Sunday, April 14, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 64

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ አድኅኖተ ለምጽ።
ምዕራፍ ፰።
                  ******  
፲፰፡ ወመጽአ ኀቤሁ አሐዱ ጸሐፊ
                  ******   
፲፰፡ ጸሐፊ ማለት አዋቂ ነኝ የሚል ሰው ወደሱ መጣ።
ወይቤሎ ሊቅ እትሉከኑ ኀበ ሖርከ።
መምሕር ልደርልህ አለው።
                  ******  
፲፱፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ለቈናጽልኒ ግበብ ቦሙ።
                  ******  
፲፱፡ ለቀበራርት ፍርክታ አላቸው።
ወለአዕዋፈ ሰማይኒ ምጽላል ቦሙ።
ለአዕዋፍም ማረፊያ መስፈሪያ ዛፍ አላቸው።
                  ******  
፳፡ ወለወልደ እጓለ እመሕያውሰ አልቦቱ ኀበ ያሰምክ ርእሶ። ሉቃ ፱፥፶፰።
                  ******  
፳፡ ለወልደ እጓለ እመሕያው ለኔ ግን ራሴን የማስጠጋበት ቦታ የለኝም ለመኳንንቱ ለካህናቱ እደርላቸው እንጂ ለኔ ለምን ታድርልኛለህ አለው።
ቈናጽል አላቸው መኳንንትን ቊንጽልን ተመያኒ ይለዋል ተንኰለኛ ነው ወያወጽእ ፊሳዮ እንዲል ክፉ መዓዛ አለው ያን አውጥቶ የሞተ መስሎ ከጉድጓዱ አፍ ወጥቶ ይተኛል። ተሐዋስያን ሲሸታቸው የሞተ መስሏቸው ሊበሉ ይቀርባሉ እያነቀ ከጉድጓድ ይዞ ገብቶ ይመገባል። መኳንንትም በተሾሙበት አገር በኛ ጊዜ ርስትህን ጉልትህን አላስመለስህ በማን ጊዜ ልታስመልስ ነው ብለው ይገጥሙታል ቢረታ ዳኝነት ቢረታ መማለጃ ይበሉታልና። ካህናትን አዕዋፍ አላቸው ለአዕዋፍ ዘር መከር እንደሌላቸው ለካህናትም ዘር መከር የላቸውምና።
አንድም በቊንጽል በዖፍ ለተመሰለ ለገንዘብ አንተ ማደሪያ አለኸው። ቊንጽል አለው ይተነኩሉበታልና። ዖፍ አለው ፈጥኖ ይጠፋልና። ወልደ እጓለ እመሕያውሰ። ልደርልህ ማለት እንጂ እደርብኝ ማለት ነው የገንዘብ ማደሪያ ሁነህ በየት ልደርብህ አለው።
አንድም ቊንጽል ዖፍ ለተባለ ለዲያብሎስ ማደሪያ አንተ አለኸው የተመቸ ተንኮለኛ ነውና። ዖፍ ፈጥኖ ያስታልና በውሳጤ ቤትከ ኢትርግም ብዑላነ እስመ ዖፈ ሰማይ ያወጽኦ ለነገርከ እንዲል። ወልደ እጓለ እመሕያውሰ የዲያብሎስ ማደሪያ ሁነህ ሳለህ በየት ልደርብህ አላድርብህም አለው።
አንድም ለቊንጽል ለዖፍ ላንተ ማደረያ ገሃነም አለህ እኔ ግን አላድርብህም። ቊንጽል አለው ጥንቈላ መስሎት ተምሬ በታምራቱ እበላበታለሁ ብሎ በተንኰል መጥቷልና። ዖፍ አለው በጥቂት ቀን ነጥቄ እሄዳለሁ ብሎ መጥቷልና።
አንድም ለቈናጽል ለአይሁድ ማደሪያ ገሃነም አላቸው። በአዕዋፍ በሐዋርያት እኔ አድርባቸዋለሁ በአይሁድ ግን አላድርባቸውም። ምጽላል ባለው አቡኳር የሚል አብነት ይገኛል የጭቃ ቤት የምትሠራ ዖፍ አለችና።
                  ******  
፳፩፡ ወይቤሎ ካልእ እምአርዳኢሁ እግዚኦ አብሐኒ እቅድም ወእሑር ወእቅብሮ ለአቡየ።
                  ******  
፳፩፡ ከሕዝቡ አንዱ አሰናብተኝ አስቀድሜ ሂጄ አባቴን ልቅበር አለው። ከጉባዔው ከዋለ ሁሉንም ደቀ መዝሙር ማለት ልማድ ነውና እንዳህ አለ እንጂ ከሕዝቡ አንዱ ነው። ሙቷል ቢሉ ልቅበረው አልሞተም ቢሉ ልርዳው አለው።
                  ******  
፳፪፡ ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ አንተሰ ትልወኒ ።
                  ******  
፳፪፡ አንተስ ተከተለኝ አለው። ለጊዜው በእግር ተከተለኝ ፍጻሜው በግብር ምሰለኝ አለው።
ወኅድጎሙ ለምዉታን ይቅብሩ ምውታኒሆሙ፡፡
ሙተዋል ቢሉ ሙታን እናት አባትህን ሙታነ ሕሊና ዘመዶቻቸው ይቅበሯቸው አንድም አልሞቱም ቢሉ ሙታነ ሕሊና እናት አባትህን ሙታነ ሕሊና ዘመዶቻቸው ይርዷቸው ያጥቧቸው፡፡
አንድም ሙታነ ሕሊና እናት አባትህን ምውት ገንዘባቸው ይርዳቸው ያጥባቸው።
                   ******  
፳፫፡ በከመ ዓኅድአ ለባሕር ወዓሪጎ ውስተ ሐመር ተለውዎ አርዳኢሁ። ማር ፬፥፴፮።
                   ******  
፳፫፡ ከመርከብ በወጣ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ተከተሉት፤
                   ******  
፳፬፡ ወናሁ ዓቢይ ድልቅልቅ ኮነ በውስተ ባሕር
                   ******  
፳፬፡ ባሕሩ ተናወጸ።
እስከ ሶበ ይደፍኖ ለሐመር ማዕበለ ባሕር ።
ማዕበሉ መርከቡን አሰጥመዋለሁ እስኪል ድረስ።
ወውእቱሰ ይነውም።
እሱ ግን ተኝቶ ነበር ኖመ ከመ ውሉደ ሥጋ እንዲል።
                   ******  
፳፭፡ ወቀርቡ አርዳኢሁ ወአንቅሕዎ
                   ******  
፳፭፡ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው ቀሰቀሱት።
ወይቤልዎ እግዚኦ አድኅነነ ከመ ኢንሙት።
አቤቱ ከስጥመት አድነን አሉት።
                   ******  
፳፮፡ ወይቤሎሙ ምንት ያፈርሃክሙ አሕፁፃነ ሃይማኖት።
                   ******  
፳፮፡ እናንት ሃይማኖት የሌላችሁ ምን ያስፈራችኋል ከሱ ጋራ ሳለን ጥፋት አያገኘንም በሱ ስም አምነን እንድናለን አትሉም አላቸው፡፡
ወተንሢኦ ገሠፆሙ ለነፋሳትኒ ወለማዕበለ ባሕር።
ተነሥቶ ነፋሳትን ማዕበለ ባሕርን ገሰጻቸው፡፡
ወኮነ ዐቢ ዛኅን
ታላቅ ጸጥታ ተደረገ ማለት ጸጥ አለ።
                   ******  
፳፯፡ ወአንከሩ ሰብእ
                   ******   
፳፯፡  ሕዝቡ አደነቁ።
ወይቤሉ መኑ እንጋ ውእቱ ዝንቱ ዘይትኤዘዙ ሎቱ ባሕርኒ ወነፋሳትኒ።
ባሕር ነፋሳት የሚታዘዙለት ይህ ማነው አሉ።
አንድም ወዓሪጎ ብለህ መልስ ኦሪትን በሠራ ጊዜ ነቢያት፤ ወንጌልን በሠራ ጊዜ ሐዋርያት በግብር መሰሉት።
ወናሁ ዓቢይ ድልቅልቅ ኮነ በውስተ በሕር።
በሰውነታቸው መከራ ጸናባቸ ው።
እስከ ሶበ ይደፍኖ ለሐመር።
ሕጋቸው ኦሪትን ሕጋቸው ወንጌልን አስተዋቸዋለሁ እስኪል ድረስ።
ውእቱሰ ይነውም
ትእግሥቱን መናገር ነው።
ቀርቡ ወአንቅሕዎ
አቤቱ ከመከራ አድነን ብለው ለመኑት።
ምንት ያፈርሃክሙ አኅዑፃነ ሃይማኖት።
መከራ ብትቀበሉ ክብር ይበዛላችኋል እንጂ ምን ያደርጋችኋል ምን ያስፈራችኋል አላቸው።
ወተንሢኦ ገሠፆሙ
ከትዕግሥቱ ወጥቶ መከራውን አራቀላቸው
ወኮነ ዓቢይ ዛኀን።
መከራው ራቀላቸው።
አንድም ወዓሪጎ
ተባሕትዎ በያዘ ጊዜ ባሕታውያን፤ ወደ መስቀል በወጣ ጊዜ ሰማዕታት በግብር መሰሉት በሰውነታቸው መከራ ጸናባቸው ገድላቸውን እስኪያስተዋቸው ድረስ ትዕግሥቱን መናገር ነው። ለመኑት እናንት ሃይማኖት የሌላችሁ ምን ያስፈራችኋል። መከራ ክብር ያበዛላችኋል እንጅ ምን ያደርጋችኋል አላቸው ከትእግሥቱ ወጥቶ ለሰማዕታት ነበልባል አብርዶ አንበሳ አሰግዶ ለባሕታውያን ቶራ እንዲታለብላቸው ዛፍ እንዲያፈራላቸው አድርጎ ረዳቸው መከራው ቀረ።
                   ******   
በእንተ አጋንንት ዘብሔረ ጌርጌሴኖን።
፳፰፡ ወበጺሖ ማዕዶተ ጌርጌሴኖን ተቀበልዎ ፪ቱ እለ አጋንንት ወፂዖሙ እመቃብራት። ማር ፭፥፩፡፡ ሉቃ ፰፥፳፮፡፡
፳፰፡ ጌርጌሴኖን በደረሰ ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተቀበሉት።
                  ******   
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
06/08/2011 ዓ.

No comments:

Post a Comment