Sunday, May 5, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 82

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ሰዊት።
ምዕራፍ ፲፪።
                    ******     
፳፩፡ ወበስመ ዚአሁ ይትአመኑ አሕዛብ።
                    ******     
፳፩፡ አሕዛብም በስሙ እስኪያምኑ ድረስ ያለው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ።
ተግኅሠ እምህየ።
አንድም በንስሐ በኀዘን የሚቀጠቀጥ በተስፋ የሚጢያጢያስ አዳም አይጠፋም በዕለተ ዓርብ አቸናፊ ፍርዱ በአጋንንት እስኪመለስ ድረስ አሕዛብ በስሙ እስኪያምኑ ድረስ ብሎ የተናገረው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ።
አሕየዎሙ።
ሞተ ሥጋው ለሞተ ነፍሱ ምልክት እንደሆነ ድኅነተ ሥጋውም ለድኅነተ ነፍሱ ምልክት ነውና።
አንድም ይሁድ በአጋንንት በቅንዓት የሚቀጠቀጥ በቅንዓት የሚጢያጢያስ አይሁዳዊ አይጠፋም። አሸናፊ ፍርዱ በአይሁድ በ፵ ዘመን እስኪመለስ ድረስ። አሕዛብም በስሙ እስኪያምኑ ድረስ ያለው ይደርስ ይፈጸም ዘንድ።
ተማከሩ ይቅትልዎ።
አንድም መቃ መስዬ የፍግ እሳት ወንጌል አትጠፋበትም አሸናፊ ፍርዱ በአይሁድ በአጋንንት እስኪመለስ ድረስ። አሕዛብም በስሙ እስኪያምኑ ድረስ። ያለው ይደርስ ይፈጸም  ዘንድ። ገሠፆሙ (ሐተታ) መቃ መስዬ አላት ወንጌልን። መቃ መስዬ በጋውን ማንም ሲጠቀጥቀው ይበጃል፡፡ ክረምት በሆነ ጊዜ በያለበት ያፈላል ወንጌልም ስትነገር አንድ ሰው በሰማዕትነት ይሞታል ታምራት ይደረጋል ብዙ ሰው ያምናል። የፍግ እሳት ከአንድ ላይ ያቃጠሉት እንደሆነ ሁለተኛ ሦስተኛ አቃጥሉኝ አይልም ተያይዞ ይነዳል ወንጌልም በመቶ ሐያ ቤተ ሰብ ተጀምራ እስከ ምጽአት ድረስ ስትነገር ትኖራለችና።
አንድም ብርዓ ቅጥቁጠ ኢይሰብር ወሡዓኒ ዘይጠይስ ኢያጠፍዕፅ ይላል አብነት ተዉ ያጠፋችኋል ቢሏቸው ስንኳን እኛን ሊያጠፋ አስኳሉ የወጣለት የዕንቊላል ቅርፍትስ እንኳ አያደቅም። የሚያጢያጢስ የጧፍ ኩስታሪስ እንኳ አያጠፋም ይሉታል ብሎ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ፈለሰ እምህየ።
                    ******     
በእንተ ዕውር ወጽሙም ዘቦቱ ጋኔን።
፳፪፡ ወእምዝ አምጽኡ ኀቤሁ ዘጋኔን ዕውረ ወጽሙመ ወበሐመ
                    ******     
፳፪፡ ከዚህ በኋላ ጋኔን ዕውር ደንቆሮ ድዳ ያደረገውን ሰው ወደ እሱ አመጡ።
ወፈወሶ እስከ ውእቱ ዕውር ወጽሙም ነበበሂ ወርእየሂ ወሰምዓሂ።
ዕውረ ሥጋው በታምራት ዕውረ ነፍሱ በትምህርት እስኪያይ በሐመ ሥጋው በታምራት በሐመ ነፍሱ በትምህርት እስኪናገር። ጽሙመ ሥጋ በታምራት እስኪሰማ ድረስ አዳነው
                    ******     
፳፫፡ ወተደሙ ኵሎሙ አሕዛብ፡፡
                    ******     
፳፫፡ አሕዛብ ሁሉ አደነቁ።
ወይቤሉ አኮኑ ዝንቱ ወልደ ዳዊት።
ያላመኑት። የጥቡዕ የዳዊት ልጅ አይደለምን ይህን ያህል ርኅራኄ ከማን አገኘው ብለው ያመኑት ግን የርኅሩኅ የዳዊት ልጅ አይደለምን ምነዋ ቢያደርግ አሉ
                    ******     
፳፬፡ ወፈሪሳውያንሰ ሰሚዖሙ ይቤሉ ዝንቱሰ ኢያወፅእ አጋንንተ ዘእንበለ በብዔል ዜቡል መልአኮሙ ለአጋንንት። ማቴ ፱፥፴፬፡፡ ማር ፫፥፳፪፡፡ ሉቃ ፲፩፥፲፭።
                    ******     
፳፬፡ ፈሪሳውያን ግን ሰምተው ትጠፋለች ብለው ተአምራት ይደረጋል ሰው ይሰበሰባል ወንጌል ትሰፋለች ኦሪት የንጉሥን ጭፍራ በንጉሥ ቀላጤ እንዲያስወጡት ከአለቃቸው ከብዔል ዜቡል ተጨዋውቶ ያወጣቸዋል እንጂ ያለዚያ አያወጣቸውም አሉ።
                    ******     
፳፭፡ ወአአመሮሙ እግዚአ ኢየሱስ ሕሊናሆሙ ይቤሎሙ ኵላ መንግሥት እንተ ትትናፈቅ በበይናቲሃ ትማስን። ሉቃ ፲፩፥፲፯፡፡
                    ******     
፳፭፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገራቸውን አውቆባቸው እርስ በርሷ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች አላቸው ንጉሡ እንዝመት ሲል ሠራዊቱ አንዘምትም ቢሉ።
ወኵላ ሀገር።
እርስ በርሷም የምትለያይ ሀገር አትጸናም ትፈታለች ሹሙ እንገብር ሲል ሕዝቡ አንገብርም ቢሉ።
ወእመሂ ቤት እንተ ትትናፈቅ በበይናቲሃ ኢትቀውም።
እርስ በርሷም የምትለያይ ቤትም አትጸናም ትፈርሳለች። በባለቤቱ ደጋ እንሁን ሲል ቤተ ሰቡ ቈላ እንሁን ቢሉ።
                    ******     
፳፮፡ ወእመሰ ሰይጣን ያወፅእ ሰይጣነ ተናፈቀኬ በበይናቲሁ።
                    ******     
፳፮፡ ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣው ከሆነ እርስ በርሱ ተለያያ።
                    ******     
፳፯፡ እፎ እንከ ትቀውም መንግሥቱ።
                    ******     
፳፯፡ መንግሥቱስ እንደምን ትጸናለች፤ (ሐተታ) ምን መንግሥት አለው ቢሉ ዮሐንስ ወልደ ማሪት እንዳየው። አባቱ መምለኬ ጣዖት ነበረ ለጣዖት ሊሰዋ ሲሄድ አስከትሎት ሄደ ሠውቶ እስኪወጣ እንቅልፍ መጣበት ተኛ በሕልሙ ዲያብሎስ በአምሳለ ንጉሥ ዘውዱን ደፍቶ ከዙፋኑ ሁኖ ኃያላኑን በቀኝ በግራ በፊት በኋላ አቁሞ ያየዋል ከዳሪ መጥቶ ንገሩልኝ ይላል ይነግሩለታል ይገባል ወዴት ነበርህ ይለዋል ከሀገር ምን አድርገህ መጣህ ይለዋል ባልና ሚስቱን ነገር ከአለቀ በኋላ አጣልቼ አለያይቼ መጣሁ ይለዋል በስንት ቀንህ ነው አለው በ ፲፩ ቀኔ ነው አለው፡፡ አስወጣው አለው፡፡ ሌላው መጥቶ ንገሩልኝ አለ ይነግሩለታል ግባ በሉት ይላል ይገባል ወዴት ነበርህ አለው ከምድር ድምበር፡፡ ምን አድርገህ መጣህ ይለዋል ወንድማማች አጣልቼ አጋድዬ መጣሁ ይለዋል በስንት ቀንህ ነው ይለዋል በ፳ ቀኔ ነው አለው አስወጣው ይላል ይወጣል፡፡ ደግሞ ሌላው መጥቶ ንገሩልኝ ይላል ይነግሩለታል ግባ በሉት ይላል ይገባል ወዴት ነበርህ ይለዋል ከገዳም ምን አድርገህ መጣህ ይለዋል ፵ ዘመን የዘጋውን መነኵሴ አስቼ ዓለማዊ ሥራ አሠርቼው መጣሁ አለው በስንት ቀንህ አለው በዘመኑ ልክ ተዋግቼ አለው አንተንስ ሊያነግሡህ ይገባል ብሎ ከዙፋኑ ወርዶ ዘውዱን ደፍቶ ሲያነግሠው አየ፡፡ ሲነቃ የመነኮሳት መከራቸው የጸና ክብራቸው እንጂ ቢበዛ ነው ብሎ አምኑዋል ተጠምቋል መንኩሷል
                    ******     
፳፰፡ ወእመሰ አነ በብዔል ዜቡል አወፅኦሙ ለአጋንንት ውሉድክሙ በምንት ያወፅእዎሙ
                    ******     
፳፰፡ እኔ አጋንንትን በብዔል ዜቡል የማወጣቸው ከሆነ ልጆቻችሁ ሐዋርያት በማን ስም ያወጧቸዋል በኔ ስም አይደለምን
ወበእንተዝ እሙንቱ ፈታሕተ ይከውኑክሙ።
ስለዚህ ነገር ማለት እናንተ በብዔል ዜቡል ያወጻል ስላላችሁኝ ሐዋርያት በኔ ስም የሚያወጧቸው ስለሆነ እነሱ መፈራረጃ ይሆኑባችኋል።
                    ******     
፳፱፡ ወእመሰ አነ በመንፈሰ እግዚአብሔር አወፅኦሙ ለአጋንንት ዮጊኬ በጽሐት ላዕሌክሙ መንግሥተ እግዚአብሔር
                    ******     
፳፱፡ እናንተ አጋንንትን በብዔል ዜቡል ያወጣቸዋል የምትሉኝ ከሆነ እኔ ግን አጋንንትን በመንፈሰ እግዚአብሔር የማወጣቸው ከሆነ ሥልጣነ እግዚአብሔር ልታጠፋችሁ ተቃጥታባችኋለች፡፡
አንድም እናንተ በመንፈሰ እግዚአብሔር ያወጣቸዋል ካላችሁኝ እኔም በመንፈሰ እግዚአብሔር የማወጣቸው ከሆነ መንግሥተ እግዚአብሔር ልጅነት ልትሰጣችሁ ቀርባለች
                    ******     
፴፡ ወአልቦ ዘይክል መኑሂ በዊአ ቤተ ኃያል ወበርብሮ ንዋዮ
                    ******     
፴፡ ከአርበኛ ቤት ገብቶ ገንዘቡን መዝረፍ የሚቻለው የለም።
እመ ኢቀደመ ዓሢሮቶ ለኃያል
አስቀድሞ እጁን ካልያዘው
ወእምዝ ይበረብር ቤቶ።
እጁን ከያዘ በኋላ ገንዘቡን ይወስዳል እንደዚህም ሁሉ ሰይጣንን በ፫ቱ አርእስተ ኃጣውእ ድል ነሥቼዋለሁና አወጣዋለሁ እንጂ ያለዚያ አላወጣውም፡፡
                    ******     
፴፡ ዘኢኮነ ምስሌየ ዕድውየ ውእቱ
                    ******     
፴፡ በቦታ በቅዳሴ ከኔ ጋራ አንድ ያይደለ ዲያብሎስ ባለጋራዬ ነው፡፡
ወዘኢይትጋባእ ምስሌየ ይዘርወኒ።
በቦታ በቅዳሴ ከኔ ጋራ አንድ ያይደለ ዲያብሎስ በምዕመናን እንዳላድርባቸው ያደርገኛል። የምዕመናንን ዝርወት አንድ አድርጎ ይዘርወኒ አለ።
አንድም ዘኢኮነ ምስሌየ  በሃይማኖት በጉባኤ ከኔ ጋራ አንድ ያይደለ ይሁዳ ባለጋራዬ ነው። ወዘኢይትጋባእ በሃይማኖት በጉባዔ ከኔ ጋራ አንድ ያይደለ ይሁዳ በመፅመናን አንድም በሱ እንዳላድርበት ያደርገኛል።
                    ******     
፴፩፡ ወበእንተዝ እብለክሙ ኵሉ ኃጢአት ወጽርፈት ይትኃደግ ለሰብእ። ማር ፫፥፳፰፡፡ ሉቃ ፲፪፥፲፡፡
                    ******     
፴፩፡ ስለዚህ ሰውን የሰደበ ሁሉ ኃጢአቱ ይሰርይለታል ብዬ እነግራችኋለሁ ።
ወዘሰ ጸረፈ ላዕለ መንፈስ ቅዱስ ኢይትኃደግ ሎቱ፡፡
መንፈስ ቅዱስን የሰደበ ግን ማለት ሕፁፅ ያለ ኃጢአቱ አይሰረይለትም።
                    ******     
፴፪፡ ወዘሰ ነበበ ቃለ ላዕለ ወልደ እጓለ እመሕያው ይትኃደግ ሎቱ
                    ******     
፴፪፡ ወልደ እጓለ መሕያው ክርስቶስን ግን ዕሩቅ ብእሲ ያለ ይሰረይለታል
ወዘሰ ነበበ ላዕለ መንፈስ ቅዱስ ኢይትኃደግ ሎቱ
መንፈስ ቅዱስን ሕፁፅ ያለ ግን ኃጢአቱ አይሰረይለትም። ይህን ማለቱ ይገባዋል ብሎ አይደለም ለወልድ ምክንያት አለው ሥጋ ለብሷል። ለመንፈስ ቅዱስ ግን ምክንያት የለውምና ከተዘጋ ቤቱ ከተደፈነ እሳቱ እንዲሉ።
አንድም አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ መንፈስ ቅዱስ በአምሰለ ርግብ ወርዶ ሳይመሰክርለት ዕሩቅ ብአሲ ያለ ኃጢአቱ ይሰረይለታል። አብ ዝንቱ ውእቱ ብሎ ከመሰከረ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ከመሰከረለት በኋላ ግን ዕሩቅ ብአሲ ያለ አይሠረይለትም።
አንድም ሕዝባዊን የሰደበ ኃጠአቱ ይሰረይለታል። ኤጲስ ቆጶሱን የሰደበ ግን ኃጢአቱ አይሰረይለትም።
አንድም ሥጋዊ ተዘምዶን ያፈረሰ ኃጢአቱ ይሰረይለታል መንፈሳዊ ተዘምዶን ያፈረሰ ግን ኃጢአቱ አደሰረይለትም። ኃጢአት ሥጋውያት ይሰረያ በጾም ወበጸሎት። ኃጢአትሰ መንፈሳውያት ኢይሰረያ በጾም ወበጸሎት ዘእንበለ ዳዕሙ በምንኩስና እንዲል። እንዲህ ማለት ንስሐ ከገባ አይሰረይለትም ማለት አይደለም ከቀኖና ቀኖናውን ከፍዳ ፍዳውን ማብለጥ ነው፡፡
ኢበዝ ዓለም ።
በዚህም ዓለም ሁኖ።
ወኢበዘይመጽእ ዓለም።
በሚመጣውም ዓለም ሁኖ አይሰረይለትም። በወዲህስ ይሁን በወዲያማ ምን ንስሐ አለ
አልቦቱ ለሰብእ ንስሐ እምድኅረ ሞት ይል የለም ቢሉ። ኃጢአቱን ለቄሱ ነግሮት ቀኖና ተቀብሎ ጀምሮት ቢሞት ሳይጀምረውም ቢሞት መካነ ንስሐ አለ ከዚያ አድርሶ ይወጣልና እንዲህ አለ።
አንድም ወትዴሎ አበሳነ ምስለ ኵሉ ዘገበርነ እንዲል ያለማነውም ያጠፋነውም በፍትሐ እግዚአብሔር ይመረመራል ያለማነው በዝቶ ያጠፋነው ያነሰ እንደሆነ እንገባለን ያለማነው አንሶ ያጠፋነው የበዛ እንደሆነ ግን አንገባምና።
                    ******     
፴፫፡ እመ አኮ ግበሩ ዕፀ ሠናየ ወፍሬሁኒ ሠናይ።
                    ******     
፴፫፡ እመ አኮ ዋዌ ነው መልካም ዛፍ አድርጉ ፍሬውም መልካም ማለት የአብርሃም ልጆች ነን በሉ የአብርሃምን ሥራ ሥሩ።
አንድም ተነሣሕያን ነን በሉ እኔም ተራድቼ የተነሳሕያንን ሥራ ላሰራችሁ።
ወእመ አኮ ግበሩ ዕፀ እኩየ ወፍሬሁኒ እኩይ። .
ወይም ክፉ ዛፍ አድርጉ ፍሬውም ክፉ ማለት የሰይጣን ልጆች ነን በሉ የሰይጣንን ሥራ ሥሩ እሱስ አያዛቸውም እንዳይተውት ያውቃልና።
አንድም በአፋቸው እንወድሃለን ይሉታል በልቡናቸው ይጠሉታል በአፋችሁም በልቡናችሁም ውደዱኝ። ያለዚያ ግን በአፋችሁም በልቡናችሁም ጥሉኝ።
አንድም ሥራውን የአምላክ ሥራ ነው ይላሉ እሱን ዕሩቅ ብእሲ ይሉታል ሥራዬን የአምላክ ሥራ ነው በሉ እኔንም አምላክ ነው በሉ ያለዚያ ግን እኔንም ዕሩቅ ብእሲ በሉ ሥራዬንም የዕሩቅ ብእሲ ሥራ ነው በሉ።
አንድም ታምራቱን ይወዳሉ ትምህርቱን ይጠላሉ በእንተ ሠናይሰ ግብርከ ኢንዌግረከ አላ በበይነ ፅርፈትከ እንዲል ታምራቱንም ትምህርቱንም ውደዱ ያለዚያ ግን ትምህርቱንም ታምራቱንም ጥሉ።
እስመ እምፍሬሁ ይትዓወቅ ዕፅ።
ዛፍ በፍሬው ይታወቃልና።
                    ******     
በእንተ ጽልሁት ዘፈሪሳውያን
፴፬፡ ኦ ትውልደ ዓራዊተ ምድር በአይቴ ትክሉ ሠናየ ተናግሮ እንዘ እኩያን አንትሙ።
፴፬፡ እናንት የእባብ ልጆች ክፉዎች ስትሆኑ መልካም መናገር እንደምን ይቻላችኋል በልቡናችሁ ዕሩቅ ብእሲ የምትሉ ስትሆኑ እኔን የባሕርይ አምላክ ማለት እንደምን ይቻላችኋል።
                    ******     
   ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
27/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment