Thursday, May 2, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 79

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
በከመ ተፈነዉ ሐዋርያት።
ምዕራፍ ፲፩።
                    ******   
፲፫፡ እስመ ኵሎሙ ነቢያትኒ ወኦሪት እስከ ዮሐንስ ተነበዩ
                    ******     
፲፫፡ ኦሪትም ነቢያትም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ አስተምረዋልና
                    ******
፲፬፡ ወእመሰ ትፈቅዱ ትትወከፍዎ ዝ ውእቱ ኤልያስ ዘሀለዎ ይምጻእ።
                    ******     
፲፬፡ ናሁ አነ እፌኑ መልአኪየ ተብሎ የተነገረ ለኤልያስ ነው እንጂ መቼ ለዮሐንስ ነው እንዲሉት አውቆ አመጣ እንዲሉትም አውቆ ማምጣት ልማድ ነው  እንዳለፈው በል፡፡ ምዕራፍ ፭ ቍ ፲፯። ሚል ፬፥፭፡፡ ልትቀበሉትስ ክወደዳችሁ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ዮሐንስ ነው።
(ሐተታ) ዮሐንስ ኤልያስን በምን ይመስለዋል ቢሉ ኤልያስን ፀጓር ይለዋል ዮሐንስንም ዘልብሱ ፀጕረ ገመል ይለዋልና። ኤልያስን ጸዋሚ ተሐራሚ ዝጉሐዊ ባሕታዊ ይለዋል ዮሐንስንም ጸዋሚ ተሐራሚ ዝጉሐዊ ባሕታዊ ይለዋልና፡፡ ኤልያስ መገሥፀ አክዓብ ወኤልዛቤል እንደሆነ ዮሐንስም መገሥፀ ሄርድስ ወሄሮድያዳ ነውና። ኤልያስ ለደኃራዊ ምጽአቱ መንፈቅ ተቀድሞ እንዲያስተምር። ዮሐንስም ለቀዳማዊ ምጽአቱ መንፈቅ ተቀድሞ አስተምሯልና።
                    ******     
፲፭፡ ዘቦ ዕዝን ሰሚዓ ለይስማዕ
                    ******     
፲፭፡ ኤልያስ የተባለ በቁሙ ኤልያስ እንዳይደለ ዮሐንስ እንደ ሆነ ዕዝነ ልቡና ያለው ያስተውል።
                    ******     
፲፮፡ በመኑ አስተማስሎሙ ለሰብአ ዛቲ ትውልድ።
                    ******     
፲፮፡ ቤተ አይሁድን በምን እመስላታለሁ ምሳሌ ቢያጣላት፡፡ አንድም ይመስሉ ደቂቀ ለማለት።
ይመስሉ ደቂቀ አለ ይነብሩ ውስተ ምሥያጥ።
ከአደባባይ የተቀመጡን።
ወይጼውዑ ቢጾሙ
ባልንጀሮቻቸው የሚጠሯቸውን።
                    ******     
፲፯፡ ወይቤልዎሙ አንዘርነ ለክሙ ወኢዘፈንክሙ።
                    ******     
፲፯፡ የዘፈን ዜማ ቀነቀንላችሁ አልተቀበላችሁንም
አስቆቀውነሂ ለክሙ ወኢበከይክሙ፡፡
የልቅሶ ዜማ ቀነቀንላችሁ አልተቀበላችሁንም የሚሉ ልጆችን ይመስላሉ።
                    ******     
፲፰፡ እስመ መጽአ ዮሐንስ እንዘ ኢይበልዕ ወኢይሰቲ ወይቤልዎ ጋኔን ቦቱ።
                    ******     
፲፰፡ ዮሐንስ ሳይበላ ሳይጠጣ ቢያስተምር የማያስበላ የማያስጠጣ ጋኔን አድሮበታል ብላችሁታልና አስቆቀውነሂ ላለው።
                    ******     
፲፱፡ ወመጽአ ወልደ እጓለ እመሕያው እንዘ ይበልዕ ወይሰቲ ወይቤልዎ ነዋ ብእሲ በላዒ ወሰታዬ ወይን አርከ መጸብሐን ወሐጥአን ።
                    ******     
፲፱፡ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ እየበላ እየጠጣ ቢያስተምር መብል መጠጥ ወጻጅ የኃጥአን የመጸብሐን ወዳጅ ብላችሁታልና፡፡ አንዘርነ ለክሙ ላለው።
(ሐተታ) ሕጻናቱ አራቱ ፆታ ናቸው አንዱ ፆታ የዘፈን ዜማ ቀነቀኑ አንዱ ፆታ ተቀበሉ አንዱ ፆታ ዝም አሉ በዳር ያሉ አንዱ ፆታ እኒያ ሲቀበሉ አኒህ ዝም ማለታቸው ደስ ባይላቸው እንጅ ነው ብለው የልቅሶ ዜማ ቀነቀኑ የተቀበሉ ተቀበሉ ያልተቀበሉ ዝም አሉ። የዘፈን ዜማ የቀነቀኑ አርድእተ ክርስቶስ የተቀበሉ ኃጥአን መጸብሐን ያልተቀበሉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን የልቅሶ ዜማ የቀነቀኑ አርድእተ ዮሐንስ፡፡
አንድም ሦስቱ ፆታ ናቸው አንዱ ፆታ የዘፈን ዜማ ቀነቀኑ አንዱ ፆታ ተቀበሉ አንዱ ፆታ ዝም አሉ እኒህ ሲቀበሉ እኒያ ዝም ማለታቸው ደስ ባይላቸው እንጅ ነው ብለው የዘፈን ዜማ የቀነቀኑት መልሰው የልቅሶ ዜማ ቀንቅነዋል የተቀበሉ ተቀበሉ አንቀበልም ያሉ ዝም አሉ የተቀበሉ ሐጥአን መጸብሐን አንቀበልም ያሉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን የጌታን ትምህርት በዘፈን የዮሐንስን በልቅሶ መስሎ ተናገረ ስለምን ቢሉ በጌታ ትምህርት ታምራት ተደርጎበታል ልጅነት ተገኝቶበታል። በዮሐንስ ትምህርት ግን ልጅነት አልተገኘበትም ታምራት አልተደረገበትምና ምነው ያውስ ቢሆን የዮሐንስ ቀድሞ የጌታ አይከተልም ቃል ሳለ የባሪያ ቃል አናስቀድምም ብለው በብያኔ አስቀድመውታል ነገር ግን ሁሉም አንድ ነው። ዮሐንስ ሳይበላ ሳይጠጣ ማስተማሩ ታምራት መስሏቸው ይሳቡ እንደሆነ ብሎ። ጌታ እየበላ እየጠጣ ማስተማሩ በፍቅር ለመሳብ ነው። ከዚያም ቢያጠምዱ ከዚያም ቢያጠምዱ ለመያዝ እንደሆነ።
ወጸድቀት ጥበብ እምደቂቃ ወእምግባራ።
ጥበብ ወልድ ከሥራዋ ከልጆቹዋ የተነሣ ከበረች። ጸድቀት እምኔየ ትዕማር እንዲል አንድም ደቂቃ በምግባራ በሥራዋ ልጆቹዋን ረታች ጸድቀተኒ ትዕማር እንዲል አንድም ጥበብ ወልድ ከልጆቹዋ ይልቅ በሥራዋ ከበረች።
                    ******     
ዘከመ ኄሶን
ለአህጉር ኢነሳሕያት ።
                    ******     
፳፡ ወእምዝ አኀዘ እግዚእ ኢየሱስ ይኂሶን ለአህጉር እለ በውስቴቶን ገብረ ኃይለ ብዙኃ
፳፡ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ደጋግ ታምራት ያደረገባቸውን ምኵራባት ይነቅፋቸው ጀመር።
                         ******     
   ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
24/08/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment