Saturday, May 11, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 87

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ሰዊት።
ምዕራፍ ፲፫።
                    ******     
፳፭፡ ወእንዘ ይነውሙ ሰብኡ መጽአ ጸላዒሁ ወዘርዓ ክርዳደ ማዕከለ ሥርናይ ወኃለፈ።
                    ******     
፳፭፡ ሰዎቹ ተኝተው ሳለ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል ክርዳድ ዘርቶ ሄደ።
                    ******     
፳፮: ወሶበ በቈለ ሥርናይ ወፈረየ አሜሃ አስተርአየ ክርዳድኒ።
                    ******     
፳፮፡ ሥንዴው በበቀለና ባፈራ ጊዜ ያን ጊዜ ክርዳዱም ታየ ማለት ተለይቶ ታወቀ።
                    ******     
፳፯፡ ወመጺኦሙ አግብርቲሁ ለበዓለ ገራህት ይቤልዎ አኮሁ ሠናየ ዘርዓ ዘራዕከ ውስተ ገራህትከ።
                    ******     
፳፯፡ ብላቴኖቹ መጥተው ባለቤቱን አቤቱ በእርሻህ በጎ ዘር ዘር
ተሀ አልነበፈቷምን ።
እምአይቴ እንከ ሎቱ ክርዳድ
ክርዳድ ከወዴት ተገኘ አሉት
                    ******     
፳፰፡ ወይቤሎሙ ብእሲ ፀራዊ ገብረ ዘንተ።
                    ******     
፳፰፡ ጠላት ሰው ይህን አደረገ። አንድም እጓለ ፀራዊ ይላል የጠላት ልጅ እንዲህ አደረገ
ወአግብርቲሁሰ ይቤልዎ ትፈቅድኑ እንከ ንሑር ወንጻሕይዮ።
ብላቴኖቹም ሂደን  ክርዳዱን ነቅለን ልንጥለው ትወዳለህን አሉት።
ወይቤሎሙ አልቦ
አይሆንም አላቸው፡፡
                    ******     
፳፱፡ ከመ እንዘ ተዓርዩ  ክርዳደ ኢትምሀዉ ምስሌሁ ሥርናየኒ።
                    ******     
፳፱፡ ክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውን እንዳትነቅሉ።
                    ******     
፴፡ ኅድግዎሙ ይልሐቁ ኅቡረ እስከ ጊዜ ማዕረር።
                    ******     
፴፡ ተዋቸው እስከ መከር ድረስ በአንድነት ይኑሩ፡፡
ወበጊዜ ማዕረር እብሎሙ ለእለ የዓፅዱ ዕርዩ ቅድመ ክርዳደ ወዕሥርዎ በበከላስስቲሁ በአውዕድዎ በእሳት፡፡
መከር በደረሰ ጊዜ የሚያጭዱትን አስቀድማችሁ ክርዳዱን ከስንዴው አይታችሁ በየነዶው አሥራችሁ በእሳት አቃጥሉት፡፡
ወሥርናዮሰ አስተጋብዑ ውስተ መዛግብትየ
ሥንዴውን ግን በጎታ በጎተራ በሪቅ ሰብስቡት እላቸዋለሁ፡፡
አንድም ወእንዘ ይነውሙ ሰብኡ ብለህ መልስ፡፡ ሐዋርያት ካለፉ በኋላ ዲያብሎስ አርዮስን፡፡ ሠለስቱ ምዕት ካለፉ በኋላ መቅዶንዮስን መቶ አምሳው ካለፉ በኋላ ንስጥሮስን ማስነሣቱን መናገር ነው፡፡
ወሶበ በቈለ በተሸመ ባስተማረ ጊዜ ክህደቱ ኑፋቄው ተገልጦ ታወቀ፡፡ ደቀ መዝሙር ከመምህሩ ቤት ሳለ ክህደቱን ኑፋቄውን አይገልጸውምና፡፡ ወመጺኦሙ አግብርቲሁ መላእክት ቀርበው አምጻኤ ዓለማት ፈጣሬ ዓለማት ጌታችን አቤቱ በዚህ ዓለም በጎ ትምህርት አስተምረህ አልነበረምን፡፡ እም አይቴ እንከ ሎቱ ክርዳድ፡፡ ይህ ክህደት ኑፋቄ ከወዴት መጣ አሉት፡፡ ወይቤሎሙ ፀራዊ ገብረ ዘንተ፡፡ ጠላቴ ዲያሎስ እንዲህ አደረገ፡፡
አንድም የጠላቴ የዲያብሎስ የግብር ልጁ መናፍቅ እንዲህ አደረገ፡፡ ሰው በባሕርይ እንዲራባ እርሱም በግብር ይራባልና፡፡
(ሐተታ) መላእክት የሚጠይቁት ጌታ የሚመልስላቸው ሆኖ አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም በጎ ትምህርት አስተምሮ አልነበረም ይህ ክህደት ኑፋቄ ከወዴት ተገኘ ብለው በመረመሩት ጊዜ ክህደት ኑፋቄ የተገኘ ከዲያብሎስ እንደሆነ የሚያውቁበትን ዕውቀት ከእርሱ ማግኘታቸውን መናገር ነው፡፡
ወአግብርቲሁሰ ይቤልዎ ትፈቅድኑ ንሑር ንጻሕይዮ፡፡ ኃጥኡን ከጻድቅ ለይተን ልናጠፋው ትወዳለህ አሉት፡፡ ወይቤሎሙ አልቦ አይሆንም ከመ እንዘ ትጸሐይዩ ኃጥኡን እናጠፋለን ስትሉ ጻድቁን እንዳታጠፉ የኃጥኡ ዳፋ ጻድቁን ይዳፋ እንዲሉ፡፡ ለይቶ ማጥፋት ይቻላቸው የለም፡፡ ይህም በኖኅ በሎጥ ታውቋል ብሎ ከእነዚህ የሚወለዱ በንስሐ የሚመለሱ ብዙ አሉና፡፡ ኅግዎሙ ተዋቸው እስከ ዕለተ ምጽአት በአንድነት ይኑሩ፡፡ ወበጊዜ ማዕረር ምጽአት በደረሰ ጊዜ መላእክትን አዛቸዋለሁ፡፡ እርዩ ቅድመ አስቀድማችሁ ኃጥአንን ከጻድቃን ለይዋቸው፡፡ ወእስርዎ በበከላስስቲሁ፡፡ በየወገናቸው በገሃነም ሥቃይ አምጹባቸው ወሥርናዮሰ ጻድቃንን ግን በመንግሥተ ሰማይ አኑሯቸው እላቸዋለሁ፡፡
(ሐተታ) መዛግብት አላት በብዙ ወገን ትወረሳለችና፡፡ እስመ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ወምዕራፍ ቦቱ እንዲል፡፡
አንድም ትመስል ብለህ መልስ፡፡ መንግሥተ ሰማይ ሊቀ ማኅበር በእርሻው የተበጠረች የተንጠረጠረች ዘርን የሚዘራ ገበሬን ትመስላለች ገራህት ገዳም፡፡
አንድም መንግሥተ ሰማይ ሥርዓተ ማኅበር ገበሬ በእርሻው የዘራት የተበጠረች የተንጠረጠረች ዘርን ትመስላለች፡፡ ገራህት ልቡና ወእንዘ ይነውሙ አበው ሥርዓት ሠርተው ካለፉ በኋላ ዲያብሎስ ክፉ ሕሊና ማምጣቱን መናገር ነው፡፡ ወሶበ በቈለ ሥራ እሠራለሁ ባለ ጊዜ ክፉ ሕሊና ተለይቶ ታወቀ ወመጺኦሙ መላእክት ቀርበው ጌታን ለሰው በጎ ሕሊናን ፈጥረህለት አልነበረምን ይህ ክፉ ሕሊና ከወዴት ተገኘ አሉት፡፡ በእሲ ፀራዊ ጠላቱ ዲያብሎስ እንዲህ አደረገ አላቸው፡፡
(ሐተታ) መላእክት የሚጠይቁት እርሱም የሚመልስላቸው ሆኖ አይደለም፡፡ ለሰው በጎ ሕሊና ፈጥሮለት አልነበረም ይህ ክፉ ሕሊና ከወዴት ተገኘ ብለው በመረመሩ ጊዜ ክፉ ሕሊና የሚገኝ ከዲያብሎስ እንደሆነ የሚያውቁበትን ዕውቀት ከጌታ ማግኘታቸውን መናገር ነው፡፡ ወአግብርቲሁሰ መላእክት ክፉውን ሕሊና ልናጠፋው ትወዳለህን አሉት ወይቤሎሙ አልቦ አይሆንም እስመ እንዘ ተአርዩ፡፡ ክፉውን ሕሊና እናጠፋለን ስትሉ በጎውን ሕሊና እንዳታጠፉ፡፡ ኅድግዎሙ ተዋቸው እስከ ተባህትዎ ድረስ በአንድነት ይኑሩ፡፡ ወበ ጊዜ ማዕረር በተባሕትዎ ጊዜ ሥርዓት የሚሠሩ አበውን አዛቸዋለሁ፡፡ አስቀድማችሁ ክፉውን ሕሊና ከበጎው ሕሊና ለይታችሁ  በየአገባቡ በቀኖና አርቁት።
ወሥርናዮሰ በጎውን ሕሊና ግን በመንፈስ ቅዱስ አስጠብቁት እላቸዋለሁ። መዛግብት አለው መንፈስ ቅዱስን ስለ ሀብቱ ብዛት።
                    ******     
በእንተ ምሳሌ ዘሕጠተ ሰናፔ
፴፩፡ ካልዕተ ምሳሌ አምጽአ ሎሙ፡፡ ማር ፬፥፴፩፡፡ ሉቃ ፲፫፥፲፱፡፡
                    ******     
፴፩፡ ሁለተኛ ምሳሌ ሌላ ምሳሌ መሰለላቸው።
እንዘ ይብል ትመስል መንግሥተ ሰማያት ኅጠተ ሰናፔ እንተ ነሥኣ ብአሲ ወዘርኣ ውስተ ገራህቱ።
መንግሥተ ሰማይ ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ወንጌል ተስፋ። ተስፋ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሽው የሰናፍጭ ቅንጣት የሚዘራ ገበሬን ትመስላለች። ገራህት ይህ ዓለም።
አንድም መንግሥተ ሰማይ ሕገ ወንጌል ገበሬ በእርሻው የዘራት ሰናፍጭን ትመስላለች ገራህት ልቡና።
(ሐተታ) ሰናፍጭ ፍጽምት ናት ነቅ የለባትም ወንጌልም ነቅዓ ኑፋቄ የለባትምና። ሰናፍጭ ላይዋ ቀይ ውስጧ ነጭ ነው። ወንጌልም በላይ ደማችሁን አፍሱ ትላለች በውስጥ ግን ሕገ ተስፋ ናትና።
አንድም ሰናፍጭ ጣዕሟ ምረሯን ያዘነጋዋል፤ ወንጌልም ተስፋዋ መከራዋን ያዘነጋዋልና።
አንድም ሰናፍጭ ቊስለ ሥጋን ታደርቃለች። ወንጌልም ቊስለ ነፍስን ታደርቃለችና።
አንድም ሰናፍጭ ደም ትበትናለች ወንጌልም አጋንንትን መናፍቃንን ትበትናለችና፡፡
አንድም ከምትደቈስበት ተሐዋስያን አይቀርቡም። ወንጌልም ከምትነገርበት አጋንንት መናፍቃን አይቀርቡምና። ሰናፍጭ ስትደቈስም ስትበላም ታስለቅሳለች። ወንጌልም ሲማሯትም ሲያስተምሯትም ታሳዝናለችና። ሰናፍጭ ከበታችዋ ያሉትን አታክልት ታመነምናለች፤ ወንጌልም የመናፍቃንን ጉባዔ ታጠፋለችና። ሰናፍጭ አንድ ጊዜ የዘሯት እንደሆነ ባመት ባመት ዝሩኝ አትልም ተያይዛ ስትበቅል ትኖራለች። ወንጌልም በመቶ ሐያ ቤተ ሰብ ተጀምራ እስከ ምጽአት ድረስ ስትነገር ትኖራለችና።
                    ******     
፴፪፡ ወይእቲ ትንዕስ እምኵሉ አዝርዕት።
                    ******     
፴፪፡ ስትዘራ ከአዝርዕት ሁሉ ታንሳለች።
ወሶበ ልህቀት ተዓቢ አምኵሉ አሕማላት።
ባደገች ጊዜ ግን ከአዝርዕት ሁሉ ትበልጣለች፤ እንደእሷ ካሉ ከዖፍ ዘር ከጎመን ዘር።
ወትከውን ዕፀ ዐባየ።
ደግ ዕፅ ትባላለች።
እስከ ይመጽኡ አእዋፈ ሰማይ ወያጸልሉ ታሕተ አዕፁቂሃ።
አዕዋፍ መጥተው ማረፊያ መስፈሪያ ዛፍ እስኪያደርጓት ድረስ።
አንድም ወይእቲ ትንዕስ ብለህ መልስ። ወንጌል ስትነገር ከሁሉ ታንሳለች። በመቶ ሐያ ቤተ ሰቡ መዠመሯን ትንዕስ አለ፡ በጉባዔ በተነገረች ጊዜ ግን ከሕግጋት ሁሉ ትበልጣለች። ወትከውን። ደግ ሕግ ትሆናለች። ወይመጽኡ ሕዝብ አሕዛብ እስኪያምኑባት ድረስ።
አንድም ትመስል ብለህ መልስ። በጥምቀት በተአምኖ ኃጣውእ ያሉ ሰዎች በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ያሉ ሰዎችን ይመስላሉ። ወይእቲ ትንዕስ። በጥምቀት የሚሰጠው ጸጋ በመጠን ነውና። ትንዕስ አለ ያም ኃጢአቱን ሲናገር ተዋርዶ ነውና። ወሶበ ልህቀት። በጥምቀት ያገኘውን ጸጋውን በሥራ ባሰፋው ጊዜ ያም ቀኖናውን በፈጸመ ጊዜ ከሰው ሁሉ ይበልጣል። ወትከውን። ደግ ሰው ይባላል ወይመጽኡ። ሰው ሁሉ መጥቶ ከእግሩ ወድቆ አትርሳኝ እስኪለው ድረስ።
                    ******     
በእንተ ምሳሌ ዘብሑእ።
፴፫፡ ካልዕተ ምሳሌ ነገሮሙ። ሉቃ ፲፫፥፳፩፡፡
                    ******     
፴፫፡ ለቀረበው ካልዕት ይላል ሁለተኛ ምሳሌ፤ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው።
ትመስል መንግሥተ ሰማያት ብኁዓ ዘነሥአት ብእሲት ወአብኅዓቶ ውስተ ሠለስቱ መሥፈርተ ሐሪፅ።
መንግሥተ ሰማያት እንዳለፈው፤ በሦስት መሥፈሪያ ዱቄት የሸሸገችው ማለት ሦስት መስፈሪያ ዱቄት የለወሰችበትን ሴት የያዘችውን።
ወአብኀአ ኵሎ።
ሁሉን ወደ ምፀት የሳበ እርሾን ትመስላለች። ብኁዕ ጌታ ብእሲት ጥበቡ ውስተ ሠለስቱ መስፈርተ ሐሪፅ፤ ሥጋን ነገር ነፍስን ደመ ነፍስን ያዋሃደችው።
ወአብኅአ ኵሎ።
በተዋሕዶ ሥጋን የባሕርይ አምላክ ማድረጉን መናገር ነው።
አንድም ብእሲት መምሕራን ብኁዕ ወንጌል። ውስተ ሠለስቱ ወንጌል መሠራቷ ለሦስቱ ነገድ ነውና ለነገደ ሴም ለነገደ ያፌት ለነገደ ካም፡፡ ወአብኅአ ኵሎ በወንጌል ሁሉ መክበሩን መናገር ነው።
አንድም ብእሲት መምህራን ብኁዕ ጥምቀት ውስተ ፫ቱ፤ ጥምቀት በሦስቱ ስም ነውና። ወአብኅዓ ኵሎ በጥምቀት ሁሉ መክበሩን መናገር ነው።
አንድም ብእሲት ቀሳውስት ብኁዕ፤ ሥጋው ደሙ ውስተ ሠለስቱ። ለቀድሶተ ሥጋ ወነፍስ ወመንፈስ ብለው ይሰጣሉና ወአብኅዓ ኵሎ በሥጋው በደሙ ሁሉ መክበሩን መናገር ነው።
አንድም ብእሲት ቡርክት ነፍስ። ብኁዕ ጸጋ ጥምቀት ውስተ ፫ቱ መሥፈርተ ሐሪፅ ውስተ ፫ቱ መክፈልተ ሕሊናሃ እንዲል። ሥራውን በሦስት ወገን ትሠራዋለች በወጣኒነት በማዕከላዊነት በፍጹምነት ክብሩንም በዚያው ልክ ትወርሰዋለችና። ወአብኅዓ ኵሎ። በሥራው ሁሉ መክበሩን መናገር ነው፤
አንድም ብኁዕ ጌታ ብእሲት ዮሴፍ ኒቆዲሞስ። ውስተ ሠለስቱ፤ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር መኖሩን መናገር ነው። ወአብኅዓ ኵሎ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ አንድ ወገን ሁኖ መነሣቱን መናገር ነው፡፡
                    ******     
፴፬፡ ወዘንተ ኵሎ ተናገረ እግዚአ ኢየሱስ በምሳሌ ለአሕዛብ። ማር ፬፥፴፬፡፡
                    ******     
፴፬፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአሕዛብ ይህን ሁሉ በምሳሌ አስተማራቸው።
ወዘእንበለ በምሳሌ ኢተናገሮሙ።
ያለምሳሌ ግን አላስተማራቸም አለ በዚህ ቀን። አንድም በሆነ ምሳሌ እንጂ ባልሆነ ምሳሌ አላስምራቸውም።
                    ******     
፴፭፡ ከመ ይትፈጸም ዘተብሀለ በነቢይ እንዘ ይብል እከሥት በምሳሌ አፉየ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት። መዝ ፸፯፥፪፡፡
                    ******     
፴፭፡ አፌን በምሳሌ እገልጣለሁ የጥንቱንም ምሳሌ አስተምራለሁ ተብሎ በነቢይ የተነገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ በከመ ይቤ አሳፍ የሚል አብነት ይገኛል ለዳዊት ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት መዘምራን ነበሩት አለቆቻቸው አሳፍ ቆሬ ኤማን ኤዶትም ይባላሉ በየአለቆቻቸው ከአራት ተከፍለው አሥራ ሁለት አሥራ ሁለት እየሆኑ በሐያ አራቱ ጊዜ ይጸልያሉ ልክ ናቸው እሱም ከአደባባይ በማይወጣበት ነገር በማይሰማበት ጊዜ እየገባ ይጸልያል ሥራ መፍታት የለም በዚህ ጊዜ አጽምዑ ለአሳፍ ደርሶት ነበርና ስለዚህ በከመ ይቤ አሳፍ የሚል አብነት ይገኛል፡፡
                    ******     
በእንተ ፍካሬ ዘምሳሌ ክርዳድ።
፴፮፡ ወእምዝ ኀደጎሙ ለአሕዛብ ወቦአ ውስተ ቤት።
፴፮፡ ከዚህ በኋላ ሕዝቡን በአፍአ ትቶ ከቤት ገባ
                    ******     
   ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
03/09/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment