====================
የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ
ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ
፩።
******
፩፡
መጽሐፈ ልደቱ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
******
ወንጌላውያን
ሲጽፉ ራሳቸውን መሠረት አያደርጉም፡፡ ሌሎች ግን ራሳቸውን መሠረት ያደርጋሉ፡፡ ምንም የሚገልጽላቸው መንፈስ ቅዱስ ቢሆን የሚጽፉ
ከራሳቸው አንቅተው ነውና። ዳግመኛ ካንድ አገር ሁነው ጽፈው ወደ አንዱ አገር ይሰዱታልና። ወንጌላውያን ግን የሚጽፉ ጌታ የተናገረውን
ነው እንጂ ከራቸሳው አንቅተው አይደለምና በመካከል ሁነው ይጽፋሉና። ዳግመኛ ምንም አንዱም አንዱ ወሀሎ ፩ዱ ብእሲ ቢል ነንር ለማያያዝ
ነው።
፩፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ ቍጥር ይህ ነው። ጸሐፊዮ ለብእሲ ከመ ዘሞተ ወበውእቱ መዋዕል ወፅአ ትእዛዝ እምኀበ አውግስጦስ
ቄሣር ከመ ይጸሐፍ ኵሉ ዓለም እንዲል። አንድም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ ወግ ታሪክ ይህ ነው። ስማ ለዳቤር ትካት ሀገረ
መጽሐፍ እንዲል። የወግ የታሪክ ሀገር ሲል ነው። ወግ የነትእማርን የነራኬብን የነሩትን ያመጣል። ታሪክ ወለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ
ከመዝ ውእቱ ልደቱ ብሎ ያመጣል፡፡ ልደቱ ለእግዚእነ አለ፡፡ ብዙ ልደታት አሉና ከዚያ ሲለይ፡፡ ልደተ አዳም እምድር፣ ልደተ ሔዋን
እምገቦ፣ ልደተ አቤል እምከርሥ፣ ልደተ በግዕ እም ዕፅ፣ ልደተ ሙታን እመቃብር አለ። እኒያ አውጭ ይሻሉ። እሱ ግን በገዛ ሥልጣኑ
ነውና። የልደቱን ነገር ብቻ ይናገራልና መጽሐፈ ልደቱ አለ ምነው ቢሉ። መጽሐፍ ባንድ መጀመር ኋላ ብዙ ማምጣት ልማድ ነው። ከዚያ
ሁሉ ኦሪት ዘልደት ይላል። የሥነ ፍጥረትን ብቻ ተናግሮ ይቀራልን? መጽሐፈ ልደቱ ባለው በጥቁር አንድ ይላል የንዑስ ምዕራፍ አኃዝ
ነው፡፡
ማቴዎስ
መጽሐፈ ልደቱ፣ ማርቆስ አንተ ውእቱ ወልድየ፣ ሉቃስ ወይመስሎሙ ወልደ ዮሴፍ፣ ዮሐንስ ቀዳሚሁ ቃል ያለውን ሁሉም የጌትነት ነገር
ከሆነ ብሎ አራቱ የተባበሩበት ሲል ፩ዱ ይላል፡፡ ፫ቱ ቢል ማርቆስን አውጥቶ፡፡ በሦስተኛው ሰንጠረዥ ማርቆስ የለምና።
ወልደ
ዳዊት ወልደ አብርሃም ሉቃስ ፫፥፴፩፡፡ የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ፡፡
ከነገሥታት
ዳዊት ከአበው አብርሃም ብቻ ይወልዱታልና እንዲህን አለ ቢሉ። ትንቢት የተነገረ ለኒህ ነውና። ትንቢትማ ከነገሥታት ለሰሎሞን አነ
እከውኖ አባሁ ወውእቱ ይከውነኒ ወልድየ ተብሎ። ከአበውም ለሴም ለይኅድር እግዚአብሔር ውስተ ቤቱ ለሴም ተብሎ ተነግሮ የለም ቢሉ
የሚበዛ የሉህ ነውና በሚበዛው ተናገረ፡፡
አንድም
ተስፈ ለተስፋ ሲያነጻጽር በዘፀአከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር ያለውንና እስመ እምፍሬ ከርሥከ አነብር ያለውን ተስፋ ለተስፋ
ሲያነጻጽር።
አንድም
ዳዊት ሥርወ መንግሥት ነው አብርሃምም ሥርወ ሃይማኖት ነውና። እስመ አብርሃም ኮነ ሥርወ ሃይማኖትነ ወሃይማኖቶሙ ለአይሁድ እንዲል።
የዳዊትን ሥርወ መንግሥትነት ኋላ ያመጻል፡፡
አንድም
እግዚአብሐር ፈጣሪያቸውን ዳዊት ንጉሣቸውን ወያኃሥሥዎ ለእግዚአብሔር አምላኮሙ ወለዳዊት ንጉሦሙ እንዲል፡፡ ዳዊትንም ከመውደዳቸው
የተነሣ የነገሠውን ሁሉ ዳዊት ይሉት ነበር። ወሶበ ሰምዓ ዘንተ ዳዊት ደንገፀት ነፍሱ ወነፍሰ ኵሉ ሕዝቡ እንዲለው አካዝን።
አንድም
ያላመኑት ያመኑትን ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መሆኑን ሰፍራችሁ ቈጥራችሁ አስረክቡን ብለዋቸው ነበርና ስለዚሀ እንዲህ አለ። ክፍለ
ዘመንም ለመናገር። በዚያውስ ላይ አብርሃም አይቀድምም ዳዊት አይከተልም ቢሉ አባቱን አያውቅ አያቱን ይናፈቅ ይሉኛል ብሎ፡፡ ለጌታም
ከአብርሃም ዳዊት ይቀርበዋልና።
አንድም
እርካብ ተረግጦ ወደ ኮርቻ መውጣት ባዳራሽ ገብቶ ወደ እልፍኝ ማለፍ እንዲመች። ወልደ ዳዊት ብሎ ወልደ አብርሃም ሲሉ ይመቻልና።
አንድም
ጌታን ወልደ ዳዊት ዳዊትን ወልደ አብርሃም አለው፡፡
አንድም
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ዋዌ የቀረው ነው፡፡
አንድም
የጌታ ጥቅል ስሙ ነው፡፡ ዕውራን በሆሣዕና ተሣሃለነ ወልደ ዳዊት እንዳሉ። ወልደ አብርሃም ብሎ ለጌታ ቀጸለለት፡፡
አንድም
ይዞ ለመሄድ ይመቸኝ ብሎ ይዞት የሚሄድ አብርሃምን ነውና ወደ ኋላ አደረገው።
******
፪፡
አብርሃም ወለዶ ለይስሐቅ።
******
፪፡
አብርሃም ይስሐቅን ወለደው፡፡
ከአጋር
የተወለደ እስማኤል ከኬጡራ የተወለዱ ፯ቱ ሕፃናት ያሉ አይደለምን? ስለምን ይስሐቅን ለይቶ አነሣው ቢሉ ነቢይ የሆነ እንደሆነ ልደተ
አበውን ጠንቅቆ ይቈጥራልና መላውን ያነሣል። ወንጌላዊ ግን የሚሻ የጌታን ልደት ነውና። የጌታም መወለድ ከይስሐቅ ነው እንጅ ከነዚያ
አይደለምና።
አንድም
ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም። ትንቢት እምይስሐቅ ይሰመይ ለከ ዘርዕ ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌ ይስሐቅ መሥዋዕት ሁኖ ቀርቧል። ጌታም መሥዋዕት
ሁኖ ይቀርባልና።
ወይስሐቀኒ
ወለዶ ለያዕቆብ፡፡
ይስሐቅም
ያዕቆብን ወለደ።
እነዚያስ
ዕለት እናት ባያገናኛቸው ነው እኒህማ ዕለት እናት አገናኝቷቸው ፩ድ ቀን ተጸንሰው አንድ ቀን የተወለዱት ኤሳውን ስለምን ለይቶ
ተወው ቢሉ። ነቢይ የሆነ እንደሆነ ልደተ አበውን ጠ ንቅቆ ይቈጥራልና መላውን ያነሣል፡፡ ወንጌላዊ ግን የሚሻ የጌታን ልደት ነውና፡፡
የጌታም መወለድ ከያዕቆብ ነው እንጂ ከኤሳው አይደለምና።
አንድም
ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም። ትንቢት ኮከብ ይሠርቅ እምያዕቆብ ወያአትት ኃጢአተ እምእስራኤል ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌም በጸውዖተ ሐዋርያት አብዝተው ያመጣሉ ከዚያው ከፍለው ይናገሩታል። ያዕቆብ ከወንድሙ ከኤሳው ተጣልቶ
ወደ አጐቱ ወደ ላባ ሲሄድ ከምንጭ አጠገብ ደረሰ። ውኃው ደንጊያ ተገጥሞ አባግዕ ከደንጊያው ሰፍረው ኖሎት ተሰብስበው አገኘ። ምነው
ከፍታችሁ አታጠጧቸውም አላቸው። መላው ኖሎት እንጂ ካልተሰበሰቡ ከፍቶ ማጠጣት አይሆንልንም አሉት። ውኃው ኩሬ ነው ጠላት ጥቂት
ራሱን ሁኖ መጥቶ መርዝ እንዳይበጠብጥበት ለ፶ ለ፷ የሚከፈት ደንጊያ ገጥመው ይሄዳሉ። እሱ ብቻውን ከፍቶ አጠጥቶላቸዋል፡፡ ያዕቆብ
የጌታ፣ ደንጊያው የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ፣ ውኃው የጥምቀት፣ አባግዕ የምዕመናን፣ ኖሎት የነቢያት የካህናት ምላሌ፡፡
ወያዕቆብኒ
ወለደ ይሁዳሃ ወአኃዊሁ።
(ዘፍ
፳፩፥፫፡፡ ፳፭፥፳፭፡፡ ፳፱፥፴፭፡፡)
ያዕቆብም
ይሁዳን ወንድሞቹን ወለደ። የይስሐቅን ልደት በተናገረ ጊዜ እለ እስማኤልን፣ የያዕቆብን ልደት በተናገረ ጊዜ ኤሣውን አላነሣ ከዚህ
አሁን ደርሶ ይሁዳሃ ወአኃዊሁ አለ ምነው ቢሉ ጌታ ካሥራ ሁለቱ ነገድ ይወለዳልና፡፡
አንድም
ነቢይ ቢሆን አባቶቻችንን ከቍጥር አይለያቸውም ነበር ወንጌላዊ ስለምን ለይቶ ተዋቸው ብለው አይሁድ ደገኛዪቱን ሕገ ወንጌልን ከመቀበል
በተከለከሉ ነበርና።
አንድም
ለምሳሌ ይመቸኝ ብሎ፡፡ ካሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ያልተወለደ ምድረ ርስትን አይወርስም፡፡ ያሥራ ሁለቱ ሐዋርያትንም ትምርት ያልተቀበለ
መንግሥተ ሰማያትን አይወርስምና፡፡ ያውስ ቢሆን ይሁዳን ለይቶ ማንሣቱ ስለምነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም፡፡ ትንቢት ኢይጠፍዕ
ምስፍና ወምልክና እምአባሉ ለይሁዳ እስከ አመ ይረክብ ዘጽኑሕ ሎቱ ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌውን አሁን ያመጣል። ዘፍ ፵፱፥፲።
******
፫፡
ወይሁዳኒ ወለደ ፋሬስሃ ወዛራሃ እምትዕማር፡፡
******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ
በየነ
ደብረ
ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
13/06/2011
ዓም
No comments:
Post a Comment