Tuesday, February 26, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 18


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
                  ******
፲፩፡ ወኢዮስያስኒ ወለደ ኢኮንያንሃ ወአኃዊሁ አመ ፍልሰተ ባቢሎን፡፡
                  ******
፲፩፡ የባቢሎን ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በዘመቱ ጊዜ የኢየሩላሌም ሰዎች ተማርከው ወደ ባቢሎን በወረዱ ጊዜ ኢዮስያስም ኢኮንያንን ወንድሞቹን ወለደ፡፡ ሐተታ ወንጌላዊ ስቶን ዘንግቶ የልጅ ልጁን ልጁ ብሎ አጎቶቹን ወንድሞቹ ብሎ እንደነገሠ ጊዜ የተደረገውን ለልደቱ ሰጥቶ ተናገረ ቢሉ ስቶም ዘንግቶም አይደለ፡፡ ልማድ ይዞ ነው እንጂ የልጅ ልጁን ልጁ አለ ልማድ ይዞ፡፡ ያዕቆብ ከላባ ኮብልሎ ሚስቶቹን ልጆቹን ይዞ በመጣ ጊዜ ላባ ሦስት ቀን የሄደውን አንድ ቀን ገሥግሦ ደርሶ ለምንት ትሰርቀኒ ደቂቅየ ወአዋልድየ ከመ ዘበኵናት ፄወወ ወሚመ ኢይደልወኒኑ አስዓም ደቂቅየ ወአዋልድየ ብሎታል፡፡ አጎቶቹንም ወንድሞቹ አለ ልማድ ይዞ የአብርሃም ቤተሰቦችና የሎጥ ቤተሰቦች በሣር በውኃ ምክንያት ቢጣሉ ለምንት ንትዔመፅ እንዘ አኃው ንሕነ በበይናቲነ ለእመ አነ የማን ሔር አንተ ፀጋመ ወለእመ ፀጋም አነ ሑር አንተ የማነ ብሎታል፡፡
እንደ ነገሠ የተደረገውን ለልደቱ ሰጥቶ ተናገረ። ይህንም ልማድ ይዞ ነው፡፡ ደቂቅከ ይነብሩ ፈላስያነ ብሔሩ ነኪር ወይቀንይዎሙ ግብጽ ፬ተ ፻ተ ዓመተ እንዳለ፡፡ በግብጽ የሚኖሩት ሁለት መቶ ዐሥራ አምስት ዘመን ሲሆን በከነዓን የሚኖሩትን ደርቦ ስደቱን ከሰሙት ብሎ እንደተናገረ። አሁንም ፄዋዌውን ከሰሙት ብሎ እንደ ነገሠ ጊዜ የተደረገውን ለልደቱ ሰጥቶ ተናገረ።
ታሪክ ኢዮስያስ በነገሠ ባሥራ ሦስት ዓመት ኤልያቄም ኢኮንያንን ይወልዳል። በዚህ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ይህ ልጅ በነገሠ ጊዜ ፄዋዌ ይደረጋል ብሎ ትንቢት ተናግሯል፡፡ የኢዮስያስ መላ ዘመነ መንግሥቴ ሠላሳ አንድ ነው። ኢኮንያን በተወለደ ባሥራ ስምንት ኢዮስያስ በነገሠ በሠላሳ አንድ ዓመት ፈርዖን ኒካዑ ዘመተ፡፡ ኒካዑ ማለት አንካሳ ማለት ነው። ስለ ምን ዘመተ ቢሉ ንጉሠ በብነግን ለመውጋት።
አንድም መንግሥት ለማዳረስ፡፡ ከመ ያብጽሕ እዴሁ ላዕለ ፈለገ አፍራጢን እንዲል፡፡ ቀድሞ የሀገራችን ነገሥታት መንግሥት ለማዳረስ አኵሱም ይወጡ እንደነበረ መጥቶ ሰፈረ። ንጉሠ እስራኤል ካንት ፀብ የለኝምና መንገድ ሰጠኝ አለው። ለሕዝቡ ቢነግራቸው እኛስ ሀገራችንን የአሕዛብ መገሥገሻ አናደርጋትም አሉት። አይሆንም በሌላ መንገድ ሂድ አለው፡፡ እንግዲያውማ የመጣሁበትን ሳላደርግ የምመለስ ነኝ ብሎ ኃይለኛ ንጉሥ ነውና ተጋፍቶ ሄደ፡፡ ኢዮስያስም ሰልፎ ቆየው ኢዮስያስ በነፍጥ ተመቶ ወደቀ አስከሬናቸውን ይዘው ወደ አምባ ተጠጉ፡፡ እሱም ፀብ የለውምና አልፎ ሄደ አምባ ገብተው ኢዮስያስን ቀብረው ልጁን ዮአክስን አንግሠው ተቀመጡ፡፡ ንጉሠ በብነግን ወግቶ ሦስት ወር ኑሮ ግብሩን ተገብሮ ወደ ኢየሩሳሌም ቢመለስ አገሪቱን ጫ ብላ አገኛት፡፡ የዚህች ሀገር ኃያላን እንደ ቀትር ንብ ይናደፉ ነበረ ወዴት ሄደዋል ብሎ ጠየቀ፡፡
አንድም የቀሩት መጥን ሲያገቡልኝ እነዚህ የማያገቡልኝ በምን ምክንያት ነው ብሎ ጠየቀ። አንድም የዚች አገር ንጉሥ ተመቶ ነበር አለን ሞተ ብሎ ጠየቀ። እሱማ ሙቶ አምባ ገብተው እሱን ቀብረው ልጁን ዮአክስን አንግሠው ተቀምጠዋል ብለው ነገሩት። በሀገራቸው ሥርዓት ፈሊጥ የለም የገደለ ያንግሥ የዘመተ ይመለስ አይሉም ብሎ አምባውን ሰብሮ ዮአክስን አሥሮ ኤልያቄምን አንግሦላቸው ሄድዋል፡፡ ኤልያቄም ማለት ቆመ ለነ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ኢቆመ ለክሙ ሲል ኢዮአቄም ብሎታል፡፡ ግብጽ ከሄደ በኋላ ሦስት ዓመት ይገብርለታል፡፡ ወተቀንየ ኢዮአቄም ንጉሠ ይሁዳ ለንጉሠ ግብጽ ሠልስተ ዓመተ እንዲል። በአራተኛው ዓመት ናቡከደነጾር ዳር ዳር መውጋት ጀመረ መንገድ ተያዘብኝ ብሎ ግብር ነሣ ባምስተኛው ዓመት መጥቶ ገብር አለው። ንጉሥ ፍርድ ልበስ ፈርኦን ኒካዑ አባቴን ገድሎ ወንድሜን አስሮ እኔን አንግሦ ግብሩን ተገብሮ ሄደ፡፡ አንድ ባሪያ ለሁለት ጌታ መገዛት እንደምን ይሆንለታል አለው፡፡ አሕዛብ ፍርድ ጠነቀቅን ባዮች ናቸውና የዚያን ያንካሳ መዳረሻ ሳላሳይህ የዕለት ራት የጣት ቀለበት ልትለኝ አይገባህም ብሎ ግብጽ ወርዶ ፈርኦን ኒካዑን ገድሎ ሦስት ዓመት ኑሮ ባቢሎን ዘግብጽ አሰኝቷት ተመልስዋል፡፡ ከተመለሰም በኋላ ለሦስት ዓመት ይገብርለታል አሥር አንድ ዓመት ይሆናል ከዚህ በኋላ ሞት ቢያምረው በሰማይ የለ ዱር በእሥራኤል የለ ግብር ብሎ ግብር ነሣው፡፡ እሱም ተክል ለማየት ወጥቶ ሳለ ከለዳውያን ገድለውታል።
አንድም በእደ እግዚአብሔር ታሞ ሙቷል፡፡ ልጁን ኢኮንያንን አነገሡ ኢኮንያን ሦስት ወር እንደ ነገሠ ናቡከደነጾር ተመልሶ መጣ ይተወኛል መስሎት ወባት ገባ፡፡ እሱን አስሮ  ሕዝቡን ማርኮ ሲሄድ እናቱ ናታን ከመንገድ ቆይቶ ልጅ ሳለሁ የልጅ ልጅ አዋቂ ሳለሁ አላዋቂ  ታላቅ ሳለሁ ታናሽ አንግሠውብኝ ነበር የዚህን ግፍ አይቶ እግዚአብሔር መንግሥትን ላንተ አሳልፎ ከሰጠህ ንጉሥ ፍርድ ልበስ አለው፡፡ ምን ላድርግልህ አለው፡፡ አንግሠኝ አለው፡፡ ሕዝቡን ማርኬ እወስዳቸዋለሁ በማን አነግሥሃለሁ አለው፡፡ በሀገሬ እኔ አውቃለሁ ተክል በሚኩተኵቱት በገበራርት አንግሠኝ አለው፡፡ አንግሦት ሄዷል ስሙን ሴዴቅስያስ አለው። ባትከደኝ ማለት ነው። እሱም አምባውን እያጸና ግብሩን እየሰደደ ስምንት ዓመት ኖረ፡፡ በዘጠነኛው ዓመት እንደ ወንድሙ ሞት ቢያምረው በእሥራኤል የለ ግብር በሰማይ የለ ዱር ብሎ ግብር ነሣው። አስቀድሞ ፀባኢተ ሞዓብን ፀባኢተ ሶርያን ስዶ አስከበበው ኋላም እሱ ፪ት ዓመት ከ፮ ወር ይከበዋል፡፡ ወተገፍትዓት ሀገር ይላል የዘመነ ረኃብ ሰው ቀዩ ይጠቁራል ጥቁሩ ይነጣልና። አንድም እኩሉ እንገብር እኩሉ እንዋጋ በማለት ተለያዩ። ናቡከደነጾር ሥርዓት ሠርቶላቸው ነበር ሰው የሞተባቸው እንደሆነ መቃብር አይከልከሉ እያወጡ በየርስታቸው ይቅበሩ ብሎ በዚያ ልማድ ዋይ ሸሸ ተበላሸ ብላችሁ ይዛችሁኝ ውጡ አላቸው። ዋይ ሸሸ ተበላሸ እያሉ ይዘውት ሲሄዱ ያ ምንድነው ብሎ ጠየቀ። በምን አውቆ ቢሉ ሰው በዝቶ ነበርና።
አንድም ፍርድ ያደላባት ሴት ነግራበት የእሥራኤል ንጉሥ ሞቶ በሠራህላቸው ሥርዓት ሊቀብሩት ይወስዱታል አሉት። የወዳጅ እንጂ አስከሬን አጥቦ ገንዞ መቅበር ይገባል ወደኔ አምጡት ብሎ አስመጥቶ መግነዙን ፈተው ቢያዩት ዓይኑ ቆለል ቆለል ሲል ተገኝቷል ወተናገሮ ፍትሐ እንዲል ወቀሰው። መርጬ ባነግሥህ ምነው ከዳኸኝ። ከከዳኸኝስ በኋላ ወይ እችላለሁ ብለህ አትዋጋ ወይ አልችልም ብለህ አትገብር በዚያውስ ላይ እኔን ከዚህ አኑረሀ ወዴት ልትሄድ ኖሯል ብሎ መኳንንቱን ፍረዱልኝ አላቸው። እችላለሁ ብሎ አይዋጋ አልችልም ብሎ አይገብር ሞት ይገባዋል አሉ፡፡ ፍርድስ አላወቃችሁም ሞቱ ለብእሲ ዕረፍቱ ሞትማ ዕረፍት አይደለምን እኔ አውቃለሁ ብሎ ፯ ለመንግሥት የደረሱ ልጆች ነበሩት ከፊቱ በሠይፍ አስመታቸው፡፡ እሱንም ክፉ ባየበት ዓይኑ በጎ አይይበት ብሎ ሁለት ዓይኖቹን በፍላት አውጥቶ ትብትብ አሸክሞ ዱር ለዱር በፈረስ ጭራ እያስጎተተ ባቢሎን ይዞት ወርዷል፡፡ ከዚያም ባቄላ ሲፈጭ ከወፍጮ ስር ልቡ ፈርሶ ሞቱዋል ወይከውን መቃብሪከ ታኅተ እግረ ማኅረፅ ያለው የነቢዩ ቃል ይደርስ ይፈጸም ዘንድ፡፡ የዮአክስ ሦስት ወር የኢኮንያን ሦስት ወር ከመንፈቅ የሴዴቅያስ ዓሥር ዓመት ከመንፈቅ አሥራ አንድ ዓመት የኤልያቄም ዓሥራ አንድ። የኢዮስያስ ዓሥራ ስምንት እርባ ይሆናል፡፡ ይኸ ሁሉ ዘመን እያለ ፄዋዌውን ሰሙት ብሎ እንደ ነገሠ ጊዜ የተደረገውን ለልደቱ ሰጥቶ ተናገረ አንድም ከዚህ ሁሉ ሐተታ ለመዳን ዘአመ ፍልሰተ ባቢሎን የሚል ይገኛል እሥራኤል ተማርከው ባቢሎን በወረዱ ጊዜ የነገሠ ኢኮንያንን ወለደ ይህ አያሳስትም። ፄዋዌ ሥጋው ለፄዋዌ ነፍሱ ምልክት እንደሆነ ሚጠተ ሥጋው ለሚጠተ ነፍስ ምልክት ነውና። እሥራኤል ተማርከው ባቢሎን መውረዳቸው ነፍሳት ገሃነም ለመውረዳቸው ምሳሌ ነውና፡፡ እሥራኤል ከባቢሎን መውጣታቸው ነፍሳት ከሲኦል ከገሃነም ለመውጣቸው ምሳሌ ነውና። ኤልያቄምን የሚጽፈውም የሚተወውም አለ፡፡ የተወው እንደ ሆነ መጽሐፈ ኤርምያስን አቃጥሎ ነበርና በመጽሐፍ መጻፍ አይገባውም ብሎ። ይኸማ እንዳይሆን ጌታ ግብር ይጸየፋል እንጂ ባሕርይ ይጸየፋልን ብሎ ለቊጥር ይመቸኛል ብሎ ያውስ ቢሆን በሱ ዕጣ ወጥቶበታልን ብሎ። ግድፈተ ጸሐፊ ነው ይህን ለምን ይሻዋል ቢሉ እሳቸው ከሠሩላቸው ሥርዓት ካስተማሯቸው ትምህርት ቢወጡ እንዲህ ያለ መከራ አገኛቸው። እናንተም ከሠራንላችሁ ሥርዓት ካስተማርናችሁ ትምህርት ብትወጡ እንዲህ ያለ መከራ ያገኛችኋል ለማለት፡፡
                  ******
፲፪፡ ወእምድኅረ ፍልሰተ ባቢሎን ኢኮንያንኒ ወለደ ሰላትያልሃ።
፲፪፡ የኢየሩሳሌም ሰዎች ተማርከው ባቢሎን ከወረዱ በኋላም ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
17/06/2011 .

No comments:

Post a Comment