፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
“መድኃኔዓለም
ክርስቶስ በቀራንዮ ስቁል፣ በለኒ መሐርኩከ በእንተ ማርያም ድንግል” እንዳለ ደራሲ መድኅን ዓለም ክርስቶስ በቀራንዮ ስለዓለም ኃጢአት
ተሰቅሏል፡፡ በደሙ ፈሳሽነት ዓለምን ከኃጢአት ቆሻሻ ሊያነጻት በደል የሌለበት እርሱ በመስቀል ላይ ተቸነከረ፡፡ ስለእኛ ብሎ የማይታመመው
ታመመ፤ የማይሞተው ሞተ፤ የማይቀበረው ተቀበረ፡፡ በዚህ ሁሉ የመዳናችን
ምክንያት የሆነችውን እመሕይወት ድንግል ማርያምን እናስባታለን፡፡ ጌታችን መታመሙን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን፣ መነሣቱን፣
ማረጉን የተመለከትነው ከድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ ነውና ድንግል ማርያምን እናመሰግናታለን፡፡
መድኃኔዓለም
የዓለም ጌታ የዓለም መድኃኒት ሆይ! በደል ሳይኖርብህ እንደበደለኞች ከበደለኞች ጋራ በቀራንዮ ኮረብታ ላይ በእንጨት መስቀል ላይ
የተሰቀልህ አንተ ስለእናትህ ስለ ቅድስተ ቅዱሳን ስለንጽሕተ ንጹሐን ስለ ወላዲተ አምላክ ስለ ደንግል ማርያም ብለህ ይቀር በለኝ
ማረኝ ራራልኝ እያልን እንለምነዋለን፡፡ ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ዘንድ ታማልደናለች፡፡ የዛሬ መናፍቃን “በለኒ መሐርኩከ በእንተ
ኢየሱስ” እያሉ አምላካቸውን እንደ አማላጅ ሲያደርጉት ይታያሉ፡፡ ይህ በጣም ውርደት የውርደትም ውርደት ነው፡፡ ያልተማረ ሰው የሚናገረው
ከንቱ ንግግር ነው፡፡ “መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቀራንዮ ስቁል፣ በለኒ መሐርኩከ በእንተ ኢየሱስ” ቢባል ትርጉሙ ምንድን ነው? ትርጉም
አልባ መሆኑን ልብ በሉ፡፡
መድኃኔዓለም
የምንለው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ታዲያ “ስለኢየሱስ ክርስቶስ ብለህ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሆይ ማረኝ ራራልኝ” ብለን እንጸልይ
ዘንድ ማን ነው ይህን ከንቱ ፈራሽ ነገር በልቡናችን ውስጥ የተከለው? ኢየሱስ ከመድኃኔዓለም ይለምናል ማለት ነው? ኢየሱስ እና
መድኃኔዓለም ይለያያሉ ማለት ነውን? በፍጹም አይለያዩም አንድ ናቸው፡፡ ይሄ በጣም ውርደት ነውና ፈራሽ የሆነ ከንቱ ነገርን ከምታመጡ
ትክክለኛውን ልመና እንዲህ ብላችሁ ለምኑ “መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቀራንዮ ስቁል፣ በለኒ መሐርኩከ በእንተ ማርያም ድንግል”፡፡
መናፍቃን ሆይ አትድከሙ የመዳናችን ምክንያት ድንግል ማርያም ናት፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ እስኪ ስለነገረ መስቀሉ እንነጋገር፡፡ ነገረ መስቀሉን ስናስብ የተደረገልንን የቤዛነት ሥራ ከማስታወሳችንም በተጨማሪ በግራና በቀኝ
የተሰቀሉትን ወንበዴዎች እና ከእግረ መስቀሉ ሥር የቆሙትን ቅዱሳን እንዲሁም በሰማይና በምድር የተደረጉ ተአምራትን እናስብበታለን፡፡
በመጀመሪያ የተደረገልንን የቤዛነት ሥራ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ነገረ መስቀሉ በልባችን ጽላት
ከተሳለ ኃጢአትን እናደርግ ዘንድ እጅ አንሰጥም፡፡ ምክንያቱም ለቤዛ ዓለም በመስቀል ላይ እጆቹን ዘርግቶ የተሰቀለውን ክርስቶስ
በፊታችን እየተመለከትን ኃጢአትን የምናስብበት ጊዜ የለምና፡፡ ዮሐንስ ፊቱ ሳይፈታ ቁጽረ ገጽ ሆኖ ዘመኑን ሁሉ ያሳለፈው በመስቀሉ
ሥር ቆሞ ለቤዛ ዓለም እጁ በመስቀል ላይ የተዘረጋውን ክርስቶስ ተመልክቶ ነው፡፡ እኛ ህግ ጥሰን ትእዛዝ አፍርሰን አምላክነትን
ሽተን አትብሉ የተባልነውን በልተን ስለበድልነው ከሰማይ የወረደልን የፍቅር ባለቤት አምላካችን ፈጣሪያችን ጌታችን መድኃኒታችን እርሱ
ነው ከመስቀሉ ላይ ዕርቃኑን ተሰቅሎ ያየነው፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤
የሰው ፍቅር ኃያል ወልድን ከሰማይ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው” ይላል፡፡ ለመስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠ ስለሰው ልጆች
ፍቅር ሲል እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የእኛ ፍቅር አገብሮት አንዳች ኃጢአት ሳይኖርበት ሰማያዊ መለኮት ምድራዊውን ደካማ ሥጋ ተዋሕዶ
የቤዛነት ሥራውን ሠርቷል፡፡ ይህን የቤዛነት ሥራ የፈጸመው በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ አደባባይ በተተከለው ዕፀ መስቀል ላይ እጅና
እግሮቹን ተቸንክሮ ተሰቅሎ ሞቶ ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት መዝ ፸፫÷፲፪ ላይ “ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር፤ በምድርም
መካከል መድኃኒትን አደረገ” እንዳለው በምድር ማእከል በሆነችው በቀራንዮ እጆቹን እና እግሮቹን ለችንካር ጎኑንም ለጦር ሰጠ፡፡
“ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል፤ የአባቶች ተስፋ
በድንግል ማርያም ተፈጸመ፡፡ የነጻነት አርማ መስቀልም በቀራንዮ አደባባይ ተተከለ” እንዲል ደራሲ (መልክአ ሥላሴ)፡፡ የነቢያት
ትንቢት የአበው ተስፋ የተፈጸመው በንጽሕተ ንጹሐን በቅድስተ ቅዱሳን በእመ ብርሃን በወላዲተ አምላክ በድንግል ማርያም ነው፡፡ በቀራንዮ
አደባበይ በተተከለው መስቀል ተሰቅሎ የተመለከትነው ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ ነውና የድኅነታችን መጀመሪያ ንጽሕት ዘር ድንግል
ማርያም ናት፡፡
ነገረ መስቀሉን ስናስታውስ ድንግል ማርያምን ማስታወስ ግዴታችን ነው እርሷ ባትኖር ኖሮ ጌታ
ሥጋን ተዋሕዶ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ባልተመለከትነውም ነበር፡፡ ስለዚህም “የመመኪያችን ዘውድ የድኅነታችን መጀመሪያ የንጽህናችንም
መሠረት አንች ነሽ” እያልን ቅዱስ ኤፍሬም እንዳመሰገናት እኛም እናመሰግናታለን፡፡ ስለዚህ ነው ነገረ መስቀሉን ስናስብ ይህን የተደረገልንን
የቤዛነት ሥራ ማሰብ ይገባናል የምንለው፡፡ ጌታ ለመስቀል ሞት ቀራንዮ አደባባይ የደረሰው እንዲሁ በቀላሉ አልነበረም በርካታ ድብደባዎችን፣
ግርፋቶችን፣ እንግልቶችንና መከራዎችን ተቀብሎ ነው እንጅ፡፡ ሊቃውንቱ ጌታ የተቀበላቸውን መከራዎች “13ቱ ሕማማተ መስቀል” ብለው
አስተምረውናል፡፡ እነዚህም ተአስሮ ድኅሪት፣ ተስሕቦ በሐብል፣ ወዲቅ ውስተ ምድር፣ ተከይዶ በእግረ አይሁድ፣ ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ፣
ተጸፍዖ መልታህት፣ ተወክፎ ምራቀ ርኩሳን፣ ተኮርዖተ ርእስ፣ አክሊለ ሶክ፣ ፀዊረ መስቀል፣ተቀንዎ በቅንዋት፣ ተሰቅሎ በዕፅ እና
ሰሪበ ሐሞት ናቸው፡፡ እነዚህን መከራዎች ትኩሳቱን አብርዱልኝ መከራውን አስታግሱልኝ ሳይል ስለእኛ በትህትና እና በትዕግሥት የተቀበላቸው
ናቸው፡፡ ስለዚህ በነገረ መስቀሉ ውስጥ ይህንን ሁሉ መከራ የተቀበለውን ኢየሱስ ክርሰቶስ እንመለከትበታለንና በሕይወት ለመጽናት
ይጠቅመናል፡፡
ሌላው ነገረ መስቀሉን ስናስብ ግራና ቀኝ ያሉትን ወንበዴዎች ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ እነዚህ
ወንበዴዎች የኃጥአንና የጻድቃን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በዓለም ፍጻሜ ጊዜ ኃጥአንን በግራው ጻድቃንን በቀኙ አቁሞ ዘለዓለማዊውን ፍርድ
ይፈርዳልና በዚያ ምሳሌ እርሱ ባወቀ ይህን አድርጓል፡፡ ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስብ በዓለም ፍጻሜ ጊዜ የሚጠብቀን ፍርድ ምን
ይሆን “ሁሩ እምኔየ” እንባል ይሆን ወይስ ደግሞ “ንዑ ኀቤየ” እንባል ይሆን ብለን ነገረ ምጽአትን እናስታውስበታለንና በቤቱ ለመጽናት
እንተጋለን፡፡ እዚህ ላይ በተለይ በቀኝ የተሰቀለውን ጥጦስ በምግባር በሃይማኖት እንመስለው ዘንድ ወደ ሰማይ ቀና ብለን ሦስቱን
ወደ ምድርም ዝቅ ብለን አራት ተአምራትን ተመልክተን “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ፤ አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ”
ልንል ይገባናል፡፡ እነዚያ ሰባቱ ተአምራት ያለአንዳች ነገር እንዳልተደረጉ ራሳችንን ልናሳስበው ይገባናል፡፡ ይህን ሁሉ ተአምር
ሳይከፈልብን እየተመለከትን እንደ ዳክርስ የጥፋት ዕቅዳችንን ማቀድ የለብንም፡፡ ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስብ የተፈጸሙትን ተአምራትም
ማስታወስ ይገባናል ማለት ነው፡፡
ሌላው ነገረ መስቀሉን ስናስብ ከእግረ መስቀሉ አጠገብ ሆነው ዓይናቸውን ወደ ላይ አቅንተው
የተሰቀለውን ጌታ የሚመለከቱትን እና መከራ መስቀሉን አስበው ፊታቸውን በእንባ ያራሱ ቅዱሳንን ማሰብ አለብን፡፡ ዮሐ ፲፱÷፳፭ ላይ
“በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እኅት፣ የቀለዮጳም ሚስት
ማርያም፣ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር” ይላል፡፡ በእግረ መስቀሉ የቆሙት ወንጌላዊው ዮሐንስ እና እነዚህ ቅዱሳን ናቸው፡፡
ለዚህ ክብር የደረሱት መከራውን ሁሉ ታግሰው ፍርሐታቸውን ሁሉ አርቀው ነው፡፡ እስከ ቀራንዮ አደባባይ መከራውን ታግሰን ፍርሐታችንን
አርቀን ከእግረ መስቀሉ ሥር ካልተገኘን “እነኋት እናትህ” ዮሐ ፲፱÷፳፯ ለመባል አንችልምና እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ መጓዝ አለብን፡፡
ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ከልባችን ጽላት ልንጽፈው ያስፈልገናል፡፡
ሌላው ነገረ መስቀሉን ስናስታውስ ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡
መምህረ አህዛብ ቅዱስ ጳውሎስ ፩ኛ ቆሮ ፩÷፲፰ ላይ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል
ነው” ይለናል፡፡ ስለዚህ እነዚህን የመስቀሉ ላይ ቃሎች ሁልጊዜም ማስታወስ ማሰብ ይገባናል ማለት ነው ምክንያቱም ኃይለ እግዚአብሔር
ነውና፡፡ ጌታችን በመስቀሉ ሳለ የተናገራቸው ለእኛ ብርታት ጽናት ድኅነት የሚሆኑ ፯ ቃላት አሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ አጽርሐ መስቀል
በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም
፩. አምላኪየ አምላኪየ ነጽረኒ ወለምንት ኀደገኒ
፪. አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ
፫. ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ
፬. ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ
፭. ወአንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ውስተ ገነተ
፮. አባ አማሐፅን ነፍስየ ውስተ
፯. ተፈጸመ ኩሉ እነዚህን
ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡ ስለዚህ ነገረ መስቀሉን
ስናስብ እነዚህን የርኅራኄ ቃላት ማስታወስ ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡
በመጨረሻም ክርስቶስን ለመከተል በቤቱም ለመጽናት የግድ መከራ መስቀሉን ማስታወስ እንደሚኖርብን
ጌታችን የተናገረውን እንመለከታለን፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፬ ላይ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ”
ይለናል፡፡ ስለዚህ ነው ነገረ መስቀሉን ማሰብ በቤቱ እንድንጸና ይረዳናል ማለታችን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተልና በቤቱ ለመጽናት
በመጀመሪያ ራስን መካድ ያስፈልጋል፡፡ ራስን መካድ የቀደሙትን አባቶችና እናቶች አብነት አድርጎ እውቀቴ፣ ሀብቴ፣ ትምህርቴ፣ ወገኔ ዘመዴ፣ ገንዘቤ ንብረቴ ሳይሉ መድኃኔዓለም
ክርስቶስንና ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን በመከተል ህገ እግዚአብሔርን ማክበር፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን መጠበቅና ምሥጢራተ
ቤተክርስቲያንን መፈጸም፣ በጊዜውም ያለጊዜውም ፀንቶ መገኘት ነው፡፡ ሐዋርያት በዚያ ዓይነት መከራ ውስጥ ሳሉ ወንጌልን ያስተምሩ
የነበረው ራሳቸውን ስለካዱ መስቀሉንም ስለተሸከሙ ነበር፡፡ ራሳቸውን ለሞት ሰጥተዋልና ሞትን አይፈሩም ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም በቤቱ
ለመጽናት ፈተናና መከራውን መሰቀቅ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይካድ ብሏልና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስን ስንከተለው ምግቤ ምን ይሆን፣ ቤተሰቦቼስ እንዴት ይሆኑ ይሆን ሀብት ንብረቴስ እንዴት ይሆን እያልን ማሰብ የለብንም
ለዚህ ነው በመጀመሪያ ራሳችንን መካድ የሚስፈልገው፡፡
ራሳችንን ከካድን በኋላ መስቀሉን እንሸከማለን፡፡ መስቀሉ መከራው ነው፤ መስቀሉ ስቃዩ ነው፤
መስቀሉ መራብ መጠማቱ ነው፤ መስቀሉ መታሰሩ ነው፤ መስቀሉ መደብደብ መገረፉ ነው፤ መስቀሉ ሥጋን ብቻ ለሚገድሉት ራስን ለሞት አሳልፎ
መስጠቱ ነው፡፡ ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ስናስታውስ በቤቱ እንጸናለን ማለታችን በእነዚህ ነገሮች ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም
በባርነት ቀንበር አትያዙ” ገላ ፭÷፩ ላይ ይለናል፡፡ ስለዚህ በመስቀል ሞቶ ነጻነት የሰጠንን አምላክ በማስታወስ በባርነት ቀንበር
ዳግም እንዳንያዝ በቤቱ መጽናት ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡ ይህን ማድረግ የምንችለው ወይም ዳግም በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ፤
በሰይጣን ምክር ዳግም እንዳንታለል የምንሆነው፤ የምንበረታው ደግሞ ነገረ መስቀሉን ማሰብ ስንችል ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ገላ ፫÷፩
ላይ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ በዐይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ ዐዚም
ያደረገባችሁ ማነው” ይላል፡፡ ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ሁልጊዜም ማሰብ እንደሚገባን ቅዱሱ ሐዋርያ ያስተምረናል፡፡ ነገረ መስቀሉን
እንዳናስብ የሚያደርገን ዐዚም እንደሆነ ነው የሚገልጽልን፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ነገረ መስቀሉን ማሰብ ማስታወስ በቤቱ እንድንጸና እና
ከቤቱ እንዳንወጣ ይጠቅመናል፡፡
ጌታ ሆይ ስለእናትህ ስለድንግል ማርያም ብለህ ማርሁህ ይቅርም አልሁህ በለኝ!!!
(አቤቱ ለምን ርቀህ ቆምህ ከሚለው ያልታተመ መጽሐፌ የተወሰደ)
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍
© መልካሙ በየነ
ጥቅምት ፳፯
/ ፳፻፲ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍✝✍