Monday, May 6, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 83

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ሰዊት።
ምዕራፍ ፲፪።
                    ******     
በእንተ ጽልሁት ዘፈሪሳውያን
፴፬፡ ኦ ትውልደ ዓራዊተ ምድር በአይቴ ትክሉ ሠናየ ተናግሮ እንዘ እኩያን አንትሙ።
                    ******     
፴፬፡ እናንት የእባብ ልጆች ክፉዎች ስትሆኑ መልካም መናገር እንደምን ይቻላችኋል በልቡናችሁ ዕሩቅ ብእሲ የምትሉ ስትሆኑ እኔን የባሕርይ አምላክ ማለት እንደምን ይቻላችኋል።
እስመ እምተረፈ ልብ ይነብብ አፍ።
ልብ ያሰበውን አፍ ይናገራልና
                    ******     
፴፭፡ ኄር ብእሲ እምሠናይ መዝገበ ልቡ ያውፅአ ለሠናይት። ሉቃ ፮፥፵፭።
                    ******     
፴፭፡ በጎ ሰው በጎ ነገር ከሚያስብበት ልቡናው በጎ ነገርን አውጥቶ ይናገራል ።
ወእኩይሰ ብእሲ አምእኩይ መዝገበ ዓመፃሁ ያወፅኣ ለእኪት
ክፉ ሰው ግን ክፉ ነገር ከሚያስብበት ልቡናው ክፉ ነገርን አውጥቶ ይናገራል።
                    ******     
፴፮፡ አንሰ እብለክሙ ኵሉ ሰብእ ዘይነብብ ንባበ ጽሩዓ ያገብኡ ሎቱ በእንቲአሁ ቃለ በዕለተ ደይን
                    ******     
፴፮፡ እኔ ግን ተርታ ነገርን በሚናገር ሰው ሁሉ በፍርድ ቀን ፍዳውን ያመጡበታል ብዬ እነግራችኋለሁ።
(ታሪክ) እንዳንድ ባሕታዊ ከሚረዳበት ገዳም ወጥቶ በተባሕትዎ ይኖራል ከማኅበሩ አንዱ ሊጠይቀው ሄደ እነ እገሌ እንደምን ሁነዋል ብሎ ጠየቀው የበቁ ሁነዋል አለው። አንድ ሕሙየ ግብር ነበር እገሌሳ አለው እሱስ ከሁሉ በልጧል አለው አፍ፤ እስካሁን የነገርኸኝ ሁሉ ሐሰት ነው። ለልማዱ ጌታ በአምሳለ ንጉሥ ሲገኝለት እሱም የብርሃን ካባ ለብሶ በቀኝ ሲቆም የሚያየው ነው፤ እንደ ወትሮው የብርሃን ካባ ለብሶ በቀኝ እቆማለሁ ብሎ ሲሄድ ምስለኔዬ ወሬኛዬ መንግሥት ተበላላጩ መጣህ ንሳ ያዘው ሲል እሻላሁ ብሎ ሲሄድ ከካባው ተገፎ ሲቀር አየ እንዲህ ብዬ በተናገርሁት ፈጣሪዬ ፈርዶብኝ ነውን ብሎ ንስሐ ቢገባ በሰባት ዓመቱ ጌታ እንደ ጥንቱ በአምሳለ ንጉሥ ሲገኝ እሱም የብርሃን ካባ ለብሶ በቀኝ ሲቆም አይቷል።
                    ******     
፴፯፡ እስመ እምቃልከ ትጸድቅ
                    ******     
፴፯፡ ከአነጋገርህ የተነሣ ትከብራለህና
ወእምቃልከ ትትኴነን
ከአነጋገርህ የተነሣ ይፈረድብሃልና። ኢዮብ መጠንከ አምቃለ አፉከ። ሰሎሞን ሕይወት ወሞት ውስተ እደ ልሳን። ሲራክ ኃሳርከሂ ወክብርከ እምቃለ አፉከ ያሉትን ቃል ለውጦ አነበበው፡፡
                    ******     
በእንተ ትእምርተ ዮናስ
፴፰፡ ወአሜሃ መጽኡ ሰብእ እምጸሐፍት ወእምፈሪሳውያን ወይቤልዎ ሊቅ ንፈቅድ እምኀቤከ ትእምርተ ንርአይ
                    ******     
፴፰፡ ያን ጊዜ ከጸሐፍት ከፈሪሳውያን ወገን የሚሆኑ ሰዎች መጥተው መምህር ምልክት ልታሳየን እንወዳለን አሉት።
(ሐተታ) እሱ ሰው ሁኖ በቋንቋቸው በዕብራይስጥ ቢያስተምራቸው እንደ ሙሴ ባሕር ከፍለህ ጠላት ገድለህ ደመና ጋርደህ መና አውርደህ እንደ ኢያሱ በረድ አዝንመህ ፀሐይ አቁመህ እንደ ጌዴዎን ፀምር ዘርግተህ ጠል አውርደህ እንደ ኤልያስ ሰማይ ለጉመህ እሳት አዝንመህ ልታሳየን እንወዳለን አሉት።
                    ******     
፴፱፡ ወአውሥአ ወይቤሎሙ ትውልድ ዕሉት ወዓማፂት ወዘማዊት ትእምርተ ተኃሥሥ፡፡ ማቴ ፲፮፥፬። ሉቃ ፲፩፥፳፱። ፩፡ቆሮ ፩፥፳፪፡፡
                    ******     
፴፱፡ ሴሰኛ አሉተኛ ትውልድ ቤተ አይሁድ ምልክትን ትሻለች። ቤተ አድሁድን ዘማ አላቸው ዘማ ነገሩ አንድ ሲሆን ዕለት ዕለት ወንድ ሊለወጥላት እንድትወድ ቤተ አይሁድም ዕለት ዕለት ትምህርት ቢለወጥላቸው ይወዳሉና
ወትእምርትሰ ኢተውሀባ ዘእንበለ ትእምርተ ዮናስ ነቢይ።
ምልክት ግን ዮናስ ከአደረገው ምልክት በቀር ያልተደረገላት የቀረባት የማይደረግላት የማይቀርላት የለም። ሁሉን ስትዘነጋው ይህን አትዘነጋውምና ኋላ በመጨረሻ ተዘከርነ ዘይቤ ዝንቱ መስሐቲ ስመ ሕያው ውእቱ አመ ሣልስት ዕለት እትነሣእ አዝዝ እንከ ይዕቀቡ መቃብሪሁ ይላሉና ።
                    ******     
፵፡ እስመ በከመ ነበረ ዮናስ ውስተ አንበሪ ሠሉሰ መዋዕለ ወሠሉሰ ለያልየ ከማሁ ሀለዎ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይንበር ውስተ ልበ ምድር ሠሉሰ መዋዕለ ወሠሉሰ ለያልየ። ዮሐ ፪፥፩።
                    ******     
፵፡ ዮናስ በከርሠ አንበሪ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት እንደ ኖረ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ይኖር ዘንድ አለውና ።
                    ******     
፵፩፡ ሰብአ ነነዌ ይትነሥኡ አመ ዕለተ ደይን ምስለ ዛ ትውልድ። ዮሐ ፫፥፭።
                    ******     
፵፩፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን በቤተ አይሁድ በጠላትነት ይነሡባታል።
ወይትፋትሕዋ።
ይከራከሯታል ።
ወያስተሐፍርዋ።
ምላሽ ያሳጧታል።
እስመ ነስሑ በስብከተ ዮናስ
ዮናስ ቢያስተምር አምነዋልና
ወናሁ ዘየዓቢ እምዮናስ ሀሎ ዝየ።
ከዮናስ የሚበልጥ እነሆ ከዚህ አለ ማለት ቤተ አይሁድ ግን እግዚአ ዮናስ ክርስቶስ ቢያስተምራቸው አናምንም ብለዋልና። ጌታ ዮናስን እስከነ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታዕ ነነዌ ሀገር ዐባይ እያልህ አስተምር አለው አይሆንም አንተ መሐሪ ነህ እኔ እንዲህ ብዬ አስተምሬ ብትምራቸው ነቢየ ሐሰት እባል የለም አለው ሁለተኛ ሂድ አላልሁምን አለው ዮናስ ማለት ርግብ የዋህ ማለት ነውና ይህ ሁሉ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ቢያገኘኝ አይደለም ብሎ ወተኃጥአ እምገጸ እግዚአብሔር ወሖረ ተርሴሰ ይላል ተርሲስ ወደሚባል ሀገር ሲሄድ ኢዮጲ ከሚባል ባሕር ደረሰ ወረከበ ሐመረ ዘይነግድ ብሔረ ተርሴስ ይላል በሀገራቸው ከየብሱ ባሕሩ ይበዛልና ነጋድያን በመርከብ ተጭነው ወደ ተርሴስ ሲሄዱ አገኘ ወተዐሰበ ሐመረ በንዋይ ይላል ገዝቶ ባንድነት ተጭኖ ሄደ ምንት ተግባርከ ወአይ ብሔርከ ወአይ ሕዝብከ አሉት አይ ብሔርከ ላሉት አይመልስላቸውም አይ ሕዝብከ ላሉት ዕብራዊ ነኝ። ወምንት ተግባርከ ላሉት የማመልከው ሰማይን ምድርን የብስን ባሕርን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው አላቸው ከጥልቅ ባሕር ሲደርሱ ነፋስ መጣ ማዕበል ሞገድ ተነሣ መርከባቸው ሊሰጥም ሆነ ወገደፉ ሣህሎሙ ይላል፡፡ ገንዘባቸውን እያወጡ ይጥሉ ጀመር እንደ ማሟረት። ወንሕረ ዮናስ ውስተ ከርሠ ሐመር ይላል ሊቀ ሐመር ከሚተኛበት ገብቶ ተኝቷል አንዱ ሂዶ ተንሥእ ወጸውእ ስመ አምላክከ አለው። እግዚአብሔርን አመልካለሁ ብሏቸው ነበርና ነገሩን አይቶ ይህ የመጣ በኔ ምክንያት ነው እኔን ካልጣላችሁኝ ጸጥ አይልላችሁም አላቸው እሳቸውም ሰውስ ብንጥል እዳ ይሆንብናል ዕጣ እንጣጣል ብለው ዕጣ ቢያወጡ ወወረደ ዕፃ ላእለ ዮናስ እንዲል በዮናስ ዕጣ ወጣበት ወረደ ማለቱ ግን ከራሳቸው አድርገው ያወጡታልና ፈቃድህስ ከሆነ ዕዳ አይሆንብንም ብለው አውጥተው ጣሉት የታዘዘ አንበሪ ተቀብሎ ዋጠው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አሳድሮ በአንፃረ ነነዌ አውጥቶ ጣለው ከዚህ በኋላ ወሰበከ ምሕዋረ አሐቲ ዕለት ይላል ያንድ ቀን መንገድ ሲቀር ያኑ አስተማረ። ያገሩ ንጉሥም ይኸን ነገር በሰማ ጊዜ ከዙፋኑ ወርዶ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ንስሐ ገባ የወንድ ሙሽራ ከጫጉላው የሴት ሙሽራ ከመጋረጃዋ ይውጡ ኢይትረአዩ ሰብእ ወእንስሳ ሰዎችም እንስሳትም ከእንጨት ከሳር ከውሀ አይሰማሩ ብሎ አዋጅ ነገረ ያጠፋልኛል ብሎ ቢያይ የማያጠፋለት ሆነ እኔ አስቀድሜ የፈራሁት ይኸን አልነበረምን ብሎ አሰበ፡፡ ዮናስ የሚል ድምጽ አሰማው ሊያደርግልኝ ነው ብሎ ከከተማው ዳር ወገብረ ላቲ ንስቲተ ልጎተ ይላል ጎጆ ሰርቶ ተቀመጠ እንቅልፍ መጣበት ተኝቶ ነቃ። ሁለተኛ ቢነቃ ቅል በቅላ ጎጆውን አልብሳለት አገኘ ደስ ብሎት ተኛ የታዘዘ ትል ቆርጦ ጣላት ደረቀች ዋዕይ ተሰማው ቢነቃ ደርቃ አገኛት አዘነ ጥቀኑ ትቴክዝ ታዝናለህን አለው አዎን ቢለው አንተስ ላልተከልሃት ውሀ ላላጠጣሃት ታዝናለህ። አንሰኑ ኢይምህካ ለነነዌ ሀገር ዘሀለዉ በውስቴታ ፈድፋደ ዘይበዝኁ እም ፲ቱ ወ፪ቱ እልፍ እለ ኢፈለጡ የማኖሙ ወፀጋሞሙ እኔስ ግራና ቀኝ ሳይለዩ ለሚወረውሩ ከ፲ራ ፪ት እልፍ የሚበዙ ኃያላን ላሉባት ለነነዌ እኔ አላዝንላትምን፡፡
አንድም ግራና ቀኝ ያለዩ ከአሥራ ሁለት ዕልፍ የሚበዙ ሕፃናት ላሉባት ለነነዌ እኔ አላዝላትምን አለው እሱም ነቢየ ሐሰት እንዳይባል እሳቱ እንደ ደመና ሁኖ ታይቷል የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ ንስሐቸውም እንዳይቀር ተመልሶላቸዋል በናሆም ስንክሳር ግን ወበልዓ አሐደ ኅብረ ይላል ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር አጥፍቲል ብሏል ይህም አልቀረ በሦስተኛው ትውልድ ተወግታ ጠፍታለች ስልምናሶር ዓቢይ ሰናክሬምን ዓቢይ ሰናክሬም ንዑስ ሰናክሬምን ይወልዳል ወሶበ ሰምዑ ሙስናነ ለነነዌ ሀገር ዓባይ ተፈሥሑ ቂሮስ ወአኽሻዊሮስ እንዲል በንዑስ ሰናክሬም ፆር ሰደው አስወግተዋታል፡። ይህም ሊታወቅ ጦቢት ሲሞት ጦብያን ልጁን ይህች ሀገር ጠፊ ናት ዮናስ የተናገረው ነገር አይቀርምና ሜዶን ሂደህ ኑር ገንዘባችነን ከነገባኤል አምጣ ብሎት ሙቷል፡፡ ዮናስ ነነዌ ወርዶ ማስተማሩ ስለምን ቢሉ አብነት ለመሆን ሐዋርያት ወንጌልን ሊያስተምሩ በሄዱ ጊዜ እኒህ ለምን ይመጣሉ ቀድሞ ነቢያት መጥተው አያስተምሩን ነበር በምን ነገር ነው እንዳይሉ ልማድ እንጂ ነው ቀድሞም ነቢያት ያስተምሩን ነበር ብለው እንዲቀባሏቸው።
፫ መዓልት ፫ ሌሊት መሆኑ ስለምን ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም፡፡ ትንቢት በሠኑይ ዕለት ይቀሥፈነ ወበሠሉስ መዋዕል ይሤርየነ ወያሐይወነ። ወአመ ሣልስት ዕለት ንትነሣእ ወአመ ሣልስት ዕለት ሦጣ ለነፍሱ ውስተ ሥጋሁ ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌም ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ መልቶ የነበረውን ውሀ ከሦስት ከፍሎ አንዱን እድ ውቅያኖስን ለይትጋባዕ ማይ ውስተ ምዕላዲሁ ብሎ በዙሪያው ወስኖታል አንዱን እጅ ሐኖስን ከላይ ሰቅሎታል አንዱን እጅ ለይኩን ጠፈር ብሎ ባለው አጽንቶታል። ውሀው የመቃብር ምድር የጌታ ምሳሌ።
አንድም አዳም በፈታሒነቱ አንፃር መሐሪነቱ እንዳለ አውቆ ብንበድለው እንደፈረደብን ንስሐ ብንገባ እንጂ ይቅር ይለናል ብሎ እስካንገታቸው የሚያጠልቅ ባሕር ገቡ። አንቺም ከዚያ ግቢ እኔም ከዚያ እገባለሁ ብሎ አርባ ቀን ሳይሆን አንወጣም አሉ፡፡ ሰላሳ አምስት ቀን ሲሆን ዲያብሎስ መጥቶ ምሬሃለሁ ውጣ ብሎሃል አለው። አርባ ቀን ሳይሆነኝ አልወጣም ብዬ ነው የገባሁ አይሆንም አለው። ቀድሞ አትብላ ያለህን ዕፀ በለስ በልተህ ከዚህ ሁሉ ደረስህ ደግሞ ዛሬ ምሬሃለሁ ውጣ ብሎሃል ብልህ አልወጣም አልክ ላዘዘኝ እነግርልሃለሁ ብሎ የተቈጣ መስሎ ወደ ሔዋን ሄደ። እስመ ይአቲ ገራህተ ሐምሉ ይላታል የበሰላው ናትና ቢመክሩት አይሰማ ምሬሃለሁ ውጣ ብሎሃል ብለው አይሆንም አለ አላት ሂዳ ምሬያችኋለሁ ሲለንማ እንውጣ እንጂ አለችው ተያይዘው ወጡ ጥቂት እልፍ አድርጎ እኔ ማነኝ አላወቃችሁኝምን አላቸው አላወቅንህም አሉት። ዕፀ በለስን ብሉ ብዬ ከገነት ያወጣኋችሁ እኔ አይደለሁም ብሎ ቀጥቅጦ ጥሏቸው ሄደ፡፡ መልአክ መጥቶ በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ብሎሃል ብሎ ተስፋውን ነግሮ በገነት አንፃር በደብር ቅዱስ አኖራቸው። ያን እያዩ እንዲያዝኑ ከዚህ ኑሩ አልከን ምግባችንስ አሉት። ላዘዘኝ እነግራለሁ ብሎ ገነት ገብቶ ለአእዋፍ ጌታችሁ አዳም ከዚያው ነው ምግቡን ውሰዱለት አላቸው። በአንድ ሰዓት አሥራ ሁለት ዋሻ መልተውለታል። ያንዱ ዋሸ ስፋት መጠነ ምንዳፈ ሐፅ ይለዋል ሲሄዱ ወትሮ የሚያውቃቸው ናቸውና በድምፃቸው ተመሥጦ ተከተላቸው እኒያ ላዩን እየበረሩ እሱ ታቹን እየሮጠ ተካክለው ከእግረ ገነት ደረሱ። የገነት ቅጽሩ እሳት ነው እኒያ ላዩን እየበረሩ ገቡ። እሱ ጸጋው ተነሥቶታልና ተከልክሎ ቀረ። ይህ ስሑት ወዴት ይሄዳል ብሎ ቤት ያህል ደንጊያ ጫነበት ወተደብተረት ይእቲ ዕብን ላዕለ አዳም እንዲል። ሦስት ቀን እንደ ድንኳን ሁናለት ሰንብቷል ከዚህ በኋላ መልአክ አንሥቶለት ተመልሷል። ደንጊያ የመቃብር አዳም የጌታ ምሳሌ።
አንድም አብርሃም ይስሐቅን በሕሊናው በሰዋው በሦስት ቀን ተነሥቷል። ሕሊና አብርሃም የመቃብር ይስሐቅ የጌታ ምሳሌ።
አንድም ዮናስ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ አንበሪ ኑሯል ዮናስ የጌታ ከርሠ አንበሪ የመቃብር ምሳሌ። ትንቢቱን አውቆ አናግሯል ምሳሌውንም እንጂ ባወቀ አስመስሏል ምሥጢሩ እንደምን ነው ቢሉ ለአዳም ለሔዋን ለሕፃናቱ ለሥጋ ለነፍስ ለደመ ነፍስ እንደ ካሰ ለማጠየቅ።
አንድም ፫ቱ ዕድዋኒሁ ለሰብእ እንዲል ኃጢአትን ሞትን ፍዳን እንዳጠፋ ለማጠየቅ።
አንድም በዕውነትም እንደሞተ ለማጠየቅ ፈላስፎች ነፍሱ ከሥጋው ሳይለይ ደም ከልቡ ወድቆ እስትንፋሱን ይከለክለዋል ብለው ከሞተበት ሰዓት ጀምረው እስከ ሞተበት ሰዓት ድረስ አቈይተው ነው የሚቀብሩ የሚድንም አለ የሚሞትም አለ ፈጥኖ ተነሥቶ ቢሆን አልሞተም ባሉ ነበርና በእውነት እንደሞተ ለማጠየቅ ያውስ ቢሆን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ወዴት ይገኛል ቢሉ መዓልተ ዓርብ ሌሊተ ዓርብን ስቦ ሌሊተ እሁድ መዓልተ እሁድን ስቦ
አንድም ከርሠ ሐዋርያትን መቃብር ብሎ አንድም ዓርብ ከነግሕ እስከ ቀትር ብርሃን ከቀትር እስከ ሰዓት ጨለማ ሁኑዋል በሠርክ ብርሃን ሁኑዋል። ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃን እንዲል ይህ ሁለት መዓልት አንድ ሌሊት የቅዳሜ ሌሊትና መዓልቱ የእሁድ ሌሊት ይህ ነው።
                    ******     
፵፪፡ ንግሥተ ዓዜብ ትትነሣእ አመ ዕለተ ደይን ምስለ ዛ ትውልድ፡፡ ፩፡ነገ ፲፩፥፪፡፡ ሕፁ ፱፥፩፡፡
፵፪፡ በቤተ አይሁድ ትነሣባታለች
                    ******     
   ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
28/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment