Thursday, March 14, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 36



====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፬።
                  ******
፫፡ ወቀርበ ዘያሜክሮ።
                  ******
፫፡ የሚፈታተነው ዲያብሎስ ቀረበ፡፡
(ሐተታ) እንዲያው አይቀርበውም ርኅብኩ የሚል ድምፅ አሰምቶት ፍሬ ፅፅ ሲሻ አይቶት። መልኩን አጸውልጎ ታይቶት እሱም እንዲያው አይቀርብም በአምሳለ ሠዓሊ በአምሳለ ሐራሲ በቀዳዳ ሽልቻ ትኩስ ዳቦ የያዘ መስሎ ሁለት ደንንጊያ ይዞ ይቀርባልአንዱን ለአንተ አንዱን ለአኔ አድርገህ እንብላ እለዋለሁ ደንጊያውንማ ዳቦ ከማድረግ የያዝኸውን አንበላም ያለኝ እንደሆነ አዳምን አባቱንመብል ምክንያት ድል እንደነሣሁት እሱንም በመብል ምክንያት ድል እነሣዋለሁ ብሎ።
ወደቤሎ እመሰ ወልደ እግዚአብሔር አንተ በል ከመ አላ አዕባን ኅብስተ ይኩና። በዮርዳኖስ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ ሲመሰክርለት ሰምቶ ነበርና የእግዚአብሔርስ ልጅ ከሆንህ እኒህ ደንጊያዎች ኅብስት ይሁኑ ብለህ እዘዝ አለው። ቢያደርገው የሰይጣን ተአዛዚ ብዬ ዕዳ እልበታለሁ ባያደርገው ደካማ አሰኘዋለሁ። ቢያደርገው ሌላ ፆር እሻለታለሁ ባያደርገው ድካሙን አይቼ እቀርባለሁ ብሎ። ደንጊያውን ኅብስት አድርግ ማለቱ ምን ልማድ ይዞ ነው ቢሉ በዮሴፍ ልማድ። ዮሌፍን አባቱ የሱን ስንቅ ለብቻ አሲዞ ለወንድሞችህ ስንቃቸውን ሰጥተህ ወንድሞችህን ጠይቀህ ብሎ ላከው። ያሉበትን አጥቶ ሲፈልግ የሱ ስንቅ አለቀበት ከዚያ እንዳይበላ አባቱ ያላዘዘው ነው። ረኃብ ጸንቶበት ሳለ መልአክ ያባትህን ፈጣሪ ደንጊያውን ዳቦ አድርግልኝ አትለውም አለው። ወደ እግዚአብሔር ቢያመልለክት ደንጊያው ዳቦ ሁኖለትመግቧልና እንዲህ አለ።
                  ******
፬፡ ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ።
                  ******
፬፡ ጌታም መለሰ ወይቤሎ ጽሑፍ ከመ አኮ በኅብስት ከመ ዘየሐዩ ሰብእ። ዘዳ ፰፥፫። ሉቃ ፬፥፬።  ሰው የሚድነው በኅብስት ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል። አላ በኵሉ ቃል ዘይወጽእ እም አፋሁ ለእግዚአብሔር። እግዚአብሔር ዳን ያለው ይድናል ሙት ያለው ይሞታል እንጂ።
አንድም ሰው የሚድን ገበሬ በጻረበት በኅብስት ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል። እግዚአብሔር ምግብ ይሁን ያለውም ምግብ ይሆናል እንጂ እስራኤል ፵ ዘመን በትርህ አልወደቀ ጫማህ አልወለቀ ልብስህ አላለቀ እንዲሉ ከውቅያኖስ በደመና አይበት ተቋጥሮ በነፋስ ወደልጋዝ ተጭኖ መጠኑ ድንብላል አህሎ መልኩ በረድ መስሎ ወእንዘ የኃድግ ሀቦ ይላል የውርጭ ገበታ ሲነጸፍ እየዘነመላቸው አርባ ዘመን ተመግበዋልና።
አንድም ሰው የሚድን ገበሬ በጻረበት በጋረበት በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል። በዓቂበ ሕግም በትምህርትም ነው እንጂ።
(ሐተታ) የሰው ባሕርዩ ባሕርይ እንስሳዊ ባሕርይ መልአካዊ ነው። ባሕርይ እንስሳዊ ምግብ ሲያጣ ይጎዳል፣ ባሕርይ መልአካዊ ትምህርት ሲያጣ ይጎዳልና። አእምር ከመ በአማን ሲያይ ቃለ እግዚአብሔር ሲሲተ ልብ ቃላቲሁ ለእግዚአብሔር ወአምጽእ ረኃበ እክል ወጽምዓ ማይ ለብሔር ረኃብሰ እምሰሚዓ ቃለ እግዚአብሔር እንዲል።
አንድም ወልደ እንግዚአብሔርስ ከሆንህ ይህ እንደ ድንጊያ ፈዞ ያለ ሰውነትህ ኅብስተ ሕይወት ኅብስተ መድኃኒት ይሁን ብለህ እዘዝ ሲያሰኘውነው። ጌታም ሰው የሚድን በዕሩቅ ብእሲ ሥጋ እንዳይደለ ተጽፏል። አካላዊ ቃል በተዋሐደው ሥጋ ነው እንጂ አለው።
                  ******
፭፡ ወእምዝ ነሥአ ወወሰዶ ውስተ ቅድስት ሀገር።
                  ******
፭፡ ከዚህ በኋላ ወደ ቅድስት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው።
(ሐተታ) እሱስ አይወስደውም ፈቃዱን አውቆ ስለሄደለት ካህናትን ድል ነሥቼበት በማላወቅ በገዳም ቢሆን ነው እንጂ ካህናትን ድል በምነሳበት በቤተ መቅደስ ቢሆን መች ድል ይነሣኝ ነበር ብሏል ፈቃዱን አይቶ ስለሄደለት ነሥኦ ወሰዶ አዕረጎ ይላል። ወዓቀሞ ውስተ ተድባበ ቤተ መቅደስ።
ተድባብ ማዕዘንት ርእስ ይላል አብነት። ተድባብ ያለ እንደሆነ ከዝንቦው ማዕዘንት ያለ እንደሆነ ከምሕዋሩ ርእስ ያለ እንደሆነ ከጐልላቱ አቆመው።
ከዚህም በአምሳለ ሊቀ ካህናት አምሞ ጠምጥሞ መነሳስን ይዞ ይታየዋል።
ወእምዝ ነሥአ ወወሰዶ ውስተ ቅድስት ሀገር።
                  ******
፮፡ ወይቤሎ እመሰ አማን ወልደ እግዚአብሔር አንተ ቅንጽ እምዝየ  ወተወረዉ ታሕተ። መዝ ፲፩።
                  ******
፮፡ በዕውነት ወልደ እግዚአብሔር ከሆንህ ከዚህ ዘለህ ወደታች ውረድ አለው።
(ሐተታ) ቢሰበር አርፈዋለሁ ባይሰበር ምትሐት አሰኘዋለሁ ቢያደርገው ሌላ ፆር እሻለታለሁ ባያደርገው ደካማ አሰኘዋለሁ ቢያደርገው የሰይጣን ተአዛዘዚ ብዬ ዕዳ እልበታለሁ ባያደርገው ድካሙን አይቼቀርበዋለሁብሎ ነው።
እስመ ጽሑፍ ከመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይዕቀቡከ በኵሉ ፍናዊከ በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክትን ስላንተ እንዲያዛቸው ተጽፏልና። ወበእደዊሆሙ ያነሥኡከ ከመ ኢትትዐቀፍ በዕብን እግርከ እግረከ ይላል። እግርህ እንዳይሰናከል በእጃቸውም ያነሡሃል የሚል ጽሑፍ አለና። ጌታ ከላይ ጠቅሶበት ነበርና እሱም ፈንታውን ይንጐዳጐዳል።
                  ******
፯፡ ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎዕበ ጽሑፍ ኢታመክሮ ለእግዚአብሔር አምላክከ። ዘዳ ፲፮።
                  ******
፯፡ ዳግመኛ ፈጣሪህን እግዚአብሔርን አትፈታተነው የሚል ጽሑፍ አለ አለው። እንዲህ የሚል ከምን አለ ቢሉ እንደ ጊዜ ገድሉ ጠቀሰ። እስራኤል በገዳም ሳሉ ሙሴ አሥራ ሁለቱ ነገድ አውጻጽቶ ኢያሱና ካሌብን ምድረ ርስትን ሰልላችሁ ብሎ ሰደዳቸው። እሳቸውም ሰልለው ሲመለሱ ከወይኑ ዘለላ ከስንዴው ዛላ በባጢ ቀፎ ይዘው መጡ። እንደምን ሁናችሁ መጣችሁ ሀገሪቱስ እንደ ምን ያለች ናት ብለው ጠየቋቸው። ሀገሪቱስ መልካም ናት እንደዚህ ያለ ታፈራለች። ባሕቱ ርኢነ ደቂቆ ለኤናቅ ኑኆሙ ከመ አርዝ ወጽንዖሙ ከመ አውልዕ ንሕነሰ ኮነ ከመ አናብጥ በቅድሜሆሙ ምድርኒ ትረድኦሙ ወተዓቅቦሙ ብለው ፲ሩ አስገርመው አስፈርተው ተናገሩ ካሌብና ኢያሱ በፈቃደ እግዚአብሔር እንገባታለን አሉ ፲ሩ ካገባንስ አሁን ያግባን ሙሴ ተነሣ ታቦተ ጽዮንንም አንሣ እንሂድ አሉት። ሙሴ ታቦተ ጽዮንም አሁን አትነሣ እናንተም እግዚአብሔር ፈጣሪያችሁን አትፈታተኑት አላቸው። አይሆንም ብለው ሄዱ። በወሰን ያሉ አሕዛብ ገጥመው ድል አደረጓቸው፤ በዚህ ጊዜ ከባሕር ጠልቀው ከገደል ወድቀው አልቀዋል። ከዚህም ጌታ እንደ ጊዜ ገድሉ ጠቀሰው።
                  ******
፰፡ ወእምዝ ነሥኦ ዲያብሎስ ወአዕረጎ ውስተ ደብር ነዋኅ ጥቀ።
                  ******
፰፡ ከዚህ በኋላ ወደ ረጅም ተራራ አወጣው።
(ሐተታ) ነገሥታትን ድል በማልነሣበት በቤተ መቅደስ ቢሆን ድል ነሣኝ እንጅ። ነገሥታትን ድል በምነሣበት በተራራ ቢሆን መች ድል ይነሣኝ ነበር ብሏል። ፈቃዱን አውቆ ስለሄደለት አዕረጎ አለ።
ወአርአዮ መንግሥታተ ኵሉ ዓለም ወኵሎ ክብሮ። ጠጠሩን ወርቅ ብር ቅጠሉን ግምጃ አስመስሎ አሳየው አንድም መንግሥታተ ኵሉ ዓለም። ግዛቱን ሁሉ አሳየው ወኵሎ ክብሮ እንስሳትን ዓራዊትን ፈረስ በቅሎ ሠራዊት አስመስሎ አላየው። እሱስ ያይለታል ቢሉ ስለመሰለው ነው እንጅ አያይለትም። ድል መንሳቱ በምን ይታወቃል ቢሉ ባለመጽነኑ።
                  ******
፱፡ ወይቤሎ ዘንተ ኵሎ እሁበከ እምከመ ሰገድከ ሊተ ወአማኅከኒ።
                  ******
፱፡ ደፋር ነውና ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሳኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።
                  ******
፲፡ ወእምዝ ይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን። ዘዳግም ፯፥፲፫
                  ******
፲፡ ከዚህ በኋላ ከኋላዬ ወግድ አለው ራስ አይቶ የሚመጣ ጠላት ክፉ ነውና ጽኑ ባለጋራዬ ሲል ነው። ወዓቀመ አዴርሃ ሰይጣነ ላዕለ ሰሎሞን እንዲል።
አንድም እምዘድኅሬየ ይላል አብነት ከኔ በኋላ ከሚነሱ ከምዕመናን ወግድላቸው አለው። እንዲህ ባለው ጊዜ እንደጢስ ተኖ እንደ ትቢያ በኖ ጠፍቱአል።
(ሐተታ) እስከአሁን ሑር አላለው አሁን ሑር ማለቱ ስለምን ቢሉ። በቀዳሚ ጊዜ ጉየይ ወበካልዕ ጊዜ ጉየይ  ወበሣልስ ተንሥእ ወተቃተል እንዲል። አብነት ለመሆን በሦስተኛው ድል ንሱ ለማለት ንጉሥ በመንግሥቱ ጐልማሳ በሚስቱ አገዲቀና ጌታም ለአምልኮቱ ቀናዒ ነው ነውና። እስመ አነ አምላክ ቀናዒ ዘእፈዲ ኃጢአተ አብ ላዕለ ውሉድ እስከ ሣልስ ወራብዕ ትውልድ ለእለ ይጸልኡኒ። ወለእለሰ ያፈቅሩኒ እገብር ምህረተ እስከ ፲፻ ትውልድ እንዲል
ጽሑፍ ለእግዚአብሔር አምላክከ ትስግድ ወኪያሁ ባሕቲቶ ታምልክ። ለፈጣሪህ  ለእግዚአብሔር ትሰግድ ዘንድ እሱንም ብቻ ታመልክ ዘንድ ተጽፏል አለው። ሑር እምድኅሬየ ባለው ጊዜ እንደ ጢስ ተኖ እንደ ትቢያ በኖ ጠፋ አላለምን ለማን ይጠቅሰዋል ቢሉ ሰይጣንና ውሻ ምልልስ ወዳጅ ነውና ተመልሶ ይሰማዋል። አንድም እንደ አምላክነቱ አጽንቶት ሰምቶ ይሄዳል።
አንድም ወጸጋሁ ታሰምዖ እንዲል ካለበት ሁኖ እንዲሰማው አድርጎታል።
አንድም ከሐተታ ለመዳን ጥቅሱ ይቀድማል።
                  ******
፲፩፡ ወእምዝ ኀደጎ ዲያብሎስ።
፲፩፡ ከዚህ በኋላ ተወው እስከ ጊዜሁ ብሎ በሉቃስ ያቀናዋል።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
06/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment