==============================
መንግሥት እየተከተለ ያለው የዘር ፖለቲካ ዛሬ ላለንበት የእርስ በርስ ንትርክ አልፎም ጥላቻ እና ቂም ለትውልድ እንደ ቅርስ የሚያኖር ክፉ አካሄድ ነው፡፡ ይህ ክፉ አካሄድ ብዙዎችን በሰላም ከሚኖሩበት ቀዬ ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ለማፈናቀል በቅቷል፡፡ ዛሬ ቀላል በሚመስለው በዚህ የማፈናቀል፣ በዘር እና በቋንቋ የመከፋፈል አካሄድ ለመጭው ትውልድ ከባድ ጠፋሳ ጥሎ ማለፉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሀገርን አንድነት የአማኞቿን ሰላም ትጠብቃለች ተብላ ትልቅ ተስፋ የተጣለባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በዚሁ በዘር ፖለቲካው ጢስ ታፍና ቆይታለች፡፡ ይህን የዘር ፖለቲካ ጢስ የአንድነት በሮቿን በመክፈት ጢሱን እያሰወጡ ማናፈስ ሲገባ በር እና መስኮቶቿን ጥርቅም አድርገው ዘግተው ተጨማሪ ጢስ ሆነው ብቅ ያሉ መኖራቸውን ስናይ ደግሞ ዓይናችንን ይቆጠቁጠዋል፡፡
የኦሮምያ ክልል ሲኖዶስ ማቋቋሚያ ሰነድ ውስጡ በርካታ የዘር ፖለቲካን አንግቦ ተመልክቸዋለሁ፡፡ ለሌላው ቋንቋ ጥላቻ ያለባቸው የፖለቲካ “ምሑራን” ነን ባዮች “በኦሮምያ አናግረው ካልመለሰልህ ጥለኸው ሂድ” በሚለው መርሃቸው መሠረት ከኦሮምኛ ውጭ ሌላ ቋንቋ መስማት አንሻም በሚሉ አንዳንድ ሰዎች የተቀነባበረ ቤተ ክርስቲያንን የመከፋፈል ተሐድሷዊ ዘመቻ ነው፡፡ ከዚሁ ክልል ወጣን የሚሉ ታሪክ ሳያውቁ የገባቸው የመሰላቸው “ምሑራን” ነን ባዮችም ሀገራችን ቋንቋዋ “ኢትዮጵያኛ” መሆን አለበት ብለው አዲስ ቋንቋ ሊፈበርኩ ሲዳዳቸው ተመልክተናል፡፡ የእነዚህ እርሾ ነው ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ገብቶ ሊያቦካ የሚጥረው፡፡ እኔ እንደተመለከትኩት ሰነዱ ቤተ ክህነትን ጎትቶ ለፖለቲካው የማስረከብ ነው፡፡ ሰነዱ ውስጥ ያሉ ነገሮችን እንመልከት፡-
********************
ሰነዱ እንዲህ ይላል፡-
“በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያችን በኦሮሚያ ክልል ይህ መዋቅር ካለመኖሩ የተነሳ ለልዩ ልዩ ችግሮች እየተጋለጠች የምትገኝ ሲሆን ከችግሮቹ መካከልም ከመዋቅር አለመኖር ጋር የሚገናኙትን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፡-
( በክልል ደረጃ መንግስት በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተወክላ በብዛት አለመሳተፍ፡፡
( በክልል፤ ደረጃ መፈታት የሚችሉ ችግሮችን ወደ ፌዴራል ማምጣት እና ውስብስብ እንዲሆን ማድረግ፤
( በአሁኑ ሰዓት ኦሮሚያ ክልል በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ላይ ልዩ ባህሪ ያለው ችግር እንዲፈጠር እና ቤተ ክርስቲያናችን የኦሮሞ እና የሌሎች ህዝቦች የተጎናጸፉትን መብት እንደማትቀበል እየተወሰደ ወይም ትርጉም እየተሰጠ መሆኑ በብዛት የሚታይ ሲሆን ከዚህ በኋላ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ይህ ጽሕፈት ቤት መኖሩ ግድ ይላል፡፡ በሌሎች ክልሎችም ቢሆን በክልል ደረጃ የሚቋቋሙ ጽህፈት ቤቶች ቢኖራቸው ለቤተ ክርሰቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
********************
ነጥብ 1፡-
የክልል ሲኖዶስ ባለመኖሩ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ደረሰ ስለሚባለው ችግር ተጠያቂዎች ራሳችን እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር አይደለም፡፡ በክልል ደረጃ መንግሥት በሚያዘጋጀው ስብሰባ እና ሀገራዊ አጀንዳ ላይ ተወክላ መሳተፍ ያልቻለችው የክልል ሲኖዶስ ባለመኖሩ ነው የሚለው አባባል ዓላማው ቤተ ክህነትን ከቤተ መንግሥት ጋር በግድ ለማላተም ነው፡፡ መንግሥት የራሱ አጀንዳ አለው በዚያ አጀንዳ ላይ ይወያያል፡፡ ቤተ ክህነትም የራሱ አጀንዳ አለው በራሱ አጀንዳ ላይ ይወያያል፡፡ መንግሥት ቤተ ክህነትን ከፈለገ የፈለገውን አካል በደብዳቤ ጠርቶ ማወያየት ይችላል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን መንግሥት በተሰበሰበ ቁጥር ቤተ ክርስቲያንም ቅዳሴው እያጎለች አብራ እንድታጨበጭብ አይጠበቅም፡፡ መንግሥት ተሰብስቦ ቤተክህነት ሳይሳተፍበት ቀርቶ የተጎዳነው የትኛውን ነው? ለስብሰባ ተብሎ የክልል ሲኖዶስ እንዴት ይጠየቃል?
ነጥብ 2፡-
በክልል ደረጃ የሚፈቱ ችግሮችን ወደ ፌዴራል እንዲሄድና ውስብስብ እንዲሆን ያደረገው ክልል ላይ ተወካይ ስለሌለን ነው የሚለው አነጋገር ግን በዚህ ሰነድ አንቀጽ 10 ላይ ካለው ሃሳብ ጋር ይጣረሳል፡፡ አንቀጽ 10 ላይ የዚህ የክልል ሲኖዶስ ጽ/ቤት መቀመጫው አዲስ አበባ ይሆናል ይላል፡፡ ታዲያ የዚህ የክልል ሲኖዶስ መቀመጫ አዲስ አበባ ከሆነ ይህንን ሲኖዶስ ለማወያየት አዲስ አበባ ድረስ የሚደከም ከሆነ የፌዴራል መንግሥቱን ማነጋገር ምን ክፋት አለው? ወጭ አልቀነሰልንም እኮ፡፡
ነጥብ 3፡-
ቤተ ክርስቲያናችን የኦሮሞ እና ሌሎች ሕዝቦች ያገኙትን የተጎናጸፉትን መብት እንደማትቀበል ተደርጋ እንደምትቆጠር የተጻፈው በጣም ስህተት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያናችን ቀድሞ መብትን ያጎናጸፈን ማንም የለም፡፡ ማን ያጎናጸፈንን መብት ነው ቤተ ክርስቲያናችን የማትቀበለው? የተጎናጸፍነውን መብት የማያውቅ ካለ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ይጠይቅ፡፡ የሁሉ ምንጭ የሁኑ መገኛ ናት እኮ እሷ መብትን ታጎናጽፋለች እንጂ ሌላ ማንም መብትን የሚያጎናጽፍ የለም፡፡ መብት የምትሉት ሕዳር 29 የብሔር ብሔረሰብ ቀን ጊዜ በተለያየ ቀለም አጊጦ ሲጨፍሩ መዋልን ከሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ለጭፈራ ቦታ የላትም፡፡ ይህ የክልል ሲኖዶስ ለኦሮምያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጠቃሚ እንደሆነ የተገለጠው ቅስቀሳ ተቀባይነት የለውም፡፡ የክልል ሲኖዶስን ማዋቀር የቤተ ክርስቲያን ግዴታ እንደሆነ የተገለጠበት መንገድ ግን የቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አሰራር የተከተለ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶስ አላት በዚያ ሲኖዶስ መክራ ዘክራ የሚሆነውን ትወስናለች እንጂ እኛ የግድ ነው ስላልን የሚሆን ነገር አይኖርም፡፡ ሃሳብ መስጠት ይቻላል እንጂ ማስገደድ አይቻልም ሙሉ ስልጣኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ነውና፡፡ ይህ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን የክርስትናን ደረጃ አያሳይም፡፡
********************
ሰነዱ አሁንም ተጨማሪ ሃሳብ አክሎ ይቀጥላል፡-
“በተጨማሪም በክልሉ ብቻ የሚንጸባረቁ ጉዳዮች ለምሳሌ፡-
( በክልሉ በቋንቋ የሚሰጠው አገልግሎት በማነሱ ምክንያት የምዕመናን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ
( በተለየ ሁኔታ በኦሮሚያ የዋቄፈና ሃይማኖት እንቅስቃሴ እና የቤተ ክርስቲያን ፈተና እና የወደፊት ስጋት፤
( በቤተ ክርስቲያናችን የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ አገልግሎት ክፍተት ለተሃድሶ-ፕሮቴስታንት ጣምራ ዘመቻ እየከፈተ ያለው ሰፊ በር
( በገጠር የገዳማት እና አቢያተ ክርሰቲያናያት መዘጋት፤ ያልተዘጉትም አገልግሎታቸው በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ
( ፖለቲካ እና ሃይማኖት ከብሔር ጋር የሚያያዝበት ሀሳብ በስፋት የሚንጸባረቅበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ፡፡
( የሚጋጩ የታሪክ ትንታኔዎች በመኖራቸውና አፋጣኝ መፍትሔ ስለሚፈልጉ፤ ( የብዙ የሃይማኖት ተቋማት ትኩረት እና የብዙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ የኢትዮጵያም መገለጫ ክልል ነው፡፡
በመሆኑም ይህ ጽሕፈት ቤት በክልል ደረጃ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ፣ ከእነዚህ ችግሮች አብዛኛውን ለማቃለል የሚያስችለው ሲሆን በተለይም በክልሉ እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆነው የምዕመናንን ቁጥር መቀነስ እና በሌሎች ቤተ እምነቶች ያለው የምዕመናን ነጠቃን ለማስቀረት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡”
********************
ነጥብ 1፡-
ዞሮ ዞሮ ማሰሪያው የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ጉዳይ ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ በአፋን ኦሮሞ ባለማስተማራችን የምእመናን ቁጥር እየቀነሰ ሄደ ይላሉ፡፡ ታዲያ በአፋን ኦሮሞ አታስተምሩ ያለው አካል ማነው? ይህን የከለከለውን ሰው ጠቁሙን በጋራ እንታገለው፡፡ ተሐድሶና ፕሮቴስታንቶችም የአፋን ኦሮሞን ባለመጠቀማችን ስጋት ሆነውብናል ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ማብዛት የታቀደውን የክልል ሲኖዶስ በጫና ለማምጣት ካልሆነ በቀር በአፋን ኦሮሞ አስተምራችሁ መመለስ ያቃታችሁ ለምንድን ነው? ቋንቋ መጠቀምን ግን ከክልል ሲኖዶስ ጋር ማስተሳሰር ችግር አለው፡፡
ነጥብ 2፡-
የዋቄፈና ሃይማኖት ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ፈተና ስለሆነ የክልል ሲኖዶስ ይዋቀርልን የሚለው አያስሄድም፡፡ ሌሎች ሃይማኖቶች በተነሡ ቁጥር ቤተ ክርስቲያናችን መዋቅሯን ስታፈርስ ስትሰራ አንድትኖር ማነው የፈረደባት? ምን ከሀዲ ቢባል አርዮስን ንስጥሮስን መቅዶንዮስን የሚያክል ትልቅ ከሐዲ አይገኝም፡፡ አባቶቻችን ጉባዔ ሠርተው የከሐድያንን ትምህርት አውግዘው ከሐድያኑን ለይተው አሳዩን እንጂ መዋቅር ሲቀይሩ አላየንም አልተማርንም፡፡ ዋቄፈና የኦሮምያ ክልል ፈተና ሆኖ ከተገኘ መታገል ነው፡፡ ክልል ላይ አንድ ሲኖዶስ ቢቋቋም ዋቄፈናን ምን እንዲያደርገው ነው የሚጠበቅ?
ነጥብ 3፡-
የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋትን በተመለከተ ከዚህ በፊትም ጽፌዋለሁ፡፡ እዚህ ላይ አልደግመውም ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን መዘጋቷ ከምር የሚቆጫችሁ የሚያንገበግባችሁ ከሆነ ዐሥራት በኩራቱን እያወጣችሁ ካህናትን ቅጠሩ፡፡ ከአቅማችሁ በላይ ከሆነ ለዓለም አሳውቁ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን አንዲት ናትና ሁሉም የአቅሙን ይረዳናል፡፡ የክልል ሲኖዶስ ይዋቀር ቢባል ግን ለዚያ ጽ/ቤት ለደመወዝ ብቻ የሚከፈለው ገንዘብ ቀላል አይደለምና ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ ያይላል፡፡
ነጥብ 4፡-
የሃይማኖት እና የፖለቲካው ብሔርተኝነትን በተመለከተ የተባለው ነገር በዚህ ሰነድ ላይ ካለው ብሔርተኝነት የተለየ አይደለም፡፡ የብሔርተኝነት ጥጉ እኮ እንዲህ በቋንቋችን በዘራችን ተከፍለን ለብቻችን ሲኖዶስ ይዋቀርልን ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ጫፍ የደረሰ የከረረ ብሔርተኝነት የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ብሄርተኝነት መወቀስ ካለበት የሚወቀሰው የዚህ ሰነድ አዘጋጂ እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን ልትሆን አትችልም፡፡
ነጥብ 4፡-
የሚጋጩ የታሪክ ትንታኔዎች አሉ የሚለውን ግን ለታሪክ አዋቂዎች ትተነዋል፡፡ የተጻፉ ድርሳናት ይገለጡ የታሪክ ምሑራን ይመራመሩበት ይተንትኑበት፡፡ የተጋጨው የታሪክ ትንታኔ ምን እንደሆነ ግን አልተገለጠምና እኔም በዚሁ አልፈዋለሁ፡፡
ነጥብ 5፡-
የኢትዮጵያ መገለጫ ክልል ነው የሚለው ሃሳብ ግን አሳፍሮኛል፡፡ የኢትዮጵያ መገለጫ ስንት ነገር ሞልቶ 28 ዓመት ያልደፈነ ታሪክ ያለውን ክልል መገለጫዋ ማድረግ ያሳፍራል፡፡ ምናልባትም የዚህ ሰነድ አዘጋጅ ዕድሜው ከ28 ያልዘለለ ካልሆነ በቀር ክልልን የሀገራችን መገለጫ ማድረግ ነውር ነው፡፡ ክልል የተፈጠረው ከፋፍሎ ለመግዛትና ታርጋ እየለጠፉ አንዱን ከአንዱ ለማባላት በታቀደ የሴራ እና የተንኮል ፖለቲካ ነው፡፡ የሀገራችን መገለጫስ በክልል ማጠር ከዚህ አትለፍ ከዚህ አታትርፍ ከዚህ ውጣ ከዚያ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ መገለጫዋስ እንግዳ ተቀባይነት፤ ፍቅር፤ እጅን ለጸሎት መዘርጋት፤ ገነትን የሚያጠጣው የግዮን ባለቤት፣ ሳታይ ማመን፣ ለተወለደው ጌታ ሰግዳ መገበር ወዘተ ነው፡፡
በመጨረሻም ይህ ሲኖዶስ የምእመናንን ነጠቃ ያስቆምልናል ወደ ሚለው ሃሳብ እንሂድ፡፡ የምእመናንን ነጠቃ ለማስቆም ከማስተማር ከማሳመን ከማጽናት ሌላ ምን መፍትሔ የለውም፡፡ እንዴት እናስተምር እንዴት እናሳምን እንዴት እናጽናቸው የሚል ገር ጥያቄ ቢቀርብ የሁሉንም ርብርብ እናይ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲቋጠር የክልል ሲኖዶስ የሚል መሆኑ ሲታይ ክልል ያቅለሸልሻል፡፡ አሁንም እደግመዋለሁ ኦሮምያ ላይ ተከስተዋል የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት የክልል ሲኖዶስ ማዋቀር መፍትሔ አይደለም፡፡ መፍትሔው አንድ እና አንድ ነው፡፡ እሱም እጃችን ላይ ያለውን ዕድል መጠቀም!
አንድነት ሆይ ወዴት አለሽ?
No comments:
Post a Comment