Saturday, March 30, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 49



                ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፮።
                  ******
በእንተ ጾም ወጸሎት ወምጽዋት፡፡
፩፡ ወባሕቱ ዑቁ ምጽዋተክሙ ኢትግበሩ ለዓይነ ሰብእ ከመ ያስተርእዩ ሎሙ።
                  ******
፩፡ ባሕቱን የሚጽፍም የማይጽፍም አለ። ምጽዋታችሁን ሰው ይይልን ብላችሁ እንዳታደርጉ ዕወቁ።
ወእመ አኮሰ ዓስብ አልብክሙ በኀበ አቡክሙ ዘበሰማያት፡፡ ያለዚያ ግን በሰማይ አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።
፪፡ ወሶበሂ ትገብሩ ምጽዋተክሙ ኢትንፍሑ ቀርነ በቅድሜክሙ በከመ ይገብሩ መደልዋን በመራኅብት ወበአስኳት።
                  ******
፪፡ በምትመጸውቱበትም ጊዜ ግብዞች ሰው ሰብስበው ቀን ቀጥረው በተመሳቀለ ጎዳና ባደባባይ እንዲያደርጉት ቀን ቀጥራችሁ አዋጅ ነግራችሁ አታድርጉት።
አንድም ውዳሴ ከንቱ ሽታችሁ አታድርጉት። አንድ ባለጸጋ አፈ ወርቅን እንደጠየቀው፡፡ ይህን ሲያስተምር አንድ ባለጸጋ መጥቶ ምጽዋት መመጽወት እወዳለሁ። ውዳሴ ከንቱም እወዳለሁ አለው። ውዳሴ ከንቱውን ትተህ መጽውት አለው። አይሆንም ሁሉንም እወዳለሁ ይህ ከቀረ ምጽዋቱም ይቅር አለው። እንኪያስ አትተው መጽውት ሰው ዘር ይዘራል ባይጠብቀው የእሽት ያህል ያጣለታልን አንተም የዚያን ያህል ጥቂት ዋጋ አታጣም ስጥ ብሎታል።
ከመ ይትአኰቱ እምኀበ ሰብእ፤ ሰው ያይላቸው ይሰማላቸው ዘንድ።
አማን እብለክሙ ኃጒሉ ዕሤቶሙ።
ኃጒሉ ቢል የወዲያኛውን ዋጋቸውን አጡ ነሥኡ ይላል ውዳሴ ከንቱውን አገኙ ብዬ እንዳገኙ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡
                  ******
፫፡ ወአንተሰ ሶበ ትገብር ምጽዋተከ ኢታእምር ፀጋምከ ዘትገብር የማንከ።
                  ******
፫፡ አንተ ግን በምትመጸውትበት ጊዜ ቀኝ እጅህ የምትሠራውን ግራ እጅህ አትወቀው። ማለት በቀኝ እጅህ የያዝኸውን በግራ እጅህ አትያዘው። ግራ ደካማ ነው ጥቂቱን ብዙ ያስመስለዋል ልክፈልለት ያሰኛልና። ቀኝ ኃያል ነው ብዙውን ጥቂት ያስመስላል፤ ከዚህ ምን እከፍልለታለሁ ልስጠው ያሰኛልና።
አንድም ሚስትህ አትወቅብህ ሲለው ነው ፀጋም አላት የባልና የሚስት ከብት ሎሚ ከሁለት እያለች ታዳክማለችና እንዳታዳክመው ከሚስት የሚሠወር ምን አለ ቢሉ ቅንነቱማ ካለ ገንዘቡ ሁሉ ያለ በእሱ እጅ አይደለምን ከዚያው ይስጥ። ይህማ ስርቆት አይሆንበትም ቢሉ ሰጥቶ ይንገራት። አይሆንም ብትለውሳ ቢሉ ይለያዩ ጥንቱን መጋባታቸው ሰጥተው መጽውተው ሊጸድቁ ነውና።
አንድም ልጆችህ አይወቁብህ ሲል ነው። ፀጋም አላቸው ያባታችን የቁም ወራሽ የሙት አልቃሽ እያሉ ያዳክማሉና እንዳያዳክሙት።
አንድም ቤተሰቦችህ አይወቁብህ፤ ፀጋም አላቸው የጌታችን ወርቁ ለዝና ልብሱ ለእርዝና እህሉ ለቀጠና እያሉ ያዳክማሉና አንዳ ያዳክሙት።
                  ******
፬፡ ከመ በኅቡዕ ይኩን ምጽዋትከ፡፡
፬፡ ምጽዋትህ በስውር ይሆን ዘንድ።
                   ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
21/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment