Wednesday, May 8, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 85

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በእንተ ሰዊት።
ምዕራፍ ፲፫።
                    ******     
፩፡ ወበይእቲ ዕለት ወጺኦ እግዚእ ኢየሱስ እምቤት ነበረ መንገለ ሐይቀ ባሕር።
                    ******     
፩፡ በዚያች ቀን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤት ወጥቶ ከወደቡ ተቀመጠ፡፡
                    ******     
፪፡ ወተጋብኡ ኀቤሁ ሰብአ ብኵር የቤተ ብዙኃን እስከ ሶበ የዓርግ ውስተ ሐመር ወይነብር፡፡ ማር ፬፥፩።
                    ******     
፪፡ ከመርከብ ወጥቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደሱ ተሰበሰቡ።
(ሐተታ) ሰው ሲበዛ ከመርከብ ከተራራ ሆኖ ማስተማር ልማድ ነው። መምህር ከፍ ካለ ቦታ ሰማዕያን ዝቅ ካለ ቦታ ሲሆኑ ትምህርት ለሰማዕያን ይረዳልና። ወይረድ ከመ ጠል ነቢብየ እንዲል ።
ወኵሉ ሰብእ ውስተ ሐይቅ ይቀውሙ
ሕዝቡ ሁሉ ከወደቡ ተቀምጠው ነበር ወትቀውም ንግሥት በየማንከ እንዲል። ባሕር የመለኮት ሐመር የትስብእት ምሳሌ። መለኮቱን ትስብእቱን ከማመን በአፍአ እንደ ነበሩ ለማጠየቅ ውስተ ሐይቅ ይቀውሙ አለ።
አንድም ባሕር የትስብእት ሐመር የመለኮት። መለኮቱን ትስብእቱን ከማመን በአፍአ እንደነበሩ ለማጠየቅ ውስተ ሐይቅ ይቀውሙ አለ፡፡
አንድም ባሕር የጥምቀት ሐመር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ከጥምቀት ከቤተ ክርስቲያን አፍአ እንደነበሩ ለማጠየቅ ውስተ ሐይቅ ይቀውሙ አለ።
                    ******     
፫፡ ወነገሮሙ ብዙኃ በምሳሌ እንዘ ይብል። ሉቃ ፫፥፭
                    ******     
፫፡ እንዲህ ብሎ በምሳሌ ብዙ ነገራቸው።
አንድም ብዙኃ ምሳሌ ብዙ ምሳሌ ነገራቸው።
አንድም ወመሰለ ሎሙ ብዙኃ ምሳሌ ብዙ ምላሌ መሰለላቸው
(ሐተታ) ምሳሌውም በሆነ ነው እንጂ ባልሆነ ምሳሌ አይደለም ለገበሬ በዘር ለሴት በርሾ ለነጋዴ በዕንቊ ለዓሣ ወጋሪ በዘረ መትራን መስሎ አስተምሯል። በምሳሌ ማስተማሩ ስለምን ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም።
ትንቢት እከሥት በምሳሌ አፉየ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት ተብሎ ተነግሯል
ምሳሌም ቀድሞ አባቶቹ ነቢያት በምሳሌ እንበለ ምሳሌ አስተምረዋል እሱም በምሳሌ ይኸን እንበለ ምሳሌ ብፁዓንን አስተምሯልና ትንቢቱን አውቆ አናግሯል ምሳሌውንም አንጂ ባወቀ አስመስሏል ምሥጢሩ እንደ ምነው ቢሉ ላዋቂ ለመግለጽ ካላዋቂ ለመሠወር።
አንድም ደቀ መዝሙር ሁልጊዜ ተርታ ነገር ቢነግሩት አይነቃምና ለማንቃት
ናሁ ወፅአ ዘራዒ ከመ ይዝራዕ።
ገበሬ ሊዘራ ወጣ ዘሩም የተበጠረ የተንጠረጠረ ነው።
                    ******     
፬፡ ወእንዘ ይዘርዕ ቦ ዘወድቀ ውስተ ፍኖት።
                    ******     
፬፡ ጨብጦ ሲዘራ ከመንገድ የወደቀ ዘር አለ።
ወመጽኡ አእዋፈ ሰማይ ወበልዕዎ።
አዕዋፍ መጥተው የለቀሙት
                    ******     
፭፡ ወቦ ዘወድቀ ዲበ ኰኵሕ ኀበ አልቦ መሬት ብዙኀ ወውእተ ጊዜ ሠረፀ።
                    ******     
፭፡ ብዙ መሬት ከሌለው ከጭንጫ ላይ የወደቀ ፈጥኖ የበቀለ አለ።
እስመ አልቦ ዕመቅ ለመሬቱ።
ለመሬቱ ጥልቅነት የለውምና።
                    ******     
፮፡ ወሶበ ሰረቀ ፀሐይ መጽለወ ወየብሰ።
                    ******     
፮፡ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ፀውልጎ ደረቀ።
አስመ አልቦ ዕመቅ ለመሬቱ
ለመሬቱ ጥልቅነት የለውምና
                    ******     
፯፡ ወቦ ዘወድቀ ውስተ ሦክ።
                    ******     
፯፡ ከእሾህ መካከል የወደቀ ዘር አለ።
ወበቊሎ ሦክ ጠበቆ ወሐነቆ
በበቀለ ጊዜ እንዳያድግ እሾህ አጫንቆ አስቀረው።
                    ******     
፰፡ ወቦ ዘወድቀ ውስተ ምድር ሠናይ።
                    ******     
፰፡ ከበጎ ምድር የወደቀ ዘር አለ።
ወወሀበ ፍሬ።
ፍሬ ያቀረጸ ።
ቦ ዘ፻።
መቶ ቅንጣት።
ወቦ ዘ፷።
ስሳ ቅንጣት።
ወቦ ዘ፴።
ሠላሳ ቅንጣት ያቀረጸ አለ።
አንድም ናሁ ወፅአ ብለህ መልስ ጌታ ሊያስተምር ሰው ሆነ  ፀአተ ይሠሚ ሥጋዌሁ እንዲል። ከዚህ ፀአተ አለ ሐዋርያው በአተ ይለዋል።
ወእንዘ ይዘርዕ
ሰው ሁኖ ሲያስተምር በልበ ዝንጉዓን ያደረ ትምህርት አለ
ወመጽኡ አዕዋፍ
አጋንንት ያሳቱት አዕዋፍ አላቸው ለማሳት ይፈጥናሉና። ኢትሕሚ ሰብአ ውስተ ቤትከ እስመ ዖፈ ሰማይ ያወፅኦ ለነገርከ እንዲል። በልዕዎ ማለቱ የበሉት ደስ እንዲያሰኝ ሲያስቱ ደስ ይላቸዋልና
ወቦ ዘወድቀ ዲበ ኰኵሕ።
ፈጥኖ አወቅሁ ተረዳሁ ከሚል ስፍሐ አእምሮ ከሌለው ልቡና ያደረ ትምህርት አለ
እስመ አልቦ።
ስፍሐ አእምሮ ማለት ጥልቅ ዕውቀት የለውምና።
ወሶበ ሠረቀ ፀሐይ
መከራ በመጣበት ጊዜ ፈጥኖ የካደ
እስመ አልቦ።
ስፍሐ አእምሮ የለውምና።
ወቦ ዘወድቀ ውስተ ሦክ
ከባለጸጎች ልቡና ያደረ ትምህርት አለ
ወበቊሎ
ተምሮ አውቆ ሥራ እሠራለሁ ባለ ጊዜ አምስት ግብራት ያስቀሩበት ብዕል ሰፋጢት (ማለት አታላይ)፤ ብዕል ሐልዮ መንበርት (ማለት ቦታ ማሰብ፣ ትካዘ ዓለም፣ ፍቅረ ብእሲት፣ ፍቅረ ውሉድ) ናቸው፡፡
ወቦ ዘወድቀ ውስተ ምድር ሠናይት
በበጎ ልቡና ያደረ ትምህርት አለ።
ቦ ዘ፻ ወቦ ዘ፷ ወቦ ዘ፴
ሥራውን በሦስት ወገን ይሠሩታል በወጣኒነት በማዕከላዊነት በፍጹምነት ክብሩንም በዚያው ይወርሱታልና። ባለመቶ ባለ ስሳ ባለ ሠላሳ አለ።
አንድም ባለ መቶ ሰማዕታት ባለ ስሳ መነኮሳት  ባለ ሠላሳ በሕግ የጸኑ ሰብአ ዓለም ናቸው።
አንድም ሁሉም በሁሉ አሉ ብሎ ከሰማዕታት እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ቂርቆስ እንደ ፋሲለደስ ያሉት ባለመቶ፤ ከነዚያ ዝቅ ያሉት ባለስሳ፣ ከነዚያ ዝቅ ያሉት ባለ ሠላሳ ናቸው። ከመነኮሳትም እንደ አቡነ ዕንጦንስ እንደ መቃርስ እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እንደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያሉት ባለ መቶ፣ ከነዚያ ዝቅ ያሉት ባለ ስሳ ከነዚያ ዝቅ ያሉት ባለ ሠላሳ ናቸው፡፡
ከሰብአ ዓለምም እንደ ኢዮብ እንደ አብርሃም ያሉት ባለመቶ፤ ከነዚያ ዝቅ ያሉት ባለ ስሳ ፤ ከነዚያ ዝቅ ያሉት ባለ ሠላሳ ናቸው።
አንድም ቦ ዘወድቀ ውስተ ፍኖት።
ፍኖት የተባለ መንግሥተ ሰማያት ድሉት ለጻድቃን። ገሃነመ እሳት ድሉት በኃጥአን እንደሆነች ተምሮ አውቆ ሥራ እሠራለሁ ሲል አጋንንት ያስቀሩበት ነው።
ወቦ ዘወድቀ ዲበ ኰኵሕ
ኰኵሕ የተባለ ካልተማሩ አያውቁ ካላወቁ አይጸድቁ እንዲሉ እማራለሁ አውቃለሁ ሲል ሳይማር ሳያውቅ የቀረ ነው
ወቦ ዘወድቀ ውስተ ሦክ።
ሦክ የተባለ ትሩፋት አፍአዊን ሠርቶ ትሩፋት ስውርት የቀረችበት ነው
ወቦ ዘወድቀ ውስተ ምድር ሠናይት
ምድር ሠናይት ያለው ሁሉንም የሠራ ነው
ቦ ዘምእት ወቦ ዘስሳ ወቦ ዘሠላሳ።
ይህም ወሥርዓተ ፍድፋዴ ዓለማውያን አስተጋብአ ለኀበ ሠለስቱ ክፍል እንዲል፤ ሰማዕታትን በበጎ ልጅ መነኮሳትን በበጎ ሎሌ ሕጋውያንን በበጎ ባሪያ መስሎ ይናገራል። በጎ ልጅ አባቱ ሳለ ከአባቱ ጋራ ይወጣል ይወርዳል። አባቱ ከሞተ በኋላ በአባቱ ርስት ዘምቶ ይሞታል፤ የሰማዕታት መደበኞች ሐዋርያት ናቸው በጎ ልጅ ከአባቱ ጋራ እንዲወጣ እንዲወርድ ሐዋርያትም ጌታ ባለ ከጌታ ጋራ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ሲወጡ ሲወርዱ ኑረዋል። አባቱ ከሞተ በኋላ በአባቱ ርስት ዘምቶ እንዲሞት ጌታ ከሞተ በኋላ ወንጌልን ሲያስተምሩ በሰማዕትነት ሙተዋልና። በጎ ሎሌም ጌታው ሸማ አጥበህ ማገር ቈርጠህ ና ያለው እንደሆነ ጌታዬ አይችልም ብሎ ነው እንጂ ለወጥ የሚሆን ዓሣ፤ የሚማገርበት ልጥ ይዤ ብሄድ ይከፋልን ብሎ ልብሱን አጥቦ ዓሣውን ይዞ ማገሩን ቈርጦ ልጡን ጨምሮ ይዞ ይሄዳል። መነኮሳትም ሚስት አግብታችሁ አስራት በኵራት ቀዳምያት አውጥታችሁ እንግዳ ተቀብላችሁ ሥጋውን ደሙን በሚገባ ተቀብላችሁ ኑሩ ቢላቸው። ባሕርያቸው ደካማ ነው አይቻላቸውም ብሎ ነው እንጂ ከሕገ ሥጋ ሕገ ነፍስ ከሕገ እንስሳ ሕገ መላእክት እንዲበልጥ ታውቆ የለም ብለው ከሴት ርቀው ንጽሕ ጠብቀው ይኖራሉና፣ በጎ ባሪያ የቆመውን ቀረጥ የተኛውን ፍለጥ ቢሉት ያዘዙትን ሁሉ ያደርጋል። ሕጋውያንም ባዘዛቸው ትእዛዝ በሠራላቸው ሥርዓት ጸንተው ይኖራሉና። ወእንዘ ዝሩት ይእቲ ማዕከለ አድባር ወአውግር ወቈላተ ገዳም ተጋቢኣ ትከውን አሐተ ጵርስፎራ እንዲል። መቶው፤ ስሳው፣ ሠላሳው ቅንጣት ተሰብስቦ አንድ ኅብስት እንዲሆን ፤ ሰማዕታትም መነኮሳትም ሕጋውያንም በግዕዝ ርትዕት አንድ ናቸው።
                    ******     
፱፡ ዘቦ ዕዝን ሰሚዓ ለይስማዕ
                    ******     
፱፡ ሰሚ ጆሮ ያለው ደስማ ማለት ፍኖት የተባለ በቁሙ ፍኖት እንዳይደለ ልበ ዝንጉዓን እንደሆነ ኰኵሕ የተባለ በቁሙ ኰኵሕ እንዳይደለ ስፍሐ አእምሮ የሌለው ልቡና እንደሆነ። ሦክ የተባለ በቁሙ ሦክ እንዳይደለ ብዕል ሰፋጢት ሐልዮ መንበርት ያስቀሩበት እንደሆነ ዕዝነ ልቡና ያለው ያስተውል።
                    ******     
፲፡ ወቀሪቦሙ አርዳኢሁ ይቤልዎ በእንተ ምንት በምሳሌ ትትናገሮሙ ለሕዝብ
፲፡ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው ለሕዝቡ በምሳሌ ስለምን ታስተምራቸዋለህ አሉት።
                    ******     
   ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
30/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment