Tuesday, March 26, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 46

 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፭።
                  ******
፳፯፡ ሰማዕክሙ ዘተብሀለ ለቀደምትክሙ ኢትዘምው። ዘፀ ፳፥፲፬።
                  ******
፳፯፡ ለቀደሙ ሰዎች አትሰስኑ የተባለውን ሰምታችኋል።
                  ******
፰፡ ወአንሰ እብለክሙ ዘርእያ ለብእሲት ወፈተዋ ወድአ ዘመወ ባቲ በልቡ።
                  ******
፰፡ እኔ ግን ሴትን ያየ ሁሉ ፈጽሞ በደለ ብዬ እነግራችኋለሁ ርእይን መከልከሉ ቢሉ አዎነ አርቆጠር ነው።
አንድም ፈተዋ ያለውን ይሻል አይቶ ባገኘኋት ቢል።
                  ******
፳፱፡ እመኒ ዓይንከ ዘየማን ታስሕተከ ምልሐ ወግድፋምላዕሌከ፡፡ ማር ፱፥፵፮። ማቴ ፲፰፥፱።
                  ******
፳፱፡ ቀኝ ዓይንህ ምክንያተ ስሕተት ብትሆንብህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት። እስመ ይኄይሰከ ነቋረከ ትባእ ውስተ መንግሥተ ሰማያት እምትባእ ውስተ እሳተ ገሃነም ምስለ ክ፪ሆን አዕይንቲከ፡፡
ዛሬ ሁለት ዓይን ኑሮህ ኋላ ገሃነም ክትገባ በዚህ ዓለም ሳለህ ከሁለት ዓይንህ አንዱ ጠፍቶ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና። ይህን ያደረጉ ብዙ ናቸው ከዚያው ግን ስምዖን ሰፉዬ አሣዕን። አንዲት ሴት ወይዘሮ መጥታ ጫማ ስፋልኝ አለችው ሰፍቶ ሰጣት  እየተመላለሰች አስቸገረችው፡፡ ጫማውን ነው ሰፍቸ ሰጥቸሻለሁ ምን ያመላልስሻል አላት። ይህ ሁሉ ምክንያት ነው አንተን ብወድህ ነው አለችው፡፡ በምን ነገር አላት። መልከ መልካም ነህና አለችው፡፡ ምኔ መልከም ነው ቢላት ሁለንተናህ መልካም ነው ይልቁንም በዓይንህ ይጸናብኛል አለችው፡፡ ትወጅዋለሽ አላት አዎን አለችው። ይህማ ምን ቁም ነገር አለው ውሀ አይደለም ብሎ በያዘው መንጐል አውጥቶ ሰጥቷታል።
                  ******
፴፡ ወእመኒ እዴከ ዘየማን ታስሕተከ ምትራ ወግድፋ እምላዕሌከ።
                  ******
፴፡ ቀኝ እጅህ ምክንያተ ስሕተት ብትሆንብህ ቈርጠህ ጣላት።
እስመ ይኄይሰከ ይታኃጐል አሐዱ እምአባልከ እምኵሉ ሥጋከ ይትወደይ ውስተ እሳተ ገሃነም።
በዚህ ዓለም ከሕዋሳትህ አንዱ ሳይጐል ኑረህ ኋላ ገሃነም ብትወርድ በዚህ ዓለም ከህዋሳትህ አንዱ ጎድሎ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና። ይህን ያደረጉ ብዙ ናቸው። ከዚያው ግን አባስ ካህነ ሮሜ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘሀገረ አንጾኪያ። አባስ ካህነ ሮሜ በተአምረ ማርያም ታውቋል አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘአንጾኪያ ቀድሞ አረማዊ ነበረ ኋላ አምኖ ተጠምቆ ተምሮ ተሾሟል። በሀገራቸው የተሾመው ፯ ቀን ቀድሶ ያቆርባል በዚያ ልማድ በመስቀል እየባረከ ሲዞር ቀድሞ በአረማዊነት ሳለ በግብር የምታውቀው ሴት መለያ ይሁነኝ ብላ እጁን ነከሰችው ጦር ተነሳበት ከዚህ ሁሉ ያደረሰችኝ ይህች እጅ አይደለችም ብሎ ከዕቃ ቤት ገብቶ እጁን ቆርጦ ጣላት፣ አባታችን ገብተህ ቀድስልን አሉት አይቻለኝም አላቸው። ሁለተኛ ገብተህ ቀድስ አሉት አይቻለኝም አላቸው፡ ይህ ሰው ወደ ቀደመ ግብሩ ተመለሰን ብለዋል፡፡ ወደ እመቤታችን አመለከተ እድ ብርህት ቀጠለችለት ገብቶ ሲቀድስ የእጁ ብርሃን እየበዘበዘ የማያሳያቸው ሆነ ወጥተው አባታችን ነገሩ ምንድነው ግለጥልን አሉት፡፡ ምንጣፋን ግለጡት አላቸው ቢገልጡት ወድቃ አገኙዋት ይህች የኔ እጅ ናት ይህች እመቤታችን የሰጠችኝ ናት ብሏቸዋል።
ወእመኒ እግርከ ዘየማን ታስሕተከ ምትራ ወግድፋ እምላዕሌከ።
ቀኝ እግርህ ምክንያተ ስሕተት ብትሆንብህ ቆርጠህ ጣላት፡፡ እስመ ይኄይሰከ ይትጐኃል ፩ዱ እምአባልከ እምኩሉ ሥጋከ ይትወደይ ውስተ እሳተ ገሃነም፡፡ በዚህ ዓለም ከሕዋሳትህ አንዱ ሳይጎድል ኑረህ ኋላ ገሃነም ክትወርድ በዚህ ዓለም ከሕዋሳትህ አንዱ ጐድሎ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና። ይህን ያደረጉ ብዙ ናቸው ከዚያው ግን አባ መርትያኖስ በዓቱ ከመንደር አጠገብ ነው ከበረሃ ውሎ ወደ ማታ  ሲመለስ ዘማት ተሰብስበው አይተው ይህ መነኮስ ኃያል ጽኑዕ ነው፡፡ የሚያስተው የለም አሉ፡፡ አንዲቱ እኔ ባስተውስ ባታስችውስ ተባብለው ተወራርደዋል።
አሁን በጊዜ የሄድኩ እንደሆነ አይቀበለኝም ብላ ሲመሽ ሒዳ እጅ ጸፋች። ወጥቶ ማነሽ አላት ከሩቅ አገር የመጣሁ የእግዚአብሔር እንግዳ ነኝ የምጠጋበት አጥቸ አውሬ ይጣላኛል ወንበዴ ይቀጠቅጠኛል ብዬ ቁሜያለሁ አለችው፡፡ እሱም ባስገባት ፆር ይነሳብኛል አይሆንም ብላት ነግደ ኮንኩ ወኢተወከፍክሙኒ ያለው ይፈርስብኛል እያለ ያወጣ ያወርድ ጀመረ። ነግደ ኮንኩ ወኢተወከፍክሙኒ ያለውስ ኪፈርስብኝ ጦሩን እታገሰዋለሁ ብሎ እሳቱን አንድዶላት እሱ እልፍ ብሎ ጸሎቱን ያዘ እሷም የምትቀባውን ትቀባ የምታጤሰውን ታጤስ ጀመር። መዓዛው ቢያስቸግረው እግሩን ከእሳቱ ማገደው የእሷን መዓዛ እስኪያጠፋው እስኪለውጠው። ምትራ ያለው ለዚህ ይመቻል፤ እሷም አባቴ አላበጀሁም ብላ ንስሐ ገብታለች፡፡
አንድም ገልጣ እንተኛ አለችው እንተኛማ ካልሽ ከእሳቱ ላይ እንተኛ አላት ይህማ ይፈጀን የለም አለችው የዚህን ዓለም እሳት ያልቻልነው የወዲያኛውንማ ዓለም እሳት እንደምን እንችለዋለን አላት፡፡ አባቴ አላበጀሁም ማረኝ ብላ ንስሐ ገብታለች እሱም አመንኵሷት በዓቱን ለቆላት ሂዷል፡፡
አንድም ዓይን የተባለች ሚስት ናት። ከዐይን የሚሠወር እንደሌለ ከሚስትም የሚሠወር የለምና። ሚስትህ ያልሆነ ሥራ ላሠራህ ብትል ፈቃዷን አፍርስባት ዛሬ በዚህ ዓለም የሚስትህን ፈቃድ ፈጽመህ ኑረህ ኋላ ገሃነም ክትገባ። በዚህ ዓለም የሚስትህን ፈቃድ አፍርሰህ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና። እጅ የተባሉ ልጆች ናቸው፡፡ ወድቆ ይነሱ በእጅ ዘግይቶ ይከብሩ በልጅ እንዲሉ። ልጆችህ ያልሆነ ሥራ እናሠራህ ቢሉ ፈቃዳቸውን አፍርስባቸው፡፡ በዚህ ዓለም የልጆችህን ፈቃድ ፈጽመህ ኑረህ ኋላ ገሃነም ክትወርድ። በዚህ ዓለም የልጆችህን ፈቃድ አፍርሰህ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና። እግር የተባሉ ቤተ ሰብእ ናቸው፡፡ ቤተ ሰቦችህ ምክንያተ ስሕተት ሁነው ያልሆነ ሥራ እናሠራሀ ቢሉ ፈቃዳቸውን አፍርስባቸው፡፡ በዚህ ዓለም የእሳቸውን ፈቃድ ፈጽመህ ኑረህ ኋላ ገሃነመ እሳት ክትገባ በዚህ ዓለም ፈቃዳቸውን አፍርሰህ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና።
አንድም እንዳይንህ እንደ እጅህ እንደ እግርህ የምትወደው ወዳጅህ ያልሆነ ሥራ አሠራሃለሁ ቢልህ ፈቃዱን አፍርስበት። በዚሀ ዓለም የሱን ፈቃድ ፈጽመህ ኑረህ ኋላ ገሃነም ክትገባ። በዚህ ዓለም የሱን ፈቃድ አፍርሰህ ኑረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና።
አንድም ምድራውያን ነገሥታት ዓይን በፍላት እጅ እግር በስለት እንዲቀጹ ሌዋውያን ካህናት ዓይንን በአንቃዕድዎ እጅን በሰፊሀ እግርን በቀዊም ሰርተው ቀጽተው እንዲኖሩ። አንተም ዓይንህን በአንቃዕድዎ እጅህን በሰፊህ አግርህን በቀዊም ሥራ ቅጻ።
                  ******
፴፩፡ ሰማዕክሙ ዘተብህለ ለቀደምትክሙ ኵሉ ዘይድኅር ብእሲቶ ይጽሐፍ ላቲ መጽሐፈ ሕዳጋቲሃ ወየሀባ። ዘዳ ፳፬፥፩፡፡ ማቴ ፲፱፥፯-፱፡፡ ማር ፲፥፬-፲፪፡፡ ሉቃ ፲፮፥፲፰፡፡ ፩፡ቆሮ ፯፥፲።
                  ******
፴፩፡ ከናንት አስቀድሞ ለነበሩ ሰዎች ሚስቱን የሚፈታ ሰው ሁሉ የምትፈታበትን ነውር የሚነግር ደብዳቤ ጽፎ ሰጥቶ ይፍታት የተባለላቸውን ሰምታችኋል። እንዳለፈው በል።
                  ******
፴፪፡ አንሰኬ እብለክሙ ከመ ኵሉ ዘይድኅር ብሲቶ ዘእንበለ ትዘሙ በላዕሌሁ ለሊሁ ረሰያ ዘማ።
                  ******
፴፪፡ እኔ ግን ሳትሰስንበት ሰነፈች ደረቀች ብሎ ሚስቱን የፈታ ሰው ሁሉ ዘማ አሰኛት ብዬ እነግራችኋለሁ።
ወዘሂ አውሰበ ኅድግተ ዘመወ በነውር የተፈታችውን ያገባ በደለ። በምን ያውቀዋል ቢሉ አቡን እጨጌ ይፍቱኝ ባለማለቷ። ኋላ እንደምን ትሁን ቢሉ የፍርድ መጽሐፍ በጕጕዓ ብሎ ወስዶታል። ንስሐ መግባቷን መምሀረ ንስሐዋ ጎረቤቶቿ መስክረውላት ታግባ ብሏል።
አንድም ሰማዕክሙ ብለህ መልስ።
ኦሪትን የሚተው ሰው ሁሉ ወንጌልን ተክቶ ይተው የወንጌልን ሥራ ሳይሠራ ግን ኦሪትን የተወ ሰው ወንጌልን ኃላፊት ሕግ አደረጋት። ከተዋትም በኋላ ወደ ኦሪት ቢመለስ በደለ ኃጥእ ተብሎ ይፈረድበታል።
አንድም መልስ። ይህን ዓለም የሚተው ሰው ሁሉ መንግሥተ ሰማያትን ተክቶ ይተው። የምናኔ ሥራ ይሥራ። ወአንሰ እብለክሙ። የምናኔ ሥራ ሳይሠራ ይህን ዓለም ተውሁ የሚል ሰው ግን መንግሥተ ሰማያትን ኃላፊት ርስት አደረጋት። ከመነነም በኋላ ወደኋላም ቢመለስ በደለ ኃጥእ ተብሎ ይፈረድበታል።
                  ******
፴፫፡ ወካዕበ ሰማዕክሙ ዘተብሀለ ለቀደምትክሙ ኢትምሐሉ በሐሰት። ወባሕቱ አግብዑ መሐላክሙ ለእግዚአብሔር። ዘሌዋ ፲፱፥፲፪፡ ዘፀ ፳፥፯፡፡ ዘዳ ፭፥፲፩፡፡ ያዕቆ ፭፥፲፪፡፡
                  ******
፴፫፡ ለቀደሙ ሰዎች በዕውነት እንጂ በሐሰት በስመ እግዚአብሔር እንጂ በስመ ጣዖት። ዳኛ ፈርዶባችሁ ባለጋራ አውርዶላችሁ እንጂ ዳኛ ሳይፈርድባችሁ ባለጋራ ሳያወርድላችሁ አትማሉ ያሏቸውን ሰምታችኋል።
                  ******
፴፬፡ ወአንሰ ብለክሙ ኢትምሐሉ ግሙራ።
፴፬፡ እኔ ግን ፈጽማችሁ አትማሉ እላችኋለሁ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
18/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment