====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲።
******
፩፡ ወጸውዖሙ ለ፲ቱ ወ፪ቱ አርዳኢሁ፡፡ ማር ፫፥፲፫፡፡ ሉቃ ፮፥፲፫፡፡ ፱፥፩፡፡
******
፩፡ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጸራቸው፡፡ ማለት ሾማቸው፡፡
ወወሀቦሙ ሥልጣነ ዲበ መናፍስት ርኩሳን ከመ ያውፅእዎሙ ወይፈውሱ ኵሎ ድውያነ ወሕሙማነ።
አጋንንት ያወጡ ድውያን ይፈውሱ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው ማለት ለሹመታቸው ምልክት ዱያነ ፈውሱ ሙታነ አንሥኡ እለ ለምጽ አንጽሑ ብሎ ገቢረ ታምራትን ሰጣቸው፤ ንጉሥ ደጃዝማች በሾመ ጊዜ ለሹመቱ ምልክት ሰንደቅ አላማ ማሠሬ ነጋሪት ሰጥቶ እንዲሰደው። አሥራ ሁለት መሆናቸው ስለምን ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም።
ትንቢት፤ ኤርምያስ ለሊሁ ኢየሱስ ይመጽእ ውስተ ዓለም ወየኀሪ ፲ወ፪ተ ሐዋርያተ ወይከይድ ውስተ ደብረ ዘይት ዘአነ ርኢኩ ሥግወ ብሏል። ኤልሳዕም በራእዩ ወናሁ ይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር ወየኅሪ ፲ተ ወ፪ተ ዕፀወ ባሉጥ ብሏል።
ምሳሌም ያዕቆብ ከአዋልደ ከነዓን አልተጋባም ሶርያ ወርዶ ፲፪ት ሕፃናት ወልዷል ጌታም ባሕርየ መላእክትን ባሕርይ አላደረገም የአዳምን ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ሹሞ መስደዱን መናገር ነው። ኢነሥኦ ለዘነሥኦ እመላእክት ዘእንበለ ዳዕሙ እምዘርአ አብርሃም እንዲል። ለነዚያ ሦስት ምውታን አሥራው አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ አሏቸው ለኒህም ሦስት ሕያዋን አሥራው ሥላሴ አሏቸውና በአሥራ ሁለቱ ምዕዛረ ፀሐይ በአሥራ ሁለቱ አልህምተ ብርት በአሥራ ሁለቱ መገብተ ሰሎሞን በአሥራ ሁለቱ የቤት አለቆች በአሥራ ሁለቱ ጉበኞች ምሳሌ። ወግዕዙ እስራኤል ወበጽሑ ኀበ ቦ ፲ ወ፪ቱ አንቅዕት ወ፸ ተመርት ይላል። አሥራ ሁለቱ አንቅዕት ያሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ፸ ተመርት የ፸ አርድዕት ምሳሌ።
አንድም በልብሰ አሮን ባሉ በአሥራ ሁለቱ አዕናቊ ምሳሌ። በደብረ ሲና ከዙፋኑ እግር በተገኙ በ፲፪ቱ አዕናቊ፤ ኤልያስም ፬ ቻል ውሃ አምጡ ብሎ ድግሙ ሠልሱ ብሏቸዋል በዚያ ምሳሌ ኢያሱ ዮርዳኖስን ሲሻገር አሥራ ሁለት ድንጊያ ከአፍአ አግብቶ በውስጥ ተክሏል አሥራ ሁለት ድንጊያ ከባሕሩ አውጥቶ አሸክሞ ወስዶ ፮ን በጌባል ፮ን በገሪዛን አሰተክሏቸዋል ሰዎቹ የሐዋርያት ድንጊያው የመከራቸው ምሳሌ። ትንቢቱን አውቆ አናግሯል ምሳሌውንም እንጂ ባወቀ አስመስሏል ምሥጢሩ እንደምን ነው ቢሉ ለ፬ ባሕርያት ሦስት ሦስት ግብር አላቸው። አሥራ ሁለት ይሆናል ካራቱ ባሕርያት የተፈጠረ ሰውን እጠብቅባቸዋለሁ ሲል።
******
፪፡ ወዝውእቱ አስማቲሆሙ ለ፲ቱ ወ፪ቱ ሐዋርያት።
******
፪፡ ያሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስማቸው ይሀ ነው። ሐዋርያት ማለት ደጃዝማች ቀላጤ ምጥው ፍንው ሃያጂ ማለት ነው። ደጃዝማች በተሾመበት አገር ገብቶ የተቀበለውን ሹመት ሽልማት ሰጥቶ ያከብረዋል። ካሀን ቢሆን አስራቱን በኩራቱን ሰጥቶ ያከብረዋል። ይህን የማይሻ መነኩሴ ቢሆን ከእግሩ ወድቆ አቡነ ዘበሰማያት ይቀበላል ለመነኩሴው ክብሩ ነው ያልተቀበለውን ዓይን በፍላት እጅ እግር በስለት ይቀጣል።
ሐዋርያት ትምርታቸውን የተቀበሏቸውን በልጅነት ያከብራሉ ሀብት ሥርየት ይሰጣሉ ያልተቀበሏቸውን በሌጌዎን ይነጻሉ በነፋስ ይሰቅላሉና። ቀላጤም፤ በደለኛ ወታደር ካልገዛው አገር ገብቶ ያልፈላ ያስጠምቃል ያልቦካ ያስጋግራል፤ የተበደለ ድሃ ከንጉሥ ሄዶ ይጮሃል ባዳራሽ ተገኝቶ ቀላጤ ሰጥቶ ይሰደዋል ያ ቀላጤ ባብርሃን የገባውን በጨለማ በፀሐይ የገባውን በዝናም አስወጥቶ የተሰበረ እንጨቱን የተቀዳ ውሀውን ያስመልስለታል። በደለኛ ወታደር ካልገዛው አገር ገብቶ ያልፈላ እንዲያስጠምቅ ያልቦካ እንዲያስጋግር ዲያብሎስ ያልፈጠፈውን ፍጥረት ያልገዛውን ሰውነት ፭ ሽህ ከ፭፻ ዘመን ኃጢአት ሲያሰራ ጣዖት ሲያስመልክ መኖሩን መናገር ነው፡፡ የተበደለ ድሃ ከንጉሥ ሂዶ እንደመጮህ ነቢያት አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ ማለታቸውን መናገር ነው ንጉሥ ባዳራሽ ተገኝቶ ቀላጤ ሰጥቶ እንደመስደድ ቃለ እግዚአብሔር ሰው ሁኖ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ሹሞ መስደዱን መናገር ነው። ቀላጤ በብርሃን የገባውን በጨለማ በፀሐይ የገባውን በዝናም እንዲያስወጣ ሐዋርያትም በደዌ የገባውን በታምራት በክህደት የገባውን በትምርት ማስወጣታቸውን መናገር ነው። የተሰበረ እንጨቱን እንዲያስመልስለት በአዳም የሄደውን ልጅነት አስመልሰዋልና ፍንው፤ ወናሁ አነ እፌንወክሙ ከመ አባግዕ ማዕከለ ተኵላት ብሎ እንዲያመጣው ምጥው ከፍንው ይገባል ሃያጅም አለ ይህ ሁሉ ካልሄዱ አይገኝምና።
ቀዳሚ ስምዖን ዘተሰምየ ጴጥሮስ።
አንዱ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን ነው። (ሐተታ) ጴጥሮስ ማለት መርግ ማለት ነው መርግ ከወደላይ ሲመጣ ያስፈራል። እሱም ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ እያለ ሲያስተምር ያስፈራልና።
አንድም ሻፎ ደንጊያ ማለት ነው ይህ ሥጋን ከአጥንት ይለያል። እሱም ምዕመናንን ከመናፍቃን ይለያልና።
አንድም ደንጊያ ማለት ነው ይህን የቀን ሐሩር የሌሊት ቊር አይለውጠውም። እሱም በመከራ አይለወጥምና።
አንድም ከዋው ደንጊያ ማለት ነው ያ እየፈጋ ይሄዳል። እሱም ከ፲፩ዱ ስብከት ሁሉ እየገባ ያስተምራልና።
ወእንድርያስ እኊሁ።
ወንድሙ እንድርያስ ነው። (ሐተታ) እንድርያስ ማለት ተባዕ ለመስቀል በኵረ ሐዋርያት ማለት ነው።
******
፫፡ ወያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
፫፡ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ ነው
******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
13/08/2011 ዓ.ም
Sunday, April 21, 2019
ወንጌል ቅዱስ ክፍል 71
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment