Sunday, March 31, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 51


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፮።
                  ******
፱፡ አንትሙሰ ሶበ ትጼልዩ ከመዝ በሉ። ሉቃ ፲፩፥፪፡፡
                  ******
፱፡ እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ።
(ሐተታ) አብዝታችሁ አትጸልዩ ብሎ ነበርና አጭር ጸሎት፡፡ ጩኸችሁ አትጸልዩ ብሎ ነበርና የሕሊና ጸሎት፡፡ ቋሚ ለጓሚ ገረድ ደንገጽር ሲቆሙ ሲቀመጡ ሲተኙ ሲነሱ የሚጸልዩት አጭር ጸሎት ሠራልን።
አቡነ ዘበሰማያት።
በሰማይ ያለህ አባታችን። አቡነ በሉኝ አለ አምላክነ እግዚእነ መምህርነ በሉኝ አላለም። ቀድሞ ነቢያት ከግብርናተ ዲያብሎስ እንዳልወጡ ሲያጠይቁ አምላክነ እያሉ ይጸልዩ ነበር። እኛ ግን ከግብርናተ ዲያብሎስ እንዳወጣን ሲያጠይቅ አቡነ በሉኝ አለ፡፡ እግዚእነ መምህርነ በሉኝ አላለም፡፡ ጌታ ሎሌውን መምህር ደቀ መዝሙሩን ቢወደው ያበላዋል ያጠጣዋል የልቡናውንም ምሥጢር ያጫውተዋል እንጂ። ርስቱን አያወርሰውም። ርስቱን ግን የሚያወርስ ለልጁ ነው። እሱ ግን የማታልፍ ርስቱን መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናልና፡፡
አንድም ወበከመ ይምህር አብ ውሉዶ ከማሁ ይምህሮሙ እግዚአብሔር ለአለ ይፈርህዎ እንዲል አባት ለልጁ እንዲራራ ይራራልናልና። ዘበሰማያት አለ ከምድራዊ አባት ሲለይ። ምድራዊ አባት ሲወልድ በግዘፍ ሲያሳድግ በግዘፍ ነው፡፡ ኋላም ኃላፊ ርስቱን ያወርሰዋል ኋላ ሞትን ያስከትልበታል። እሱ ግን ሲወልደን በረቂቅ ሲያሳድገንም በረቂቅ ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናል ኋላም ሐይዉ ከመ መላእክትን ያስከትልልናልና፡፡
አንድም ጌታ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን ስለ ልዕልናው በሰማይ አለ ይባላልና። ዘበአንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት እንዲል፡፡
አንድም ጸሎቱ በሰቂለ ሕሊና ይሁን ሲል እንዲህ አለ።
ይትቀደስ ስምከ።
ስመ ወላዲ ስመ ተወላዲ ስመ ሠራዊ ይለይልን በሉኝ።
አንድም ስምየሰ መሐሪ ወመስተሣህል ያልኸው ይጽናልን በሉኝ።
አንድም መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ስምህን አመስግነው ቅድስናህን ተሳትፈው እንደዲኖሩ። እኛም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለን አመስግነንሀ ቅድስናህን ተሳትፈን እንድንኖር አድርገን በሉኝ አለ።
                  ******
፲፡ ትምጻእ መንግሥትከ፡፡
                  ******
፲፡ መንግሥተ ሰማይ ትምጻልን በሉኝ። ትምጻእ ማለቱ ግን ከወዲያ ያለች ከወዲህ የሌለች ሁና ከወዲያ ወዲህ የምትመጣ፤ ከወዲህ ያለች ከወዲያ የሌለች ሁና ከወዲህ ወዲያ የምትሄድ ሁና አይደለም፡፡ ትገለጽልን በሉኝ ሲል ነው እንጂ። አኮ እምካልእ መካን ዘይመጽእ ለአስተርእዮ ኀቤሆሙ አላ ሀሉ ኅቡዓ ወምሉዓ ማዕከሌሆሙ ወውሣጤሆሙ እንዲል።
አንድም ልጅነት ትሰጠን በሉኝ ሲል ነው። መተርጉምኒ ሰመያ ለትምጻእ መንግሥትከ ሱታፌ መንፈስ እንዲል።
ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ።
መላእክት በሰማይ ሊያመሰግኑህ ፈቃድህ እንደሆነ እኛም እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን በሉኝ።
አንድም ኋላ ሙተን ተነሥተን ልናመሠግንህ ፈቃድህ እንደሆነ ዛሬም በሕ
ይወተ ሥጋ ሳለን እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን በሉኝ። ከማሁ ማንሻ፡፡
አንድም መላእክት በሰማይ አመስግነውህ ያው ምስጋናው ምግብ ሆኑዋቸው እንዲኖር።
                  ******
፲፩፡ ከማሁ በምድር ሲሳየነ ዘለለዕለትነ ሀበነ ዮም። ዘፍጥ ፳፰፥፳፡፡ ምሳ ፴፥፰፡፡ ፩፡ጢሞ ፮፥፰፡፡ ማር ይስ ፲፪ ም።
                  ******
፲፩፡ ለእኛም በዚህ ዓለም ሳለን የዕለት ምግባችንን ስጠን በሉኝ። በዚህም መጻሕፍት ተባብረውበታል። ያዕቆብ በኦሪት እምከመ ረከብኩ እክለ ዘእበልዕ ወልብሰ ዘእትኤረዝ ይከውነኒ እግዚአብሔር አምላኪየ ብሏል። ጳውሎስም እምከመ ረከብነ ሲሳየነ ወአራዘነ የአክለነ ብሏል። ሠለስቱ ምዕትም በሕንፃ መነኮሳት ኢትኩን መፍቀሬ ወርቅ ወብሩር ዘእንበለ በአምጣን ዘየአክል ለሕይወትከ ለሲሳይከ ወለአራዝከ በአቅም ብለዋል። ማር ይስሐቅም እመቦ ዘተርፈ እምፍቅደ ዕለትከ ሀቦ ለነዳይ ብሏል። ለፍጹማን የሆነ እንደሆነ በቁሙ የዕለት ምግብ ነው። ለሰብአ ዓለም ግን ያመት ልብስ ያመት ምግብ ዘር አስቀርቶ የቀረውን መስጠት ነው።
አንድም ሥጋህን ደምህን ንስሐን ትምርትን ዓስበ ጸሎታችንን ስጠን ባሉኝ።
                  ******
፲፪፡ ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንሕነኒ ንኅድግ ለዘአበሰ ለነ።
                  ******
፲፪፡ እኛም የበደለንን ይቅር እንል ዘንድ በደላችንን ይቅር በለን በሉኝ። ይህማ ማስተላለክ አይሆንም ቢሉ አይሆንም ሰው ይቅር ማለቱ እኔንም እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል ብሎ ነውና።
አንድም ከአኃው አንዱ ተነሥቶ አብሑኒ ከመ እወስከ አሐደ ቃለ ላዕለ አቡነ ዘበሰማያት አላቸው። አባሕናከ ንብብ አሉት፡፡ ረስየነ ያለበት ነው ብሏል፡፡ ይቅር ማለቱ ቅሉ ያለአንተ ፈቃድ አይሆንም ሲል፡፡
                  ******
፲፫፡ ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት፡፡
                  ******
፲፫፡ አቤቱ ወደ ኃጠአት ወደ ክህደት ወደ መከራ ወደ ገሃነም አታግባን በሉኝ።
አላ አድኅነነ ወባልሃነ አምኵሉ አኩይ።
ከኃጢአት ከክህደት ከመከራ ከገሃነም አድነን እንጂ።
እስመ ዚአከ ይእቲ መንግሥት መንግሥተ ሰማይ ገንዘብህ ናትና፡፡
ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም።
ከሃሊነት ጌትነት ለዘላለሙ ገንዘብህ ናትና።
አሜን፡፡
በእውነት።
                  ******
፲፬፡ እስመ ለእመ ኃደግሙ ለሰብእ አበሳሆሙ የኃድግ ለክሙኒ አበሳክሙ አቡክሙ ሰማያዊ። ሲራክ ፳፰፥፫። ማቴ ፲፰፥፴፭፡፡ ማር ፲፩፥፳፭፡፡
፲፬፡ እናንተ ይቅር ብትሉ ሰማያዊ አባታችሁ የናንተንም ኃጢአት ይቅር ይላችኋልና ይቅር ይላችሁ ዘንድ ይቅር በሉ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
23/07/2011 ዓ.ም

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 50

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፮።
                  ******
፬፡ ከመ በኅቡዕ ይኩን ምጽዋትከ፡፡
                   ******
፬፡ ምጽዋትህ በስውር ይሆን ዘንድ።
ወአቡከ ዘይሬእየከ በኅቡዕ የአሥየከ ክሡተ።
ስትመጸውት ተሠውሮ የሚያይህ፤ አንድም ተሠውረህ ስትመጸውት የሚያይህ ሰማያዊ አባትህ ጉባኤውንስ ከሻኸው በጻድቃን በሰማዕታት በመላእክት በኃጥአን በአጋንንት ፊት ገልጾ ዋጋህን ይሰጥሃል።
                  ******
፭፡ ወሶበሂ ትጼልዩ ኢትኩኑ ከመ አሕዛብ።
                  ******
፭፡ ግብዞች አትሁኑ።
እስመ ያፈቅሩ በመኳርብት በውስተ መዓዝነ መራህብት ቀዊመ ወጸልዮ ከመ ያስተርእዩ ለዓይነ ሰብእ።
ሰው ይይልን ሰው ይስማልን ብለው በምኩራብ ባደባባይ ቁሞ መጸለይን ይወዳሉና፡፡ በምኩራብማ መጸለይ እንዲገባ ለማጠየቅ ሙሴን ወንድምህ አሮን ድምፅ ያለው ልብስ ለብሶ ያን እያሰማ ገብቶ ይጸልይ ሕዝቡም እሱን አብነት አድርገው ገብተው ይጸልዩ ብሎት የለምን ቢሉ ከዚያው መካነ ጸሎት መካነ ትምሕርት መካነ ተግሣፅ አለ። እኒህ ግን መካነ ጸሎቱን ትተው በመካነ ተግሣፅ ቁመው ይታያሉና። አማን እብለክሙ ኃጕሉ ዕሤቶሙ።
እንዳለፈው በል፡፡
                  ******
፮፡ ወአንተሰ ሶበ ትጼሊ ባዕ ቢተከ ወእፁ ኆኅተከ ወጸሊ ለአቡከ።
                  ******
፮፡ አንተ ግን በምትጸልይበት ጊዜ ከቤትህ ገብተህ ደጅህን ዘግተህ ወደ ሰማያዊ አባትህ ጸልይ፡፡
አንድም በምትጸልይበት ጊዜ ሕዋሳትሕን ሰብስበህ በሰቂለ ሕሊና በነቂሐ ልቡና ሁነህ ወደ ሰማያዊ አባትህ ወደ እግዚአብሔር አመልክት።
ወአቡከ ዘይሬእየክ በኅቡዕ የዓሥየከ ክሡተ።
ተሰውረህ ስትጸልይ የሚያይህ ሰማያዊ አባትህ ዋጋህን ይሰጥሃል፡፡
                  ******
፯፡ ወእንዘ ትጼልዩ ኢትዘንግዑ ከመ አሕዛብ፡፡
                  ******
፯፡ ስትጸልዩ እንደ አሕዛብ አብዝታችሁ አትጸልዩ። ግብር ዘአልቦ ምጣኔ ገዓር ውእቱ ወለገዓርኒ ይተልዎ ዝንጋኤ እንዲል።
አንድም ጨኸችሁ አትጸልዩ። ኢትክላህ በሕቁ አላ ዘምር በመጠን ከመ ኢይዘንግዑ አኃው እንዲል።
እስመ ይመስሎሙ በአብዝኆ ንባቦሙ ዘይስምዖሙ።
አብዝተው ጩኸው በመጸለያቸው የሚሰማቸው ይመስላቸዋልና።
                  ******
፰፡ ኢትትመሰልዎሙኪ።
                  ******
፰፡ አብነት አታድርጓቸው።
እስመ የአምር አቡክሙ ሰማያዊ መፍቅደክሙ ዘእንበለ ትስአልዎ።
እናንተስ አብዝታችሁ ጩኸችሁ ሳትለምኑት ሰማያዊ አባታችሁ የምትሹትን አውቆ ያደርግላችኋል።
                  ******
፱፡ አንትሙሰ ሶበ ትጼልዩ ከመዝ በሉ። ሉቃ ፲፩፥፪፡፡
፱፡ እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ።
                   ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
22/07/2011 ዓ.ም

Saturday, March 30, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 49



                ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፮።
                  ******
በእንተ ጾም ወጸሎት ወምጽዋት፡፡
፩፡ ወባሕቱ ዑቁ ምጽዋተክሙ ኢትግበሩ ለዓይነ ሰብእ ከመ ያስተርእዩ ሎሙ።
                  ******
፩፡ ባሕቱን የሚጽፍም የማይጽፍም አለ። ምጽዋታችሁን ሰው ይይልን ብላችሁ እንዳታደርጉ ዕወቁ።
ወእመ አኮሰ ዓስብ አልብክሙ በኀበ አቡክሙ ዘበሰማያት፡፡ ያለዚያ ግን በሰማይ አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።
፪፡ ወሶበሂ ትገብሩ ምጽዋተክሙ ኢትንፍሑ ቀርነ በቅድሜክሙ በከመ ይገብሩ መደልዋን በመራኅብት ወበአስኳት።
                  ******
፪፡ በምትመጸውቱበትም ጊዜ ግብዞች ሰው ሰብስበው ቀን ቀጥረው በተመሳቀለ ጎዳና ባደባባይ እንዲያደርጉት ቀን ቀጥራችሁ አዋጅ ነግራችሁ አታድርጉት።
አንድም ውዳሴ ከንቱ ሽታችሁ አታድርጉት። አንድ ባለጸጋ አፈ ወርቅን እንደጠየቀው፡፡ ይህን ሲያስተምር አንድ ባለጸጋ መጥቶ ምጽዋት መመጽወት እወዳለሁ። ውዳሴ ከንቱም እወዳለሁ አለው። ውዳሴ ከንቱውን ትተህ መጽውት አለው። አይሆንም ሁሉንም እወዳለሁ ይህ ከቀረ ምጽዋቱም ይቅር አለው። እንኪያስ አትተው መጽውት ሰው ዘር ይዘራል ባይጠብቀው የእሽት ያህል ያጣለታልን አንተም የዚያን ያህል ጥቂት ዋጋ አታጣም ስጥ ብሎታል።
ከመ ይትአኰቱ እምኀበ ሰብእ፤ ሰው ያይላቸው ይሰማላቸው ዘንድ።
አማን እብለክሙ ኃጒሉ ዕሤቶሙ።
ኃጒሉ ቢል የወዲያኛውን ዋጋቸውን አጡ ነሥኡ ይላል ውዳሴ ከንቱውን አገኙ ብዬ እንዳገኙ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡
                  ******
፫፡ ወአንተሰ ሶበ ትገብር ምጽዋተከ ኢታእምር ፀጋምከ ዘትገብር የማንከ።
                  ******
፫፡ አንተ ግን በምትመጸውትበት ጊዜ ቀኝ እጅህ የምትሠራውን ግራ እጅህ አትወቀው። ማለት በቀኝ እጅህ የያዝኸውን በግራ እጅህ አትያዘው። ግራ ደካማ ነው ጥቂቱን ብዙ ያስመስለዋል ልክፈልለት ያሰኛልና። ቀኝ ኃያል ነው ብዙውን ጥቂት ያስመስላል፤ ከዚህ ምን እከፍልለታለሁ ልስጠው ያሰኛልና።
አንድም ሚስትህ አትወቅብህ ሲለው ነው ፀጋም አላት የባልና የሚስት ከብት ሎሚ ከሁለት እያለች ታዳክማለችና እንዳታዳክመው ከሚስት የሚሠወር ምን አለ ቢሉ ቅንነቱማ ካለ ገንዘቡ ሁሉ ያለ በእሱ እጅ አይደለምን ከዚያው ይስጥ። ይህማ ስርቆት አይሆንበትም ቢሉ ሰጥቶ ይንገራት። አይሆንም ብትለውሳ ቢሉ ይለያዩ ጥንቱን መጋባታቸው ሰጥተው መጽውተው ሊጸድቁ ነውና።
አንድም ልጆችህ አይወቁብህ ሲል ነው። ፀጋም አላቸው ያባታችን የቁም ወራሽ የሙት አልቃሽ እያሉ ያዳክማሉና እንዳያዳክሙት።
አንድም ቤተሰቦችህ አይወቁብህ፤ ፀጋም አላቸው የጌታችን ወርቁ ለዝና ልብሱ ለእርዝና እህሉ ለቀጠና እያሉ ያዳክማሉና አንዳ ያዳክሙት።
                  ******
፬፡ ከመ በኅቡዕ ይኩን ምጽዋትከ፡፡
፬፡ ምጽዋትህ በስውር ይሆን ዘንድ።
                   ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
21/07/2011 ዓ.ም

Thursday, March 28, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 48


                 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፭።
                  ******
፵፪፡ ወለኵሉ ዘሰአለከ ሀቦ። ዘዳ ፲፭፥፯-፰፡፡
                  ******
፵፪፡ ለለመነህ ሁሉ ስጠው።
ወለዘይፈድቅ ይትለቃሕ እምኔከ ኢትክልዖ። ካንተ ሊበደር የሚወደውን አትከልክለው፤ እንደ ዮሐንስ መሐሪ መጥተው አበድረን ሲሉት መክፈቻውን ሰጥቶ ወደዕቃ ቤቱ ይሰዳቸዋል የሚበቃቸውን ያህል ይዘው ይሔዳሉ። አምጥተው የሰጡት እንደሆነ ይቀበላል፡፡ ባይሰጡት ግድ የለውም ነበር።
                  ******
፵፫፡ ሰማዕክሙ ዘከመ ተብሀለ ለቀደምትክሙ አፍቅር ቢጸከ ወጽላእ ጸላኢከ፡፡ ዘሌ ፲፱፥፲፰፡፡
                  ******
፵፫፡ ከናንተ አስቀድሞ ለነበሩ ሰዎች ወዳጅህን ውደድ ጠላትህን ጥላ ያሏቸውን ሰምታችኋል። አፍቅር ቢጸከ ይሁን ጽላእ ጸላኢከ የሚል በኦሪት ወዴት አለ ቢሉ ባጸፋው ተናገረ፡፡ ወዳጅህን ውደድ ማለት ጠላትህን ጥላ ማለት ነውና።
አንድም ተጻረርዎሙ ለሜዶናውያን ኢትርስዖ ለአማሌቅ ያለውን ለውጦ አነበበው።
                  ******
፵፬፡ ወአንሰ እብለክሙ አፍቅሩ ጸላእተክሙ። ሉቃ ፮፥፳፯፡፡ ሮሜ ፲፪፥፴፡፡ ግብ፡ሐዋ ፯፥፶፱፡፡ ሉቃ ፳፫፥፴፬፡፡
                  ******
፵፬፡ እኔ ግን ጸላታችሁን ውደዱ እላችኋለሁ።
ወባርክዎሙ ለእለ ይሰድዱክሙ፡፡
ከሀገራችሁ አስወጥተው የሚሰዷችሁን መርቋቸው፡፡ ከቦታችሁ ከሀገራችሁ አያናውጣችሁ ከመንግሥተ ሰማያት አያውጣችሁ እያላችሁ።
ሠናየ ግበሩ ለእለ ይፃረሩክሙ፡፡
ለሚጣሏችሁ በጎ ሥራ ስሩላቸው።
ወጸልዩ በእንተ እለ ይትዔገሉክሙ።
ሥቃይ ለሚያጸኑባችሁ ጸልዩላቸው። እንዳንድ ምዕመን ዘመነ ዓላውያን ሁኖ አንድ ዓላዊ መከራ ያጸናበታል ጌታዬ ምረረ ገሃነምን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ባያውቅ እንጂ ነው። እንዲያውቅ አድርገው እያለ ይጸልይለታል ኋላ ዘመነ ዓላውያን አልፎ ዘመነ ክርስቲያን ሆነ፡፡ ያ ክርስቲያን ዛሬ ቢያገኘኝ እንደምን ያደርገኝ ነበር አለ። እሱስ ቀድሞም እንዲህ እያለ ይጸልይልህ ነበር አሉት። እኒህ ክርስቲያን ምግባራቸው የቀና መሆኑ ሃይማኖታቸው እንጂ የቀና ቢሆን ነው ብሎ ተመልሶ አምኖዋል ተጠምቋል።
                   ******
፵፭፡ ከመ ትኩኑ ውሉዶ ለአቡክሙ ዘበሰማያት።
                   ******
፵፭፡ የሰማያዊ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ማለት ሰማያዊ አባታችሁን ትመስሉ ዘንድ።
እስመ ውእቱ ያሠርቅ ፀሐየ ላዕለ ኄራን ወእኩያን።
ፀሐይን ለበጎዎችም ለክፉዎችም ያወጣልና።
ወያዘንም ዝናመ ላዕለ ጻድቃን ወኃጥአን፡፡
ዝናምን ለጻድቃንም ለኃጥአንም ያዘንማልና። ፀሐይ ሥጋው ደሙ ዝናም ወንጌል ነው፡፡ በእንቢተኝነታቸው ይቅርባቸው እንጂ ሥጋው ደሙ ወንጌል የተሠራ ለሁሉ ነውና።
                   ******
፵፮፡ ወእመሰ ዘአፍቀረክሙ ታፈቅሩ ምንትኑ ዕሤትክሙ።
                   ******
፵፮፡ የወደዳችሁንማ ብቻ ብትወዱ ዋጋችሁ ምንድነው።
አኮሁ መጸብሐንሂ ከማሁሰ ይገብሩ።
የወደዳቸውንማ ብቻ መውደድ አጣሮችስ ያደርጉት የለምን፡፡ ይህንስ አጣሮችም ያደርጉታል፡፡ ባንዱ አገር ያሉ አጣሮች ባንዱ አገር ካሉ ጋራ ይጠቃቀማሉና።
                   ******
፵፯፡  ወእመሂ ተአማኅክሙ ቢጸክሙ ባሕቲቶ ምንት እንከ ፍድፋዴ ገበርክሙ።
                   ******
፵፯፡ ወንድማችሁን ብቻ የምታከብሩ ከሆነ አብልጣችሁ ምን ትሩፋት ሠራችሁ። ምንት ፍድፋዴ ዘገበርክሙ፡፡ የሠራችሁት ትሩፋት ምንድነው።
አኮኑ አሕዛብኒ ከማሁሰ ይገብሩ፡፡
ወንድማቸውንማ ብቻ መወደድ አሕዛብስ ያደርጉት የለም ይህንስ አሕዛብም ያደር
ጉታል፡፡
                   ******
፵፰፡ አንትሙሰ ኩኑ ፍጹማነ ከመ አቡክሙ ሰማያዊ ፍጹም ውእቱ።
                   ******
፵፰፡ እናንተስ ሰማያዊ አባታችሁ ሁሉን አስተካክሎ በመውደድ ፍጹም እንደሆነ ሁሉን አስተከክላችሁ በመውደድ ፍጹማን ሁኑ።
                   ******
በእንተ ጾም ወጸሎት ወምጽዋት፡፡
ምዕራፍ ፮።
፩፡ ወባሕቱ ዑቁ ምጽዋተክሙ ኢትግበሩ ለዓይነ ሰብእ ከመ ያስተርእዩ ሎሙ።
፩፡ ባሕቱን የሚጽፍም የማይጽፍም አለ። ምጽዋታችሁን ሰው ይይልን ብላችሁ እንዳታደርጉ ዕወቁ።
                   ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
20/07/2011 ዓ.ም

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 47


 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፭።
                  ******
፴፬፡ ወአንሰ እብለክሙ ኢትምሐሉ ግሙራ።
                  ******
፴፬፡ እኔ ግን ፈጽማችሁ አትማሉ እላችኋለሁ።
ኢበሰማይ።
በሰማይም ሁኖ ከሰማይ የመጣ መቅሠፍት አይሳተን። ሰማይ ተንዶ ይጫነን እያሉ ይምላሉና፡፡
እስመ መንበሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ።
የእግዚአብሔር ዙፋኑ ነውና።
ወኢበምድር።
በምድርም ሁኖ ምድር ይክዳን ምድር ተከፍቶ ይዋጠን እያሉ ይምላሉና።
እስመ መከየደ እገሪሁ ይእቲ።
መመላለሻው ናትና።
                  ******
፴፭፡ ወኢበኢየሩሳሌም።
                  ******
፴፭፡ በኢየሩላሌምም ሁኖ ከበረከተ ርስት አያሳትፈን ከምድረ ርስት ያውጣን እያሉ ይምላሉና።
እስመ ሀገሩ ይእቲ ለንጉሥ ዓቢይ።
የደግ ንጉሥ የእግዚአብሔር የመመለኪያው አገር ናትና።
                  ******
፴፮፡ ወኢበርእስክሙ ኢትምሐሉ።
                  ******
፴፮፡ በራሳችሁም አትማሉ እንዲህ ያድርገን እያሉ ይምላሉና፡፡
ወኢበስእርተ ርእስክሙ።
በራሳችሁ ፀጉር አትማሉ። እንደ ራሳችን ፀጉር ያጥቁረን የራሳችንን ፀጉር ያህል አሞራ መጥቶ ይብላን እያሉ ይምላሉና።
እስመ ኢትክሉ አሐተ እምስእርተ ርእስክሙ ኢአፃዕድዎ ወኢአጽልሞ።
ከራሳችሁ ፀጉር አንዱን ነጩን ጥቁር፤ ጥሩቁን ነጭ ማድረግ አይቻላችሁም፡፡
                  ******
፴፯፡ ወይኩን ባሕቱ ነገርክሙ እመሂ እወ እወ ወእመሂ አልቦ አልቦ። ያዕ ፭፥፲፪፡፡
                  ******
፴፯፡ ነገራችሁ ዕውነቱን ዕውነት ሐሰቱን ሐሰት ይሁን እንጂ።
(ሐተታ) እወ ቢለው ያምንለታልን ቢሉ ይመንለት ወንጌል መሠራቷ ለሁሉ ነው እንጂ ለአንድ ብቻ ነውን ይላሉ ባያምንለትሳ ቢሉ መሐላውን በገንዘብ ያስቀረው፤ ገንዘብ ባይኖረውሳ ቢሉ ይማል። ዕዳው ባማዪው ይሆናል እንጂ በማዩ አይሆንምና፤ ወለእመ ኢተክህለ ይከውን ጌጋይ ላዕለ ዘአምሐሎ እንዲል። ሐዋርያ ጳውሎስ ወሙፃፁ ለቅሥት የሐልቅ በመሐላ ይላል። ከዚህ ጌታ ኢትመሐሉ አለ እንደምነው አይጣላም ቢሉ አይጣላም። ሐዋርያ የርትዑን ጌታ የትሩፋቱን ተናገረ፡፡
አንድም ሁሉም ርትዕ ነው። ሐዋርያ ዳኛ ፈርዶባችሁ ባለጋራ አውርዶላችሁ ማሉ ሲል ነው። ጌታ ዳኛ ሳይፈርድባችሁ አትማሉ ሲል ነውና፡፡
አንድም ኢበሰማይ ብለህ መልስ።
በመለኮት አትማሉ ባሕርዩ ነውና።
ወኢበምድር፡፡
በትስብእት አትማሉ ባሕርዩ ነው።
ወኢበኢየሩሳሌም።
በሥጋው በደሙ አትማሉ ባሕርዩ ነውና።
ወኢበርእስክሙ፡፡
በክርስቶስ አትማሉ ንሕነ አባል ወውእቱ ርእስ እንዲል፡፡
ወኢበስእርተ ርእስክሙ፡፡
በጻድቃን በሰማዕታት አትማሉ።
እስመ ኢትክሉ።
ከጸድቃን ከሰማዕታት አንዱን ኃጥዕ ጻድቅ፤ ጻድቁን ኃጥእ ማድረግ አይቻላችሁምና።
ወፈድፋደሰ እምእሉ እምእኩይ ውእቱ።
ከእወና ከአልቦ የወጣ ግን ከሰይጣን የተገኘ ነው።
                  ******
፴፰፡ ሰማዕክሙ ዘተብሀለ ዓይን ቤዛ ዓይን ወስን ቤዛ ስን። ዘፀ ፳፩፥፳፬። ዘሌ ፳፬፥፳። ዘዳ ፲፱፥፳፩፡፡
                  ******
፴፰፡ ዓይን ቢጠፋ ዓይን ይጥፋ ጥርስ ቢሰበር ጥርስ ይሰበር የተባለውን ሰምታችኋል። ቤዛነቱ ለሚመጣው ለሌላው ነው፡፡
                   ******
፴፱፡ ወአንሰ እብለክሙ ኢትትቃወምዎ ለእኩይ በእኩይ። ሉቃ ፮፥፳፱፡፡ ፩፡ ቆሮ ፮፥፯።
                   ******
፴፱፡ እኔ ግን ክፉውን ሰው በክፉ ነገር ድል አትንሱት ክፉውን ግብር በክፉ ግብር አታጥፉት እላችኋለሁ። ወለዘሂ ጸፍዓከ መልታሕቴከ እንተ የማን ሚጥ ሎቱ ካልዕታሂ። ቀኝ ፊትሕን ቢመታህ ግራ ፊትሕን አዙረህ ስጠው። ፈቃደ ሥጋህን ተው ቢልህ ፈቃደ ነፍስህን ተውለት።
                   ******
፵፡ ወለዘሂ ይፈቅድ ይተዓገልከ መልበሰከ ኅድግ ሎቱ ክዳነከሂ፡፡
                   ******
፵፡ መጐናጠፊያህን ሊቀማህ ቢወድ ቀሚስህን ደርብለት።
(ታሪክ) እንዳንድ ባሕታዊ ወምበዶች እራቸውን አጥቦ አብልቶ አጠጥቶ አሳደራቸው፡፡ ሌት ተነሥተው እሱን አስረው መብራት አብርተው ያለ ገንዘቡን ይዘው ሄዱ። ከሄዱ በኋላ መብራት አብርቶ ቢያይ ሁለት ድሪም የምታወጣ ጸምር አገኘ፡፡ ይህቺም ላንድ ጉዳይ ትሆናችኋለች ብሎ ተከትሎ ወስዶ ሰጣቸው፡፡ ይህ ሰው እንዲህ ማድረጉ ከዚህ የበለጠ ዋጋ እንዳለ ቢያውቅ እንጂ ነው ብለው ተመልሰው ንስሐ ገብተው የሚኖሩ ሁነዋል።
አንድም አፍአዊ ግብርህን ሊያስትውህ ቢወድ ውሣጣዊ ግብርህን ተውለት፡፡
                   ******
፵፩፡ ወለዘሂ አበጠከ አሐደ ምዕራፈ ሑር ምስሌሁ ፪ተ።
                   ******
፵፩፡ ትብትብ አሸክሞ አንድ ምዕራፍ ቢወስድህ ይህማ የግድ አይደለምን ብለህ የፈቃድ ሁለት ምዕራፍ ተሸክመህ ውሰድለት፡፡ መምህረ ንስሐህ አንድ ሱባዔ ቀኖና ቢሰጥህ ይህስ ተስማምቶኛል ጨምርልኝ ብለህ ከሱ አስፈቅደህ ሁለት ሱባዔ ጹም፡፡
                   ******
፵፪፡ ወለኵሉ ዘሰአለከ ሀቦ። ዘዳ ፲፭፥፯-፰፡፡
፵፪፡ ለለመነህ ሁሉ ስጠው።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
19/07/2011 ዓ.ም