Wednesday, February 20, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 15


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
                  ******
፫፡ ወይሁዳኒ ወለደ ፋሬስሃ ወዛራሃ እምትዕማር፡፡
(ዘፍ ፴፰፥፳፱፡፡ ፩፡ጴጥ ፪፥፬፡፡ ሩት ፬፥፲፰፡፡)
                  ******
፫፡ ይሁዳም ፋሬስን ዛራን ከትዕማር ወለደ። የይስሐቅን ልደት በተናገረ ጊዜ ሳራን፣ የያዕቆብን ልደት በተናገረ ጊዜ ርብቃን፣ የይሁዳን የወንድሞቹን ልደት በተናገረ ጊዜ እለ ልያን እለ ራሄልን አላነሣ አሁን ደርሶ እምትዕማር አለ ምነው ቢሉ ይህች ምክንያት ያላት ናት። ይሁዳ ሴዋ የምትባል ሚስት አግብቶ ኤርን አውናንን ሴሎምን ይወልዳል፡፡ ኤር ማለት ፀሐይ ማለት ነው፡፡ አውናን ማለት ወይን ማለት ነው፡፡ ሴሎም ማለት መስተሳልም ማለት ነው።
ለበኵሩ ለኤር ከአሕዛብ ወገን ትዕማር የምትባል ብላቴና አምጥቶ አጋባው፡፡ አባቴ ማግባቴን ባይፈቅድልኝ ነው እንጂ ማግባቴንማ ቢፈቅድልኝ ከኃያላኑ ከእስራኤል ወገን ያጋባኝ አልነበረምን ብሎ ተጸይፎ የማይደርስባት ሆነ። እግዚአብሔር ትዕቢት አይወድምና በዚህ ምክንያት ቀሠፈው። ኋላ በኦሪት የሚሠራው በሕገ ልቡና ተገልጾለት ዓቅም ዘርዓ ለእኁከ ብሎ ለአውናን አጋባው። እሱም ሥራውን እየሠራ ከዓዌ ዘርዕ በአፍአ ሆነ፤ ልጅ ቢወለድ ለሱ ለስሙ መጠሪያ ይሆነዋል እንጂ ለኔ ምን ይሆነኛል ብሎ፤ እግዚአብሔር ምቀኝነት አይወድምና ቀሠፈው፡፡
በሳራ ወለተ ራጉኤል አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን በጭንዋ አድሮ ሰባቱን ባሎቿን እንደገደለባት ይህች ብላቴና ልጆቼን ትጨርስብኛለች ብሎ በፈሊጥ ያሳናብታታል። ሑሪ ቤተ አቡኪ ወንበሪ መበለተኪ እስከ አመ ይልኅቅ ወልድየ ሴሎም ብሎ አድጎ ሳለ እንዳላደገ አድርጎ። እሷም እያዘነች ሂዳለች። ማዘንዋ ግን ዝሙት ቀረብኝ ብላ አይደለም እመቤታችን ጌታችን ከቤተ ይሁዳ ይወለዳሉ ሲሉ ትሰማ ነበርና ከባለተስፋ ቤት ወጥቼ ሄድሁ ብላ ነው እንጂ፡፡
በዚያ ወራት ሚስቱ ሴዋ ሞተችበት። መዋዕለ ኀዘኑ ሲፈጸም ቴምናታ ወደምትባል ሀገር በጎቹን ሊያሸልት በሚሄድበት ጊዜ ናሁ ይሁዳ ሐሙኪ የዓርግ ውስተ ቴምናታ ከመ ይቅርፅ አባግዒሁ ብለው ነገሯት፡፡ ሴሎም እንዳደገ ያላትም ነገር እንዳልተፈጸመላት ባየች ጊዜ እንዳታለለኝ ላታለው ብላ ልብሰ ዘማ ለብሳ ጃንጥላ አስጥላ ድንኳን አስተክላም ቢሉ ከተመሳቀለ መንገድ ቆየችው። እስራኤል ሴት ሲያዩ አልፎ መሄድ አይሆንላቸውም ነበረና በጄ በዪኝ አላት በዚያውስ ላይ ሚስቱ ሞተችበት ማለት ለዚህ ይመቻል። ምንተ ትሁበኒ አስበ ደነስየ አለችው። እፌኑ ለኪ ፩ መሐስዓ ጠሊ የፍየል ጠቦት እልከልሻለሁ አላት። ሀበኒ አኀዘ መያዣ ስጠኝ አለችው። ምን አለኝና ቢላት ቀለበትህን፣ ኩፌትህን፣ ዘንግህን ስጠኝ አለችው፡፡ መያዣ ሰጥቶ ተገናኝቶ ይሄዳል። እሷም ዘማ አይደለችምና ልብስዋን አሰልባ እንደ ጥንቷ ተቀመጠች። የበግ መልከኛው ኢራስ አዶሎማዊ ይባላል። ይኸን ጠቦት ወስደህ ለዚያች ዘማ ሰጥተህ ገንዘባችንን ይዘህ ና ብሎ ላከው፡፡ ቢፈልግ አጣት አይቴ ቤታ ለዘማ እያለ ይጠይቅ ጀመር፡፡ እኛስ በሀገራችን ዘማም የለብን አሉት። ተመልሶ አጣኋት አለው፡፡ ብታገኛት ትሰጣት ነበር እንጂ ካጣሃትማ ገንዘባችን ከኛ በዚያውም ላይ ዛሬስ የያዕቆብ ልጆች ጠገቡና አይቴ ቤታ ለዘማ እያሉ ዘማ ሲፈልጉ ይዞራሉ ሆነ ባሉን ነበር አለው።
ከሦስት ወር በኋላ ትዕማር መርዓትከ ፀንሰት በዝሙት ብለው ነገሩት። በምን አውቀው ቢሉ ከሦስት ወር በኋላ ፅንስ እየገፋ ጡት እየጠቆረ ይሄዳልና፡፡ በዚያ ወራት በአሕዛብ ሰልጥኖባቸው ነበረና በደንጊያ ወግራችሁ በእሳት አቃጥላችሁ ግደሏት ብሎ አዘዘ፡፡ አድርሱኝ አለቻቸው የማያደርስዋት ሆነ። እንኪያስ ኅልቅት ዘመኑ ዝ ኩፌት ዘመኑ ዝ ሕለት ዘመኑ ብላችሁ ስጡልኝ አለቻቸው፡፡ ወስደው ሰጡት አይቶ ጸድቀተኒ ትዕማር ረታችኝ ጸድቀት እምኔየ ከኔ ይልቅ ተሻለች ከኔ የተነሣ ከበረች ብሎ ተናግሯል። መንታ እንደፀነሰች አውቃ በምትወልድበት ጊዜ መወልዲቱን አስቀድሞ የተወለደውን በኩሩን እንድናውቀው ቀይ ሐር እሠሪበት አለቻት፡፡ አስቀድሞ ዛራ እጁን ሰደደ ፈትለ ለይ ሐር አሰረችበት፡፡ ፋሬስ እሱን ወደ ኋላ ስቦ ተወለደ። ፋሬስ ማለት ጣሽ ጠምሳሽ ክፍለት ፍልጠት ኃያል ማለት ነው፡፡ ዕፁብ በእንቲአከ ማለት ነው። ፅፁብ በእንቲአከም ማለት ያየነው ቀርቶ ያላየነው ወጣ ማለት ነው። ዛራ ማለት ወለት ድክምት ማለት ነው ደክሞ ተወልዷልና ። ቅድመ ዘርኢናሁ ዝኒ ሠረቀ ማለትም ነው። ቀይሕ ፈትለ ለይ ማለት ነው፡፡ መልከ መልካም ማለት ነው፡፡ ዛህራ ይላል በዓረብ መልከ መልካም ሲል ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው፡፡ ይሁዳ የእግዚአብሔር አብ ኤራስ አዶሎማዊ የቅዱስ ገብርኤል በግዕ የእግዚአብሔር ወልድ ሕልቀት የሃይማኖት ኩፌት የአክሊለ ሦክ ሕለት የመስቀል ትዕማር የቤተ አይሁድ። ትዕማር ማያዣ ይዛ ቀረች እንጂ ዋጋዋን እንዳላገኘች ቤተ አይሁድም ትንቢቱን ተስፋውን ሰምተው ቀሩ እንጂ በክርስቶስ አላመኑምና፡፡
አንድም የምሳሌ ምሳሌ፡፡ ትዕማር የምኩራብ፣ ምኩራብ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ፤ ትዕማር ልጆችን ከአባታቸው ከይሁዳ አገኘች እንጂ ከልጆች እንዳላገኘች። ቤተ ክርስቲያንም ምዕመናንን ከእግዚአ ነቢያት ከእግዚአ ካህናት ከክርስቶስ አገኘች እንጂ ከነቢያት ከካህናት አላገኘችምና።
አንድም ትዕማር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ፣ ትዕማር ከልጆችም ካባትም ዘርን እንዳልተጸየፈች፣ ቤተ ክርስቲያንም ከሕዝብ ከአሕዛብ ከሐቃል ከሀገሪት ከግዙር ከቆላፍ ያመኑትን ሁሉ ትቀበላለችና። ለዘመጽአ ኀቤየ ኢይሰድዶ ወኢያወጽኦ አፍአ እንዲል፡፡
ፋሬስ የኦሪት ዛራ የወንጌል ምሳሌ። ዛራ አስቀድሞ እጁን እንዳወጣ ወንጌልም በመልከ ጼዴቅ ታይታ ጠፍታለችና። ፋሬስ እሱን ወደ ኋላ ስቦ እንደ ተወለደ በመካከል ኦሪት ተሠርታለች። ዛራ በኋላ እንደተወለደ ወንጌል ኋላ ተሠርቻለችና።
እደ ዛራ የቀሳውስት ፈትለ ለይ የሥጋው የደሙ ምሳሌ። ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ ትዕማር በሃይማኖት እንደከበረች አሕዛብም በሃይማኖት እንዲከብሩ ለማጠየቅ። በእስራኤል ዘለፋ ለአሕዛብ ተስፋ ለመሆን። በልደተ ሥጋ ይመካሉና፡፡ ለኛስ ክርስቶስ ከትዕማር ተወልዶልን የለም ለማለት፡፡ በዓቂበ ሕግ ይመከሉና የሕግ አፍራሽ ልጆች አይደላችሁምን ለማለት። ክርስቶስ በዳዊት ከበረ ይላሉና ዳዊት በክርስቶስ ከበረ እንጅ እሱማ የትዕማር ልጅ አይደለም ለማለት።
ወፋሬስኒ ወለደ  ኤስሮምሃ
ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ።
ወኤስሮምኒ ወለደ አራምሃ።
ኤስሮምም አራምን ወለደ።
             ******
፬፡ ወአራምኒ ወለደ አሚናዳብሃ፡፡
     (ዘኁ ፯፥፲፪)
             ******
፬፡ አራምም አሚናዳብን ወለደ፣
ወአሚናዳብኒ ወለደ ነዓሰንሃ።
አሚናዳብም ነዓሶንን ወለደ።
ወነዓሶንኒ ወለደ ሰልሞንሃ።
ነዓሶንም ሰልሞንን ወለደ።
             ******
፭፡ ወሰልሞንሂ ወለደ ቦኤዝሃ እምራኬብ፡፡
     (ሩት ፬፥፳፪፡፡ ፩፡ነገ ፲፮፥፩)
፭፡ ሰልሞንም ቦዔዝን ከራኬብ ወለደ።
             ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
14/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment