Wednesday, March 20, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 41


 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፭።
                  ******
፭፡ ብፁዓን የዋሀን፡፡ ኢሳ ፲፩፥፪፡፡
                  ******
፭፡ ኃዳግያነ በቀል የሆኑ ከየውሃት ጠባይዓዊ የደረሱ ንዑዳን ክቡራን ናቸው። አንድም ሰውነታችንን መክረን አስተምረን ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለው በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን የሚኖሩ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡

እስመ እሙንቱ ይወርስዋ ለምድር።

ምድር መንግሥተ ሰማይን ይወርሳሉና። (ሐተታ) ምድር አላት ይህ አልፎ በዚህ የምትተካ ስለሆነች፤ ምድራውያን ጻድቃን የሚወርሷት ስለሆነ። በምድር በሠሩት ሥራ የምትወረስ ስለሆነች። በምድር ተድላ ሥጋ እንዲፈጸም በመንግሥተ ሰማይም ተድላ ነፍስ ይፊጸማልና። ወሥርዓተ እግዚእነሰ አሰፈወነ በብሂሎቱ ብፁዓን የዋሃን አስመ እመሙንቱ ይወርስዋ ለምድር ከመ ሎሙ ይእቲ መንግሥተ ሰማያት እንዲል።
                  ******
፮፡ ብፁዓን እለ ይርኅቡ ወይጸምፁ በአንተ ጽድቅ፡፡
                  ******
፮፡ አብዝተንማ ከተመገብን ሰውነታችነን ወስኖ ገቶ ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለው ከሚበሉት ከሚጠጡት ከፍለው የሚራቡ ንዑዳን ክቡራን ናቸው። እስመ ኵሉ ዘያነዲ ርእሶ እምነ መባልዕት ብዙኃት ውእቱ ይክል እኂዞተ ሥጋሁ እንዲል።

አንድም ጨርሰንማ ከተመገብነ መንግሥተ ሰማያትን በምን እንዋጃታለን ብለው ከፍለው ለነዳያን ሰጥተው የሚራቡ የሚጸሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው።

አንድም ከመብልዓ ኃጢአት የሚራቡ ከስቴ ኃጢአት የሚጸሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው።

አንድም ለፍቅሩ የሚሳሱ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው። ጸምዓት ነፍስየ ለከ እንዲል።

አንድም በመማር በማስተማር በሃይማኖት በምናኔ በንስሐ የሚራቡ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡

እስመ እሙንቱ ይፀግቡ።

የረኃብ አጸፋው ጽጋብ ነውና ይጸግቡ አለ እንጂ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና ሲል ነው፡፡ ይጸምዑ ባለው አጸፋ ይረውዩ የሚል ይገኛል።
                  ******
፯፡ ብፁዓን መሀርያን፡፡
                  ******
፯፡ ለሰው የሚያዝኑ የሚራሩ ንዑዳን ክቡራን ናቸው። (ሐተታ) ምሕረት ሥጋዊ ምሕረት መንፈሳዊ ምሕረት ነፍሳዊ አለ፡፡ ምሕረት ሥጋዊ ቀዶ ማልበስ ቆርሶ ማጉረስ ቢበድሉ ማሩኝታ ቢበደሉ ይቅርታ ነው፡፡ ምሕረት መንፈሳዊ ክፉው ምግባር በጎ ምግባር መስሎት ይዞ ሲኖር መክሮ አስተምሮ ክፉውን ምግባር አስትቶ በጎውን ምግባር ማሠራት ነው፡፡ ምሕረት ነፍሳዊ ክፉው ሃይማኖት በጎ ሃይማኖት መስሎት ይዞት ሲኖር ክፉውን ሃይማኖት አስትቶ በጎውን ሃይማኖት ማስያዝ ነው፡፡

አንድም ምህረት ሥጋዊ አይለወጥም፤ ምሕረት መንፈሳዊ ክፉውን ሃይማኖት ክፉውን ምግባር በጎ ምግባር በጎ ሃይማኖት መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምሮ ክፉውን ሃይማኖት አስትቶ በጎውን ማስያዝ፡፡ ክፉውን ምግባር አስትቶ በጎውን ማሠራት ነው። ምሕረት ነፍሳዊ መጥዎተ ርእስ ነው።

ታሪክ እንደ አንጢላርዮስ እንደ እኁ ቅዱስ፡፡ ይህ አንጢላርዮስ ባለጸጋ ነው፡፡ ንፉግ ነው፡፡ ነዳያን ሲያልፍ አይተው ይህ ጽኑ ጨካኝ ባለጸጋ ለሰው አያዝንም አሉ፡፡ አንዱ እኔ ሄጄ ሰጥቶኝ በልቼ ብመጣስ ባትመጣስ ተወራርዶ ሂዷል፡፡ ምግቡን አቅርቦ እጁን ታጥቦ በሚመገብበት ጊዜ ስመ እግዚአብሔር ጠራበት እንዳይሰጠው ተርቧል እንዳይነሣው ስመ እግዚአብሔር ጠራበት፡፡ ተናዶ ዳቦውን ወርውሮ ግንባሩን ገመሰው፡፡ ደሙን አብሶ ዳቦውን ጐርሶ ለምልክት ጥቂት ይዞ ሄደ። በዚህ ሌሊት ራእይ ያያል ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ መላእክተ ጽልመት እያዳፉ ይዘዋት ሲሄዱ መላእክተ ብርሃን ሲከተሏት እናተ ከዚህ ምን አላችሁ ሲሏቸው፡፡ ምነው ትላንት ለድኃ ሰጥቶ የለም ይሏቸዋል፡፡ መታው እንጂ መቸ ሰጠው አሏቸው፡፡ ይመስክር ተባብለው መጥተው መስክር አሉት ኦ ባዕል ትማልም ዘአጽገብከኒ አምጽኡከኑ ዝየ ወኢተዓውቀኒ ደም እምጽንዓ ረኃብ ብሎ መስክሮ ሲያስለቅቃት መላእክተ ብርሃን እጅ ሲያደርጓት አየ። ሲነጋ በዚህ ዓለም ሳሉ በገንዘብ ቢያውቁበት እንዲህ ያለ ጥቅም አለን? ብሎ ነዳያንን ሰብስቦ ያለ ገንዘቡን ጨርሶ መጽውቶ ሲሄድ ነዳያን ከመንገድ አገኙት፡፡ ገንዘብ ትሰጣለህ ቢሉን መጥተን ነበር አሉት ቀደም ብላችሁ መጥታችሁ ቢሆን ከፍዬ እሰጣችሁ ነበረ አሁንማ ጨርሻለሁ አላቸው። እንደምን እንሁን አሉት። እኔን ሸጣችሁ ተከፈሉ አላቸው። ለሠላሳ ወቄት ሸጠውታል። ከተሸጠበት አገር ከብት ያውላል ማታ የሚያልበው ደም ይሆናል። በዚህ ሰው እጅ ለመረዳት አልበቃችሁም ለማለት፡፡ ሲያርስ ውሎ ማታ ሣሩን አለምልሞ ውሀውን አፍልቆ ይመግባቸዋል፡፡ በዚህ ዕፁብ ዕፁብ ሲሉ ከተወለደ ጀምሮ ተናግሮ የማያውቅ ድዳ ሰምቶ የማያውቅ ደንቆሮ ነበር እፍ ቢለው ድዳው ተናግሯል ደንቆሮው ስምቷል በዚህ ዕፁ ሲሉ ተሰውሯል።

እኁ ቅዱስ በአሕዛብና በክርስቲያን መካከል ባለች በወሰን አገኤጲስ ቆጶስነት ተሹሞ ይኖራል። አሕዛብ ክርስቲያንን እየማረኩ ሲወስዱ ገንዘብ እየሰጠ ይመልሳቸዋል። አንዲት ድኃ ልጁዋ ተማረከባት መጥታ ገንዘብ ስጠኝ አለችው፡፡ ገንዘቤን ጨርሻለሁ እኔን ተክተሽ ልጅሽን መልሺ አላት። እሱን ተክታ ልጁዋን መልሳለች፡፡ ከሄደበት አገር የንጉሡ ልጅ ሞተችበት ኃዘን እንደጸናበት አይቶ ልጅህን ባነሣልህ ምን ባደረግህልኝ አለው፡፡ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሃለሁ አለው፡፡ ይህንንስ አልሻም ከእኔም አስቀድሞ ከእኔም በኋላ የተማረኩትን ክርስቲያን ትሰጠኝ እንደሆነ ላስነሣልህ አለው። ይሁንልህ አለው። አስነሥቶለት ከእሱም አስቀድሞ ከእሱም በኋላ የተማረኩትን ክርስቲያን ይዞ ወጥቷል። በዚህም ጌታን መስሎታል ጌታ እሱ ሰው ሳይሆን ከእሱ አስቀድሞ የነበሩትን ሰው ከሆነም በኋላ ሲኦል የወረዱትን አንድ ቀን በዕለተ ዓርብ ይዞ ለመውጣቱ ምሳሌ። አንድም በንስሐ ለሰው የሚያዝኑ ቀሳውስት ንዑዳን ክቡራን ናቸው።

እስመ ሎሙኒ ይምህርዎሙ፡፡

ለእሳቸውም ሥላሴ ያዝኑላቸዋል ይራሩላቸዋልና።
                  ******
፰፡ ብፁዓን ንጹሐነ ልብ። መዝ ፳፫፥፬፡፡
፰፡ ከንጽሐ ልቡና የደረሱ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
11/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment