======================================================
“በኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት አስፈላጊነትና አደረጃጀት” በሚል ስም የተዘጋጀው የክልል
ሲኖዶስ ማቋቋሚያ ሰነድ የዘር ፖለቲካችን አምጦ የወለደው የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው፡፡ ምናልባትም ይህን ያዘጋጁት ሰዎች
በቅንነት አስበውት ከሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስበው ለምእመናን ተጨንቀው ከሆነ መልካም በሆነ ነበር ነገር ግን ከሰነዱ በስተጀርባ
የአክራሪ ብሄርተኞች እጅ እንዳለበት የታወቀ ነው፡፡
በቋንቋችን
እንደ ባህላችን እንደ አካባቢያችን እንማር እናስተምር እንቀድስ እናወድስ የሚለው ጥያቄ እጅግ በጣም መልካም ነው፡፡ ይህን ሰነድ
ለቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠበት በጥቅምት 2011 ላይ አንብቤዋለሁ፡፡ ለክርስትና ካላቸው እውነተኛ ፍቅር የመነጨ ነው ብየ አስቤም ነበር
ዛሬ ላይ ሳየው ግን የዚያ ግልባጭ ሆኖብኛል፡፡ የፖለቲካ ሰዎች ነን የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦች ቋንቋ ላይ ያላቸው የተዛባ አመለካከት
ወደ ቤተ ክህነታችንም ዘው ብሎ መግባቱን በደንብ ተመልክቸበታለሁ፡፡ ቋንቋን የሰጠን አምላካችን ነው፡፡ ስለዚህ በፈለግነው ቋንቋ
ሰው በሚገባው በማንኛውም መንገድ ማስተማር የእውነተኞች የሐዋርያት መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን መሠረት በማድረግ እኔ የአጵሎን
ነኝ እኔ ደግሞ የጳውሎስ እኔ ግን የጴጥሮስ ነኝ ወዘተ እያልን በቋንቋችን
ምክንያት መከፋፈል የለብንም፡፡ የእገሌ ቋንቋ ከእገሌ ይበልጣል የእገሌ ደግሞ ያንሳል አይባልም፡፡ ቋንቋ እስካግባባ ድረስ ምንም
ብልጫ የለውምና፡፡ (በእኛ በሰዎች ዘንድ ስለምንግባባበት ቋንቋ ብቻ ነው የምናገር)
********************
ሰነዱ
እንዲህ ይላል፡-
“ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለሰባኪስ እንዴት
ይሰማሉ” ሮሜ 10፡14 በተባለው መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን የተመሰረተችው በህዝቡ ቋንቋ ስለመሆኑ ክርስቶስ ሐዋርያትን ከመረጠ
በኋላ ሂዱ አስተምሩ እስከ አለም ዳርቻ ብሎ ሲያሰማራቸው የህዝቡን ባህል እና አኗኗር በማክበር በህዝቡ ቋንቋ እንዲያስተምሩ መመርያ
ስለተሰጣቸው ወንጌል ለዓለም ሊዳረስ የቻለው በህዝቡ ቋንቋ ትምህርተ ወንጌል ስለተሰጠ ነው፡፡ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን
በአብዛኛው ለአገልግሎት የምትጠቀመው ግእዝ ቋንቋ ሲሆን ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ አማርኛን መጠቀም ጀምራለች፡፡ የአሁኑ የቅርብ
ጊዜ ጅምርም ቢሆን በአፋን ኦሮሞ አገልግሎት ለመስጠት ቢሞከርም የሚጠው አገልግሎት እና የሚፈለገው አገልግሎት መጠን ባለመጣጣሙ
የተገኘው ውጤት አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ከላይ እንደተጠቀሰው ምዕመኑ በሚሰማው ቋንቋ መንፈሳዊ አገልግሎት ፍለጋ እና በመደለል
ወደ ሌላ የእምነት ተቋማት ተበትኗል”
*******************
የምናስተምረው
አካል በሚገባው ቋንቋ እናስተምር እንደማለት የቀና ሃሳብ የለም፡፡ ሐዋርያትም በ72 ቋንቋ ያስተምሩ የነበረው ሕዝቡ እንዲሰማቸውና
ወደ እውነተኛው መንገድ እንዲመጡ ለማድረግ እንደሆነ ግልጥ ነው፡፡ ዋናው ዓላማ ሕዝቡ እውነተኛ ወንጌልን እንዲማር እና እንዲያውቅ
ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ እስከገባው ድረስ በማንኛውም ቋንቋ ብናስተምር ምንም ችግር የለውም፡፡ ከሌሎች እምነቶች የምንለየውም
በራሳችን ቋንቋ እና ባሕል ማስተማር መቻላችን ነው፡፡ ስለዚህ በሀገራችን በሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉ ብናስተምር መልካም ነው፡፡ ችግር
መስሎ የሚታየኝ ከራስ ውጭ ያለን ቋንቋ መጠየፉ ላይ ነው፡፡
እኔ እግዚአብሔር
ቢገልጥልኝ ሁሉንም ቋንቋ ብችልና እየዞርኩ ባስተምር ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር ግን ከምችለው ቋንቋ ውጭ አላውቅም፡፡ በማንኛውም ቋንቋ
የሚነገርን የእግዚአብሔር ቃል ግን እሰማለሁ፡፡ ዐረብኛ አልችልም ግን የግብጾችን CTV እከታተላለሁ፡፡ ነፍሴ በሚሰጠው ትምህርት
ትማራለች ታውቀዋለችና የሥጋ ጆሮዬ ግን አይሰማም፡፡ ትምህርቱ ለነፍስ ነውና ነፍሳችን ትማርበታለች፡፡ ስለዚህ በምንችለው ቋንቋ
ማስተማር አትራፊ እንጂ አክሳሪ አይደለም፡፡ ችግር ሆኖ የሚታየው የሌላውን በመጠየፍ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆንክ ከቤተ ክርስቲያን
ውጣ የሚለው የቋንቋ አምልኮ ነው፡፡
ምእመኑ
በሚሰማው ቋንቋ ባለመማሩ ወደ ሌሎች እምነቶች ሄዷል የሚለው ግን አሳማኝ አይደለም፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ከአማርኛ ውጭ ሌላ
ቋንቋ መናገርም መስማትም አይችልም፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አይቀርም የሚቀደሰው የሚያስቀድሰውም በግእዝ ነው፡፡ ነገር ግን
በግእዝ ስለሆነ ሃይማቴን ልለውጥ ሲል አላየሁም፡፡ ግእዝን ለመማር ይጥራል እንጂ ሃይማኖት መቀየርን ምርጫው አያደርግም፡፡ ኦሮምያ
ላይ አለ የተባለው ጉዳይም ቋንቋውን በማጥናት መጽናት እንጂ ሃይማኖት መቀየር መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሌላ ቋንቋ የመስማት የመናገር
ፍላጎት አናሳ መሆን የወለደው ችግር መስሎ ይታየኛል ያም ሆነ ይህ ግን በራስ ቋንቋ መማር ማስተማርን ማንም አይከለክልምና የክልል
ሲኖዶስ ይዋቀር ብሎ መጠየቅ መፍትሔ አይመስለኝም፡፡
*******************
ሰነዱ
ይቀጥልና፡-
“ከዚህ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንቱ የሚጠበቅባትን
ባለመወጣትዋ የምትተችባቸው ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
-የአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖር፡፡ ሚሽነሪዎች
በ1889 ዓ.ም በአፋን ኦሮሞ ያሳተሙ ቢሆንም ኦሮቶዶክስ ግን ከ120 ዓመት በኋላም በዝግጅት ላይ ነኝ ማለቷ፤
-አፋን ኦሮሞ ቋንቋ በሚገባ አለመጠቀም፡፡ ለአብነትም
በደብዳቤ ልውውጥ እንዲሁም በሚለጠፉ ማስታወቅያዎች የክልሉን ቋንቋ አለመጠቀም
-በቤተ ክርስቲያን ስም የተጻፉ የኦሮሞን ህዝብ
የሚሳደቡ መጻሕፍት ጉዳይ ላይ መልስ አለመስጠት፤
-ከቤተ ክርቲስቲያን ሚዲያ እንኳ በአፋን ኦሮሞ
አገልግሎት የሚሰጥ አለመኖር እና በሌሎች የኃይማኖት ተቋማት ግን በምዕመናን ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሚዲያዎች መብዛት”
ይህንን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት አሁን የታሰበው
በክልል ደረጃ የሚደራጀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት በአዲስ መንፈስ እና ዘመኑን በዋጀ
አደረጃጀት ተዋቅሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች አገልግሎት መስጠት ቢጀምር ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሄ ይሆናል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ
ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ችግሮቹ ከዚህ እየከፉ ሄደው ወደፊት በኦሮሚያ ክልል አገልግሎት የሚሰጡ አብያተ ክርስቲያናትን
የምናገኘው በትላልቅ ከተሞች ብቻ ይሆናል፡፡
*******************
ቤተ ክርስቲያናችን
በሌሎች ስለምትተችበት ነጥቦች አንሥተዋል፡፡ እነዚህ ነጥቦች ግን የክልል ሲኖዶስ በማዋቀር የሚፈቱ ትችቶች አይደሉም፡፡ አንዳንዶችም
ዝም ብለው የተጻፉ ይመስላሉ፡፡
ነጥብ
1፡-
“የአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖር፡፡ ሚሽነሪዎች
በ1889 ዓ.ም በአፋን ኦሮሞ ያሳተሙ ቢሆንም ኦሮቶዶክስ ግን ከ120 ዓመት በኋላም በዝግጅት ላይ ነኝ ማለቷ”
የመጽሐፍ
ቅዱስ በኦሮምኛ ቋንቋ አለመተርጎም ድክመት ነው፡፡ ይህን መሥራት ያለበት ራሱን የቻለ አካል ቤተ ክርስቲያናችን አላት፡፡ በነገራችን
ላይ በአማርኛ ተርጉሞ የምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስስ በእውነት በትክክል በእኛ ሊቃውንት ታይቶ የተተረጎመ ነው ወይ? ቤተ ክርስቲያናችን
ብዙ ፈተናዎች ስለነበሩባት ትርጉም ሥራ ላይ ብዙም አልገፋችበትም፡፡ ከዐረብ ከእብራይስጥ ከጽርዕ ወዘተ ወደ ግእዝ በመመለስ እስካሁን
ድረስም በግእዝ ተጽፈው በሌሎች ቋንቋዎች ያልተተረጎሙ በርካታ መጻሕፍት አሉ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገራችን ቋንቋ ሆኖ ለረዥም
ዘመናት የኖረው ግእዝ ነውና በግእዝ አንደተጻፉ ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶችን ወደ አማርኛ መልሰዋቸዋል፡፡ በዚያ ልክ ግን ወደ ኦሮምኛ
እና ወደ ትግርኛ እና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች አልተተረጎሙም፡፡ ይህ የተደረገው ግን ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ቋንቋ ማስተማር እንዳለባት
ዘንግታ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን የክልል ሲኖዶስ ከመፍጠር ይልቅ ይህን መሥራት የሚገባውን አካል መጠየቅ ተገቢ ነው ብየ
አስባለሁ፡፡ በዚያ ላይ የትርጉም ሥራ እንዲህ በቀላሉ ቶሎ የሚደርስ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሀሳብ በመስጠት እንዲፋጠን
በመጠየቅ መፍትሔ መፈለግ የሁላችን ድርሻ ነው፡፡
ነጥብ
2፡-
“አፋን ኦሮሞ ቋንቋ በሚገባ አለመጠቀም፡፡ ለአብነትም
በደብዳቤ ልውውጥ እንዲሁም በሚለጠፉ ማስታወቅያዎች የክልሉን ቋንቋ አለመጠቀም”
ድብዳቤ
እና የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ዓላማቸው መልክትን በቀላሉ ማስተላለፍ ነው፡፡ በዚህ ላይ መልእክት አስተላላፊው እና መልእክት ተቀባዩ
የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ ካላቸው በዚያ ይጠቀማሉ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ሁለቱን አካላት የሚያግባባ አንድ የጋራ ቋንቋ ከሌለ ግን በአስተርጓሚ
መግባባት ግድ ማለቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ማስታወቂያ ስትለጥፉ ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ ጽፋችሁ ብትለጥፉ ማነው የሚከለክለው? የቤተ
መንግሥቱን አሠራር እንከተል የምንል ከሆነ ግን የፌዴራል መንግሥቱ ለክልል መንግሥታት ደብዳቤ ሲጽፍ በምን ቋንቋ ነው የሚጽፈው?
ለኦሮምያ ክልል የፌዴራል መንግሥቱ በኦሮምኛ ደብዳቤ ጽፎ ልኮ ያውቃል ወይ? መግባባት በምንችልበት በማንኛውም ቋንቋ መጻጻፍ ይቻላል፡፡
ማነው ይህን አታድርግ ብሎ የከለከለ? ማስታወቂያ ለመለጠፍ ደብዳቤ ለመጻፍ የክልል ሲኖዶስ ይዋቀር ያሰኛል ወይ?
ነጥብ
3፡-
“በቤተ ክርስቲያን ስም የተጻፉ የኦሮሞን ህዝብ
የሚሳደቡ መጻሕፍት ጉዳይ ላይ መልስ አለመስጠት”
በቤተ
ክርስቲያን ስም የተጻፉ ማንኛውንም ሕዝብ የሚሳደቡ መጻሕፍት ካሉ መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን ማቃጠልም ይገባል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብን
የሚሳደቡ የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ይኖራሉ ብየ አላስብም፡፡ ነገር ግን መጻሕፍት በተጻፉበት ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረውን የቃላት
አጠቃቀም ዛሬ በምንሰጠው ትርጓሜ የምንተረጉማቸው ከሆኑ ስድቦች መመሰላቸው አይቀርም፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ጊዜ ሐዋርያትን
የዓለም ጨው ብሏቸዋል፡፡ ጨው የሚለው ቃል በዚያ ዘመን አልጫን የሚያስወግድ ምግብን የሚያጣፍጥ ማለት ነው፡፡ አንባቢም የሚለዳው
በዚያ መልኩ ነበር፡፡ ለዛሬ ሰው ጨው ብትለው ግን የሚረዳው የበሽታ ምንጭ መሆኑን ነው፡፡ ጨው ሲባል የሚመጣበት የኩላሊት፤ የጨጓራ
በሽታ ነው፡፡ ታዲያ ጨው ዛሬ ተነሥተን ሐዋርያትን የዓለም ጨው ናችሁ መባል የለባቸው ስድብ ነውና ብንል ችግሩ ያለው የተጻፈበትን
እና ያነበብንበት ዘመን ልዩነት ነው፡፡ በተለያዩ መጻሕፍት ስናነብ “ጋላ” “ሻንቅላ” ወዘተ የሚሉ ቃላት አሉ፡፡ እነዚያ ቃላት
የተጻፉ ከደርግ ዘመን በፊት በነበሩ መጻሕፍት ላይ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ትርጓሜያቸው ሲታይ “አረሚ” “ያላመነ” “የክርስትና ጠላት”
“የዐምሐራ ጠላት” ወዘተ የሚል ነው፡፡ እነዚህ ቃላት የሆነ ሕዝብን የሚሰድቡ ሳይሆኑ ኢ አማንያንን የሚገልጡ ቃላት ነበሩ፡፡ ዛሬ
ላይ ሆነን ስናነባቸው ግን ስድቦች ናቸው፡፡ ልዩነቱ ቃሉ የተጻፈበት ዘመን እና እኛ ያነበብንበት ዘመን ላይ ያለ የቃሉ ትርጓሜ
ነው፡፡ እነዚህ ቃላት ስድቦች ሆነው ከተገኙ እንዲቀየሩ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የተሐድሶ መናፍቃን
ናቸው ይህን ጥያቄ አንግበው የተመለከትናቸው፡፡ እነዚያ ተሐድሶዎቹ ዓላማቸው የኦሮሞ ሕዝብን የተሰደበ አስመስለው በማቅረብ ቤተ
ክርስቲያናችንን ማስነቀፍ ነው፡፡ የቆዩ መጻሕፍት “ዐምሐራ” ሲሉ ክርስቲያን ማለታቸው እንጂ የዛሬውን የአማራ ሕዝብ ማለታቸው አልነበረም፡፡
ምናልባት ዛሬ አማራ በምንለው ክልል ግን ክርስቲያኖች በብዛት ኖረውበት ሊሆን ይችላል፡፡ ዐምሐራ ማለት ግን በዚያ ዘመን ክርስቲያን
ማለት እንጂ የሆነ ሕዝብ እንዳልተወከለበት ግልጥ ነው፡፡ “ጋላ” የሚለውን ቃል “ጸረ ዐምሐራ” ብለው ሲተረጉሙም የክርስቲያን ጠላት
ማለት እንጂ የአማራ ሕዝብ ጠላት ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን በዛሬው ትርጓሜ ከተመለከትነው ግን መበላላታችን አይቀሬ ነው፡፡
እስ እናቶቻችንን ጠይቁ “ዐምሐራ እና እስላም ነን” ይላ እኮ፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ አንገናኝም እንጣላለን ሲሉ “ዐምሐራ እና እስላም
እንዳንሆን” ሲሉ ይሰማሉ፡፡ በዚህ ትርጓሜ ዐምሐራ የሚለው ክርስቲያን ማለት እንጂ ሕዝብ ማለት እንዳልሆነ ግልጥ ነው፡፡ በቅርቡ
ለመጣ ለእንደእኛ ዓይነቱ ግን በዛሬው ትርጓሜ ነው የምንረዳው፡፡ ስለዚህ የሚሳደቡ መጻሕፍት አሉ ከተባለ ለይቶ ለሊቃውንት ጉባዔ
ማቅረብ እንጂ ሲኖዶስ ማዋቀር መፍትሔ አይደለም፡፡
ነጥብ
4፡-
“ከቤተ ክርቲስቲያን ሚዲያ እንኳ በአፋን ኦሮሞ
አገልግሎት የሚሰጥ አለመኖር እና በሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ግን በምዕመናን ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሚዲያዎች መብዛት”
ይህ እንደአጠቃላይ
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን መሠራት ያለበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ያላት አንድ የቴሌቪዥን ሚዲያ ነው፡፡ ፕሮቴስታንቶች ግን ለቁጥር
አዳጋች የሆነ ሚዲያ አላቸው፡፡ ገንዘቡ ካለ ይህን ሚዲያ ማቋቋም ይቻላል፡፡ ይህን ለማቋቋም ገንዘብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ለቤተ
ክርስቲያናችን ካሰብን እየተደራጀን ክፍያውን እየፈጸምን ሚዲያዎችን እናቋቁም፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ቤተ ክርስቲያናችን ያላት መዋቅር
በቂ ነው የክልል ሲኖዶስ እንዲዋቀር አያስገድድም፡፡
*******************
ሰነዱ
አሁንም ይቀጥልና፡-
“በመሆኑም ይህ ሰነድ በክልል ደረጃ ያለውን የመዋቅር
ክፍተት ለመሙላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በማቋቋም ለመገልገል እና ጽሕፈት
ቤቱ የሚመራበት ደንብ እና የሚኖረው አደረጃጀት ምን እንደሚመስል የያዘ ነው” ይላል፡፡
ከላይ
በችግር መልክ የተገለጡትን ነገሮች በዚህ ሰነድ በተገለጠው የክልል ሲኖዶስ መፍታት ይቻላል ወይ? የተገለጡ ችግሮችስ የክልል ሲኖዶስ
እንዲዋቀር ያስገድዳሉ ወይ? አሁን ባለው የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር መፍታት የማንችልበት ምን አስገዳጅ ሁኔታስ አለ?
አንድነት
ሆይ ወዴት አለሽ?
No comments:
Post a Comment