Saturday, March 9, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 31


 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፫።
                  ******
፮፡ ወያጠምቆሙ ለኵሎሙ በፈለገ ዮርዳኖስ እንዘ ይትአመኑ ኃጣውኢሆሙ።
                  ******
፮፡ ኃጢአታቸውን እየነገሩት በዮርዳኖስ ያጠምቃዋው ነበር። እገሌ ተጠመቅ በማየ ንስሐ ከመ ትኵን ረድኦ ለክርስቶስ እያለ።
(ሐተታ) ጥምቀት ከሦስት ወገን ነው። መዝገበ ውሉድ ፍቁራን የምትባል የጌታ ጥምቀት፣ ጥምቀተ ዮሐንስ፣ ጥምቀተአይሁድ። ጥምቀተ አይሁድና ጥምቀተ ዮሐንስማ አንድ አይሆንም ሁሉም ልጅነት አያሰጥ ቢሉ አንድ አይደለም ከሰውነታቸው ሰውነቱ እንዲበልጥ ከጥምቀታቸውም ጥምቀቱ ይበልጣል።
አንድም ስምንት ወገን ነው ፬ቱ ምሳሌ በ፬ቱ አማናዊ። ምሳሌ አጥመቃ ለምድር በማየ አይህ። ወለኵሎሙ አበዊነ አጥመቆሙ ሙሴ በደመና ወበባሕር። ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት ያለው። ጥምቀተ ዮሐንስ ይህ ምሳሌ ነው። አራቱ አማናዊ መዝገበ ውሉድ ፍቁራን የምትባል የጌታ ጥምቀት አንብዓ ንስሐ፣ ደመ ሰማዕት ባሕረ እሳት።
                  ******
፯፡ ወሶበ ርእየ ብዙኀነ አሕዛበ እምፈሪሳውያን ወሰዱቃውያን እንዘ ይመጽኡ ውስተ ጥምቀቱ ጽሚተ። ሉቃ ፫፥፯።
                  ******
፯፡ ከጸሐፍት ከፈሪሳውያን ወገን ብዙ ሰዎች ጻድቃን መስለው ኃጢአታቸውን ሠውረው አልባሌ መስለው ተርታ ልብስ ለብሰው የኦሪትን መፍረሻ የወንጌልን መታነጫ እናያለን ብለው እሱ ወደሚያጠምቅበት ሲመጡ ባየ ጊዜ።
(ሐተታ) እስራኤል አይደሉም ስለምን አሕዛብ አላቸው ቢሉ ስለብዛታቸው። አንድም በጸያፍ የገባ ግብረ አሕዛብ ይሠራሉና። በአባታቸው በፋሬስ ፈሪሳውያን በሳዶቅ ሰዱቃውያን ተብለዋል በአባትም ስም መጠራት ልማድ ነው። በዔቦር ዕብራውያን በይሁዳ አይሁድ እንደ ተባሉ።
ወይቤሎሙ ኦ ትውልደ አራዊተ ምድር መኑ አመረክሙ ትጕየዩ እመቅሰፍት ወእመንሱት ዘይመጽእ።
እናንት የፍኝት እባብ ልጆች በነፍስ በሥጋ ከሚመጣው መከራ ትድኑ ዘንድ ማን ነገራችሁ። እመቅሰፍት ወእመንሱት ወእመዓት ዘይመጽእ ይላል። በጥጦስ በሐሳዊ መሢሕ በምጽዓት ከሚመጣው መከራ ትድኑ ዘንድ ማን ነገራችሁ። ሊማሩለት አንዳልመጡ ያውቅ የለምን ቢሉ የማይጠቀም ከጉባዔው አይመጣምና። አንድም የሹም ሰነፍ ባይለፈልፍ እንዲሉ። ንግር ወኢታርምም ብሎታልና። አባቶቻቸው ወደው ባወጡት ስም ትውልደ አራዊተ ምድር አላቸው። ወንድማቸውን ዮሴፍን ሸጠው በልተው እኩይ አርዌ በልዖ ብለው ነበርና።
ትውልደ አራዊተ ምድር ያላት አርዌ ገሞራዊት ናት። አፈ ማኅፀኑዋ ጠባብ ነው ዘሩን ባፏ ትቀበለዋለች አባለ ዘሩን ቆርጣ ታስቀረዋለች። በፅንስ ጊዜ ኦባት ይሞታል በሚወለዱበትም ጊዜ አፈ ማኅፀኑዋ ጠባብ ነውና ሥጋዋን በልተው ሆዷን ቀደው ይወጣሉ። በዚህ ጊዜ እናት ትሞታለች። እኒህም እንደ አባት የሚሆኑዋቸውን ነቢያትን እንደ እናት የሚሆኑዋቸው ሐዋርያትን ገድለዋልና። ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም እንተ ትቀትሎሙ ለነቢያት ወትዌግሮሙ ለሐዋርያት እለ ተፈነዉ ኀቤሃ ብሎ እንዲያመጣው።
                  ******
፰፡ ግበሩኬ እንከ ፍሬ ሠናየ ዘይደልወክሙ ለንስሐ።
                  ******
፰፡ ከእንግዲህስ ወዲህ ለማመን የሚያበቃችሁን ሥራ ሥሩ።
                  ******
፱፡ ወኢይምሰልክሙ ዘታመሥጡ በብሂለ ዘትብሉ አብ ብነ አብርሃም። ዮሐ ፰፥፴፱።
፱፡ አብርሃምን ያህል አባት ሳለን ትውልደ አራዊተ ምድር ይለናል በማለት ትውልደ አራዊተ ምድር ከመባል የምትድኑ አይምሰላችሁ።
                  ******
እንዲሉት አውቆ አመጣ እንዲሉትም አውቆ ማምጣት ልማድ ነው። ብፁዓን ብፁዓን እያለ ሲያስተምር ሰምተው ኦሪትን ነቢያትን ሊያሳልፋቸው መጥቷል እንዲሉት አውቆ ኢይምሰልክሙ ዘመጻእኩ እስዓሮሙ ለኦሪት ወነቢያት ዘእንበለ ዳዕሙ ከመ እፈጽሞሙ እንዳለ። ወኢትሁቦ ለጻድቅከ ይርአይ ሙስና ቢላቸው ይህንማ ዳዊት የተናገረው ለራሱ አይደለም እንዲሉት አውቆ ታበውሁ ናሁ ኦ ሰብእ ንንግርክሙ ክሡተ በእንተ ዳዊት ርእሰ አበው ቀደምት ከመሂ ሞተ ወተቀብረ እንዳለ። ከዚህም እንዲህ አለ።
እብለክሙ ከመ ይክል እግዚአብሔር እምእላንቱ አዕባን አንሥኦ ውሉድ ለአብርሃም። እግዚአብሔር ለአብርሃም ከነዚህ ከአሕዛብ ልጅ ማስነሳት አቅሞ ውሉድ ይላል መተካት እንዲቻለው ይቻለዋል ብዬ እነግራችኋለሁ። አንሥኦ ውሉድ አንሥኦ ውሉደ ይላል። እላንቱ አላቸው አሁን ያሉ በመካከል ነውና ኋላ ብሔረ ጌርጌሴኖን ገባ ብሎ እንዲያመጣው። አዕባን አላቸው ደንጊያ ያመልካሉና አንድም ይቡስ ነው ይቡሳነ አእምሮ ናቸውና። ቈሪር ነው ቈሪራነ አእምሮ ናቸውና። ክቡድ ነው ክቡዳነ አእምሮ ናቸውና።
                  ******
፲፡ እስመ ናሁ ተሠይመ ማሕፄ ውስተ ጕንደ ዕፀው ይንበር።
፲፡ ምሳር ዓፅቁን ከግንዱ ሊለይ ተቃጥቷልና።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
01/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment