====================
በ፬ቱ ከዋክብት ይመሰላሉ
ሕልመልሜሌክ፣ ምልክኤል፣ ምልኤል፣ ናርኤል ይባላሉ፡፡ እሊህ ዓመቱን
ካራት ይከፍሉታል፡፡ ዘጠና አንድ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ (፺፩ ቀን ካሥራ
አምስት ኬክሮስ) ይደርሳቸዋል፡፡ ፀሐይን ተከትለው ሥጋዊ ምግብ ይመግባሉ፡፡ አራቱ ወንጌላውያንም ዘመኑን ካራት ተካፍለው ፀሐየ
ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን ተከትለው መንፈሳዊ ምግብና ይመግባሉና፡፡
ባራቱ ክፍለ ዘመን ይመሰላሉ፡፡
ጸደይ፣ ክረምት፣ መፀው፣ ሐጋይ ናቸው፡፡ ጸደይ ወርኃ ዘርዕ ነው
። ማቴዎስ በዚህ ይመሰላል ምሳሌ ዘርእን ከሁሉ ይልቅ አምልቶ ፤ አስፍቶ አብዝቶ ጽፏልና፡፡ ዳግመኛም ወርኃ መሬት ነው ። እሱም
ምድራዊ ልደቱን ይጽፋልና፡፡
ክረምት ወርኃ ማይ ነው ።
ማርቆስ በዚህ ይመሰላል ፤ እሱም በጥምቀት ይጀምራልና፡፡
መፀው ወርኃ ነፋስ ነው፡፡
ሉቃስ በዚህ ይመሰሳል፡፡ በአምሳለ ነፋስ የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስን ነገር መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል
ይጼልለኪ እያለ ይጽፋልና፡፡
ሐጋይ ወርኃ እሳት ነው ።
ደረቅ ነው ዮሐንስ በዚህ ይመሰላል፡፡ መስተፃርር መስተቃርን የሌለበት ደረቅ ቃል ፤ ቀዳሚሁ ቃል እያለ ይጽፋልና፡፡
ባ፬ቱ አንስተ ያዕቆብ ይመሰላሉ፡፡
ልያ፣ ባላ፣ ዘለፋ፣ ራሄል ይባላሉ ። ማቴዎስ በልያ ይመስላል ። በመጀመሪያ እንደወለደች እሱም ከሁሉ አስቀድሞ ይጽፋልና፡፡
ማርቆስ በባላ ዓመተ ራሄል
ይመሰላል ። ከልያ ቀጽላ እንደወለደች ከማቴዎስ ቀጽሎ ይጽፋልና ። እሷ እመቤቷን አህላ መስላ እንደወለደች እሱም ቀዳሚሁ በማለት
ጌታው ዮሐንስን ይመስላልና።
ሉቃስ በዘለፋ ዓመተ ልያ
ይመሰላል፡፡ ከባላ ቀጽላ እንደወለደች ከማርቆስ ቀጽሎ ይጽፋልና ። እሱዋ እመቤቷን አኽላ መስላ እንደወለደች ምንም እሱ ሽቅብ እሱ
ቁልቁል ቢቆጥሩ ልደተ አበውን በመቁጠር ጌታው ማቴዎስን ይመስላልና፡፡
ዮሐንስ በራሄል ይመሰላል
ከሁሉ በኋላ እንደወለደች ከሁሉ በኋላ ይጽፋልና። እሱዋ ፍቅርት በኀበ ያዕቆብ ይላታል እሱንም ረድእ ዘያፈቅሮ ይለዋልና፡፡
በ፬ ብሔረ ነገሥት በ፰ቱ
ብሔረ ኦሪት ይመሰላሉ፡፡ ይህ ሁለት አራት ይሆናል እንዲህ ያለስ ብዙ አለ ብሎ ሙሴ አራት አድርጐ የጻፈውን ኃይለ ቃሉን አውጻጽቶ
አንድ አድርጎ ጽፎ ዳግም ሕግ ብሎታል። ወንጌልም አራት ሁና ተጽፋ አንድ ሕግ ለመባሏ ምሳሌ ነውና፡፡
በ፳ አቀብተ ቤተመቅደስ ይመሰላሉ፡፡
፬ት ፭ት ይሆናሉ እንዲህ ያለስ ብዙ አለ ብሎ ፭ት ፬ት ይሆናሉ ሁለቱ ከውስጥ ሁነው ተወካፍያነ መባዕ ናቸው፡፡ ፯ቱ በአፍኣ ሁነው
ኢይባዕ ሞዓባዊ ወአሞናዊ እስከ ሣልስ ወራብዕ ትውልድ ያለውን ይጠብቃሉ፡፡ አራቱ ካምስቱ አራቱ ከስድስቱ አራቱ ከሰባቱ ቆመ ብእሲ
ይሆናሉ፡፡ እኒህ ካምስት ቦታ ሁነው የማይገባውን እንዳይገባ እንዲከለከሉ አራቱ ወንጌላውያንም ፭ቱን አእማደ ምሥጢር አስተምረው
ከምእመናን ልቡና ክህደት ኑፋቄ እንዳይገባ ይከለክላሉና፡፡
በ፬ መሠረታተ ቤተ መቅደስ
ይመሰላሉ፡፡ ከታች ድልድሉ ሰባት ክንድ ነው በዚያው ላይ ባ፭ት ሰው ቁመት ልክ በዚያ ላይ በ፮ት ሰው ቁመት ልክ በዚያ ላይ በ፯ት
ሰው ቁመት ልክ በዚያ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጿል በቤተ መቅደስ ላይ ብርሃን ሰፍሮ ይታይ ነበር። ፬ መሠረት ያ፬ቱ ወንጌላውያን፣
መቅደስ የምእመናን፣ ብርሃን የጌታ ምሳሌ። ፬ቱ ወንጌላውያን ባስተማሯቸው በምእመናን ጌታ ለማደሩ ምሳሌ ።
በ፬ቱ ገጻተ ኮኵሕ ባራቱ
ገጻተ ታቦት ይመሰላሉ። ወንጌል ለሆሣዕና ባራት መዓዝን ትነበባለችና ይህስ ሁሉ መዓዝነ ዓለም ካለው ይገባል ብሎ ወንጌል መሠራቷ
ስለ አራት ነገር ነውና። ለጥምቀት፣ ለተክሊል፣ ለፍትሐት፣ ለቁርባን።
መዋዕለ ጽሕፈት ተናግረናል።
አገርም ማቴዎስ በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ጨርሱዋል ወፈጸማ በህንድ እንዲል። ማርቆስ በግብጽ በሮምም ይላል ። ሉቃስ በመቄዶንያ
ዮሐንስ በኤፌሶን።
ልሳንም ማቴዎስ በዕብራይስጥ፣
ማርቆስ በሮማይስጥ፣ ሉቃስና ዮሐንስ በዮናኒ። ዮሐንስን ለይቶ በፅርእ ይላል እንደ በቅላ እንደ ሐማሚን ጥቂት ጥቂት የልሳን መለያየት
ነው፡፡ ወንጌልሂ ሶበ ተጽሕፈ ፩ዱ እምአከለ ወየአክልሂ ይላል፡፡
ወንጌል ካራቱ አንዱ ቢጻፍ በበቃ ነበር ለልጅ ልጅም ይበቃ ነበር ይህስ እንዳይሆን ካንዱ የሌለው ካንዱ አለ ካንዱ ያለው ካንዱ
የለም ብሎ ሶበ ተጽሕፈ ፩ደ አራቱ አንድ ሁኖ ቢጻፍ በበቃ ነበር
ለልጅ ልጅም ይበቃ ነበር ቦታ አንድ ሳያደርጋቸው ዘመን ሳያገናኛቸው ቋንቋ ሳያጋጥማቸው አራት አድርገው ጽፈውት አንድ ሁኖ ቢገኝ
የእግዚአብሔር ነገሩ የመንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩ እንደሆነ ሊታወቅ አራት አድርገው ጽፈውታል እንጂ፡፡ ሶበ ተጽሕፈ ፩ዱ እም እከለ ወየአክልሂ፡፡
ከዚህም ሥጋዊ ምግብናን ከሦስት
እንደከፈለ መንፈሳዊ ምግብና ከሦስት ከፈለ፡፡ ሰው ከተወለደ ጀምሮ እስከ ሃያ ዓመት ያለው ምግበ ነፋስ ነው ብር ብር እያለ የሚሠራውን
አያውቅም። ወኢይክል ያእምር ዘውስተ ነፍሱ እንዲል። ከሃያ እስከ አርባ ያለው ዘመን ምግበ እሳት ነው ማወቁን ያውቀዋል እየተናደደ
ይሠራዋል። ከአርባ እስከ ስሳ ያለው ምግበ ማይ ነው ሰውነቱ እየደከመ ይሄዳል፤ ተመልሶ የሕፃንነቱን ሥራ ልሥራ ቢል አይቻለውም
ከተወለደ እስከ ሃያ ዘመን ያለው ከአዳም እስከ ሙሴ ያለው ዘመነ አበው ነው። የሚሠራውንም ሥራውን እንዳያውቀው ጽድቅና ኃጢአት
ተለይቶ አይታወቅም ነበር ምንም እነ ሄኖክ እነ ኢዮብ አንድ አንድ ሰዎች ቢያውቁት ፤ ዛሬ ከቤተ መንግሥት የተመከረውን ምክር ሁለት
ሦስት ባለሟሎች ቢያውቁት እንጂ ሁሉ እንዳያውቀው፤ ከሃያ እስከ አርባ ያለው ዘመነ ኦሪት ነው ያ እየተናደደ ዐውቆ እንዲሠራው በኦሪትም
ጽድቅና ኃጢአት ተለይቶ ታውቋል። ሰው እልክ እየገባ የሚሠራው ሁኑዋልና፤ ወኃየል ዝኩ ሕገ ኃጢአት ዘውስተ አባልየ ወፄወወኒ መንገሌሁ
እንዲል ካርባ እስከ ስሳ ያለው ዘመነ ወንጌል ነው ያ ሰውነቱ እየደክመ እንዲሄድ ኃጢአት ጠፍቷል። ወደክመ ሕጉ ለኃጢአት እንዲል
ተመልሶ የሕፃንነቱን ሥራ ልሥራ ቢል እንዳይቻለው ወንጌልንም ሊለውጣት የተቻለው የለምና።
ይኸን አርእስት ፫ቱ ፻ ሰጥተዋል
በምን ምክንያት ቢሉ ዲዮቅልጥያኖስ መክስምያኖስ የሚባሉ ሁለት ዓላውያን ነገሥታት ተነሥተው አብያተ ጣዖታት ይትረኃዋ አብያተ ክርስቲያናት
ይትዓፀዋ ብለው ዐዋጅ ነገሩ አብያተ ክርስቲያናት ተተኮሱ መጻሕፍት ፈለሱ ከምእመናንም ወገን የሚሞቱት ሞቱ የሚሰደዱትም ተሰደዱ
ዘመኑም አርባ ዘመን ነው፡፡ ከመከራው ጽናት የተነሣ ዘመነ ሰማእታት ብለውታል፡፡ ተባርዮ የማያስቀር እግዚአብሔር መፍቀሬ ሃይማኖት
ራትዕ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን አነገሠላቸው፡፡ አዋጁን ባዋጅ መለሰው አብያተ ክርስቲያናት ይትረኃዊ አብያተ ጣዖታት ይትዓፀዋ ብሎ፡፡
በዘመነ አርዮስ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ ብሎ ተነሣ። በዚህ ምክንያት ጉባኤ በኒቅያ ይሁን ብሎ ዐዋጅ ነገረ።
ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት
ሊቃውንት ተሰብስበው አርዮስን አውግዘው ለይተው ሃይማኖት መልሰው አጽንተው በሚለያዩበት ጊዜ ለመጻሕፍት ሁሉ አርእስት ሰጥተዋል።
መልእክተ ያዕቆብ፣ መልእክተ ጴጥሮስ፣ መልእክተ ዮሐንስ፣ መልእክተ ይሁዳ፣ መልእክተ ጳውሎስ፣ ብሥራተ ማቴዎስ፣ ብሥራተ ማርቆስ፣
ብሥራተ ሉቃስ፣ ብሥራተ አብ ትሩፍ ረድእ ተናጋሪ በመለኮት ዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ ፍቁረ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ብለው፡፡ ስለምን
ቢሉ የጸሐፊው ደግነት የታወቀ እንደሆነ የመጽሐፉም ደግነት ይታወቃል ብለው ይደልዎ ለዘያነብብ ቅድመ ይዝክር ስሞ ለበዓለ መጽሐፍ
ወእምዝ ያንብብ ወይምሀር እንዲል። ወንጌል ብሥራት ስብከት ቢል አንድ ነው፡፡ ወንጌል ብሂል በልሳነ ጽርእ ወትርጓሜሁ ስብከት እንዲል
፤ ዲያብሎስ እንደተሻረ ወልደ እግዚአብሔር እንደነገሠ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ እንደጠፋ ትናገራለችና፡፡
ልመናው ክብሩ ይደርብንና
ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ማቴዎስ የጸፈው ወንጌል ይህ ነው፡፡
እስከዚህ ድረስ ያለው መቅድምና
ታሪክ ነው፡፡ የወንጌሉን አንድምታ ከዚህ ቀጥለን በምንጽፋቸው ክፍሎች እንመለከታለን፡፡
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
12/06/2011 ዓም
No comments:
Post a Comment