Thursday, February 21, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 16

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፩።
             ******
፭፡ ወሰልሞንሂ ወለደ ቦኤዝሃ እምራኬብ፡፡
     (ሩት ፬፥፳፪፡፡ ፩፡ነገ ፲፮፥፩)
             ******
፭፡ ሰልሞንም ቦዔዝን ከራኬብ ወለደ።
በኦሪት ባዖስ ይለዋል፡፡ ከዚህ ቦዔዝ አለ እንደምነው ቢሉ ላንድ ሰው ሁለት ስም አለው። አንድም በጸያፍ የገባ እሷንም በኦሪት ረዓብ ዘማ ይላታል፡፡ ከዚህ ራኬብ አለ እንደምነው ቢሉ ላንዲት ሴት ሁለት ስም አላት። አንድም በጸያፍ የገባ፡፡ ራኬብ ማለት ዘትትረከብ ለኵሉ ማለት ነው፡፡
የይስሐቅን ልደት በተናገረ ጊዜ ሳራን፣ የያዕቆብን ልደት በተናገረ ጊዜ ርብቃን የይሁዳን የወንድሞቹን ልደት በተናገረ ጊዜ ልያን ራሄልን አላነሣ ከዚህ ደርሶ ስለምን አነሣ ቢሉ ምክንያት ያላት ናት። ኢያሱ በሰጢን ሰፍሮ ሳለ ካሌብና ሰልሞንን ኢያሪኮን ሰልላችሁ ኑ ብሎ ሰደዳቸው፡፡ ደጋ ደጋውን ሲሰልሉ አድረው ኢያሪኮ ከቆላው ሲደርሱ ነጋባቸው፡፡ አሕዛብ አይተው አወቋቸው፡፡ በምን ምክንያት ቢሉ ሲፈሩ አይተው።
አንድም የጉበኛ ዓይኑ ባካና ነውና ዓይናቸው ሲባክን አይተው። አንድም በልብሳቸው በአካላቸው እስራኤል ቅርፀ ቀላል ናቸው ልብሳቸውም ነጭ ነው። አሕዛብ ግን ቁመተ ገፋፋ ልብሰ አዳፋ ናቸውና።
የኢያሪኮ ቅጽሯ ሰባት ነው፡፡ ራኬብ ሕዝቡን ትቀበል ነበር ቢሉ ስድስቱን ወደ ውሥጥ አንዱን ወደ ውጭ አድርጋ ከስድስተኛው ዛኒጋባ ጥላ ትኖር ነበር መኳንንቱን ትቀበል ነበር፡፡ ባሉ ስድስቱን ወደ ውጭ አንዱን ወደ ውሥጥ አድርጋ ከስድስተኛው ዛኒጋባ ጥላ ትኖር ነበር። ገብተው ሰውሪኝ አሏት ከሰገነት አውጥታ በቀርከሃ አቴና ጠቅላ አቆመቻቸው፡፡ እንዲመጡ አውቃ ፍርፋሪ ጥላ ውኃ አፍሳ ትቆያቸዋለች፡፡ መጥተው የእስራኤል ጉበኞች ካንቺ ገብተዋል ስጭን አሏት። መግባትስ ገብተው ነበር ሕቀ በደሩክሙ እህል ቀምሰው ውኃ ጠጥተው ሄዱ አለቻቸው። መግባታቸውን ብታምንላቸው መውጣታቸውን ያመነችልን መስሏቸው ገብተን እንይ ሳይሉ ተመልሰው ሄዱ፡፡ ኋላ ገብታ ትወርሱ ሀገረነ ወትቀትሉ ነገሥታቲነ  አለቻቸው በምን አውቀሽ አሏት። እስመ እግዚአብሔር ወደየ ፍርሃተ ውስተ ልበ ኃያላኒነ። ኃያላኑ ሲፈሩ ሲሸበሩ ያድራሉ፡፡ ላምሳ ለስሳ የሚከፈተው የብረት ሳንቃ ከመዝ ሀለወነ ንትረኃው እያለ በገዛ እጁ የሚከፈት ሆነ። ነገር ግን አሕዛብ ተድላ ሲያደርጉ እኔ አላደረግሁምና ደርባችሁ እንዳታጠፉኝ ማሉልኝ አለቻቸው። እሳቸውም ጠንቅቀው ይምላሉ። አንች ለኛ እንዲህ ብለሽ ኋላ ለዘመዶችሽ ነግረሽ ፈጣሪያችን በቸርነቱ ቢያድነን ከመሐላ ንጹሐን ነን ከደጅሽ ሰንደቅ አላማ ትከዪበት ከመስኮትሽ ሐር ዝጊበት ሰውሽ ከቅጽር በአፍአ አይውጣ ወጥቶ ቢሞት በኛ እዳ የለብንም አሏት። እሷም መክራ ትሰዳቸዋለች፤ አሕዛብና ጕንዳን መንገድ ከያዘ አይለቅምና ሦስት ቀን በመንገድ አትሂዱ በዱር ሂዱ በመዓልት አትሂዱ በሌሊት ሂዱ ብላ መክራ ሰደደቻቸው፡፡ እንደ ነገረቻቸው አድርገው ኢያሱ ካለበት ደረሱ። እንደምን ሁናችሁ መጣችሁ አላቸው። እንዲህ ያለች ሴት አግኝተን ሰውራ ሰደደችን አሉት። ከአሕዛብ ወገን እንዲህ ያለች ሴት መገኘቷ ፈቃደ እግዚአብሔር እንጂ ቢሆን ነው ብሎ አልዋለም አላደረም ዕለቱን ተነሥቷል፡፡
መጀመሪያ አንድ ጊዜ ዙሮ ሰፈረ ከዚያም ጥቂት ጥቂት አልፍ እያለ ይሰፍራል፤ እንዲህ እንዲህ እያለ እስከ ስድስት ቀን ይሰነብታል፡፡ በሰባተኛው ቀን ኃያላኑን በቀኝ በግራ በፊት በኋላ አሰልፎ ካህናቱን ልብሰ ተክህኖ አልብሶ ታቦተ ጽዮንን አሸክሞ ስድስት ጊዜ ዙራችሁ በሰባተኛው የነጋሪት ድምፅ ስትሰሙ አውኩ ደንፉ አላቸው፡፡ እንዲህ ማለቱ አሕዛብ ቊጡዓን ናቸው ወጥተው ይገጥሙኛል ድል አደርጋቸዋለሁ ብሎ ነው። ስድስት ጊዜ ዙረው በሰባተኛው የነጋሪት ድምፅ ሲሰሙ አወኩ ደነፉ ቅጽሩ ባራት ማዕዘን ፈረሰ ተናደ፡፡ አሕዛብን አጥፍቶ ኢያሪኮን እጅ አድርጎ አድሯል፡፡
ሰልሞን ከዚች ሴት ደጅ ጦሩን አቆመ፣ ያች ያልኩህ ሴት ይህች ናት ብሎ ግዳይ ጣለለት ባርኬልሃለሁ አግባት። ልጅ ትውለድልህ አለው። እሱዋን አግብቶ ቦዔዝን ይወልዳል፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሴ ነው ኢያሱ የጌታ፣ ኢያሪኮ የምዕመናን፣ አሕዛብ የአጋንንት ምሳሌ። ኢያሱ አሕዛብን አጥፍቶ ኢያሪኮን እጅ እንዳደረገ ጌታም አጋንንትን ድል ነሥቶ ምዕመናንን ገንዘብ ለማድረጉ ምሳሌ፡፡ መስኮት የከናፍረ ምዕመናን፣ ሐር የሥጋው የደሙ፣ ሰንደቅ ዓለማ የመስቀል ራኬብ የአሕዛብ። ብዙ ወንድ ስታወጣ ስታገባ ኑራ ኋላ ባንድ በሰልሞን እንደ ተወሰነች። አሕዛብም ብዙ ኃጢአት ሲሠሩ ብዙ ጣዖት ሲያመልኩ ኑረው ባንድ በጌታ አምነው ለመኖራቸው ምሳሌ። ሰልሞንና ካሌብ የኦሪትና የወንጌል ምሳሌ ናቸው፡፡ ሰላይነታቸው በዚህ ዓለም እንደሆነ ወንጌልና ኦሪትም የተሠሩ በዚህ ዓለም ነውና፡፡ ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ፡፡ ሐተታ እንዳለፈው እንደ ትዕማር በል።
ወቦዔዝኒ ወለደ ኢዮቤድሃ እምነ ሩት፡፡
ቦዔዝም ኢዮቤድን ከሩት ወለደ። የይስሐቅን ልደት በተናገረ ጊዜ ሳራን፣ የያዕቆብን ልደት በተናገረ ጊዜ ርብቃን፣ የይሁዳን የወንድሞቹን ልደት በተናገረ ጊዜ እነ ልያን እነ ራሄልን አላነሣ፤ ከዚህ ደርሶ ይህ ችን አነሣ ምነው ቢሉ ምክንያት ያላት ናት።
አቤሜሌክ የሚባል ካህንም ጨዋም ነው ቢሉ ሚስቱ ኑኃሚን ትባላለች፡፡ ኑኃሚን ማለት ፍሥሕት ጥዕምት ማለት ነው፡፡ ልጆቻቸውም መሀሎን ኬልዎን ይባላሉ፡፡ በረኃብ ምክንያት ደወለ ሞዓብ ተሰደው ሲኖሩ ለታላቁ ልጁ ለመሀሎን ሩትን ለታናሹ ለኬልዎን ዑርፍን አጋብቷቸው ሲኖር አስቀድሞ አባት ሞተ ከዚህ በኋላ ልጆቹ ሞቱ። ኑኃሚን እንደዚህ ሁና ስትኖር ከእስራኤል ወገን መንገደኛም ቢሉ ነጋዴም ቢሉ ሰው መጣ፡፡ ሀገራችን እንደምን ሁኑዋል ብላ ጠየቀችው። ሀገራችንማ ለምቷል ቀንቷል ምን ታጥቶ የወይኑ ዘለላ ጋን ይመላ የስንዴው ዛላ እፍኝ ይመላ አላት። ሠናይ ለብእሲ ለአመ ይከውን መቅበርቱ ውስተ ርስቱ እንዲል እንኪያስ ከሀገሬ እሞታለሁ እቀበራለሁ ብላ መንገድ ጀመረች ሁለቱ ምራቶችዋ ተከተሏት። አላትና ትተካልናለች አትሉኝ ፈጅቻለሁ ወልዳ ታደርስልናለች አትሉኝ አርጅቼአለሁ ተመለሱ አለቻቸው፡፡ ዑርፍ ከሞቱ አቴቴ ምን አለኝ ካማቴ የምትል ያልታደለች ናትና ስማት እጅ ነሥታት ተመለሰች። ሩት ግን ከሞቱ አቴቴ ምን አለኝ ካማቴ የማትል ደግ ሴት ናትና አገርሽ አገሬ ፈጣሪሸ ፈጣሪዬ ነው ከሞትሽበት እሞታለሁ ከተቀበርሽበት እቀበራለሁ ብላ ተከትላት ሄደች። የሀገሯ ሰዎች ይወዷት ነበርና ኑኃሚን ኑኃሚን መጣች እያሉ ተቀበሏት ምን ፍሥሕት ጥዕምት ትሉኛላችሁ መራር ኅዝንት ትክዝት በሉኝ እንጂ። መሊዕየ ወፃእኩ ወዕራቅየ ገባእኩ፡፡ ከባል ከልጅ ወጥቼ ብቻዬን ተመለስኩ አለቻቸው። በሀገራቸው ሞቱን ካልሰሙ ቦታውን ለሌላ አይሰጡበትምና ቤቷን ጠርገውላት ገባች። ሩት እየወጣች እየወረደች የሞያ እየዋለች ትመግባታለች።
ከዕለታት ባንድ ቀን ከቡዔዝ አዝመራ ሄዳ ስትለቅም  ቡዔዝ ለሠራተኞች ምሳ አሲዞ መጣ፡፡ እግዚአብሔር ምስሌክሙ አላቸው ኃይል ይሰጣችሁ ሲል ኦሆ በከመ ቃልከ እንደ ቃልህ ይደረግልን አሉት፡፡ ይህች ሴት ወዴት ናት ብሎ ጠየቀ፡፡ በምን ምክንያት ቢሉ አሕዛብ መልከ መልካሞች ናቸውና በመልኳ።
አንድም አጥርታ ስትለቅም አይቶ። አንድም ስትፈራ አይቶ። እስራኤል የሆኑ እንደሆነ አራሪ ለማራሪ ማራሪ ለአዕዋፍ ይተዋሉ፡፡ ከኑኃሚን ጋራ የመጣች ሞዓባዊት ናት አሉት ለዚችስ ገቢረ ሠናይ ይገባል ብሎ ጠርቶ ካጠገቡ አድርጎ ከእንጀራው ርሶ ከወጡ አጥቅሶ ሰጣት፡፡ ወዲያው ሥራት ይሠራላታል ከእንግዲህ ወዲህ አትከልክሏት ከመካከል ገብታ ትልቀም አትቅረጥዋት የሰበሰበችውን ተሸከሙላት ጊዜ ሲያጋጥማችሁም ከምትጠጡት ስጥዋት ብሎ ይሠራላታል እርሷንም ይመክራታል። እስራኤል ቀናተኞች ነን ካንዳ አዝመራ የዋለ ካንዱ አይውልም። ትልዊዮን ለአዋልድየ። አዝመራው እስኪከተት ዛሬ ወዴት ውለዋል እያልሽ እየጠየቅሽ ከኔ አዝመራ ዋይ አላት እርስዋ ናሁ አመትከ ረከበት ሞገሰ በቅድሜከ ብላ እጅ ነሣች። የሰበሰበችውን ይዛ የተረፋትን በቀሚስዋ ኪስ ቋጥራ ሄደች፡፡ ብትሰፍረው አሥር መስፈሪያ ሁኑዋል ያሥሩ ቃላት ምሳሌ። ያን ሰጥታት ስትመገብ ዛሬ ከማን አዝመራ ውለሽ ኑሯል አለቻት። ከቦዔዝ አዝመራ አለቻት። አንች ባታውቂው ነው እንጅ እሱማ የባልሽ የመሀሎን ርስት ጒልት ያለ በእሱ እጅ እንጂ ነው አንቺ ለኔ በጎ ሥራ ብትሠሪ እኔም ላንቺ በጎ ሥራ መሥራት ይገባኛልና አውድማ የሚጥልበትን ቀን ጠይቀሽ ንገሪኝ አለቻት። ጠይቃ ነገረቻት ገላዋን አጥባ ሽቱ ዘግባ ደኅና ልብስ አልብሳ የሴቶች ወግ አድርሳ መክራ ትሰዳታለች። እስራኤል ሲበሉ ቢያይዋቸው አይወዱምና ከክምር ስር ተሠውረሽ አምሽተሽ ሲተኛ ቀርበሽ ከእግሩ ስር ተኚ። አንቺ ማነሽ ይልሻል እኔ ባርያህ ሩት ነኝ አወራረስ አቆራረስ ይገባኛል ብዬ መጥቻለሁ በዪው፡፡ ከዚህ በኋላ አምላከ እስራኤል ያለው ይደረግልሻል አለቻት። እንደነገረቻት እስኪበሉ ከክምር ስር ተሰውራ ቆይታ ሲተኛ ቀርባ ከእግሩ ስር ተኛች፡፡ አንቺ ማነሽ አላት እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ አወራረስ አቆራረስ ይገባኛል ብዬ መጥቻለሁ አለችው፡፡ ከቀደመው ደግነትሽ የዛሬው ይብለጥ አረጋዊ ነው ብለሽ ወደ ሕፃን መልክ ክፉ ነው ብለሽ ወደ መልከ መልካም ደኃ ነው ብለሽ ወደ ባለጠጋ አለመሄድሽ ነገር ግን ከኔ ይልቅ አወራረስ አቆራረስ የሚገባው አለ ያ ቢያደርገው አደረገው ያ ባያደርገው ሕያው እግዚአብሔርን እንዳደርግልሽ፡፡ አሁንም ሰው ሳያይሽ ሂጂ ብሎ እንዳታፍር ፮ት መስፈሪያ ሰጥቶ ሰዷታል። የ፮ቱ ቃላተ ወንጌል ምሳሌ፣ ሲነጋ ቡዔዝ ሰው ሰብስቦ ባደባባይ ተቀምጦ ያን ሰው ሲያልፍ አይቶ አስጠራው። የመሀሎን ርስት ጒልት ያለ ባንተ እጅ ነው ይህችን ብላቴና አግብተህ ስሙን የሚያስጠራ ልጅ አትወልድምን አለው። ቀዳሚ ተሐምዎ ዘዚአየ ወዳግም ተሐምዎ ዘዚከ። እውነትህ ነው አስቀድሞ አወራረስ አቆራረስ የኔ ነው ቀጥሎ ያንተ ነው። ዘዚአየ ተሐምዎ ተሐምው አንተ የኔን አንተ ውሰደው ከሁለት ዛፍ ያለች ወፍ ሁለት ክንፏን ትነደፍ እንዲሉ እኔስ የሁለት ቤት ማቅናት የሁለት ልጅ ማሳደግ አይሆንልኝም አለው፡፡ እንኪያስ በኦሪት የሚገባውን አድርገህ ስጠኝ አለው፡፡ ጫማውን አውጥቶ ይሰጠዋል። ጫማ ለእግር ቤዛ እንደ ሆነ ኃይል ቤዛ የሚሆን ልጅ ቀረብኝ ሲል፡፡ በዚህም ቤተ ፍቱሐነ አሣዕን ተብለው እስከ ፯ ቤት ድረስ ይሰደቡበታል ጺቅ ይሉበታል ጽቁ ነህ ሲሉ፡፡ ሕዝቡም መርቀው ያጋቡታል። የያዕቆብን ቤት በልያ በራሄል ምክንያት በልጅ በከብት እንዳነጸው ያንተንም ቤት በዚች ብላቴና ምክንያት በልጅ በከብት ይነጽልህ ብላው መርቀው ይሰጡታል። እርስዋን አግብቶ ኢዮቤድን ይወልዳል። ኢዮቤድ ያለችው ኑኃሚን ናት። ኢዮቤድ ማለት መጽንዔ ርስት ጸዋሬ ርስዓን መርሥዔ ኃዘን ማለት ነው። ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ ሐተታ እንዳለፈው እንደ ትዕማር በል።
ከዚህም ጌታን ከነዚህ መወለድ አያሳድፈውም እሳቸውን ያጸራቸዋል ያከብራቸዋል እንጂ፡፡ ብርሃነ ፀሐይ ከሸለል በወደቀ ጊዜ ሸለሉን ያጸራዋል ይሰነግለዋል እንጂ ብርሃነ ፀሐይን እንዳያሳድፈው።
ወኢዮቤድኒ ወለደ ዕሤይሃ፡፡
ኢዮቤድም ዕሤይን ወለደ።
ወዕሤይኒ ወለደ ዳዊትሃ ንጉሠ፡፡
ዕሤይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ፡፡
ሐተታ በሚያመጣው ሰሎሞንሃ ንጉሠ ሮብዓምሃ ንጉሠ አብያሃ ንጉሠ አይል አሁን ደርሶ ዳዊትሃ ንጉሠ አለ ምነው ቢሉ። ዳዊት ሥርወ መንግሥት ነውና። ሥርወ መንግሥትማ ሳኦል አይደለም ቢሉ ትንቢት የተነገረ ለዳዊት ነውና፡፡ ትንቢትማ ለሳኦልስ ብንያም ተኩላ መሣጢ ይበልዕ ሲሳዮ በነግህ ተብሎ ተነግሮለት የለም ቢሉ፡፡ ያንማ እንጂ ወፍና ሠርክ ይሁብ ለመላእክቲሁ ባለው አፍርሶታል።
                  ******
፮፡ ወዳዊትኒ ንጉሥ ወለደ ሰሎሞንሃ እምነ ብእሲተ ኦርዮ።
(፪፡ነገ ፪፥፳፬)
፮፡ ዳዊት ንጉሥም ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ሰሎሞንን ወለደ።
                   ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
15/06/2011 .

No comments:

Post a Comment