Thursday, April 11, 2019

የዘር ፖለቲካ የወለደው የክልል ሲኖዶስ ጥያቄ! ክፍል 1



=======================================
ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በስፋት ሲሰራ የነበረው የዘር ፖለቲካ ዛሬ ላይ ከአቅም በላይ ወደ መሆን ሄዷል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ጳጳሳትን እንዴት መሾም እንዳለባት ሥርዓትና ሕግ አላት፡፡ ሆኖም ግን የዘር ፖለቲካው ቤተ ክህነታችንንም መቆጣጠር ከጀመረበት እና “መንግሥት በእኔ ጣልቃ አትግቢ” ብሎ በረዥም ጣቱ ቤተ ክርስቲያናችንን እየቆነጠጠ እርሱ ግን እኛን መስሎ ቤተ መቅደስ ውስጥ ተቀምጦ “ፖለቲካ በሃይማኖት፤ ሃይማኖትም በፖለቲካ ጣልቃ መግባት አይችልም” እያለ ከወንጌሉ በላይ የሚሰብክ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ጫናው ከባድ ሆኗል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳት እየተሸሙ ያሉት ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅባቸውን መስፈርት ስላሟሉ ሳይሆን የብሔር ተዋጽኦው ተጠብቆ ነው፡፡ መንግሥት በከለለው አዲስ መዋቅር ቤተ ክርስቲያናችንም አብራ ተከልላ ለየክልሎች ኮታ በመስጠት “ይደልዎ” መባል የማይገባውን ሁሉ ሾማለች፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የዘር ፖለቲካው ከባድ ጫናን ስለፈጠረ ነው፡፡ መንግሥት ተፋትቸሻለሁ አንችም ተፋችኝ ብሎ በሕገ መንግሥቱ ላይ ቢያሰፍርም ቤተ ክርስቲያናችን ግን እስካሁንም ድረስ የመንግሥትን ቀለበት እንዳሠረች ናት፡፡ ታዲያ ይህ ያላቻ ጋብቻ (የመንግሥትና የቤተ ክህነት ጋብቻ) ሲፈልጉ ተፋተናል ሲፈልጉ ደግሞ ተጋብተናል እያሉ የሚኖሩበት ለምን ሆነ?
የዘር ፖለቲካው የወለዳቸው በሃይማኖት ስም የተለጠፉ አንዳንድ ግለሰቦች ጉዳዩ ያልገባውን መንጋ እየጎተቱ የዘር ሃይማኖት ለመፍጠር ሲታትሩ እየተመለከትን ነው፡፡ ለዚህ ግንባር ቀደም የሆነው በኦሮምያ ክልል እንገኛለን የሚሉ ብዙውን የተዋሕዶ ልጅ መወከል አለመወከላቸው የማይታወቅላቸው ግለሰቦች መንግሥት ክልልን ሰርቶ እያስተዳደረ ስለሆነ እኛም የክልል ሲኖዶስ እናዋቅር ብለው ተነሥተዋል፡፡ ይህ የክልል ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያናችን እና ለአማኞቿ እስከ ምን ድረስ ነው የሚጠቅመው? የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ያጤኑ አይመስለኝም፡፡ አሁን ያለው የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር አሉ የሚባሉ ችግሮችን የመፍታት ችሎታ የለውምን? እኔ የታየኝ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ ግለሰቦች ቤተ ክህነቱንም ለመክፈል አልመው እየሠሩ እንደሆነ ነው፡፡ ዛሬ የኦሮምያ ሲኖዶስ ይፈቀድልን ባሉ ግለሰቦች የተነሣ ነገ ደግሞ በየቋንቋችን ይኸው ጉዳይ ይፈቀድልን የሚሉ ብሔርተኞች መነሣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ታዲያ አንዱ ሲኖዶስ በቋንቋችን ልክ እንዲሰነጠቅ ለምን ተፈለገ?
የሲኖዶስ አብነቶቻችን ሐዋርያት ናቸው፡፡ ሐዋርያት እነርሱ ያውቁት ከነበረው አንድ ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ 71 ቋንቋ ተገልጾላቸው በ72 ቋንቋ ዓለምን ሲያስተምሩ እና አሳምነው ሲያጠምቁ 72 ሲኖዶስ አላቋቋሙም፡፡ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ ከዚያ ያለፈ ምንም መገለጫ የለውም፡፡ መግባባት ከቻልን እኮ ሳንነጋገርም ልንግባባ እንችላለን፡፡ ታዲያ በቋንቋ ልክ ሲኖዶስን የመሰንጠቁ ዕቀድ የት ሊያደርሰን ይችላል?
2010 ዓ.ም ላይ የተዘጋጀው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤትን ማቋቋሚያ ሰነድ በውስጡ ስለያዛቸው ዝርዝር ነጥቦች ወደ ፊት እንመለከታለን፡፡ ይህ ሰነድ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት አስፈላጊነትና አደረጃጀት” በሚል ርእስ የተዘጋጀ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ የደረሰ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ የቀረቡት የዚህ ሲኖዶስ አስፈላጊነት አሁን ቤተ ክርስቲያናችን እየሠራችበት ባለው መዋቅር መፈታት የማይችል ነው ወይ? ከዚህ ጽ/ቤት ጀርባ እየተሠራ ያለው ግልጽነት የጎደለው ደባ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ የእኔ አመለካት ነው ማንም ሰው ይህንን የክልል ሲኖዶስ ደግፎ ያለ ከሆነ በሳል በሆኑ ነጥቦች ሊሞግተኝ ይችላል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን “ለኦሮምያ ጥላቻ ስላለህ ነው” የሚል ለማሸማቀቅ የሚወረወርን ድንጋይ አላይም አልሰማምም፡፡ ኦሮምያን ያነሣሁት ሌሎች በዚህ መንገድ ስላልጠየቁ ብቻ እንጂ የትኛውም ክልል ይህን ዓይነት ጥያቄ ቢጠይቅ እኔ በግሌ እሞግታለሁ፡፡

በቀጣይ ሰነዱን በዝርዝር ቃል በቃል እንመለስበታለን፡፡

አንድነት ሆይ ወዴት አለሽ?

No comments:

Post a Comment