Thursday, March 14, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 35

 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፬።
                  ******
በእንተ ተመክሮት ዘኢየሱስ።
፩፡ ወእምዝ ወሰዶ መንፈስ ገዳመ ለእግዚእ ኢየሱስ። ማር ፩፥፲፪። ሉቃ ፬፥፭።
                  ******
፩፡ ከተጠመቀ በኋላ ፈቃዱ አነሣስቶ ወደ ገዳም ወሰደው። ወሶበ ትሰምዕ እንዘ ይብለከ መንፈስ ወሰዶ ገዳመ ኢተሐሊኬ ከመ ፍጡር ውእቱ። አላ መንፈስሰ ሥምረቱ ይእቲ እንዲል።
አንድም መንፈስ ቅዱስ የሚል አብነት ይገኛል ሰማዕታትን አነሣስቶ ወደ ደም ጸድቃንን አነሣስቶ ወደ ገዳም እንዲወስድ ወሰደው ማለት አይዶደም ፈቃዳቸው አንድ መሆኑን መናገር ነው።
ተጠምቆም አልዋለም አላደረም ዕለቱን ገዳም ሂደል። እናንተም ተጠምቃችሁ አትዋሉ አትደሩ ዕለቱን ገዳም ሂዱ ለማለት አብነት ለመሆን ወደ ገዳም ሄደ አለ። አዳም ከዚህ ዓለም አፍኣ በምትሆን በገነት ድል ተነሥቶ ነበርና። እሱም ከዚህ ዓለም አፍኣ በምትሆን በገዳም በ፫ቱ አርእስተ ኃጣውእ ድል ለመንሳት። አንድም በገዳም ፆር ይቀላል ለወጣንያን አብነት ለመሆን፡፡
አንድም በገዳም ፆር ይጸናል ለፍጹማን አብነት ለመሆን።
ከመ ይትመከር እምዲያብሎስ፡፡
ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ፡ እፈተናለሁስ ብሎ ሄዶ ቢሆን ዕዳ በሆነበት ነበር። ከሄደ ዘንድ ፆሩ እየቀለመ ይሰብርበታል እንጂ። ይህንም ፆር እማርበታለሁ ብሎ አላደረገውም፡፡ ንሣእ ፩ደ መዓዴ እምአፍኣ ከመ ትኩን ፍቱነ ወስቡከ እንዲል መከራውንም ሽቶ አላመጣውም አኮ ፈቂዶ መከራሁ ለጸላኢ አላ ከመ ያብጥል ኃይሎ ለዘያሜክር በኃይሉ ለቃል ዘኮነ ፩ደ ምስለ ሥጋ እንዲል። መከራውንም አነሣስቶ አላመጣውም ኢሆከ እግዚእነ እሎንተ ሕማማተ ከመ ይኅልፉ ዲቤሁ አላ በሁከቶሙ ማሰኑ እንዲል። መዋጋቱም በሰውነቱ ነው፤ ኢሠርዓ እግዚእነ ቀትለ በመለኮቱ አላ በሥጋሁ ዘይትዌከፍ ሕማማተ እንዲል። ድል መንሳቱም በሰውነቱ ነው እንጂ በአምላክነቱ አይደለም ወኢሞዖ በኃይሉ መዋዒት እንዲል። በአምላክነቱስ ድል ቢነሳው ባልተደነቀም ነበር፡፡ ሶበሰ ሞዖ እግዚእነ በኃይሉ መዋዒት እምኢኮነ መንክረ ወእም ኢኮነት ትሩፋት ዘውስቴቱ ዘኢስብሕት ወዘኢውድስት አኮ መንክር እመ ሞዖ ኃያል ለድኩም እንዲል።
                  ******
፪፡ ወጾመ መዓልተ ወ፵ ሌሊተ፡፡
                  ******
፪፡ ፵ መዓልት ፵ ሌሊት ጾመ። ሠራዔ ሕግ ነውና ጾምን መጀመሪያ ሕግ አደረገ። አንድም ሥራውን በጾም ጀመረ።
(ሐተታ) መብል ለኃጣውእ መሠረት እንደ ሆነ፣ ጾምም ለምግባር ለትሩፋት መሠረት ናትና። እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ ወጥንተ ኵሉ ገድል ሠናይት እንዲል።
፵ መዓልት ፵ ሌሊት መሆኑ ስለምን ቢሉ ቀድሞ አባቶቹ ነቢያት ፵ ፤ ፵ ጹመዋል ከዚያ ቢያተርፍ አተረፈ ቢያጐድል አጐደለ ብለው አይሁድ ደጊቱን ሕገ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበረና፡፡
ሙሴ በ፵ ዘመኑ ለዕብራዊ ረድቶ ግብፃዊን ገድሎ በኆፃ ቀብሮታል። ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር ዕብራዊ የአዳም ግብፃዊ የዲያብሎስ የመስቀል።
አንድም የ፫ቱ አርእስተ ኃጣውእ ምሳሌ። ሙሴ ፵ ጹሞ ሕገ ኦሪትን ሠርቷል እሱም ፵ ጹሞ ሕገ ወንጌልን የሚሠራ ነውና፡፡
ሙሴ ፵ ዘመን በምድያም ኑሮ እስራኤልን ከግብፅ አውጥቷቸዋል። እሱም ፵ ጹሞ ነፍሳትን የሚያወጣ ነውና።
አንድም የእስራኤል ጉበኞች በ ፵ ቀን ተመልሰዋል። እሱም የመንግሥተ ሰማይ ጉበኛ ነውና፡፡
እስራኤል በገዳም ፵ ዘመን ኑረው ምድረ ርስት ገብተዋል። እናንተም ፵ ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ለማለት።
ኤልያስ ፵ ጹሞ ገነት ገብቷል። እናንተም ብትጾሙ ገነት መንግሥተ ሰማያት ትገባላችሁ ለማለት።
ሕዝቅኤል በፀጋማይ ጐኑ ፵ ቀን ተኝቶ ስድስት መቶ ሙታን አስነሥቷል። እናንተም ፵ ብትጾሙ ትንሣኤ ዘለክብር ትነሣላችሁ ለማለት።
ዕዝራ ፵ ቀን ከምግቡ ተከልክሎ መጻሕፍትን አጽፏል። አንሰ በውእቶን መዋዕል ኢበላዕኩ እክለ ወኢሰተይኩ ማየ። እሙንቱሰ መዓልተ ይጽሕፉ ወሠርክ ይዴረሩ እንዲል እነዚያ ቀን ሲጽፉ እየዋሉ ማታ ይመገባሉ። እሱ ግን ቀን ሲያጽፈው የሚውለውን ሌሊት ሲያስበውድር ነበር። እናንተም ፵ ብትጾሙ ምሥጢር ይገለጥላችኋል ለማለት።
እባብ አካሉ የደገደገበት እንደሆነ ፵ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ይሰነብታል፡፡ በስቊረተ ዕፅ ስቊረተ ዕብንም ቢሉ አልፎ ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለታል ይታደሳል። እናንተም አርባ ብትጾሙ ተሐድሶተ ነፍስ ታገኛላችሁ ለማለት።
ምሳሌውን አውቆ አስመስሏል ፍጻሜው እንደምን ነው ቢሉ አዳም በ ፵ ቀን ያገኘውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና ለሱ እንደካሰ ለማጠየቅ።
አንድም በ፵ ቀን ተስእሎተ መልክዕ ለተፈጸመለት ሰው ሁሉ ሊክስ እንደመጣ ለማጠየቅ። ላ፬ቱ ባሕርያት አሥር አሥሩን ለመካስ። አምስተኛ ባሕርየ ነፍስን የጨመሩ እንደሆነ ስምንት ስምንቱን ሊክስ እንደመጣ ለማጠየቅ።
ከዚህም ተራበ አልሳሳም ተዋጋ ድል አልተነሣም ወሶበ ጾመ እግዚእ ፵ መዓልተ ወ፵ ሌሊተ ከሠተ ከመ ኢሐመ ሥጋሁ አምረኃብ ወፅምዕ በኃይል ዘይደሉ ለመለኮት እንዲል። ከዚህም ሥራውን ሠርቶ ሥሩ አለ እንጂ። ባልዋጁበት ጣት የዘንዶ ጉድጓድ ይለኩበት እንዲሉ ሳይሠራ እኛን ሥሩ አላለንም ወሖሮን እግዚእ ግብራት እንዲል፤ ግብራት የተባሉ ጥምቀት፣ ተአምኖ ኃጣውእ፣ ከዊነ ሰማዕት፣ ተባሕትዎ፣ ምንኩስና።
ጥምቀት በዕደ ዮሐንስ መጠመቅ ተአምኖ ኃጣውእ ከተአማንያነ ኃጣውእ ጋራ አንድ ሁኖ መቈጠር፣ ከዊነ ሰማዕት አንሰ በአንተ ዝንቱ ተወለድኩ ወእንበይነ ዝንቱ መጻእኩ ውስተ ዓለም ከመ እኩን ሰማዕተ በጽድቅ ብሎ ከጲላጦስ ፊት ቁሞ መመስከር ተባሕትዎቀን ከምግብ ተከልክሎ በገዳም መኖር። ምንኩስና በድንግልና መኖር ነው። ረቂቅ ዘእምረቂቅ እንደ ሆነ ለማጠየቅ በኅቱም ድን ግልና ተፀነሰ በኅቱም ድንግልና ተወለደ። ዘኢይርኅብ እምዘኢይርኅብ እንደሆነ ለማጠየቅመንልትሌሊት ጸመ ዘኢይትገሠሥ እምዘኢይትገሠሥ እንደሆነ ለማጠየቅ በባሕር ላይ ሄደ። ብርሃን ዘእምብርሃን እንደሆነ ለማጠየቅ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር ገለጸ፣ ሕይወት ዘእምሕይወት እንደሆነ ለማጠየቅ ያራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አነሣ።
ወእምዝ ርኅበ።
ከዚህ በኋላ ተራበ።
(ሐተታ) ረኃቡም የፈቃድ ረኃብ ነው እንጂ እንደኛ ረኃብ አይደለም፡፡ እኛ ብንበላውንጣን ብንተወው ስልት ቀጠና ይሆንብናል። ረኀበ እግዚእነሰ አኮ ከመ ረኃበ ዚአነ አላ ገጸ ረኃቡ ፍሉጥ እምኔነ ለነሰ በግብር ይመውዓነ ወሎቱሰ በፈቃዱ እንዲል። አንድ ጊዜ ርኅበ አንድ ጊዜ ኢርኅበ ይላል እንደምነው ቢሉ። ከ፪ት አካልአካል ከሁለት ባሕርይ ፩ ባሕርይ እንደሆነ ለማጠየቅ። በእንተ ምንት ርኅበ እግዚእነ ዘእንበለ ዳዕሙ ከመ ያጠይቅ ከመ ውእቱ እም ፪ ህላዌያት እንዲል። መራቡም ለአጽድቆተ ትስብእት ለካሳ ነው፡፡
                  ******
፫፡ ወቀርበ ዘያሜክሮ።
፫፡ የሚፈታተነው ዲያብሎስ ቀረበ፡፡
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
05/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment