=====================
ብሥራተ ማቴዎስ ሐዋርያ ፩ዱ
እም ፲ ወ ፪ቱ ሐዋርያት ጸሎቱ ወበረከቱ የሀሉ ምስለ ፍቁሩ ለዓለመ ዓለም አሜን።
ይህ ቃል የሠለስቱ ምእት
ቃል ነው ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ እግዚአብሔር እምቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን በነቢያት ያናገረውን ለመፈጸም ሥጋ ሆነ
፤ ሥጋም ሁኖ ሕግ ጠባይዓዊን ሕግ መጽሐፋዊን ሲፈጽም አደገ፡፡
ሕግ ጠባይዓዊ በየጥቂቱ ማደግ
ነው ። ልህቀ በበሕቀ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ እንተ ይእቲ እሙ እንዲል ፤ ሕግ መጽሐፋዊ ሕገ ኦሪትን መፈጸም ነው ። አግዚአ
ለኦሪት ገብረ በሕገ ኦሪት ከመ ይሣየጦሙ ለእለ ውስተ ኦሪት ወገብረ በሕገ ኦሪት አንዲል፡፡ ሕገ ኦሪትን መፈጸም እንደምነው ቢሉ
በ፰ ቀን ቤተ ግዝረት መግባት በ፵ ቀን ዕጓለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዞ ከቤተ መቅደስ መግባት ካመት ሦስት ጊዜ ለገቢረ በዓል መውጣት
ነው። ፫ተ ጊዜያት ለለዓመት ለያስተርኢ ተባዕትከ እንዲል ። በቀሩት ግን ከ፳ ዓመት በታች እንዳይወጡ ሥርዐት ተሠርቶባቸዋል እሱ
ግን አሥራ ሁለት ዓመት ሲሆነው ወጥቷል ፤ መውጣቱ ለማስተማር ነው እንጂ ለሌላ አይደለምና እንዲህ እንዲህ እያለ ፴ ዘመን ሲመላው
በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ልጅነቱን አስመስክሮ ገዳም ሄደ ።
ገዳም ሄዶም ፵ መዓልት ፵
ሌሊት ጾመ መዋዕለ ጾሙ ሲፈጸም ሰይጣን በ፫ ነገር ተፈታተነው ፤ በስስት በትዕቢት በፍቅረ ንዋይ፡፡ በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት፣
በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና፣ በፍቀረ ንዋይ ቢመጣበት በጸሊዓ ንዋይ፣ ድል ነሣው ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የሚያሰኙ እሊህ ናቸው
። ዛሬም በሊህ ድል ለነሣ ሰው የቀሩት ኃጣውእ አይቆሙለትም፡፡
ከዚህ በኋላ ምድረ እሥራኤል
ገብቶ ትምህርት ታምራት ጀመረ የእጅ ታምራት አይተው የቃሉን ትምህርት ሰምተው ካሥር አህጉር ከብዙ መንደር ተውጻጽተው ያምስት ገበያ
ያህል ሰዎች ተከተሉት፡፡ ከሊህ መቶ ሃያ ቤተ ሰብእ ይመርጣል አስቀድሞ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት። ወረሰየ እምሰብአ ዚአሁ ሐዋርያት
እንዲል ፤ ቀጥሎ ሰባ ሁለቱን አርድእት ። አርአየ ወኃረየ ካልዓን ሰብአ እንዲል ፤ ፸ም ይላል በአኃዝ ቀጥሎም ሠላሳ ስድስቱን
ቅዱሳት አንስት መቶ ሃያ ቤተሰብ የሚያሰኙ እሊህ ናቸው፡፡ በሊህ ትምህርት አይከፈልባቸውም ካደረበት ያድራሉና ። የቀሩት ግን ሲማሩ
እየዋሉ ምሽት ይከለክላቸው ነበር ። ላሥራ ሁለቱ ነገደ እሥራኤል በየፃቸው እየገባ ወር ወር ይሰብክላቸው ነበር፡፡ ሦስት ዓመት
ከሦስት ወር አስተምሮ ትምህርቱ በምር ሲረዳለት ለመድኃኒተ ዓለም በቀራንዮ ተሰቀለ ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር ኢይደልዎ ለነቢይ
መዊት በአፍኣ ዘእንበለ በኢየሩሳሌም እንዲል ፤ ተሰቅሎም በሞቱ ዓለምን አድኖ ፫ መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ
።
እስመ ውእቱ ቀሰፈነ ወይፌውሰነ
ውእቱ አቍሰለነ ወይሤርየነ ወያሐይወነ በሰኑይ መዋዕል ፤ ወአመ ሣልስት ዕለት ንትነሣእ ። ወአመ ሣልስት ዕለት ሦጣ ለነፍስ ውስተ
ሥጋሁ እንዲል ፤ ተነሥቶም መጽሐፈ ኪዳንን ፵ ቀን ለሐዋርያት አስተማረ ። ጉባኤ ሠርቶ ግን ያስተማራቸው ሦስት ቀን ነው ። የትንሣኤ፣
የአግብኦተ ግብር፣ የጥብርያዶስ ወዝንቱ ሣልሱ ለእግዚእነ እንዘ ያስተርአዮሙ ለአርዳኢሁ እምድኅረ ተንሥአ እሙታን እንዲል ። በበዛው
መናገር ነው እንጂ ላንዱም ለሁለቱም ለሦስቱም ባለሟሎቹ ሳይገለጽላቸው አይውልም አያድርም ነበር፡፡
፵ው ቀን ሲፈጸም አንተሙስ
ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም ብሎ አዟቸው ዓረገ ። ባረገ ባሥረኛው በተነሣ ባምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን
ሰደደላቸው ። እስከዚያ ወዴት ኑሮ ቢሉ ባሥረኛው መዓርግ የገባን እኛ ነበርንና ከጥንት ቦታችን እንደመለሰን ለማጠየቅ፡፡ አንድም
በዘጠኙ ከተማ ያሉ መላእክት ሥጋዌውን ያላወቁ ነበሩና ለኒያ ሲያስተምር፡፡ ይህማ እንዳይሆን ፈጣሪ ፍጡር ይመስል አንዱን ሥራውን
ሲሠራ ባንዱ ይከለከልበታል ወዲያስ ቢስተምራቸው ወዲህስ ቢሰድላቸው ይሣነዋል ብሎ ሐተታ ከቀደመው ይገባል ። አንድም አሥሩን ቃላት
፲ን ሕዋሳት ጠብቄ ሰጠኋችሁ እናንተም ብትጠብቁ ፤ ይሰጣችኋል ለማለት ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ፍሩሃን የነበሩ ጥቡዓን
ሆኑ ። ከብልየት ታደሱ በአእምሮ ጎለመሱ ምሥጢር ተረጐሙ ፤ ፩ድ ቋንቋ ያውቁ የነበሩ ፸፩ ቋንቋ ተጨመረላቸው ፤ ዓመት በኅብረት
መዲናቸው ኢየሩሳሌምን አስተማሩ ወነበሩ ዓመተ ፍጽምተ በኢየሩሳሌም እንዲል ።
ከዚህ በኋላ ሑሩ ወመሐሩ
ያላቸውን ነገር ያውቃሉና ዕፃ በዕፃ ብለው ይህነን ዓለም ተካፍለው ለማስተማር በሚወጹበት ጊዜ ምድረ ፍልስጥኤም ለማቴዎስ በዕፃ
ደረሰችው፡፡ ከዚህ ገብቶ ጌታ ከፅንስ ጀምሮ ያደረገውን ታምራት ያስተማረውን ትምህርት የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው እሥራኤል ናቸውና
ከአሪት ወደ ወንጌል ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሱ አመኑ ተጠመቁ ። ትምህርት ካልደረሰበት ለማዳረስ ወጥቶ በሚሄድበት
ጊዜ በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ጻፍልን ብለውት በዚህ ምክንያት ይጽፋል፤ አንድም እሱ እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ
ይጽፍላቸዋል ። አንድም በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁድ እስጢፋኖስን በደንጊያ ወግረው ከገደሉ በኋላ እስጢፋኖስ ነበር እንጂ ባፍና
በመጣፍ የማይቻል የቀሩትንስ ሐዋርያት መበተን አይሳነንም ብለዋል፡፡
ሐዋርያትም ይኽን ሰምተው እንከሰ ንትመየጥ መንገለ አሕዛብ ብለዋል፤ ያመኑት እኛ ሐዲሳን አትክልት ነን ካልጻፋችሁልን
እንደምን ይሆናል ብለዋቸው በዚህ ምክንያት ይጽፋል አንድም ያላመኑት አይሁድ ያመኑትን ክርስቶስን ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ነው
ትሉታላችሁ እንጂ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መሆኑን እስኪ ሰፍራችሁ ቆጽራችሁ አስረክቡን ብለዋቸዋል እሳቸውም በዕውቀት ፍጹማን
አይደሉምና ከግብር ገብቶ ማስረዳት ቢሳናቸው ይልኩበታል ።
ሶቤሃኬ ተንሥአ ማቴዎስ ከመ
ተንሥኦተ ማይ ላዕለ እሳት እንዲል ተናዶ ተነሥቶ በዚህ ምክንያት ይጽፋል፡፡ አጻጻፉም ስለ፭ት ነገር ነው፡፡ ክፍለ ዘመንን ለመናገር
፤ በዘር በሩካቤ ተወለደ ብለውታልና፡፡ ዘእንበለ ይትቃረቡ ተረክበት
ፅንስተ እመንፈስ ቅዱስ ለማለት ዮሐንስ የአብዮ ብለውታልና ዘኢይደልወሂ ዕጹር ቶታነ አሣዕኒሁ እምእገሪሁ ለማለት፡፡ በብዔል ዜቡል
ያወፅኦሙ ለአጋንንት ብለውታልና በመንፈሰ እግዚአብሔር ያወፅኦሙ ለአጋንንት ለማለት፡፡ ፩ዱ እምነቢያት ብለውታልና እግዚአ ነቢያት
እንደሆነ ለማጠየቅ ፤ መዋዕለ ጽሕፈተ ማቴዎስ ጌታ ካረገ ስምንት ቢሉ ሲፈጸም ዘጠኝ ቢሉ ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው
ዓመት፡፡ ማርቆስ ጌታ ካረገ ዐሥራ አንድ ቢሉ ሲፈጸም ዐሥራ ሁለት ቢሉ ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ ባራተኛው ዐመት ሉቃስ
ጌታ ካረገ ሀያ አንደኛው ተፈጽሞ ሀያ ሁለተኛው ሲጀመር ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ ባሥራ አራት ዓመት ። ዮሐንስ ጌታ ካረገ በሠላሳ
በሠላሳ አምስትም ይላል ኔሮን ቄሣር በነገሠ በሰባት ቢሉ ሲፈጻም በስምንት ቢሉ ሲጀመር፡፡ ጸሐፍቱም ሁለቱ ከሐዋርያት ሁለቱ ከአርድእት
ናቸው ።
ሐዋርያት ጨርሰው እንዲጽፏት
ያላደረገ ሁለቱን ከአርድዕት ያጻፈ ስለምን ቢሉ ስለ ክብረ አርድእት፡፡ ጨርሰው ሐዋርያት ጽፈዋት ቢሆን አርድእት ለማስተማር በወጡ
ጊዜ እኒህማ የአፍአ ሰዎች እንጂ ናቸው የውስጥማ ሰዎች ቢሆኑ ደጊቱን ሕገ ወንጌልን ባጸፋቸውም ነበር ብለው አይሁድ ትምህርታቸውን
ከመቀበል በተከለከሉ ነበርና፡፡ ያውስ ቢሆን ጨርሰው አርድእት እንዲጽፏት ያላደረገ ሁለቱን ከሐዋርያት ያደረገ ስለምን ቢሉ ስለ
ክብረ ወንጌል፡፡ ጨርሰው አርድእት ጽፈዋት ቢሆን ይህችማ እንጂ ተርታ ሕግ ናት ደጊቱማ ሕግ ምሥጢረ ታምራትን በቤተ ኢያኤሮስ ምሥጢረ
መንግሥትን በደብረ ታቦር ምሥጢረ ምጽአትን በደብረ ዘይት ምሥጢረ ጸሎትን በጌቴሴማኒ ባዩ አዕማደ ምድር በተባሉ በልበ ሐዋርያት
እንጂ ቀርታለች እያሉ አይሁድ ደገኛይቱን ሕገ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበርና፡፡
ያውስ ቢሆን ጸሐፍቱን ከፍ
ብሎ አምስት ስድስት ዝቅ ብሎ ሁለት ሦስት ያላደረገ አራት ያደረገ ስለምን ቢሉ ጌታ ባራት በአራት ወገን የሠራው ብዙ ሥራ አለና
በዚያ መስሎ ለመናገር በዚያውስ ላይ ሥርዓተ ምድር ተሠርዓ በሥርዓተ ሰማይ እንጂ ይላል፤ በሰማይ አራት ጸወርተ መንበር ኪሩቤል
አሉ። ምነው ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ ኩሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ አጽናፈ ዓለም በእራሁ እንዲል። እሱ ይሸከማቸዋል እንጂ እሳቸው
ይሸከሙታል ቢሉ በዘፈቀደ የሚገለጽባቸው መንበሩን ተሸክመው የሚታዩ የሚቀድሱት በጸጋ የሚያድርባቸው ስለሆነ እንዲህ አለ እንጂ የሚሸከማቸውስ
እሱ ነው ።
እሊህም ገጸ ብእሲ ገጸ አንበሳ
ገጸ ላህም ገጸ ንስር ናቸው ።
ማቴዎሰ በገጸ ብእሲ ይመሰላል።
ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም እያለ ምድራዊ ልደቱን ይጽፋልና፡፡
ማርቆስ በገጸ አንበሳ ይመሰላል፡፡
አንበሳ ኑሮው ከሰው ርቆ በምድረ በዳ ነው ከዚያ ሁኖ ጣሕሩን ባሰማ ጊዜ እንስሳት ይገሠጻሉ አራዊት ይደነግጣሉ። ማርቆሰም ከተምርት
ምድረ በዳ በምትሆን በግብጽ ቀዳሚሁ ለወገጌለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ብሎ ባስተማረ ጊዜ ምእመናን ተገሥጸዋል አጋንንት መናፍቃን
ደንግጸዋልና፡፡ ዳግመኛም አንበሳ ለላህም ጌታው ነው ይሰብረዋል። እሱም ከግብጽ አምልኮተ ላህምን አጥፍቷልና፡፡ ከትምርት ምድረ
በዳነቷንም ከዚህ ይናገራሉ፡፡ ቀድሞ ሙሴ አሮን ኋላም እለ ኤርምያስ ወርደው ቢያስተምሯት አልተጠቀመችም ፍጹም ጥቅሟ ማርቆስ ነውና፡፡
ሉቃስ በገጸ ላህም ይመሰላል
አምጽኡ ላህመ መግዝዓ ወጥብሑ ንብላዕ ወንትፈሣሕ ምስሌሁ እያለ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡
ዮሐንስ በገጸ ንስር ይመሰላል፡፡
ንስር በእግሩ ይሽከረከራል በክንፉ መጥቆ ይበራል በእግሩ እንዲሽከረከር እሱም እንደ ወንድሞቹ ወልደ እጓለ እመሕያው ወረደ እምሰማይ
ብሎ ይጽፋል። በክንፍ መጥቆ እንዲበር እሱም አካል ከህልውና ተገልጾለት ቀዳሚሁ ቃል ብሎ ተናግሯልና፡፡ አንድም አንስር ዘእሙር
በብርሃነ አዕይንቲከ እንዲል የንስር ዓይኑ ጽሩይ ነው ሽቅብ ወጥቶ ረቦ ቁልቁል በተመሰከተ ጊዜ የስናፍጭ ቅንጣት ታህል ሥጋ ብትሆን
አትሰወረውም ያችን አንሥቶ ይመገባታል። እሱም አካል ከህልውና ተገልጾለት ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ተሰጥቶት ቀዳሚሁ
ቃል ብሎ ተናግሯልና፡፡
አቃወማቸውንም ከዚህ ይናገራሉ፡፡
ገጸ ብእሲ አቀዋወሙ በምሥራቅ ፊቱ ወደ ምዕራብ። ገጸ አንበሳ አቀዋወሙ በምዕራብ ፊቱ ወደ ምሥራቅ ገጸ ላህም አቀዋወሙ በሰሜን
ፊቱ ወደ ደቡብ ፤ ገጸ ንስር አቀዋወሙ በደቡብ ፊቱ ወደ ሰሜን፡፡ ማቴዎስ ጽፎ ለማርቆስ ደቀ መዛሙርት ፤ ማርቆስ ጽፎ ለማቴዎስ
ደቀ መዛሙርት ሉቃስ ጽፎ ለዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ዮሐንሰ ጽፎ ለሉቃስ ደቀ መዛሙርት መስጠታቸውን መናገር ነው፡፡ ወንጌል በጥንተ ስብከት የደረሰችበትን መናገር ነው እንጂ ኋላሰ ከሁሉ ደርሳለች።
በ፬ቱ አፍላጋት ይመሰላሉ።
እሊህ ከገነት ካንድ ከዕፀ ሕይወት ሥር ነቅተው ውኀነታቸውን ይህን ዓለም ዙረው አጠጥተው ዕፅዋትን ከይብስት ወደ ልምላሜ ከልምላሜ
ወደ ጽጌ ከጽጌ ወደ ፍሬ ያደርሳሉ። አራቱ ወንጌላውያንም ወንጌልን ካንድ ከጌታ ተምረው ይህን ዓለም ዙረው አስተምረው ምእመናንን
ከይብሰተ ኃጢአት ወደ ልምላሜ ንስሐ ከልምላሜ ንስሐ ወደ ጽጌ ትሩፋት ከጽጌ ትሩፋት ወደ ፍሬ ክብር ያደርሳሉና፡፡
እኒህም ኤፌሶን ግዮን ጤግሮስ
ኤፍራጥስ ናቸው ።
ኤፌሶን ፈለገ ሀሊብ ነው።
ርስትነቱም የሕፃናት ርስት ነው ማቴዎስ በዚህ ይመሰላል። ከመ ሀሊብ ሀለብክኒ ወከመ ግብነት አርጋዕከኒ እንዲል በዘር የሚወለዱ
የአበውን ልደት ይጽፋልና ዳግመኛ ሄሮድስ ያስፈጃቸውን የሕጻናትን ነገር ይናገራልና ግዮን ፈልገ ወይን ነው ርስትነቱም ቢጾሙ ቢስ
ልዩም ሥራቸውን ደስ ብሏቸው የሚሠሩ ሰዎች ርስት ነው። ማርቆስ በዚህ ይመሰላል። ወይን ያስተፌሥሕ ልበ ሰብእ እንጂ ይላል ወንጌሉን
ሁሉን ደስ በሚያሰኝ በዕርገት ይጨርሳልና። በዚህስ ሁሉም ይተባበሩበታል ብሎ ቅብዓ ትፍሥሕት መንፈስ ቅዱስ በሚሰጥበት በጥምቀት
ይጀምራልና፡፡ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ነው ርስትነቱም ጸዊረ ነገር የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው ። ሉቃስ በዚህ ይመሰላል። መዓር እንጂ
ክቡድ ነው። እሱም አባ ስረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ በትዕግሥትክሙ ታጠርይዋ ለነፍሰክሙ እያለ ክቡድ ክቡድ ነገር ይጽፋልና፡፡
ኤፍራጥስ ፈለገ ዘይት ነው፡፡ ርስትነቱም የሰማዕታት ርስት ነው። ዮሐንሰ በዚህ ይመሰላል ዘይት ጽኑዕ ነው። እሱም ጽንዑ እስመ
አነ ሞእክዎ ለዓለም እያለ ይጽፋልና። ዘይት ብሩህ ነው የሰውን ልቡና በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና፡፡ ዳግመኛም ዘይት እራቱን ሽቱ
ስቦ በመዓዛ አንድ ያደርጋቸዋል እሱም ወንድሞቹን በምሥጢር ይበዘብዛቸዋልና ነቅዓቸውንም ከዚህ ይናገራሉ፡፡
ቦ ዘይወፅእ እምሥራቅ ወየሐውር
ለምዕራብ ከመ ይሰቂ ዘህየ ። ቦ ዘይወፅእ እምዕራብ ወየሐውር ለምሥራቅ ከመ ይሰቂ ዘህየ ፤ ቦ ዘይነቅዕ እምሰሜን ወይሠወጥ ለደቡብ
ከመ ይሰቂ ዘህየ ። ቦ ዘይነቅዕ እምደቡብ ወየሐውር ለሰሜን ከመ ይሰቂ ዘህየ እንዲል። ማቴዎሰ ጽፎ ለማርቆስ ደቀ መዛሙርት ፤
ማርቆስ ጽፎ ለማቴዎስ ደቀ መዛሙርት ሉቃስ ጽፎ ለዮሐንስ ደቀ መዛሙርት
፤ ዮሐንስ ጽፎ ለሉቃስ ደቀ መዛሙርት መስጠታቸውን ወንጌል በጥንተ ስብከት የደረሰችበትን መናገር ነው እንጂ ከዚህ በኋላስ ከሁሉ
ደርሳለች፡፡ በ፬ቱ ነፋሳተ ምሕረት ይመሰላሉ ፤ ፬ቱ ነፋሳተ ምሕረት
፤ ለሰው ሕይወት ጽንዕ ይሆናል ፤ ሕይወት ለመሆናቸው እስመ ነፋሳት ነፍሳቲሆሙ ለማያት እስመ አምሁከተ ነፋሳት ንስሕቦ ለቁመተ
ሥጋነ እስመ ነፋስ ያገዝፎ ለፍሬ እንዲል ጽንዕ ለመሆናቸው ወገብረ
አዕማደ ሰማይ በነፋስ ። ወይዔምድ በነፋስ እሉ እሙንቱ እለ ይረብብዋ ለልዕልና ሰማይ ይላል። እኒህም በነፈሱ ጊዜ ለሰው አምስት
ነገር ይመጣለታል ፤ ጠል ዝናም ሕይወት በረከት ፈውስ ፤ አራቱ ወንጌላውያንም ባስተማሩ ጊዜ ለሰው አምስት ነገር ይገኛልና እንደ
ጠል ትምህርት እንደ ዝናም ሥጋው ደሙ እንደ ሕይወት ሕይወት መንፈሳዊ እንደ በረከት በረከት መንፈሳዊ ፤አንድም መላውም በረከተ
ኅብስትን ይጽፋሉና እንደ ፈውስ ፈውስ መንፈሳዊ አንድም ፈውስ ንስሐ ፬ቱ ነፋሳተ ምሕረት ያለሙትን የሚያጠፋ የለመለሙትን የሚያደርቁ
፰ ነፋሳተ መዓተ አሉ ። እሊህም በነፈሱ ጊዜ በሰው አምስት ነገር ይመጣል ፤ ይብሰት ሐሩር ድምሳሴ አንበጣ አናኩዕ ፬ቱ ነፋስተ
ምሕረት ያለመለሙትን የሚያደርቁ ያለሙትን የሚያጠፉ ፰ት ነፋስተ መዓት እንዳሉ ። ፬ቱ ወንጌላውያንም ያስተማሩትን የሚያስክዱ ያለሙትን
የሚያጠፉ ፤ ፰ ቤተ አይሁድ አሉ ። ኃጥአን መጸብሐን ፤ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን ረበናት መገብተ ምኩራብ ሊቃነ ካህናት ሞላሕቅተ
ሕዝብ ፤ አልመተ ዝዕላን የሚል አብነት ይገኛል መላሕቅተ ሕዝብ ማለት ነው፡፡ እኒህ ባስተማሩ ጊዜ በሰው ፭ ነገር ይታዘዛል ።
እንደ ይብሰት ይብሰተ አእምሮ እንደ ሐሩር መከራ እንደ ድምሳሴ ደጋግ ሰዎች በሥጋቸው ክፉ ሰዎች በነፍሳቸው የሚጎዱ ሁነዋል ።
እንደ አንበጣ ዓላዊ ንጉሥ መናፍቅ ጳጳስ እንደ አናኩዕ ብዝኃ ሠራዊት ፤ ፰ቱ ነፋሳተ መዓት በ፬ቱ ነፋሳተ ምሕረት ተወስነው ተገተው
እንዲኖሩ የ፰ ቤተ አይሁድም ትምህርት በ፬ቱ ወንጌላውያን ትምህርት ተወስኖ ተገቶ ይኖራልና ባራቱ ባሕርያት ይመሰላሉ ካራቱ ባሕርያት
የወጣ ፍጥረት የለም፡፡ ከ፬ቱ ወንጌለውያንም ትምህርት የወጣ የለምና በ፬ቱ መዓዝነ ዓለም ይመሰላሉ ከ፬ቱ መዓዝነ ዓለም የወጣ ፍጥረት
የለም ካራቱ ወንጌላውያንም ትምህርት የወጣ የለምና፡፡
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
11/06/2011 ዓም
No comments:
Post a Comment