Thursday, March 28, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 47


 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፭።
                  ******
፴፬፡ ወአንሰ እብለክሙ ኢትምሐሉ ግሙራ።
                  ******
፴፬፡ እኔ ግን ፈጽማችሁ አትማሉ እላችኋለሁ።
ኢበሰማይ።
በሰማይም ሁኖ ከሰማይ የመጣ መቅሠፍት አይሳተን። ሰማይ ተንዶ ይጫነን እያሉ ይምላሉና፡፡
እስመ መንበሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ።
የእግዚአብሔር ዙፋኑ ነውና።
ወኢበምድር።
በምድርም ሁኖ ምድር ይክዳን ምድር ተከፍቶ ይዋጠን እያሉ ይምላሉና።
እስመ መከየደ እገሪሁ ይእቲ።
መመላለሻው ናትና።
                  ******
፴፭፡ ወኢበኢየሩሳሌም።
                  ******
፴፭፡ በኢየሩላሌምም ሁኖ ከበረከተ ርስት አያሳትፈን ከምድረ ርስት ያውጣን እያሉ ይምላሉና።
እስመ ሀገሩ ይእቲ ለንጉሥ ዓቢይ።
የደግ ንጉሥ የእግዚአብሔር የመመለኪያው አገር ናትና።
                  ******
፴፮፡ ወኢበርእስክሙ ኢትምሐሉ።
                  ******
፴፮፡ በራሳችሁም አትማሉ እንዲህ ያድርገን እያሉ ይምላሉና፡፡
ወኢበስእርተ ርእስክሙ።
በራሳችሁ ፀጉር አትማሉ። እንደ ራሳችን ፀጉር ያጥቁረን የራሳችንን ፀጉር ያህል አሞራ መጥቶ ይብላን እያሉ ይምላሉና።
እስመ ኢትክሉ አሐተ እምስእርተ ርእስክሙ ኢአፃዕድዎ ወኢአጽልሞ።
ከራሳችሁ ፀጉር አንዱን ነጩን ጥቁር፤ ጥሩቁን ነጭ ማድረግ አይቻላችሁም፡፡
                  ******
፴፯፡ ወይኩን ባሕቱ ነገርክሙ እመሂ እወ እወ ወእመሂ አልቦ አልቦ። ያዕ ፭፥፲፪፡፡
                  ******
፴፯፡ ነገራችሁ ዕውነቱን ዕውነት ሐሰቱን ሐሰት ይሁን እንጂ።
(ሐተታ) እወ ቢለው ያምንለታልን ቢሉ ይመንለት ወንጌል መሠራቷ ለሁሉ ነው እንጂ ለአንድ ብቻ ነውን ይላሉ ባያምንለትሳ ቢሉ መሐላውን በገንዘብ ያስቀረው፤ ገንዘብ ባይኖረውሳ ቢሉ ይማል። ዕዳው ባማዪው ይሆናል እንጂ በማዩ አይሆንምና፤ ወለእመ ኢተክህለ ይከውን ጌጋይ ላዕለ ዘአምሐሎ እንዲል። ሐዋርያ ጳውሎስ ወሙፃፁ ለቅሥት የሐልቅ በመሐላ ይላል። ከዚህ ጌታ ኢትመሐሉ አለ እንደምነው አይጣላም ቢሉ አይጣላም። ሐዋርያ የርትዑን ጌታ የትሩፋቱን ተናገረ፡፡
አንድም ሁሉም ርትዕ ነው። ሐዋርያ ዳኛ ፈርዶባችሁ ባለጋራ አውርዶላችሁ ማሉ ሲል ነው። ጌታ ዳኛ ሳይፈርድባችሁ አትማሉ ሲል ነውና፡፡
አንድም ኢበሰማይ ብለህ መልስ።
በመለኮት አትማሉ ባሕርዩ ነውና።
ወኢበምድር፡፡
በትስብእት አትማሉ ባሕርዩ ነው።
ወኢበኢየሩሳሌም።
በሥጋው በደሙ አትማሉ ባሕርዩ ነውና።
ወኢበርእስክሙ፡፡
በክርስቶስ አትማሉ ንሕነ አባል ወውእቱ ርእስ እንዲል፡፡
ወኢበስእርተ ርእስክሙ፡፡
በጻድቃን በሰማዕታት አትማሉ።
እስመ ኢትክሉ።
ከጸድቃን ከሰማዕታት አንዱን ኃጥዕ ጻድቅ፤ ጻድቁን ኃጥእ ማድረግ አይቻላችሁምና።
ወፈድፋደሰ እምእሉ እምእኩይ ውእቱ።
ከእወና ከአልቦ የወጣ ግን ከሰይጣን የተገኘ ነው።
                  ******
፴፰፡ ሰማዕክሙ ዘተብሀለ ዓይን ቤዛ ዓይን ወስን ቤዛ ስን። ዘፀ ፳፩፥፳፬። ዘሌ ፳፬፥፳። ዘዳ ፲፱፥፳፩፡፡
                  ******
፴፰፡ ዓይን ቢጠፋ ዓይን ይጥፋ ጥርስ ቢሰበር ጥርስ ይሰበር የተባለውን ሰምታችኋል። ቤዛነቱ ለሚመጣው ለሌላው ነው፡፡
                   ******
፴፱፡ ወአንሰ እብለክሙ ኢትትቃወምዎ ለእኩይ በእኩይ። ሉቃ ፮፥፳፱፡፡ ፩፡ ቆሮ ፮፥፯።
                   ******
፴፱፡ እኔ ግን ክፉውን ሰው በክፉ ነገር ድል አትንሱት ክፉውን ግብር በክፉ ግብር አታጥፉት እላችኋለሁ። ወለዘሂ ጸፍዓከ መልታሕቴከ እንተ የማን ሚጥ ሎቱ ካልዕታሂ። ቀኝ ፊትሕን ቢመታህ ግራ ፊትሕን አዙረህ ስጠው። ፈቃደ ሥጋህን ተው ቢልህ ፈቃደ ነፍስህን ተውለት።
                   ******
፵፡ ወለዘሂ ይፈቅድ ይተዓገልከ መልበሰከ ኅድግ ሎቱ ክዳነከሂ፡፡
                   ******
፵፡ መጐናጠፊያህን ሊቀማህ ቢወድ ቀሚስህን ደርብለት።
(ታሪክ) እንዳንድ ባሕታዊ ወምበዶች እራቸውን አጥቦ አብልቶ አጠጥቶ አሳደራቸው፡፡ ሌት ተነሥተው እሱን አስረው መብራት አብርተው ያለ ገንዘቡን ይዘው ሄዱ። ከሄዱ በኋላ መብራት አብርቶ ቢያይ ሁለት ድሪም የምታወጣ ጸምር አገኘ፡፡ ይህቺም ላንድ ጉዳይ ትሆናችኋለች ብሎ ተከትሎ ወስዶ ሰጣቸው፡፡ ይህ ሰው እንዲህ ማድረጉ ከዚህ የበለጠ ዋጋ እንዳለ ቢያውቅ እንጂ ነው ብለው ተመልሰው ንስሐ ገብተው የሚኖሩ ሁነዋል።
አንድም አፍአዊ ግብርህን ሊያስትውህ ቢወድ ውሣጣዊ ግብርህን ተውለት፡፡
                   ******
፵፩፡ ወለዘሂ አበጠከ አሐደ ምዕራፈ ሑር ምስሌሁ ፪ተ።
                   ******
፵፩፡ ትብትብ አሸክሞ አንድ ምዕራፍ ቢወስድህ ይህማ የግድ አይደለምን ብለህ የፈቃድ ሁለት ምዕራፍ ተሸክመህ ውሰድለት፡፡ መምህረ ንስሐህ አንድ ሱባዔ ቀኖና ቢሰጥህ ይህስ ተስማምቶኛል ጨምርልኝ ብለህ ከሱ አስፈቅደህ ሁለት ሱባዔ ጹም፡፡
                   ******
፵፪፡ ወለኵሉ ዘሰአለከ ሀቦ። ዘዳ ፲፭፥፯-፰፡፡
፵፪፡ ለለመነህ ሁሉ ስጠው።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
19/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment