Tuesday, April 16, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 67


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ መጻጒዕ።
ምዕራፍ ፱።
                     ******    
ዘከመ ተጸውአ ማቴዎስ
፱፡ ወኃሊፎ እግዚእ ኢየሱስ እምህየ ረከበ ብእሴ እንዘ ይነብር ውስተ ምጽባሕ ዘስሙ ማቴዎስ።ማር ፪፥፲፬፡፡ ሉቃ ፭፥፳፯፡፡
                     ******     
፱፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያ አልፎ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል ሰው ከሚያስገብርበት ቦታ ተቀምጦ አገኘ።    
(ሐተታ) ሲያስገብር አላለም የሰው ገንዘብ ይዞ ሄደ ብለው ምክንያት እንዳያደርጉበት
ወይቤሎ ትልወኒ።
ተከተለኝ ማለት ለጊዜው በእግር ፍጻሜው ግን በግብር ምሰለኝ አለው እንዲሻው ከፍጹምነት እንዲደርስ አውቆ።
ወተንሢኦ ተለዎ።
ተነሥቶ ተከተለው ማለት ለጊዜው በእግር ፍጻሜው በግብር መሰለው
                   ******    
በእንተ ዘከመ ይደልዎሙ ለክርስቲያን ጸዊመ
፲፡ ወእንዘ ይረፍቅ ውስተ ቤት ናሁ መጽኡ ብዙኃን ኃጥአን መጸብሓን።
                   ******    
፲፡ ከቤት ገብቶ ሲበላ ብዙ ኃጥአን መጸብሓን መጡ
ወረፈቁ ምስለ እግዚእ ኢየሱስ ወአርዳኢሁ።
ከደቀ መዛሙርቱም ከሱም ጋራ ተቀምጠው በሉ። እንዲያው አይደለም ተከተለኝ ካልኸኝስ ከቤት ገብተህ ምሳ ብላልኝ ብሎታል። የቤቴን ትዳር ያየ እንደሆነ አክብሮ ያኖረኛል ብሎ አሁን ዛሬ ለጌታ የሚያድር ሰው ፈረሱን በቅሎውን ሎሌውን ገረዱን አብዝቶ እንዲታይ።
አንድም ትእምርተ ምናኔ ነው ፩፡ነገ ፱፥፱። ኤልሳዕ ዐሥራ ሁለት ጥንድ በሬ አስጠምዶ ሲያሳርስ ኤልያስ ሐሜለቱን ከራሱ ላይ ጥሎ ተከተለኝ አለው። አባቴ ተከተለኝ ካልኸኝስ ቆየኝ አንድ ጊዜ ብሎ ፲፪ን ጥንድ በሬ አርዶ ለነዳያን አብልቶ ተከትሎታልና በዚያ ልማድ።
                   ******    
፲፩፡ ወርእዮሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን ይቤልዎሙ ለአርዳኢሁ ለምንት ይበልዕ ሊቅክሙ ምስለ ኀጥአን ወመጸብሐን።
                   ******    
፲፩፡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን አይተው መምሕራችሁ ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር ለምን ይባላል አላቸው።
                   ******    
፲፪፡ ወሰሚዖ እግዚእ ይቤሎሙ ሕሙማን ይፈቅድዎ ለዓቃቤ ሥራይ።
                   ******    
፲፪፡ ጌታም በሰማ ጊዜ ባለመድኃኒትን የታመሙ ሰዎች ይሹታል።
(ሐተታ) ያበጠውን ሊያፈርጥላቸው የጎረበውን ሊልጥላቸው።
ወአኮ ጥዑያነ።
ጤነኞች ግን አይሹትም።
አንድም ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ እኔን ሕሙማን ነን የሚሉ ኃጥአን መጸብሐን ይሹኛል ደኅነኞች ነን የምትሉ እናንተ ዳን አትሹኝም
                   ******    
፲፫፡ ሑሩ ወአእምሩ ምንት ውእቱ ዘይቤ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት። ሆሴ ፮፥፮፡፡ ማቴ ፲፪፥፯፡፡ ፩፡ጢሞ ፩፥፲፫።
                   ******    
፲፫፡ ሑሩ በእግረ ሕሊና ነው ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት ያለው ምንም እንደሆነ መርምራችሁ ዕወቁ ማለት እኒህን መጸየፍ መሥዋዕት እኒህን አለመጸየፍ ምጽዋት እንደሆነ ዕወቁ።
እስመ ኢመጸእኩ እጸውዕ ጻድቃነ
ጸድቃን ነን የምትሉ እናንተን ልጠራ አልመጣሁምና።
አላ ኃጥአነ ለንስሐ ።
ኃጥአን ነን የሚሉ እኒህን ወደ ንስሐ ልጠራ መጥቻለሁ እንጅ። በዓለሙ አንድ ጻድቅ ኑሮ ያን ልጠራ አልመጣሁምና ሁሉ ኃጥእ ሁኑዋልና ያን ልጠራ መጥቻለሁ እንጅ።
                   ******    
፲፬፡ ወእምዝ መጽኡ ኀቤሁ አርዳኢሁ ለዮሐንስ ወይቤልዎ በእፎ ኢይጸውሙ አርዳኢከ፡፡ ማር ፪፥፲፪። ሉቃ ፫፥፴፫።
                   ******    
፲፬፡ ለምንት ሲል ነው በእፎ ትጼእል ሊቀ ካህናቲሁ ለእግዚአብሔር እንዲል። ከዚህ በኋላ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መጥተው ደቀ መዛሙርትህ ለምን አይጾሙ አሉት።
ንሕነሰ ወፈሪሳውያን ንጸውም ብዙኃ።
እኛ ፈሪሳውያንም ግን ብዙ እንጾማለን።
(ሐተታ) ምን ጾም አላቸው ቢሉ እሁድና ማክሰኞ ሐሙስ ይጾማሉና።
አንድም ጾመ ረቡዕ ጾመ ሐሙስ ጾመ ሰቡዕ ጾመ አሱር የሚባል ጾም አለና።
                   ******    
፲፭፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኢይክሉ ደቂቁ ለመርዓዊ ጸዊመ ወላህዎ አምጣነ ሀሎ መርአዊ ምስሌሆሙ።
                   ******    
፲፭፡ የመርዓዊ ሚዛዝት መርዓዊ ከሳቸው ጋራ ሳለ መጾም ማልቀስ አይቻላቸውም።
ወባሕቱ ይመጽእ መዋዕል አመ ይነሥእዎ ለመርዓዊ እምኔሆሙ ውእተ አሚረ ይጸውም
ነገር ግን መርዓዊ ከሳቸው የሚለይበት ጊዜ ይደርሳል ያን ጊዜ ይጾማሉ አለ። አሥርቱ ሲወጣ።
አንድም የኔ ደቀመዛሙርት ከኔ ጋራ ሳሉ መጾም ማልቀስ አይቻላቸውም እኔ ከሳቸው የምለይበት ጊዜ ይደርሳል ያንጊዜ ይጾማሉ ይነሥእዎ በሞት ቢሉ ሁለት ቀን ያከፍላሉና በዕርገት ቢሉ ዐርባ ቀን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ይጾማሉና።
                   ******    
፲፮፡ ወአልቦ ዘይጠቅብ ግምደ ደርግሀ ውስተ ስጠተ ልብስ ብሉይ።
                   ******    
፲፮፡  አዲስ ቀራጭ ባረጄ ልብስ ላይ የሚጥፍ የለም።
እስመ ይትማላዕ ሕያዎ ለልብስ።
ደኅነኛውን ተማልቶት ይሄዳልና።
ወያዓብዮ ለስጠቱ።
ቀዳዳውንም ያሰፋዋልና።
አንድም ሐዋርያትን በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነታቸው ጾምን ጹሙ የሚላቸው የለም ጾሙም ይቀራል ሰውነታቸውም ይጎዳልና፡፡
                   ******    
፲፯፡ ወአልቦ ዘይወዲ ወይነ ሐዲሰ ውስተ ዝቅ ብሉይ፡፡
                   ******    
፲፯፡  ባረጀ ራዋት ጉሽ ጠጅ የሚሾም የለም
ወይኑሂ ይትከዓው።
ቢሾሙ ግን ራዋቱም ይቀደዳል ወይኑም ይፈሳል።
ወባሕቱ ለወይንሰ ሐዲስ ውስተ ዝቅ ሐዲስ ይወድይዎ፤
ጉሹን ጠጅ ግን በአዲስ ራዋት ይሾሙታል፤
ወይትዓቀቡ ፪ሆሙ በበይናቲሆሙ።
እርስ በርሳቸው ባንድነት ይጠባበቃሉ አዲሱ ራዋት የጠጁን ፍላሎት ይችለዋል የጠጁም ፍላሎት አዲሱን ራዋት ያለፋዋልና፤
አንድም ሐዋርያትን በልጅነት ባልታደሰ ሰውነታቸው ሕግ ጠብቁ የሚላቸው የለም።
ወእመ አኮሰ ጠብቁ ቢሏቸውም ሕጉም ይፈርሳል ሰውነታቸውም ደጐዳልና ወባሕቱ በልጅነት በታደሰ ሰውነታቸው ግን ወንጌልን ጠብቁ ይሏቸዋል ወይትዓቀቡ
እርስ በርሳቸው ይጠባበቃሉ እሳቸውም ሕጉን ይጠብቁታል ሕጉም እሳቸውን ይጠብቃቸዋል።
አኮ ንሕነ ዘነዓቅቦሙ ለሕገጋት አላ እሙንቱ ሕገጋት የዓቅቡነ ለዓቂብ ወለተፀውኖ እንዲል።
                   ******    
በእንተ ወለተ ኢያኢሮስ
ወበእንተ ደም ዘይውኅዛ ።
                   ******     
፲፰፡ ወእንዘ ዘንተ ይነግሮሙ ናሁ መጽአ አሐዱ መኰንን ወሰገደ ሎቱ። ማር ፭፥፳፪። ሉቃ ፰፥፵፩፡፡
፲፰፡ ይህን ሲነግራቸው ኢያኢሮስ መጥቶ ሰገደለት።
                   ******     
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
09/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment