Monday, April 22, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 72

==================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲።
                   ******    
፫፡ ወያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
                   ******    
፫፡ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ ነው (ሐተታ) ያዕቆብ ማለት አዕቃጺ አኃዚ ማለት ነው። የቀደመው ያዕቆብ ሰኰና ኤሳውን ይዞ እንደተወለደ። እሱም ሰኰና ወንጌልን ይዞ ሲያስተምር ይሞታልና። ሰኰና ኤሳውን እንዳሰናከለ እሱም የመናፍቃንን ትምህርት ያሰናክላልና፡፡
ወዮሐንስ እኊሁ።
ወንድሙ ዮሐንስ ነው። ዮሐንስ ማለት ፍሥሐ ወኀሤት ማለት ነው። ወብዙኃን ይትፌሥሑ በልደቱ እንዲል።
ፊልስጶስ
ፊልጶስ ነው ፊልጶስ ማለት ረያጼ አፍራስ ማለት ነው አኃዜ ኵናትም ማለት ነው መፍቀሬ አኃው ማለት ነው ፊልሳዳፎስ እንዲል።
ወበርተሎሜዎስ።
በርተሎሜዎስ ነው በእብራይስጥ በር ልጅ ማለት ነው። ተክል የማጠጣት ግብር ያለው ልጅ ማለት ነው ወልደ ኃይል ወልደ የማን እንዲል። አንድም ወይን ተክሎ ዕለቱን አድርሷልና።
ቶማስ
ቶማስ ነው ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ነው። ፪ቱ አስማቲሁ ለፀሐይ አሐዱ ቶማስሰ ወ፩ዱ ኦርያሬስ አንዲል።
ወማቴዎስ መጸብሐዊ
አንዱ ማቴዎስ ነው። ማቴዎስ ማለት ኅሩይ ማለት ነው ከዚህ አውጥቶ ለዚህ መዓርግ አበቃው ለማለት ስሙን ከነግብሩ ጠራው፡፡
ወያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ።
የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ ነው (ሐተታ) እንዳለፈው።
ወልብድዮስ ዘተሰምየ ታዴዎስ፡፡
ታዴዎስ የተባለ ልብድዮስ ነው ልብድዮስ ማለት ልብደ ሠሪ ዓሣ ወጋሪ ማለት ነው። ልበ ድዮስ ይላል ካህነ አምላክ ማለት ነው። ወአምጽኡ ማሬ ዘድዮስ ለ፲ወ፪ቱ ሕዝበ ድዮስጶራ እንዲል።
አንድም ዘርዕ ወማዕረር ማለት ነው ኦሪትን እንደ ዘር ወንጌልን እንደ መከር አድርጎ አስተምሯልና፡፡
አንድም ስንዴ ዘርቶ ዕለቱን ለመሥዋዕት አድርሷልና፡፡
                   ******    
፬፡ ወስምዖን ቀነናዊ።
                   ******    
፬፡ ባልተነበበ ስሙ ይተረጉማሉ ስምዖን ያለው ናትናኤል ነው፡፡ ናትናኤል ማለት ውሁብ ሀብተ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ቀነናዊ የቃና ሰው ቀሬናዊ የቀራንዮ ሰው ቀናዒ ለሕገ አምላኩ።
ወይሁዳ አስቆሮታዊ ዘውእቱ አግብኦ።
የአስቆሮት ሰው የሚሆን ያስያዘው ይሁዳ ነው። ይህ ሰው ስሙ ከግብሩ ያልተባበረ ነው፡፡ ይሁዳ ማለት ተአማኒ በእግዚአብሔር ማለት ነበር እሱ ግን አላደረገውም ለዚህ መዓርግ ቢያበቃው ከሞቱ ገባበት ለማለት ጻፈው እንዳወጣው ለማጠየቅ በመጨረሻ አመጣው።
                   ******    
፭፡ እሎንተ አሠርተ ወ፪ተ ሐዋርያተ ፈነዎሙ እግዚእ ኢየሱስ።
                   ******    
፭፡ እሎንተ ካለ ፈነወ ፈነዎሙ ካለ ለእሎንቱ ባለ በቀና ነበር። ጌታ እኒህን ፲፪ቱን ሐዋርያት ላከ ማለት መርጦ ሾመ፡፡
(ሐተታ) ከ፭ ወገን መርጧቸዋል። ከአናምያን ከሓናጽያን ከመጸብሓን ከመሠግራን ከመስተገብራን ቤትን በአምስት ወገን ያጸኑታል በጭቃ በገለባ በሣር በደንጊያ በእንጨት። ከአራት ባሕርያት ከአምስተኛ ባሕርየ ነፍስ የተፈጠረ ሰውን አጸናባችኋለሁ እጠብቅባችኋለሁ ሲል። ከነዚህም ስማቸውን የለወጠውም ያለወጠውም አለ። በኦሪቱ ያሳለፈውም ያላሳለፈውም ግብር እንዳለ ለማጠየቅ። ስም ማውጣትም የገዥና የተገዥ ምልክት ነው ባለቤት ለቤተ ሰው ስሙን ለውጦ እንዲያወጣ
ወአዘዞሙ እንዘ ይብል ፍኖተ አሕዛብ ኢትሑሩ
በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ ማለት የአሕዛብን ሥራ አትሥሩ።
ወውስተ ሀገረ ሳምር ኢትባኡ።
ወደ ሳምራውያንም አገር አት ግቡ ብሎ አዘዛቸው።
                   ******    
፮፡ ወሑሩ ባሕቱ ኀበ አባግዕ ዘተኃጐላ እምቤተ እስራኤል።
                   ******    
፮፡ ከእስራኤል ወደጠፉ በጎች ሂዱ ማለት መምህር አብነት ትምህርት አጥተው ወደ ተጐዱ ወደ እስራኤል ሂዳችሁ አስተምሩ እንጂ ትንቢት የተነገረ ሱባዔ የተቈጠረ ለነዚህ ነውና፡፡
አንድም ትንቢት የተነገረልን ሱባዔ የተቈጠረልን እኛ ሳለን ትምህርቱን ለሌላ ቢያደርገው ከሞቱ ገባንበት ባሉ ነበርና።
አንድም በፍቅር ለመሳብ።
አንድም በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነታቸው መከራ ቢያጸኑባቸው በካዱ ነበርና እንዳይክዱ።
                   ******    
፯፡ ወሐዊረክሙ ስብኩ እንዘ ትብሉ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት
፯፡ ሂዳችሁ ደጊቱ በልጅነት ልጅነት በሃይማኖት የምትሰጥበት ጊዜ ደርሷል እያላችሁ አስተምሩ።
                   ******    
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
14/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment