለ፤ ወወድቀ ዮሴፍ ውስተ ጽኑዕ መዋግደ ሕሊና ይላል። ይህነን ሲያወጣ ሲያወርድ  ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው።
(ሐተታ) ህልም ከሦስት ወገን ነው ከሐሞት ከመልአክ ከሰይጣን የሚገኝ ነው። ከሐሞት የሚገኝ በልቀም ደም ሳፍራ ሳውዳ የሚባሉ ሐሞታት አሉ። በልቀም እሳታዊ፤ ደም ማያዊ፤ ሳፍራ ነፋሳዊ፤ ሳውዳ መሬታዊ ነው። እኒህ በሠለጠኑ ጊዜ በየኅብራቸው ሲያሳዩ ያድራሉ። ከሰይጣን የሚገኝ እንደ ሄሮድስ በስደቷ ጊዜ ከዚህ ዋለች ከዚህ አደረች እያለ ይነግረው ነበር። ከመልአክ የሚገኝ እንደ ዮሴፍ እንደ ፈርዖን እንደ ናቡከደነፆር።
እንዘ ይብል ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ። ኦ ቃለ አክብሮ ቃለ አኅሥሮ ቃለ አራኅርኆ ይሆናል። ቃለ አኅሥሮ ኦ ሐናንያ ኦ አብዳን ሰብአ ገላትያ። ቃለ አክብሮ ኦ ጳውሎስ ምንተ ትቤ ኦ አኃውየ ፍቁራን ቃለ አራኅርኆ ኦ ድንግል አዘክሪ ኦ ዮሌፍ ያለው ይህ ነው። የርኅሩኅ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ እህትህ ናትና ራራላት።
አንድም የጥቡዕ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከካህናት እጅ እንደ ተቀበልህ ከእደ መንፈስ ቅዱስ መቀበልን አትፍራ። ነሢኦታ ባለው አብነት አዕርጎታ አውፅዖታ  ዓቂቦታ ተልእኮታ ይላል። እስመ እምፍሬ ከርሥክ አነብር ዲበ መንበርከ ያለው ትንቢት እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ዳዊትን አነሣው።
እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ። ከሱዋ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና። ማቴዎስ እመንፈስ ቅዱስ ያለውን ሉቃስ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ያለውን። ኢሳይያስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ያለውን። ሊቁ ዛቲመ ትርጓሜሃ ለቅብዓት፤ እስመ መንፈስ ቅዱስ አንጽሐ ሥጋሁ ለአዳም ብሎ ወስዶታል። ንጽሕን ክብር የሚል ወዴት አለ ቢሉ ወሠዓርኮ እምንጽሑ ይላል።
                  ******
፳፩፡ ወትወልድ ወልደ።
፳፩፡ ወንድ ልጅ ትወልዳለች። ሉቃ ፩፥፴፩። ሐዋ፡ሥራ ፬፥፲፪።
                  ******
ወይሰምዮ ስሞ ኢየሱስሃ። ስሙንም ኢየሱስ ትለዋለች።
እስመ ውእቱ ያድኅኖሙ ለሕዝቡ እምኃጣውኢሆሙ። ወገኖቹ እስራኤልን በኃጢአት ከመጣባቸው ፍዳ ያድናቸዋልና ኢየሱስ ብሎ ንባቡን ያድኅኖሙ ብሎ ስሙን ከነትርጓሜው ተናገረ። ኃይሎ ለሥም ወፍካሬሁ አብጽሐ ቅዱስ መልአክ እንዲል።
                  ******
፳፪፡ ወዝንቱ ኵሉ ዘኮነ ከመ ይትትፈጸም እምኅበ እግዚአብሔር።
                  ******
፳፪፡ በነቢይ እንዘ ይብል ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ። ኢሳ ፯፥፲፬። አጸፋውን ለወንጌላዊ የሰጡ እንደሆነ እመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ትፀንሳለች በግብረ መንፈስ ቅዱስ ትወልዳለች ብሎ መልአኩ ለዮሴፍ መንገሩ ነቢይ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ብሎ የተናገረው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ አጸፋውን ለመልአኩ የሰጡ እንደሆነ እመቤታችን በድንግልና መጽነስዋ በድንግልና መውለዷ እግዚአብሔር በነቢዩ አድሮ ነቢይ ከእግዚአብሔር አግኝቶ ተገልፆለት ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ብሎ የተናገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ነው።
                  ******
፳፫፡ ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል።
                  ******
፳፫፡ ስሙም አማኑኤል ይባላል። ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ።
አማኑኤልም ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከኛ ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነው። ሐተታ ወንጌላዊ የሚጽፍላቸው በቋንቋቸው በዕብራይስጥ ነው። መልአኩም ለዮሴፍ የሚነግረው በዕብራይስጥ ነው። ምን ይተረጒማል ቢሉ ያስ ቅዱስ ቄርሎስ የንስጥሮስን ነገር ሲያስፈርድ አንተ ኅድረት ካልህ አማኑኤል ያለውን ንባብ እግዚአብሔር ምስሌነ ብሎ የተረጐመ ወንጌላዊ አበላ። ሕስወኬ ይሰመይ ወንጌላዊ ዘይተረጒም በኀቤሆሙ ብሎ ረትቶበታል ይተረጒምላቸዋል ትርጓሜው ግን በቋንቋቸው ካህናቱ የሚያውቁት ሕዝቡ የማያውቁት እንደ ጥሬ ያለ አለና ያነን ማጽናት ማጒላት ነው። መጽሐፍ በ ወ በ ዘ ያጐላል በ ወ ሲያጐላ ፍሥሐ ወ ኃሤት ፍቅር ወሰላም። በ ዘ ሲያጐላ ምንት ብከ ዘ ኢነሣአከ እምካልዕከ ወምንት ብከ ዘ ኢኮነ ውሁበ ለከ ይላል።
አንድም ዮሐንስ ወንጌላዊ የማቴዎስ ወንጌልን ለሰብአ ኤላንሳን ተርጒሞላቸዋል። በዚያ ጊዜ አማኑኤል ንባቡ ከእብራይስጥ እግዚአብሔር ምስሌነ ትርትሜው ከኤላንሳን መጥቶልናል። አማኑኤልን የመሰለ የኤላንሳን ንባብ ሳይመጣልን ቀርቷል።
አንድም የሀገራችን መላሽ አማኑኤል ያለውን የዕብራይስጡን ቋንቋ ወደ ግዕዝ ቢመልሱት እግዚአብሔር ምስሌነ ማለት ነው። እግዚአብሔር ምስሌነ ማለትም ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከእኛ ጋራ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው ብሎ ተርጒሞታል።
                  ******
፳፬፡ ወተንሢኦ ዮሴፍ እምንዋሙ ገብረ በከመ አዘዞ መልአከ እግዚአብሔር።
                  ******
፳፬፡ ዮሴፍ ከእንቅልፉ ተነሥቶ መልአኩ ያዘዘውን እንዳዘዘው አደረገ።
ወነሥኣ ለማርያም ፍኅርቱ።
ይዘሃት ውጣ እንዳለው ይዟት ወጣ። ጠብቅ እንዳለው ጠበቀ ተቀበል እንዳለው ተቀበለ።
                  ******
፳፭፡ ወኢያእመራ እስከ አመ ወለደት ወልደ ዘበኵራ።
፳፭፡ መጻሕፍት በኵር ያሉላት ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም።
                  ******
አእመራ አዳም ለሔዋን አእመራ ሕልቃና ለሐና ብእሲቱ እንዲል የግብር ዕውቀት አላወቃትም። ከወለደች በኋላስ አወቃት ማለት ነውን? ቢሉ ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው። ኢተመይጠ ቋዕ እስከ አመ ነትገ ማየ አይኅ ኢወለደት ሜልኮል እስከ አመ ሞተት እንዲል ሜልክል ከሞተች በኋላ ወለደች ማለትን ነው? ፍጸሜ የሌለው እስከ ነው።
አንድም በአንድ ኅብረ መልክዕ አላወቃትም ሲል ነው። ሥጋዌው በብዙ ኅብረ ትንቢት የተነገረለት በብዙ ኅብረ አምሳል የተመሰለለትን እሱን እንደጸነሰች ለማጠየቅ መልኳን ይለዋውጠው ነበርና። ቦ አመ ታሕመለምል ወቦ አመ ትፀዓዱ እንዲል ስንኳን የፀሐየ ጽድቅ ሰሌዳ ድንግልን ሙሴንስ እንኳ ኃላፊ ብርሃን ቢሳልበት እስራኤል ተገልበብ ለነ ብለውታል።
አንድም ኢያእመረ ይላል ወልድ የተባለ እሱ ድንግል የተባለች እርስዋ እንደሆነች አላወቀም። አጸፋውን ለወንጌላዊ የሰጡ እንደሆነ ምነው መልአኩ ነግሮት የለምን ቢሉ ፩ ከሆነ ብሎዓይን አያስረግጥምስክር አያስደነግጥ እንዲሉ። አጸፋውን ለመልአኩ የሰጡ እንደሆነ ነቢዩ ነግሮት የለምን ቢሉ ድንግል አለ እንጂ እሷን አለው ወልድ አለው እንጂ አምላክን አለው? ብሎ።
አምስት ነገር አይቶ እስኪረዳ ድረስ ኢያእመረ አላወቀም። (፩) ምጽአተ ሰብአ ሰገል ዘምስለ አምኃ፤ (፪) ሑረተ ኮከብ በካልእ ፍና፤ (፫) ሥርቀተ ስብሐተ እግዚእ፤ (፬) ዓቢይ ቅዳሴ መላእክት፤ (፭) ፍርሃተ ኖሎት። ይህን አይቶ እስኪረዳ ድረስ አላወቀም።
በኵራ በጥንት በበዓት በተቀድሶ። ወጸውዑ ስሞ ኢየሱስሃ። እስከ አመ ወለደት ወእስከ አመ ጸውዑ መጻሕፍት በኵር ያሉላት ልጁዋን እስክትወልድ ስሙንምየሱስ ብለው እስኪጸሩት ድረስ ኢያእመረ። ወአኮ በከመ ቃየን ዘእምእኵይ ወቀተሎ ለእኁሁ እንዲል። ወዘቀተሎ ሲል።
                  ******
በእንተ ምጽአተ ሰብአ ሰገል።
ምዕራፍ ፪።
፩፡  ወተወሊዶ እግዚእ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ በመዋዕለ ሄሮድስ ንጉሥ ናሁ ሰብአ ሰገል መጽኡ እምብሔረ ጽባሕ። ሉቃ ፪፥፯።
፩፡ ሄሮድስ ነግሦበት በነበረ ዘመን የይሁዳ ዕፃ በምትሆን በቤተ ልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ ሳለ በተወለደ ጊዜ ከተወለደ በኋላ። ሰብአ ጥበብ ሲል ነው ጥበብ ያላቸው ሰዎች ከወደ ምሥራቅ መጡ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
22/06/2011 ዓ.ም

Wednesday, February 27, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 21



                 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
                  ******
በእንተ ልደተ ክርስቶስ።
፲፰፤ ወለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመዝ ውእቱ ልደቱ።
                  ******
፲፰፤ የነትዕማርን የነራኬብን የነሩትን ሲናገር መጥቶ ነበርና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ እንዲህ ነው አለ። ከጥንት ሲነገር ሲያያዝ የመጣው ነው እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም።
ወሶበ ተፍኅረት ማንሻ አንድም ወለእግዚእነሰ ይላል በዘር በሩከቤ የሚወለዱ የአበውን ልደት ሲናገር መጥቶ ነበርና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግን ልደቱ እንዳህ ነው አለ። እንበለ ዘር ነው ከመዝ ያለውን ያመጣዋል። ወሶበ ተፍኅረት እሙ ማርያም ለዮሴፍ። ሉቃ ፩፥፳፯። እናቱ እመቤታችን ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ።
ዘእንበለ ይትቃረቡ ተረክበት ጽንስተ እንዘ ባ ውስተ ማኅፀና እመንፈስ ቅዱስ።
ዘእንበለ ይትቃረቡ ዘእንበለ ይትራከቡ ይላል። እሱ ሴት እንደሆነች ሳያውቃት እሱዋ ወንድ እንደሆነ ሳታውቀው ዮሴፍ ጠባቂ ሳላት አጋዥ ሳትሻ። አንድም ድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍሰ ሳላት። አንድም እምዘ ባ ካላት ከባሕርይዋ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ ተገኘች። ወገባሪሁሰ ለውእቱ ሥጋ መንፈስ ቅዱስ እስመ ውእቱ ቀብዖ ወተዋሐደ ቦቱ አምላክ ቃል እንዲል። ይህ እም በ ሲሆን ነው። እስመ እም ይተረጐም ለኀበ ብዙኅ ፍና እንዲል።
ሰማያት ወምድር ተፈጥሩ እምእግዚአብሔር አዳም ወሔዋን ተፈጥሩ እምእግዚአብሔር እንዲል። እመንፈስ ቅዱስም ቢል በመንፈስ ቅዱስ ተከፍሎ ኑሮበት አይደለም። አነጻት ሲል ነው እንጂ። ወአኮ ዘቦቱ ሥጋ ለመንፈስ ቅዱስ አላ መንፈስ ቅዱስ አንጽሐ ሥጋሃ ለማርያም ወረሰያ ድሉተ ለተወክፎ ቃለ አብ እንዲል። አነጻትም ቢል ኑሮባት አነጻት ማለት አይደለም ከለከላት ሲል ነው እንጂ። ውእቱሰ ንጹሕ እም፫ቱ ግብራት እለ ሥሩዓን በእጓለ እመሕያው ወእሙራን ቦሙ ዘውእቶሙ ሩካቤ ወዘርዕ ወሰስሎተ ድንግልና እንዲል። ከለከላትም ቢል ብታደርገው ዕዳ የሚሆንባት ሁኖ አይደለም አላደረገችውም ሲል ነው እንጂ። ከዚያ ሁሉ ወኮነ ይስሐቅ ያፈቅሮ ለዔሳው እስመ ዘውእቱ ነዐወ ይሴሰይ ብሎ ወያዕቆብሰ ንጹሕ እምዝንቱ ይላል። አሁን በኤሳው አድኖ መብላት ዕዳ  ሁኖበትን ነው? ያዕቆብን አላደረገውም ድልድል ቅምጥል ከቤት ዋይ ነው ሲል ነው እንጂ።
ልደቱን በዘር ያላደረገው እንበለ ዘር ያደረገው ስለምን ቢሉ ቀዳማዊ ልደቱን ለመግለጥ። አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለአባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት እንደተወለደ ያስረዳልና። ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደት እንዲል።
ዳግመኛ በዘር በሩካቤስ ተወልዶ ቢሆን ዕሩቅ ብእሲ ባሉት ነበርና። ሶበሰ ተወልደ በሩካቤ ብእሲ ወብእሲት ዘከማየ ብዙኃን እምተኃዘብዎ ወእምረሰይዎ ሐሰተ እንዲል።
ያውስ ቢሆን ልደቱን ተፈትሖ ካላት ያላደረገው ተፈትሖ ከሌላት ያደረገው ስለምን ቢሉ። ትንቢቱ ምሳሌው እንደተፈጸመ ለማጠየቅ። ትንቢት ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌም አዳም ከኅቱም ምድር ተገኝቷል ጌታም በኅቱም ማኅፀን ለመገኘቱ ምሳሌ ነውና። ሔዋን ከኅቱም ገቦ ተገኝታለች ጌታም ከኅቱም ማኅፀን ለመገኘቱ ምሳሌ ናትና። ቤዛ ይስሐቅ በግዕ ከኅቱም ጒንድ ተገኝቷል። ቤዛ ዓለም ክርስቶስም በኅቱም ማኅፀን ለመገኘቱ ምሳሌ ነውና። ጽምዓ እስራኤልን ያበረደ ውሀ ከኅቱም ኰኵሕ ተገኝቷል ጽምዓ ነፍሳትን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታም በኅቱም ማኅፀን ለመገኘቱ ምሳሌ ነውና።  ጽምዓ ሶምሶንን ያበረደ ውሀ ከኅቱም መንሰከ አድግ ተገኝቷል ጽምዓ ነፍሳትን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታም በኅቱም ማኅፀን ለመገኘቱ ምሳሌ ነውና። ትንቢቱን አውቆ አናግሯል። ምሳሌውንም እንጂ አውቆ አስመስሏል። ፍጻሜው እንደምን ነው ቢሉ ከመ ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዓባይ እንጂ ይላታል። ድንግል ወእም ስትባል መኖሯ አምላክ ወሰብእ ሲባል ለመኖሩ ምሳሌ ነውና።
ስትወልደው ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ ሰው ሲሆን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ ምሳሌ ናትና።
                  ******
፲፱፡ ወዮሴፍሰ ፈኀሪሃ እስመ ጻድቅ ውእቱ ኢፈቀደ ይክሥታ።
                  ******
፲፱፡ እጮኛዋ የሚሆን  ዓቃቢሃ ተለአኪሃ አገልጋይዋ ጠባቂዋ የሚሆን ዮሴፍ ግን ደግ ነውና ሊገልጣት ሊገልጥባት አልወደደም። አላ መከረ ጽሚተ ይኅድጋ ትቷት ሊሄድ ወደደ እንጂ።
ሐተታ ይህን ደግነቱን ያስቀርበታልን በኦሪት ታዞ የለምን ሚስቱን የጠረጠራት እንደሆነ ውሀ በመንቀል የገብስ ዱቄት አድርጐ ሚስቱን ይዞ ይሄዳል ከመድረኩ ስትደርስ ሊቀ ከህናቱ ክንንብሽን ግለጭ ይላታል ይግለጥብኝ በዪ ሲላት ነው። በኦሪቱ የሚደገም አለ ያነን ደግሞ ሕራረ ዕጣኑን ጨምሮ በጥብጦ ባልሽ የጠረጠረሽን አድርገሽው እንደሆነ ሥጋሽ ይበጥ ቁርበትሽ ይላጥ አጥንትሽ ይርገፍ፤ አላደረግሽው እንደሆነ በወንድ ልጅ ተበከሪ ብሎ ይሰጣታል። እርሷም መርገሙ ይደረግብኝ በረከቱ ይሁንልኝ ብላ ትጠጣዋለች። ይህ ደግነቱን ያስቀርበታልን በኦሪቱ ታዞ የለም ቢሉ ዮሴፍ ጻድቀ ወንጌል ነው እንጂ መቸ ጻድቀ ኦሪት ነዋ።
                  ******
፳፡ ወእንዘ ዘንተ ይሔሊ ናሁ አስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር ለዮሴፍ በሕልም።
ታሪክ …
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
21/06/2011 ዓ.ም

Tuesday, February 26, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 20



====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
                  ******
፲፯፡ ወኵሎንኬ ትውልድ እምአብርሃሞ እስከ ዳዊት ፲ወ፬ቱ፡፡
                  ******
፲፯፡ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ ነው።
 ወእምዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ትውልድ ፲ወ፬ቱ።
ከዳዊት እስከ ፄዋዌ ፲፬ ትውልድ ነው። ወእምፍልሰተ ባቢሎን እስከ ክርስቶስ ትውልድ ፲ወ፬ቱ። ከፄዋዌ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው።
ወኵሎንኬ ትውልድ እምአብርሃም እስከ ክርስቶስ ፵ ወ፪ቱ። ከአብርሃም እስከ ክርስቶ መላው አንድ ሁኖ ቢቈጠር አርባ ሁለት ነው። ፲ወ፬ቱ ፲፵፬ቱ ፲ወ፬ቱ ይላል። አርባ ሁለት ይሆናል። አሥራ አራት አሥራ ሰባት አሥራ ሁለት ይላል አርባ ሶስት ይሆናል። አሥራ አራት አሥራ ሰባት አሥራ አራት ይላል አርባ አምስት ይሆናል። አርባ ሁለት ያለ እንደ ሆነ ሁለቱን አግብቶ ሦስቱን ነገሥታት አውጥቶ። አርባ ሦስት ያለ እንደሆነ ከሦስቱ አንዱን አግብቶ ሁለቱን አውጥቶ። አርባ አራት ያለ እንደሆነ ከሁለቱ ከእመቤታችንና ከኤልያቄም አንዱን አግብቶ አንዱን አውጥቶ። አርባ አምስት ያለ እንደሆነ መላውን አግብቶ። ከፍ ብሎ አርባ ስድስት ዝቅ ብሎ አርባ አንድ ቢል ግድፈተ ጸሐፊ ነው። ተርትሮ የቈጠረውን ደምሮ፤ ደምሮ የቈጠረውን ተርትሮ ቈጠረ። ደምሮ የቈጠረውን ተርትሮ ተርትሮ የቈጠረውን ደምሮ ባይቈጥር አይሁድ ወንጌላዊ ተርትሮ መቊጠር እንጂ መደመር፤ መደመር እንጂ ተርትሮ መቊጠር አይሆንለትም ብለው ደገኛዩቱን ሕገ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበርና።
አንድም ተርትሮ መቊጠር የሦስትነት ደምሮ መቊጠር ያንድነት ምሳሌ። አንድም ተርትሮ መቊጠር እንደ ሦስት ምስክር ደምሮ መቊጠር ቃሉ አንድ የመሆኑ ምሳሌ። ልማ በሥሉስ ጥፋ በሥሉስ እንዲሉ። አንድም በዳንኤል ልማድ ፸ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ ያለውን ተርትሮ የቈጠረውን ደምሮ፤ ደምሮ የቈጠረውን ተርትሮ እንደ ቈጠረ። አንድም በሦስቱ ክፍለ ዘመን የተቈጠረውን ባንድ በጌታ እንደተፈጸመ ለማጠየቅ። በዘመነ አበው በዘርዕከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር ተብሎ በዘመነ ነገሥት እስመ እምፍሬ ከርሥከ አነብር ዲበ መንበርከ በዘመነ ካህናት መቅደስ ትትሐነጽ እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ወእምዝ ትትመዘበር ተብሎ የተነገረው ተስፋ ባንድ በጌታ እንደ ተፈጸመ  ለማጠየቅ።
አንድም ተርትሮ ቈጠረ ሥጋዊ ምግብና ሲለዋወጥ መጥቷል። በዘመነ አበው ምክር ተግሣፅ ሁኑዋል ያባት ለልጅ ያልፍ ነበር መጻሕፍት አልተጻፉም፤ በዘመነ መሳፍንት መጸሕፍት ተጽፈዋል መስቀል መቊረጥ ሁኑዋል። በዘመነ ካህናት እንደ ሁለቱም ሁኑዋል እንደ ዘመነ አበው ምክር ተግሣፅ ሁኑዋል። ያባት ለልጅ የማያልፍ ሁኑዋል። እንደ ዘመነ መሳፍንትም መስቀል መቊረጥ ሁኑዋል መጻሕፍት ተጽፈዋል። ደምሮ ቈጠረ መንፈሳዊ ምግብና ምንም በካህናት በኤጲስ ቆጶሳት እጅ ቢሆን አልተለወጠም አንድ ነው ለማለት።
አርባ ሁለት ባለው ለሰሎሞን ስድስት እርከን ያላት አትሮንስ ነበረችው።፡ እሱ በስድስተኛዪቱ ሁኖ ነገር ሲሰማ ሲፈርድ ይውል ነበር። ስድስቱ እርከን በሱባዔ ሲገቡት አርባ ሁለት ይሆናል። ያርባ ሁለቱ አበው ምግብና ሲፈጸም ጌታ ሰው የመሆኑ ምሳሌ። ሰሎሞን የጌታ አትሮንስ የእመቤታችን ምሳሌ።
አርባ ሶስት ባለው ለደብተራ ኦሪት አርባ ሦስት አዕማድ ነበሯት አርባ ሦስት አዕማደ ትስብእት አበው ሲፈጸሙ ጌታ ሰው ለመሆኑ ምሳሌ። አርባ አራት ባለው እስራኤል በአርባ አራተኛው ጉዞ ሰጢን ሰፍረው ርስታቸውን አይተው አድረዋል እንደዚህ ምዕመናንም ከአርባ አራተኛዪቱ ትውልድ ከእመቤታችን ተወልዶ ርስታቸው ጌታን አይተዋልና።
አርባ አምስት ባለው በአርባ አምስተኛው ጉዞ እየርስታቸው ገብተዋል። እንደዚህ ሁሉ ምዕመናንም አርባ አምስተኛ ትውልድ የሚሆን ርስታቸው ጌታን ይወርሳሉና።
                  ******
በእንተ ልደተ ክርስቶስ።
፲፰፤ ወለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመዝ ውእቱ ልደቱ።
፲፰፤ የነትዕማርን የነራኬብን የነሩትን ሲናገር መጥቶ ነበርና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ እንዲህ ነው አለ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
20/06/2011 ዓ.ም