Thursday, February 28, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 22


                ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
                  ******
፳፡ ወእንዘ ዘንተ ይሔሊ ናሁ አስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር ለዮሴፍ በሕልም።
                  ******
                  ******
ታሪክ። እመቤታችን የብፅዓት ልጅ ናት። ሦስት ዓመት ሲሆናት አባት እናቷ ወስደው ለካህናት ሰጡ። ክህናትም ተቀብለው አክብረው ከቤተ መቅደስ ያኖሯታል። አሥራ ሁለት ዓመት ትኖራለች ከዚያ ሶስት ከዚያ አሥራ ሁለት አሥራ አምስት ዓመት ይሆናል ። አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ይህች ብላቴና መጠነ አንስት አይረሰች ቤተ መቅደሳችንን ታሳድፍብናለች ትውጣልን አሉት። ዘካርያስ ሂዶ እንደምን ትሆኝ አላት። ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ አለችው። ቢያመለክት ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን በትር ሰብስበሀ ከቤተ መቅደስ አግብተህ አውጣው ምልክት አሳይልሃለሁ አለው። ቢሰበስብ ሽህ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ አምስት ለሁለት ሽህ አሥራ አምስት የጎደለው ማለት ነው። ያን አግብቶ ቢያወጣው ከዮሴፍ በትር ኦ ዮሴፍ ዕቀባ ለማርያም የሚል ተገኘ። ዕጣም ቢያወጡ ለሱ ወጣ። ርግብም መጥታ በራሱ ላይ አረፈች። እንደ ሦስት ምስክር ያም ሆነ ያም ሆነ ከእግዚአብሔር አግኝተን የሰጠንህን ከእግዚአብሔር አግኝተን እስክናሰናብትህ ወስደህ ጠብቅ አትንካ ብለው ሰጡት። ይዟት ሄደ።
ጊዜው ዓፀባ ነበርና ንግድ ሂዶ ሦስት ወር ኑሮ ቢመለስ ዮሐንስ የሚባል ፈላስፋ ወዳጅ ነበረው ሊጠይቀው መጣ። ተጨዋውተው ሲሄድ ሊሸኘው ወጣ። ይህች ብላቴና ፀንሳለች ከአንተን ነው ከሌላ አለው። እኔስ እንኳን ነቢብ ገቢር ሐልዮም አላውቅባት አለው። እንኪያስ ፀንሳለች ገብተህ ጠይቃት አለው። በምን አውቆ ቢሉ ፈላስፋ ነውና በመልኳ ገብቶ ኦ ወለተ እስራኤል መኑ ቀረጸ አክናፈ ድንግልናኪ ወእምኀበ መኑ ፀነስኪ ብሎ ጠየቃት። እመንፈስ ቅዱስ አለችው። ነገሩ ቢረቅበት ከደጁ ወድቆ የሚኖር ደረቅ ግንድ ነበርና ተክላ አለምልማ አሳይታዋለች። በዚያውስ ላይ አዕዋፍን ከባሕርያቸው እንዲራቡ አዕዋምን እንዲያፈሩ የሚያደርግ ማን ይመስልሃል አለችው ነገሩን ተረዳው።
ከዚህ በኋላ ለበዓል የሚወጡበት ጊዜ ደረሰ። ትቻት ብወጣ ያደረገችውን ታስታውቅ ከደረቷ ትታጠቅ እንዲሉ ያደረገውን አውቆ ትቷት መጣ ይሉኛል፤ ይዣት ብወጣ ሴሰነች ብለው በደንጊያ ወግረው ይገሉብኛል እያለ፤ ወወድቀ ዮሴፍ ውስተ ጽኑዕ መዋግደ ሕሊና ይላል። ይህነን ሲያወጣ ሲያወርድ  ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው።
(ሐተታ) ህልም ከሦስት ወገን ነው ከሐሞት ከመልአክ ከሰይጣን የሚገኝ ነው። ከሐሞት የሚገኝ በልቀም ደም ሳፍራ ሳውዳ የሚባሉ ሐሞታት አሉ። በልቀም እሳታዊ፤ ደም ማያዊ፤ ሳፍራ ነፋሳዊ፤ ሳውዳ መሬታዊ ነው። እኒህ በሠለጠኑ ጊዜ በየኅብራቸው ሲያሳዩ ያድራሉ። ከሰይጣን የሚገኝ እንደ ሄሮድስ በስደቷ ጊዜ ከዚህ ዋለች ከዚህ አደረች እያለ ይነግረው ነበር። ከመልአክ የሚገኝ እንደ ዮሴፍ እንደ ፈርዖን እንደ ናቡከደነፆር።
እንዘ ይብል ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ። ኦ ቃለ አክብሮ ቃለ አኅሥሮ ቃለ አራኅርኆ ይሆናል። ቃለ አኅሥሮ ኦ ሐናንያ ኦ አብዳን ሰብአ ገላትያ። ቃለ አክብሮ ኦ ጳውሎስ ምንተ ትቤ ኦ አኃውየ ፍቁራን ቃለ አራኅርኆ ኦ ድንግል አዘክሪ ኦ ዮሌፍ ያለው ይህ ነው። የርኅሩኅ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ እህትህ ናትና ራራላት።
አንድም የጥቡዕ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከካህናት እጅ እንደ ተቀበልህ ከእደ መንፈስ ቅዱስ መቀበልን አትፍራ። ነሢኦታ ባለው አብነት አዕርጎታ አውፅዖታ  ዓቂቦታ ተልእኮታ ይላል። እስመ እምፍሬ ከርሥክ አነብር ዲበ መንበርከ ያለው ትንቢት እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ዳዊትን አነሣው።
እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ። ከሱዋ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና። ማቴዎስ እመንፈስ ቅዱስ ያለውን ሉቃስ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ያለውን። ኢሳይያስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዘላዕሌየ ዘበእንቲአሁ ቀብዓኒ ያለውን። ሊቁ ዛቲመ ትርጓሜሃ ለቅብዓት፤ እስመ መንፈስ ቅዱስ አንጽሐ ሥጋሁ ለአዳም ብሎ ወስዶታል። ንጽሕን ክብር የሚል ወዴት አለ ቢሉ ወሠዓርኮ እምንጽሑ ይላል።
                  ******
፳፩፡ ወትወልድ ወልደ።
፳፩፡ ወንድ ልጅ ትወልዳለች። ሉቃ ፩፥፴፩። ሐዋ፡ሥራ ፬፥፲፪።
                  ******
ወይሰምዮ ስሞ ኢየሱስሃ። ስሙንም ኢየሱስ ትለዋለች።
እስመ ውእቱ ያድኅኖሙ ለሕዝቡ እምኃጣውኢሆሙ። ወገኖቹ እስራኤልን በኃጢአት ከመጣባቸው ፍዳ ያድናቸዋልና ኢየሱስ ብሎ ንባቡን ያድኅኖሙ ብሎ ስሙን ከነትርጓሜው ተናገረ። ኃይሎ ለሥም ወፍካሬሁ አብጽሐ ቅዱስ መልአክ እንዲል።
                  ******
፳፪፡ ወዝንቱ ኵሉ ዘኮነ ከመ ይትትፈጸም እምኅበ እግዚአብሔር።
                  ******
፳፪፡ በነቢይ እንዘ ይብል ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ። ኢሳ ፯፥፲፬። አጸፋውን ለወንጌላዊ የሰጡ እንደሆነ እመቤታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ትፀንሳለች በግብረ መንፈስ ቅዱስ ትወልዳለች ብሎ መልአኩ ለዮሴፍ መንገሩ ነቢይ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ብሎ የተናገረው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ አጸፋውን ለመልአኩ የሰጡ እንደሆነ እመቤታችን በድንግልና መጽነስዋ በድንግልና መውለዷ እግዚአብሔር በነቢዩ አድሮ ነቢይ ከእግዚአብሔር አግኝቶ ተገልፆለት ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ብሎ የተናገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ነው።
                  ******
፳፫፡ ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል።
                  ******
፳፫፡ ስሙም አማኑኤል ይባላል። ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ።
አማኑኤልም ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከኛ ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነው። ሐተታ ወንጌላዊ የሚጽፍላቸው በቋንቋቸው በዕብራይስጥ ነው። መልአኩም ለዮሴፍ የሚነግረው በዕብራይስጥ ነው። ምን ይተረጒማል ቢሉ ያስ ቅዱስ ቄርሎስ የንስጥሮስን ነገር ሲያስፈርድ አንተ ኅድረት ካልህ አማኑኤል ያለውን ንባብ እግዚአብሔር ምስሌነ ብሎ የተረጐመ ወንጌላዊ አበላ። ሕስወኬ ይሰመይ ወንጌላዊ ዘይተረጒም በኀቤሆሙ ብሎ ረትቶበታል ይተረጒምላቸዋል ትርጓሜው ግን በቋንቋቸው ካህናቱ የሚያውቁት ሕዝቡ የማያውቁት እንደ ጥሬ ያለ አለና ያነን ማጽናት ማጒላት ነው። መጽሐፍ በ ወ በ ዘ ያጐላል በ ወ ሲያጐላ ፍሥሐ ወ ኃሤት ፍቅር ወሰላም። በ ዘ ሲያጐላ ምንት ብከ ዘ ኢነሣአከ እምካልዕከ ወምንት ብከ ዘ ኢኮነ ውሁበ ለከ ይላል።
አንድም ዮሐንስ ወንጌላዊ የማቴዎስ ወንጌልን ለሰብአ ኤላንሳን ተርጒሞላቸዋል። በዚያ ጊዜ አማኑኤል ንባቡ ከእብራይስጥ እግዚአብሔር ምስሌነ ትርትሜው ከኤላንሳን መጥቶልናል። አማኑኤልን የመሰለ የኤላንሳን ንባብ ሳይመጣልን ቀርቷል።
አንድም የሀገራችን መላሽ አማኑኤል ያለውን የዕብራይስጡን ቋንቋ ወደ ግዕዝ ቢመልሱት እግዚአብሔር ምስሌነ ማለት ነው። እግዚአብሔር ምስሌነ ማለትም ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከእኛ ጋራ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው ብሎ ተርጒሞታል።
                  ******
፳፬፡ ወተንሢኦ ዮሴፍ እምንዋሙ ገብረ በከመ አዘዞ መልአከ እግዚአብሔር።
                  ******
፳፬፡ ዮሴፍ ከእንቅልፉ ተነሥቶ መልአኩ ያዘዘውን እንዳዘዘው አደረገ።
ወነሥኣ ለማርያም ፍኅርቱ።
ይዘሃት ውጣ እንዳለው ይዟት ወጣ። ጠብቅ እንዳለው ጠበቀ ተቀበል እንዳለው ተቀበለ።
                  ******
፳፭፡ ወኢያእመራ እስከ አመ ወለደት ወልደ ዘበኵራ።
፳፭፡ መጻሕፍት በኵር ያሉላት ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም።
                  ******
አእመራ አዳም ለሔዋን አእመራ ሕልቃና ለሐና ብእሲቱ እንዲል የግብር ዕውቀት አላወቃትም። ከወለደች በኋላስ አወቃት ማለት ነውን? ቢሉ ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው። ኢተመይጠ ቋዕ እስከ አመ ነትገ ማየ አይኅ ኢወለደት ሜልኮል እስከ አመ ሞተት እንዲል ሜልክል ከሞተች በኋላ ወለደች ማለትን ነው? ፍጸሜ የሌለው እስከ ነው።
አንድም በአንድ ኅብረ መልክዕ አላወቃትም ሲል ነው። ሥጋዌው በብዙ ኅብረ ትንቢት የተነገረለት በብዙ ኅብረ አምሳል የተመሰለለትን እሱን እንደጸነሰች ለማጠየቅ መልኳን ይለዋውጠው ነበርና። ቦ አመ ታሕመለምል ወቦ አመ ትፀዓዱ እንዲል ስንኳን የፀሐየ ጽድቅ ሰሌዳ ድንግልን ሙሴንስ እንኳ ኃላፊ ብርሃን ቢሳልበት እስራኤል ተገልበብ ለነ ብለውታል።
አንድም ኢያእመረ ይላል ወልድ የተባለ እሱ ድንግል የተባለች እርስዋ እንደሆነች አላወቀም። አጸፋውን ለወንጌላዊ የሰጡ እንደሆነ ምነው መልአኩ ነግሮት የለምን ቢሉ ፩ ከሆነ ብሎዓይን አያስረግጥምስክር አያስደነግጥ እንዲሉ። አጸፋውን ለመልአኩ የሰጡ እንደሆነ ነቢዩ ነግሮት የለምን ቢሉ ድንግል አለ እንጂ እሷን አለው ወልድ አለው እንጂ አምላክን አለው? ብሎ።
አምስት ነገር አይቶ እስኪረዳ ድረስ ኢያእመረ አላወቀም። (፩) ምጽአተ ሰብአ ሰገል ዘምስለ አምኃ፤ (፪) ሑረተ ኮከብ በካልእ ፍና፤ (፫) ሥርቀተ ስብሐተ እግዚእ፤ (፬) ዓቢይ ቅዳሴ መላእክት፤ (፭) ፍርሃተ ኖሎት። ይህን አይቶ እስኪረዳ ድረስ አላወቀም።
በኵራ በጥንት በበዓት በተቀድሶ። ወጸውዑ ስሞ ኢየሱስሃ። እስከ አመ ወለደት ወእስከ አመ ጸውዑ መጻሕፍት በኵር ያሉላት ልጁዋን እስክትወልድ ስሙንምየሱስ ብለው እስኪጸሩት ድረስ ኢያእመረ። ወአኮ በከመ ቃየን ዘእምእኵይ ወቀተሎ ለእኁሁ እንዲል። ወዘቀተሎ ሲል።
                  ******
በእንተ ምጽአተ ሰብአ ሰገል።
ምዕራፍ ፪።
፩፡  ወተወሊዶ እግዚእ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ በመዋዕለ ሄሮድስ ንጉሥ ናሁ ሰብአ ሰገል መጽኡ እምብሔረ ጽባሕ። ሉቃ ፪፥፯።
፩፡ ሄሮድስ ነግሦበት በነበረ ዘመን የይሁዳ ዕፃ በምትሆን በቤተ ልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ ሳለ በተወለደ ጊዜ ከተወለደ በኋላ። ሰብአ ጥበብ ሲል ነው ጥበብ ያላቸው ሰዎች ከወደ ምሥራቅ መጡ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
22/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment