Thursday, April 11, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 61


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ አድኅኖተ ለምጽ።
ምዕራፍ ፰።
                 ******   
፩፡ ወእንዘ ይወርድ እምደብር ተለውዎ ሰብእ ብዙኃን፡፡
                 ******    
፩፡ በጌታ ከብፁዓን ጀምሮ እስከዚህ ያንድ ቀን ነው። ጉባዔው ሲፈታ ብዙ ሰዎች ተከተሉት የቀሩትን አይከተሏቸውም እሱን ተከተሉት አለ ቢራቡ ይመግባቸዋል ቢታመሙ ይፈውሳቸዋል ቢሞቱ ያነሣቸዋልና።
                 ******   
፪: ወናሁ መጽአ ፩ ብእሲ ዘለምጽ ቀርበ ወሰገደ ሎቱ። ማር ፩፥፵:: ሉቃ ፭፥፲፪።
                 ******   
፪: ብዙኃን ካላቸው ለምጽ የያዘው አንድ ሰው ቀርቦ ሰገደለት።
እንዘ ይብል እግዚኦ እመሰ ፈቀድከ ትክል አንጽሖትየ።
አቤቱ ከወደድህስ እኔን ከለምጽ ማዳን ይቻልሃል።
(ሐተታ) ለምጻምን የምታስተራኩስ ኦሪትን እሱ እንደሠራት ለማጠየቅ እንዳሳለፋትም ለማጠየቅ ለልማዱ ለምጻም አይቀርብም ነበር።
                 ******  
፫፡ ወሰፍሐ እዴሁ ወገሠሦ።
                 ******  
፫፡ እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው። በሁለንተናው ሕይወት እንደሆነ ለማጠየቅ። ምትሐት እንዳይደለ ለማጠየቅ ኦሪትን እንዳሳለፋት ለማጠየቅ ለልማዱ ለምጻም አይዳሰስም ነበርና።
ወይቤሎ እፈቅድ ንጻሕ።
መዳንህን እወዳለሁ ዳን አለው
ወነጽሐ እምለምጹ በጊዜሃ።
ያን ጊዜ ከለምጹ ዳነ። በሐልዮ ፈውሶ በነቢብ አዳነው።
እስመ ሀብተ ፈውስ ዘይከውን እምኔሁ ይቀድሞ ለንባቡ እንዲል።
                 ******  
፬፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ዑራቅ ኢትንግር ወኢለመኑሂ። ዘሌዋ ፲፬፥፪፡፡
                 ******  
፬፡ ለማንም ለማን እንዳትነግር ዕወቅ አለው። ውዳሴ ከንቱ አይሻምና የሚያምኑበት ጊዜ አልደረሰምና። እስከ ትንሣኤ ድረስ ወባሕቱ ሑር አፍትን ርእሰከ ለካህን። ሂደህ ራስህን ለካህን አስበርብር እንጂ።
ወአብዕ መባዓከ በእንተ ዘነጻሕከ።
ከለምጽሕ ስለ ዳንሀ መባሕን ስጥ እንጂ።
በከመ አዘዘ ሙሴ።
ሙሴ እንዳዘዘ።
ከመ ይኩን ስምዓ ላዕሌሆሙ
ባለመኑ መፈራረጃ ይሆንባቸው ዘንድ። ምነው ያላመናችሁ ይሏቸዋል ምን አይተን እንመን ይላሉ ያውሳ ለምጻሙን እያዳነ መባው እየመጣላችሁ ትበሉ የነበረ ተብሎ አፍትን ርእሰከ ለካህን ማለቱ የሆነውንም ያልሆነውንም ለምጻም አዳንኩ እያለ ምኵራባችነን ቢያሳድፍብን ከሞቱ ገባንበት ባሉ ነበርና እንዳይሉ የለምጽን ነገር ከዚህ ይናገሩታል ለምጽ በብዙ ነገር ይመጣባቸዋል ባልና ሚስት የተማሙ እንደሆነ ከአልጋው ከምንጣፉ። የጫኝ ዋጋ ቢያስቀሩ በመጫኛው በባይበቱ። የጸሐፊ ዋጋ ቢያስቀሩ በመጽሐፉ የሐናፂ ዋጋ ቢያስቀሩ በሕንፃው ተወግቶ ኑሮ እሳትም ፈጅቶት ኑሮ ሲሽር ከትራቱ ይወጣል። ፍጹም ለምጻም አለ፤ ህንብርብር አለ። ፍጹም ለምጻሙን አይለዩትም ከቀቢጸ ተስፋ ደርሱዋልና ወደ አሕዛብ ይሄዳል ብለው። ህንብርብሩን ይለዩታል ከቀቢጸ ተስፋ አልደረሰምና ወደ አሕዛብ አይሄድም ብለው፥ ፍጹም ለምጻሙን ሥርዓት ይሠሩበታል አትከናነብ አፍህን ሸፍን ወገብህን አትታጠቅ ጫማ አታድርግ ይሉታል። ይህ የከሃዲ ምሳሌ ነው፡፡ አትከናነብ ማለታቸው ለጊዜው ደዌው ተገልጦ እንዲታይ ነው ፍጻሜው ግን ልዕልና ሃይማኖት የለህም ሲሉት ነው። አፍህን ሸፍን ማለታቸው ለጊዜው ደዌው በእስትንፋሱ ወደ ሕያዋን እንዳይናኝ ነው ፍጻሜው ግን ማስተማር አይገባህም ሲሉት ነው። ወገብሀን አትታጠቅ ማለታቸው ለጊዜው ሰውነቱ ልህሉህ ነውና እንዳይሰማው ነው ፍጻሜው ግን ንጽሕና የለህም ሲሉት ነው። ጫማ አታድርግ ማለታቸው ምግባረ ወንጌል የለህም ሲሉት ነው። አይለዩትም አለ ከሃዲ የታወቀ ነው አይስብምና። ህንብርብር የመናፍቅ ምሳሌ ይለዩታል አለ ነኝ እያለ ይስባልና።
አንድም ወእንዘ ይወርድ ብለህ መልስ። ከልዕልና ወደ ትሕትና በመጣ ጊዜ ነቢያት በግብር መሰሉት። ወናሁ መጽአ በፍዳ የተያዘ አዳም መጥቶ ሰገደለት። እግዚኦ እመሰ ፈቀድክ አቤቱ ከወደድህስ እኔን ከፍዳ ማዳን ይቻልሃል። ወሰፍሐ እዴሁ እጁን ዘርግቶ ተሰቀለለት። የማነ እዴየ መጠውክዎሙ ወኮነቶሙ ጥምቀተ እንዲል። እፈቅድ ንጻሕ መዳንህን እወዳለሁ ዳን አለው። ወነጽሐ እምለምጹ በጊዜሃ። ያን ጊዜ ፈጥኖ ከፍዳው ዳነ። ዑቅ ኢትንግር፤ ኃጢአትህን ለማንም ለማን አትናገር አለው። በአዳም መላውን መናገር ነው። ሑር ወአፍትን ለመምህረ ንስሐህ ንገር እንጂ። ወአብዕ መባዓከ ከፍዳህ ስለ ዳንክ ቀኖናህን ፈጽም እንጂ። በከመ አዘዘ ሙሴ ቄሱ እንዳዘዘ። ከመ ይኩን ስምዓ በኢተነሳሕያን መፈራረጃ ይሆንባቸው ዘንድ።
                 ******  
፭፡ ወበዊዖ ቅፍርናሆም መጽአ ኀቤሁ መስፍነ ምዕት። ሉቃ ፯፥፩።
                 ******  
፭፡ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አዝማች መጣ።
                 ******  
፮፡ ወይቤሎ ብቊዓኒ እግዚኦ ቊልዔየ ድውይ። ወሕሙም ጥቀ፡፡
                  ******  
፮፡ ልጄ ታሟል። ደዌ ጸንቶበታል
ወይሰክብ ውስተ ቤተ መፃጉዕ
ከሕሙማን ቤት ተኝቷል አለው። በሀገራቸው የድውያን ቤት አንድ ነው ለባለጸጋው የመጣው ምግብ ለድሃው እንዲተርፈው። ደዌ ከሕሙማን ወደ ሕያዋን እንዳይተላለፍ። ያልጸናበት የጸናበትን አይቶ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን።
አንድም ወይሰክብ ውስተ ቤት ብሎ ወመፃጉዕ ጥቀ ይላል ፈጽሞ ጸንቶበታል።
                  ******  
፯፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ነየ አነ እመጽእ ወእፌውሶ።
፯፡ እኔ መጥቼ አድነዋለሁ አለው።
                  ******  

ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
03/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment