====================
የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፭።
******
በእንተ ሐዲስ ኪዳን።
ተአርዮታ ምስለ ብሊት።
፲፫፡ አንትሙ ውእቱ ፄዉ ለምድር፡፡ ማር ፱፥፵፱፡፡ ሉቃ ፲፬፥፳፬።
******
፲፫፡ በዘያውም ላይ የሰው አብነት እናንተ ናችሁ። ወእመሰ ፄው ለስሐ በምንት እንከ ይቄስምዎ። ጨው ጣዕም
ባይኖረው በምን ያጣፍጡታል። ራሱን አንድም አፍርጁን ሽንኵርቱን በምን ያጣፍጡታል።
አልቦኬ እንከ ዘይበቀዕ።
የማረባው የሚጠቅመው የለም ለአፍርንጁ ለሽንኵርቱ። አንድም ለራሱ የሚያገኘው ረብሕ ጥቅም የለውም።
ዘእንበለ ዘይገድፍዎ አፍአ።
አፍአ አውጥተው ይጥሉታል።
ወይከይድዎ ሰብእ በእገሪሆሙ ሰዎች በእግራቸው ይጠቀጥቁታል እንጂ።
(ሐተታ) ቢክቡትይናዳል ቢንተራሱት ራስ ይመልጣል ከተክል ቦታ ቢያደርጉት ተክል ያደርቃል ብለው።
አንድም አንትሙ ውእቱ ፄው ለምድር የሰው አብነት እናንት ናችሁ። እናንተ አብነት ካልሆናችሁ ማን አብነት
ይሆንላችኋል።
አንድም ለሕዝቡ እናንተ አብነት ከልሆናችኋቸው ማን አብነት ይሆናቸዋል። ለሕዝቡ የምትረቧቸው የምትጠቅሟቸው
የለም።
አንድም ለራላችሁ የምታገኙት ረብሕ ጥቅም የለም። ዘእንበለ ዘይገድፍዎ አፍአ። ሕዝቡ ከልቡናቸው በአፍአ
ያወጥዋችኋል።
ወይከይድዎ። በልቡናቸው ይነቅፏችኋል እንጂ።
አንድም ሥላሴ ከመንግሥተ ሰማይ አፍአ ወደምትሆን ወደ ገሃነም ያወጧችኋል እንጂ።
ወይከይድዎ። አጋንንትም መከራ ያጸኑባችኋል
እንጂ። በማደሪያቸው ሰብእ አላቸው።
አንድም በቁሙ ሰዎች ይጠቀጥቋችኋል ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳስነሣው ፍቍራ አስነሥቶ ወዴት ነበርህ ቢለው ከኤጲስ
ቆጶሳችሁ ላይ ነበርሁ ብሏል።
******
፲፬፡ አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም።
******
፲፬፡ አብነትነታቸው በብዙ ወገን ነውና ደገመው። የሰው አብነቱ እናንተ ናችሁ።
ኢትክል ተከብቶ ሀገር እንተ ተሐንፀት መልዕልተ ደብር።
ከተራራ ላይ የተሠራች መንደር መሰወር አይቻላትም።
******
፲፭፡ ወኢየኃትዉ ማኅቶተ ከመ ያንብርዋ ታሕተ ከፈር። ማር ፬፥፳፩። ሉቃ ፰፥፲፩።
******
፲፭፡ እንቅብ ቅርጫት ሊደፉባት መቅረዝ የሚያበራ የለም።
አላ ያነብርዋ ዲበ ተቅዋማ ወታበርህ ለኵሉ እለ ውስተ ቤት
ከመቅረዝ ላይ አኑረዋት ከቤት ላሉ ሁሉ ታበራ ዘንድ ነው እንጂ።
******
፲፮፡ ከማሁኬ ይብራህ ብርሃንክሙ በቅድመ ሰብእ። ፩፡ጴጥ ፪፥፲፪።
******
፲፮፡ እንዲህም ሁሉ ሥራችሁ በሰው ፊት ይሁን።
ከመ ይርአዩ ምግባሪክሙ ሠናየ ወይሰብሕዎ ለአቡክም ዘበሰማያት።
በጎ ሥራችሁን አይተው ሰማያዊ አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲህ ያሉ የትሩፋት አበጋዝ ያስነሣልን ብለው።
(ሐተታ) ምነው በሚያመጣው ጸሊ በኅቡዕ ይል የለም ቢሉ አብነት የሚሆኑበትን ተገልጻው ይሠሩታል አብነት
የማይሆኑበትን ተሠውረው ይሠሩታልና እንዲህ አለ።
አንድም በተራራ ላይ የታነጸች መንደር ልሰወር ብትል መሰወር እንዳይቻላት የተራራው ከፍታ እንዲገልጻት።
በመቅረዝ ላይ ያለች ፋና ልሰወር ብትል መሰወር አንዳይቻላት የመቅረዙ ከፍታ እንዲገልጻት እናንተም ሥራውን አብዝታችሁ ሥሩት ግድ
በተአምራት ይገልጻችኋል ሲል ነው። ደብር ተቅዋም አንድ ወገን ሀገር ማኅቶት አንድ ወገን፤ ደብር ተቅዋምሥጋ ሀገር ማኅቶት ነፍስ
ከሥጋ ጋራ ተዋሀደች ነፍስ ሥራ ሠርታ ልትገለጽ ነው እንጂ። ተሠውራ ልትቀር አይደለም።
አንድም ደብር ተቅዋም ሰውነት ሀገር ማኅቶት አእምሮ ጠባይዕ በሰውነት ያለ አእምሮ ጠባይዕ ሥራ ሠርቶ ሊገለጽ
ነው እንጂ ተሠውሮ ሊቀር አይደለም።
አንድም ደብር ተቅዋም ሥጋ ሀገር ማኅቶት መለኮት ከሥጋ ጋራ የተዋሐደ መለኮት አስተምሮ ታምራት አድርጎት
አምላክነቱን ሊገልጽ ነው እንጂ። ተሠውሮ ሊቀር አይደለም።
አንድም ደብር ተቅዋም መስቀል ሀገር ማኅቶት ጌታ በመስቀል የተሰቀለ ጌታ ሙቶ ተነሥቶ አምላክነቱን ሊገልጽ
ነው እንጂ ሙቶ ሊቀር አይደለም።
አንድም ደብር ተቅዋም ኦሪት ሀገር ማኅቶት ወንጌል በኦሪት ላይ የተሠራች ወንጌል ባደባባይ ተገልጻ ልትነገር
ነው እንጂ። ተሠውራ ልትቀር አይደለም።
አንድም ደብር ተቅዋም ሕዝቡ ሀገር ማኅቶት ኢጲስ ቆጶስ በሕዝቡ ላይ የተሾመ ኤጲስ ቆጶስ አደባባይ ወጥቶ
ጉባዔ ሰርቶ ሕዝቡን ሊያስተምር ነው እንጂ፤ ባዳራሽ ገብቶ እልፍኝ ተከቶ ተሠውሮ ሲበላ ሲጠጣ ሊውል አይደለም።
******
፲፯፡ ኢይምሰልክሙ ዘመጻእኩ እሥዓሮሙ ለኦሪት ወለነቢያት።
፲፯፡ ኦሪትን ነቢያትን ላሳልፋቸው የመጣሁ አይምሰላችሁ።
******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ
በየነ
ደብረ
ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
14/07/2011
ዓ.ም
No comments:
Post a Comment