Wednesday, May 29, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 105

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ዘተግኅሠ ኢየሱስ እምኢየሩሳሌም።
ምዕራፍ ፲፱፡፡
                    ******     
በእንተ ዘከመ ይደልዎሙ ዕሤት ለእለ ይተልውዎ ለእግዚእ ኢየሱስ።
፳፯፡ ወእምዝ አውሥአ ጴጥሮስ ወይቤሎ ናሁ ንሕነ  ኀደግነ ኵሎ ወተሎናከ ምንተ እንከ ንረክብ።
                        ******     
፳፯፡ ጴጥሮስ መለሰ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል ምን እናገኝ ይሆን አለው፡፡
(ሐተታ) ምን ነበረውና እንዲህ አለ ቢሉ አንድ አህያ አንድ በሬ መረቡን መርከቡን ትቶ ተከትሎታልና፡፡ ይህ ሁሉ አይደለም እከብራለሁ ባይ ልቡናውን ትቶ ተከትሎታልና እንዲህ አለ።
                    ******     
፳፰፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ አንትሙ እለ ተለውክሙኒ አመ ዳግም ልደት አመ ይነብር ወልደ እጓለ እመሕያው ዲበ መንበረ ስብሐቲሁ።
                    ******     
፳፰፡ ሰው በሆንኩ ጊዜ ያመናችሁብኝ እናንተ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ በዕርገት በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ በኖረ ጊዜ።
ወአንትሙኒ ትነብሩ ዲበ ፲ወ፪ መናብርት።
በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል በመምህርነት ትሾማላችሁ።
ወትኴንኑ ፲ተ ወ ፪ተ ሕዝበ እስራኤል።
አሥራ ሁለቱን ነገደ እስራኤልን ታስተምራላችሁ፡፡
አንድም አመ ይነብር ውስተ ዓለም ሐዲስ ይላል ያመናችሁብኝ እናንተ በዕለተ ምጽአት ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ በጌትነት በተገኘ ጊዜ በአሥራ ሁለቱ ወንበር ትቀመጣላችሁ በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ። ያን ጊዜስ መቀመጥም መፍረድም የለም ዛሬ የፈረዱት ፍርድ የማይነቀፍባቸው ስለሆነ እንዲህ አለ፡፡
                    ******     
ወኵሉ ዘኃደገ አብያተ ወአኃወ ወአኃተ አበ ወእመ ወብእሲተ ወውሉደ ወገራውኃ በእንተ ስምየ ምዕተ ምክዕቢተ ይነሥእ
                    ******     
፳፱፡ በእኔ ስም አምኖ በእኔ ስም ስላመነ አባቱን እናቱን ወንድሙን እኅቱን ሚስቱን ቤቱን ንብረቱን ርስቱን የተወ ሁሉ መቶ ዕፅፍ ያገኛል አለ፡፡
(ሐተታ) መቶ እናት አባት መቶ እኅት ወንድም መቶ ሚስት ያገኛል ማለት አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም የአባትነት የእናትነት የወንድምነት የእኅትነት የሚስትነት ሥራ ይሠራለታል ሲል ነው።
ወሕይወተ ዘለዓለም ይወርስ።
በወዲያው የዘለዓለም ሕይወት መንግሥተ ሰማይን ይወርሳል፡፡
                    ******     
፴፡ ወብዙኃን ቀደምት ይከውኑ ደኃርተ ወደኃርት ይከውኑ ቀደምተ። ማቴ ፳፥፲፮፡፡ ማር ፲፥፴፩፡፡ ሉቃ ፲፫፥፴።
                    ******     
፴፡ ኋለኞች ፊተኞችን ፊተኞች ኋለኞችን ይሆናሉ ማለት ቀደምት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ደኃርት ሐዋርያትን ይሆናሉ አለ ዐሥራቱን በኵራቱን አጥተው፤ ደኃርት ሐዋርያት ቀደምት ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ይሆናሉ አለ አግኝተው፡፡
አንድም ቀደምት ሐዋርያት ደኃርት ሠለስቱ ምዕትን፤ ደኃርት ሠለስቱ ምዕት ቀደምት ሐዋርያትን ይሆናሉ ኋላ በሥራ ያሰፉታል እንጂ በጥምቀት በሚገኘው ክብር አንድ ናቸውና፡፡
                    ******     
በእንተ ምሳሌ ዘዓቀብተ ወይን፡፡
ምዕራፍ ፳።
፩፡ እስመ ትመስል መንግሥተ ሰማያት ብእሴ በዓለ ቤት ዘወፅአ ነግሃ ይትዓሰብ ገባዕተ ለዓደፀ ወይኑ።
                    ******     
፩፡ መንግሥተ ሰማይ ሕገ ወንጌል ሕገ ወንጌል ተስፋ ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ ለወይኑ ቦታ ምንደኞችን ሊስማማ ማለዳ የወጣ ባለቤትን ትመስላለችና ቀደምት ወይከውኑ ደኃርተ፤ ደኃርት ይከውኑ ቀደምተ ላለው።
አንድም ትመስላለች እኮን።
                        ******     
  ይቆየን፡፡
**********
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
21/09/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment