Sunday, April 14, 2019

“የዘር ፖለቲካ የወለደው የክልል ሲኖዶስ ጥያቄ” --- ክፍል 2

========================================
የክልል ሲኖዶስ ጥያቄን የያዘውን ሰነድ ከታች በፎቶ እንደምትመለከቱት ሃይማኖታዊነቱ ላልቶ ፖለቲካዊነቱ ጎልቶ የታየበት ነው፡፡ የዚህ ሰነድ ደጋፊዎችየክልል ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት እንጂ ሲኖዶስ እናቋቁም ስላላልን ሲኖዶስ ብለህ የጻፍከውን ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ብለህ አስተካክለው” ብለውኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች ምናልባትም የሲኖዶስን ትርጓሜ ስላላወቁት ካልሆነ በቀር በዚሁ ሰነድ እንደተገለጠው የክልሉ ጳጳሳት ጉባዔ እንደሚኖራቸው አንቀጽ 10 ላይ በግልጥ ተጽፎ ይታያል፡፡ ታዲያ በክልሉ የሚገኙ የየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጉባዔ ይኖራቸዋል ካለ ይህ ጉባዔ ምን እንዲባል ነው የሚጠበቀው? ሲኖዶስ ማለት እኮ ጉባዔ ጳጳሳት ማለት ነው ሌላ ትርጓሜ አንሰጠውም፡፡


ስለዚህ እኔም የክልል ሲኖዶስ እያልኩ እቀጥላለሁ ማለት ነው፡፡ የሰነዱን ሙሉውን ሃሳብ ለማግኘት ከታች የተያያዘውን ፎቶ ተመልከቱት፡፡ ለዛሬ እነዚህን ገጾች እንመለከታለን ወደፊት ደግሞ ወደፊት የሚገኙትን እናያለን፡፡ እኔ የምሄደው ሃይማኖታዊነታቸው ደብዝዞ ፖለቲካዊነታቸው አይሎ ባገኘኋቸው ነጥቦች ላይ ብቻ ነው፡፡ እነዚህንም ነጥቦች በቀይ መስመር አስምሬባቸዋለሁ፡፡
                     **********
ሰነዱ እንዲህ የሚል ሃሳብ ይዟል፡-
                     **********
1983 . በመጣው የመንግስት ለውጥ ምክንያት ሀገራችን የምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት የተዋቀረ በመሆኑ በክልል ደረጃ ክልሎች ተዋቅረ ህዝባቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ክልላዊ አስተዳደደር ከተቋቋመ ወዲህ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም እስከ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ክልላዊ መንግስት አስተዳደደር ተከትላ በክልል ደረጃ የራሷን ጽህፈት ቤት ከፍታ ስትገለገልበት አልቆየችም ይላል፡፡
                     **********
ይህ ሀሳብ በዋናነት 2 ነጥቦችን ይዟል፡፡ 1ኛው፡- መንግሥት 1983 . ወዲህ እከተለዋለሁ የሚለውን ፌዴራሊዝም እና የዘር ፖለቲካ ሰነዱ መደገፉን፡፡ 2ኛው፡- ከቤተ ክህነት ይልቅ የተሻለ መዋቅር የሚከተለው ቤተ መንግሥት እንደሆነ በማሳየት ቤተ ክህነትን አኮስሶ ቤተ መንግሥትን አሞግሶ መሄድ ነው፡፡
                     **********
ነጥብ 1-
1983 ወዲህ መንግሥት እየተከተለ ያለው የዘር ፖለቲካ እና ፌዴራሊዝም በብዙዎች ዘንድ ተቃውሞ የደረሰበት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ተቃውሞ ደረሰበትም አልደረሰበትም ግን መንግሥት መዋቅሩን የፈጠረው ለማስተዳደር ይመቸኛል በሚል እንጂ ቤተ ክርስቲያንም በዚያ መንገድ እንድትዋቀር አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በጻፈው ሕገ መንግሥት ላይሃይማኖት በመንግሥት መንግሥትም በሃይማኖት ጣልቃ መግባት አይችሉም” ብሎ የፍቺውን ደብዳቤ ጽፎ አኑሯል፡፡ ታዲያ በግድ ከመንግሥት ጋር መጋባት አለብኝ ብለን ብናለቃቅስ ምን ዋጋ አለን? መንግሥት በራሱ ክልል ብሎ ያዋቀረበት መንገድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኖ ዛሬ ላይ ለደረስንበት የከረረ ብሔርተኝነት አብቅቶናል፡፡ ክልል ብሎ ያዋቀረበት መንገድስ በምን መልኩ ነው? ቋንቋን ወይስ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን ወይስ ምንን መሠረት አድርጎ ነው ክልልን ያዋቀረ? የክልሎች መዋቅር በእውነት ለሀገራችን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አላመዘነም ወይ? በፖለቲካው ዓይን እንደ ምድራውያን ብትመለከቱት እንኳ ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ አይታይም እንደ አማኝ እንደ ሰማያዊ ስታዩት ደግሞ ይበልጥ ጎጅ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ የክልል መንግሥተ ሰማያት የለምና፡፡ ሰማይ ቤትም ሄደን መንግሥተ ሰማያትን ወይም ሲዖልን በክልል እንከፍላቸው ይሆን? ሰማያውያን ነን ብለን የምናስብ ከሆነ አንድ መንግሥተ ሰማያት ናት ያለችን ስለዚህም ይህን መከፋፈል አብዘተን እንጠየፈዋለን፡፡
                     **********
ነጥብ 2-
ሌላኛው ነጥብ ከቤተ ክህነት ይልቅ ቤተ መንግሥት እንደሚበልጥ የሚያሳይ ነው፡፡እምነ መንግሥት የዐቢ ክህነትከቤተ መንግሥት ቤተ ክህነት ይበልጣል ከሥርዓተ ቤተ መንግሥት ሥርዓተ ቤተ ክህነት ይበልጣል እያለች ስታስተምር ለኖረች ብቸኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህ ሃሳብ በእጅጉ የተበላሸ ነው፡፡ ቤተ ክህነት ለቤተ መንግሥት ማስተማር የምትችለው እልፍ አእላፋት ነገር እያለ የራሷን ጥላ የሰውን አንጠልጥላ እንድትሄድ መመኘት በእውነቱ ታሪኳን ካለማወቅ ትምህርቷን ካለመዝለቅ የመጣ ሃሳብ ነው፡፡
                     **********
ይህ ሰነድ አሁንም ይቀጥልና የክልል ሲኖዶስ ባለመኖሩ ደረሰ ስለሚለው ነገር ይዘረዝራል -
                     **********
“ይህ ባለመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን በክልል ደረጃ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም ያሳጣት እና ልዩ ልዩ ችግሮች በክልል ደረጃ በቤተ ክርሰቲያቱ ላይ ሲፈጠሩ መብቷን ለማስከበር አቻ መስሪያ ቤት ስለሌላት ጉዳዮችዋን በክልል ደረጃ ለማስፈጸም አስቸጋሪ ከመሆኑም አልፎ የሌሎች የእምነት ተቋማት መዋቅሩን በመጠቀም ሲደራጁ እና የሚፈልጉትን ጥቅም ሲያገኙ ቤተ ክርስቲያናችን ግን ይህንን ባለማድረጓ ብዙ ሰዎች የተለየ ትርጉም በመስጠት ቤተ ክርስቲያን ህዝብ የተቀበለውን እና ያመበነትን እንደማትቀበል በመሰበኩ ብዙ ተከታዮችዋን ለማጣት መነሻ ሆኗል”
                     **********
በዚህ ሃሳብ ላይ 3 ነጥቦች ይታያሉ፡፡ 1ኛው፡- በክልል ብትዋቀር የሚያስገኛትን ጥቅም ማጣቷን፡፡ 2ኛው፡- የሌሎች ቤተ እምነቶች የክልል መዋቅርን ሲጠቀሙ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ግን አለመጠቀሟ እንዳስተቻትና አማኞቿን እንዳሳጣት፡፡ 3ኛው፡- የመንግሥትን የክልል መዋቅር ሕዝቡ እንደተቀበለው፡፡
                     **********
ነጥብ 1-
ቤተ ክርስቲያናችን በክልል በመዋቀሯ ከማንም የምታገኘው ጥቅም የላትም ባለመዋቀሯም ከማንም ያጣችው ጥቅም የላትም፡፡ በክልል ስትዋቀር የምታገኘው የተለየ ጥቅም ምንድን ነው? ጥቅምስ ከማን የሚገኝ ነው? ቤተ ክርስቲያናችን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሀገረ ስብከት ከዚያም ወረዳ ቤተ ክህነት ከዚያም ሰበካ ጉባዔ የሚባል መዋቅር አላት፡፡ በዚህ መዋቅሯ መሠረት አንድ አማኝ ተረስቶ ቤተ ክርስቲያን አላውቅህም የምትለው የላትም፡፡ ልጆቿን በሚገባ የምታውቅበት መዋቅር አላት፡፡ በእነዚህ መዋቅሮች ሊፈታ የማይችል ምን ችግር ገጥሞ ያውቃል? የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር የሚፈታልን መንግሥት ያዋቀረው መስሪያ ቤት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ያዋቀረችው ነው፡፡ ታዲያ ችግር ሲደርስብን እንዲፈታልን የምንሄደው ወደ ቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር እንጂ ወደ መንግሥት መዋቅር ይመስል የመንግስትን መዋቅር አቻ መዋቅር ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ይፈጠር ማለት ምን ማለት ነው?
በክልል መዋቀሯ ልዩ ተጠቃሚ ሊያደርጋት የሚችለው በምን መልኩ በምን መንገድ ነው? የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በእርግጠኝት ችግር የለበትም ችግር ያለው እኛ ላይ ነው፡፡ በዚህ መዋቅር ምን ሠራን? እኛ ተኝተን ባሳለፍነው ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን ልትወቀስበት አትችልም፡፡
                     **********
ነጥብ 2-
“ሌሎች ቤተ እምነቶች የመንግሥትን የክልል መዋቅር ተከትለውታል የእኛ ግን አልተከተለችም” የሚለው ማለቃቀስ የጤና አይደለም፡፡ ሌሎች እምነቶች እኮ ሀገራችንን እየመራ ካለው መንግሥት የዘለለ ዕድሜ የሌላቸው ናቸው፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ግን ከሀገራችን ታሪክ በላይ ዕድሜ ያላት ናት፡፡ ታዲያ ከእኛ መማር ይገባቸው ነበር እንጂ እኛ ከእነርሱ ልንማር ይገባል ወይ? ሌሎች እምነቶች በቅርቡ ስለተመሠረቱ በቅርቡ ስላለው መዋቅር እንጂ ራቅ ብለው ከሐዋርያት ጀምሮ ሲያያዝ ስለመጣው መዋቅር አያውቁም ስለዚህ ከቻላችሁ እንዲያውቁት አድርጉ ካልቻላችሁ ግን ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም ብላችሁ ዝም ብትሉ ሳይሻል አይቀርም፡፡ የሚገርመው ነገር ሌሎች እምነት ድርጅቶች የክልል መዋቅርን በመከተላቸው እኛ ግን ባለመከተላችን ብዙ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያናችን ወደ ሌሎች እምነቶች እንደገቡ የተገለጠበት መንገድ ነው፡፡ በእውነት ይህን ምክንያት አድርጎ ሃይማኖቱን የቀየረ ሰው ካለ እሱ መጀመሪያም ከእኛ ወገን አልነበረም ማለት ነው፡፡
                     **********
ነጥብ 3-
“መንግሥት እየተከተለ ያለውንክልል መዋቅር እና አከላለል ሕዝቡ ተቀብሎታል” በሚል የተቀመጠው ሃሳብ ግን አወዛጋቢ ነው፡፡ ስንት ሰው ነው ይህን የክልል አከላለል የተቀበለው? እስኪ ጥናት ይደረግ፡፡ የክልል አከላለሉ ትክክል እንዳልሆነ፤ ክልል የሚለው ስምም በራሱ እንዲጠፋ የሚማጸን ብዙ ሰው ነው ያለ፡፡ ይህን በጥናት አረጋግጡት፡፡ የራስን የግል ፍላጎት ግን በሌሎች ላይ መጫን አይቻልም አይፈቀድምም፡፡
                     **********
ሰነዱ አሁንም እንዲህ ሲል ይቀጥላል፡-
                     **********
“በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ በመጠቀም የመንግስትንም አደረጃጀት በማክበር እና በማስከበር እንዲሁም በመከተል እራሷን አደራጅታ ህዝቦችዋን ካልጠበቀች በስተቀር ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባታል” ይላል፡፡
                     **********
እዚህ ላይ የተነሣው ሃሳብ ቤተ ክርስቲያን የግድ ከመንግሥት በታች ሆና መንግሥት ባስቀመጠላት መዋቅር መመራት ግዴታዋ እንደሆነ ተደርጎ ነው የተገለጠው፡፡መንግሥት ያስቀመጠውን አደረጃጀት ማክበርና ማስከበር እንዲሁም መከተል ሕዝቦቿንም በዚያ መልኩ መምራት ግዴታዋ ነው፤ ይህን ካላደረገች ግን ችግር ይገጥማታል” በማለት የማይፈጸም ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ አሁንም እደግመዋለሁ ሀገርን ለመምራት ከተፈለገ መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር መጠቀም ያተርፈዋል እንጂ አያከስረውም፤ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን መዋቅር ብትጠቀም ግን ትከስራለችና አታተርፍም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክህነት ከቤተ መንግሥት በብዙ እጥፍ ትልቃለችና፡፡ ወደድንም ጠላንም ቤተ ክህነት ከመንግሥት የተሻለች ናት፡፡ እኛ ሳይወዱን በግድ ከመንግሥት ጋር እየተለጠፍን ባበላሸነው ነገር የቤተ ክህነት ኃያልነት ሊተች አይገባውም፡፡
                     **********
ሰነዱ አሁንም ይቀጥልና ቤተ ክርስቲያናችን የመንግሥትን መዋቅር ጠብቃ ባለመጓዟ ስለደረሰባት አደጋ ይዘረዝራል፡፡
                     **********
“ከተጋረጡባት አደጋዎች በከፊል ስንመለከት፡-
 - በኦሮሚያ ክልል ገጠር አከባቢዎች የብዙ አብያተ ክርስትያናት መዘጋት፡፡ - የምዕመናን ቀኖናዊ ሕይወት መዳከም፡፡
- በአፋን ኦሮሞ የኦርቶዶክስ መዝሙር በብዛት ስለማይገኙ ያሉትም ቢሆን ያልተዳረሱ በመሆናቸው (ለአብነትም የሰርግ፤ የበዓላት መዝሙሮች እና ወረቦች ባለመኖራቸው) ምዕመናን በሌሎች የእምነት ተቋማት የተዘጋጁ መዝሙሮችን አፋን ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ በማዳመጥ ወደ ሌሎች ሃይማኖቶች መሳብ፤ - ኦርቶዶክሳዊ የአፋን ኦሮሞ የሚዲያ እጥረት
- በአፋን ኦሮሞ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ለሚሰነዘሩ ነቀፌታዎች መልስ አለመስጠት ፤ አለመከታተል እና በህግ ሊጠየቁ የሚገቡ ጉዳዮችንም ጭምር በዝምታ ማለፍ፤
- የአፋን ኦሮሞ ቅዳሴ በአብዛኛው አህጉረ ስብከቶች አለመጀመር
- በቤተ ክርስቲያናችን ተተርጉሞ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ በአፋን ኦሮሞ አለመኖር (በ1899 ዓ.ም በኦኔሲሞስ ቢተረጎምም ትርጓሜው በፕሮቴስታንቶች የአስተምህሮ ስለ ተተረጎመ ብዙ ቦታዎች ላይ በተለይ በመሠረታዊ ምስጥራት ያዘሉ ንባቦች ላይ የተለየ ትርጉም በሚሰጠው መጽሐፍ በመጠቀማቸው፤ ምዕመናንን እያሳሳተ ይገኛል፡፡
- የቤተ ክርስቲያን ተተኪ አገልጋዮች የሚፈሩበት የአብነት ት/ቤቶች በብዛት አለመደራጀት፣ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ በተለይም የቋንቋ ጉዳይ እጅግ ሊታሰብበት የሚገባ ነው” ይላል፡፡
                     **********
ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ያዋቀረውን የክልል አደረጃጀት ባለመጠቀሟ የተጋረጠባት አደጋ ከላይ በተዘረዘረው መልኩ የቀረበ ነው፡፡ የክልል ሲኖዶስ ቢቋቋም ግን እነዚህ አደጋዎችን እንደሚከላከል ነው የሚናገሩት፡፡ በመጀመሪያ በኦሮሚያ ክልል እነዚህ አደጋዎች ተፈጠሩ ሲባል የሌሎች ክልሎች ተሞክሮ እንዴት ነው ብሎ ማየትስ አይገባም ነበር ወይ? በሌሎች ክልሎች ውስጥ ከኦሮምያ ክልል ቀድመው የክልል ሲኖዶሶች ተዋቅረዋል ወይ? ካልተዋቀሩባቸውስ እነዚህን ኦሮምያ ላይ አደጋ ናቸው የተባሉት ነጥቦች በሌሎች ክልሎች ላይ እንዴት አደጋ ሊሆኑ አልቻሉም? እነዚህን ነጥቦች እስኪ ቆም ብለን እንመርምራቸው፡፡
በእውነት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት ከክልሉ ይልቅ ወረዳ ቤተ ክህነቱ እና ሰበካ ጉባዔው አይቀርቡትም ወይ? በእውነት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት አሥራት በኩራትን ማውጣት እንጂ የክልል ሲኖዶስ ማዋቀር ነው ወይ መፍትሔው? የምዕመናንን ቀኖናዊ ሕይወት ለማሻሻል የክልል ሲኖዶስ ይዋቀር ከማለት ይልቅ የንስሐ አባት ማዘጋጀት ይበጃል፡፡ በቀኖናዊ ሕይወቱ የደከመ ሰው ክልል ሄዶ ሕይወቱን እንዲያስተካክል ነው የተፈለገው?
በአፋን ኦሮሞ መዝሙር እና ስብከቶችን ለማሰራጨት የክልል ሲኖዶስ ምን ይሠራል? በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጁ ብዙ መዝሙራት አሉ ስብከቶችም እየተሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህ በቂ ናቸው ወይስ አይደሉም ለሚለው መቼም ቢሆን የሚያልቅ ትምህርት እስከሌለን ድረስ በቂ አይደሉም፡፡ ታዲያ መዝሙር ለማሳተም የክልሉ ሲኖዶስ ምን ይሠራል? መዘመር የሚችል ሰው በአፋን ኦሮሞ ስለሆነ ቀረጻ አናደርግም ያለው አካል ካለ ያን አካል ያሳውቁን በጋራ እንታገለው፡፡ በአፋን ኦሮሞ ስብከቶችን ማዘጋጀት አትችሉም ያለ አካል ካለ የሁላችን ጠላት ነውና በጋራ እንታገለው፡፡ እነዚህ አደጋዎች ግን የክልል ሲኖዶስ ቢዋቀርም ባይዋቀርም ካልሠራን አደጋዎች ከሠራን ደግሞ መዳኛዎች ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች በእኛ እጅ ላይ ያሉ ስለሆኑ ከሌሎች ክልሎች ልምድ መውሰድ ጥሩ ነው፡፡ በትግርኛ እና በአማርኛ መዝሙራት ሲዘጋጁ ስብከቶች ሲቀረጹ የክልል ሲኖዶስ አላስፈለጋቸውም ታዲያ ኦሮምያ ላይስ ያን ማድረግ ማን ነው የሚከለክለው?
በአፋን ኦሮሞ ከመናፍቃን ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የክልል ሲኖዶስ አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡ የክልሉ ሲኖዶስ ምን ሊፈጥር ይችላል? የአፋን ኦሮሞ ቅዳሴ እንዲጀመር ለማድረግ ከቀዳሾቹ ጋር መወያየት እንጂ የክልል ሲኖዶስ ማዋቀር መፍትሔ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ እንዳልሆነ የሚያሳይ እንዲህ ያለው ነጥብ ነው፡፡ ክልል ላይ ሲኖዶስ ካዋቀርን ከአፋን ኦሮሞ ውጭ የሚናገሩ ሊቃውንትን ከአገልግሎት ለማገድ ይቀለናል በሚል እንጅ ለምእመናን ተጨንቀው የጀመሩት አይመስለኝም፡፡ ቅዳሴው የሚቀደሰው ለነፍሳችን እንጂ ለሥጋችን እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ እምነታችን ደግሞ ምድራዊት ሳትሆን ሰማያዊት ናት፡፡ ቋንቋችን ደግሞ የሥጋችን መግባቢያ ምድራዊ ነው፡፡ በሰማይ ሁላችን የምንግባባው አምላክን የምናመሰግነው በአንድ ቋንቋ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ይህን ቋንቋ ይዘን አንሄድም፡፡ በሚገባን ቋንቋ እንማር እናስተምር የሚለው በጎ ሃሳብ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን በቋንቋችን ልክ ሲኖዶስ ማዋቀር አይጠበቅብንም፡፡
በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖሩ ችግር ነው በትክክል አለመኖሩን ባላረጋግጥም፡፡ እሱ መኖር እንዳለበት ማንም ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን የአፋን ኦሮሞ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘጋጅልን ብሎ ለመጠየቅ የክልል ሲኖዶስ ማዋቀር መፍትሔ ነው ወይ? ተተኪ መምህራንን ለማሰልጠን የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማደራጀት እኛ አንበቃም ወይ? ከእኛ የሚጠበቀውን ነገር ምን አድርገናል? አብነት ትምህርት ቤቶችን ለማደራጀት ከክልል ሲኖዶስ ይልቅ ሰበካ ጉባዔው ወረዳ ቤተ ክህነቱ እና ሀገረ ስብከቱ ቅርቦቹ አይሆኑም ወይ?
ይህ ሰነድ እንደ እኔ እይታ ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ ጎልቶብኛል፡፡ በተለይ የቋንቋ ነገር ይታሰብበት የሚለውን ነጥብ ስመለከት ደግሞ ጠባብ ብሔርተኞች ስለ ቋነቋ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ሙሉ በሙሉ የወሰደ መስሎ ታይቶኛል፡፡ እገሌ እገሌ ተብለው በስም የሚጠቀሱ የዘር ፖለቲካ አራጋቢዎች ቋንቋችንን ለማስፋፋት በሌሎች ቋንቋ አለመነጋገር መፍትሔ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ ነው መስማት ከቻልን መስማት በቻልነው መናገር ከቻልን መናገር በቻልነው ቋንቋ እንግባባ፡፡ ከቻልን ደግሞ እንደ ኤፍሬም ሶርያዊ እና እንደ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ያንዳችን ቋንቋ ለልላኛችን እንዲገለጥልን እና ያለ አስተርጓሚ እንድንግባባ እንጸልይ፡፡ ከቻልን የዓለምን ሁሉንም ቋንቋ እንወቅ ካልቻልን ግን በምንችለው ቋንቋ እንግባባ፡፡
በምትችሉት መልኩ በመረጃ ላይ ተደግፋችሁ ሞግቱኝ እንወያይበት እንመካከርበት እስከ የት ሊያደርሰንስ ይችላል? ያልታየኝን አሳዩኝ፡፡
አንድነት ሆይ ወዴት አለሽ?

No comments:

Post a Comment