Sunday, March 10, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 32


 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፫።
                  ******
፲፡ እስመ ናሁ ተሠይመ ማሕፄ ውስተ ጕንደ ዕፀው ይንበር።
                  ******
፲፡ ምሳር ዓፅቁን ከግንዱ ሊለይ ተቃጥቷልና። ማለት የእናንተን ልጅነት ከአብርሃም አባትነት ሊለይ ሥልጣነ እግዚአብሔር ተቃጥቷልና ኢይምሰልክሙ በብሂለ ዘትብሉ ላለው፤ ወንጌል ሕገ አሕዛብ ወሕዝብ ሁና ተሠርታለችና፤ እብለክሙ ከመ እግዚአብሔር ይክል አንሥኦ ውሉድ ላለው፤ መለኮት ከሥጋ ተዋሕዷልና መኑ አመረክሙ ላለው ክፉውን ሕሊና ከበጎ ሕሊና ሊለይ ሥልጣነ ክህነት ተቃጥቷልና ግበሩኬ እንከ ፍሬ ሠናየ ዘይደልወክሙ ለንሰሐ ላለው፤ ኲሉኬ ዕፅ ዘኢይፈሪ ፍሬ ሠናየ ይገዝምዎ ወውስተ እሳት ይወድይዎ፤ በጎ ፍሬ የማያፈራውን ዕፅ ሁሉ ይቈርጡታል በእሳት ያቃጥሉታል፤ በኔ ትምህርት አምኖ በጎ ሥራ የማይሠራውን ሰው ሁሉ ነፍሱን ከሥጋው ይለዩታል በገሃነም ሥቃይ ያመጡበታል፡፡
                  ******
፲፩፡ አንሰኬ አጠምቀክሙ በማይ ለንስሐ፡፡ ማር ፩፥፰፡፡ ሉቃ ፫፥፲፮፡፡ ዮሐ ፩፥፮፡፡ ግብ፡ሐዋ ፩፥፭።
                  ******
፲፩፡ በዚህ ያልተያያዘ በሉቃስ የተያያዘ ነው ባለጸጎች መጥተው ምንተ ንግበር አሉት። ዘቦ ፪ኤ ክዳናት የሀብ ፩ደ ለዘአልቦቱ ወዘሂ ቦ እክል ከማሁ ይግበር አላቸው፤ ኃጥአን መጸብሐን መጥተው ምንተ ንግበር አሉት። አልቦ ፍድፋዴ ዝትገብሩ እምዘተአዘዝክሙ አላቸው አንበሳ ወደቅ የወርቅ ተኩስ የግምጃው መከንጃ የላሙን መንጃ እያሉ የሚወስዱት አላቸውና። የደል ጭፍራ መጥተው ምንተ ንግበር አሉት። ኢትትዓገሉ ወኢትሂዱ መነሂ አላ ንበሩ በበሲሳይክሙ አላቸው ዮሐንስ አንዲህ ብሎ ማስተማሩ ክርስቶስ እንጂ ቢሆን ነው ብለዋል፡፡ እኔስ ለጠጅ ቢረሌን ለልብስ ገላን እንዲያጽቡለት ለሱ ጥምቀት በሚያበቃ ጥምቀት አጠምቃችኋለሁ ለሱ ተአምኖ ኃጣውእ በሚያበቃ ተአምኖ ኃጣውእ አስተምራችኋለሁ እንጂ ክርስቶስ አይደለሁም፡፡
ወዘይመጽእ እምድኅሬየ ውእቱ ይጸንዕ እምኔየ ከኔ በኋላ የሚመጣው እሱ ከኔ አስቀድሞ የነበረው ነው አለ። የባሕርይ አምላክ ነው። ዘኢይደልወኒ አእፁር ዓሣዕኖ ጫማውን ልይዝ የማይገባኝ።
(ሐተታ) የንጉሥን የንግሥትን ጫማ ትበቃለህ ያላሉት ሰው አይዝምና። አንድም ባሕርዩን ልመረምር ከማይቻለኝ። አንድም እሱ ከሚያደርገው ከታምራቱ ከትሩፋቱ አንዱን ላደርግ ከማይቻለኝ። አንድም አሣዕነ መርገምን ከምዕመናን ለአንዱ አርቅለት ዘንድ ከማይቻለኝ ከኔ አስቀድሞ የነበረ ነው።
ውእቱሰ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ቅዱስ ወበእሳት። እሱ ግን በጀ ብትሉ በመንፈስ ቅዱስ በጀ ባትሉ በገሃነመ እሳት ያጠምቃችኋል። ገሃነምሰ ምድር ይእቲ እንተ ኢትመልዕ ማየ እንዲል። አንድም በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ያጠምቃችኋል። (ሐተታ) መንፈስ ቅዱስን እሳት አለው፤ እሳት ምሉዕ ነው። መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና፤ እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገለጽም።
መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሊያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጅ አድሮ ሳለ አይታወቅምና እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው። ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፡፡ እሳት ጣዕምን መዓዛን ያመጸል። መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን መዓዛ ጸጋን ያመጣልና። እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል። ከመጠን ወጥቶ የሞቁት እንደሆነ ግን ያቃጥላል። መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጸፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀስፋልና፤ እሳት በላዒ ለዓማፅያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ እንዲል፤ እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋት ይቀበላልና፤ እሳት ውሀ ገደል ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል። መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋልና እሳት ዱር ይገልጸል መንፈስ ቅዱስም ምሥጢር ይገልጻልና እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ይመቻልና እሳት ከዛኅላቸው ሳይሳተፍ ሰባቱን መዓድናት ያጸራቸዋል መንፈስ ቅዱስም ከግብራቸው ሳይሳተፍ ሁሉን ያነጻልና ይእቲ ታነጽሕ ወኢትረስሕ እንዲል። እሳት ካንዱ ፋና አምሳ ስልሳ ፋና ቢያበሩለት ተከፍሎ የለበትም። መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ሲሰጥ ይኖራልና፡፤ ይእቲ ትሁብ ወኢትቀብል እንዲል በእሳት ቀድሞ ሰብአ ሰዶም ሰብአ ገሞራን ከአስራኤል አንዱን ኅብር አጥፍቶበታል ለመዓት እንጅ ለምሕረት አልተፈጠረም እንዳይሉ ለምሕረትም እንደ ተፈጠረ ለማጠየቅ፡፡ አንድም ሸክላ ሠሪ ሠርታ ስትጨርስ ነቅዕ ያገኘችበት እንደሆነ እንደ ገና መልሳ ከስክሳ በውሀ ለውሳ በእሳት ታድሰዋለች። ተሐድሶም በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ዛቲ እሳት እንተ ኮነ ይትዓፀፋ አዳም እንበለ ይትዓዶ ትእዛዘ እግዚአብሔር ፈጣሪሁ አመ ነበረ ውስተ ገነት ወሶበ በልዓ እምፅፀ ዕልወት ተዓርቀ ወኢረከባ እስከነ መጽአ አዳም ዳግማዊ ወአልበሶ እኑመ እማይ ወእመንፈስ እንዲል፡፡
                  ******
፲፪፡ ዘመሥኤ ውስተ እዴሁ ዘቦቱ ያነጽሕ ዓውደ እክሉ።
                  ******
፲፪፡ ፍሬውን ከገለባ የሚለይበት መንሽ በእጁ ተይዞ ያለ፡፡
ወያስተጋብእ ሥርናዮ ውስተ መዛግብቲሁ።
ፍሬውን ከገለባው ለይቶ በሪቅ በጎታ በጎተራ የሚሰበሰብበት ወኃሠሮሰ ያውዒ በእሳት ዘኢይጠፍዕ።፡ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት የሚያቃጥል እሱ ያጠምቀክሙ በል ወደ ወርቅ ሂዶ ዘኢይጠፍዕ አለ። አንድም ዘመሥኤ ብለህ መልስ። ጣቱ ሶስት ነው ቢሉ የሶስትነት መያዣው ያንድነት ሁለት ነው ቢሉ ንዑና ሑሩ የሚልበት ሥልጣን ገንዘቡ የሚሆን። ዘቦቱ ያነጽሕ ዓውደ እክሉ ዘውእቱ ፍጥረተ ሰብእ ብሎ ወስዶታል ሊቁ። ጸድቃንን ከኃጥአን የሚለይበት።
ወያስተጋብእ ሥርናዮ ውስተ መዛግብቲሁ። ጻድቃንን ከኃጥአን ለይቶ በመንግሥተ ሰማያት የሚያኖርበት። መዛግብት ብሎ አበዛ በብዙ ወገን ትወረሳለችና። እስመ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ወምዕራፍ ቦቱ አንዲል። ወኃሠሮሰ ያውዒ በእሳት ዘኢይጠፍዕ። ኃጥአንን ከጸድቃን ለይቶ በገሃነም ሥቃይ የሚያመጣበት ሥልጣን ገንዘቡ የሚሆን። አንድም ክፉውን ሕሊና ከበጎው ሕሊና የሚለይበት ሥልጣነ ክህነት ገንዘቡ የሚሆን። ወሥርናዮሰ በጎውን ሕሊና ከክፉ ሕሊና ለይቶ በመንፈስ ቅዱስ የሚያስጠብቅበት እሱ። መዛግብት ብሎ አበዛ ስለ ሀብቱ ብዛት ወኃሠሮሰ። ክፉውን ሕሊና ከበጎ ሕሊና ለይቶ በቀኖና የሚያጠፋበት ሥልጣነ ክህነት ገንዘቡ የሚሆን እሱ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ያጠምቃችኋል፡፡
                  ******
በእንተ ጥምቀተ እግዚእ ኢየሱስ
፡ ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምዮሐንስ፡፡ ማር፩፥፱፡፡
፡ ለጌታ ሠላሳ ሲመላው ለዮሐንስ መንፈቅ ሲተርፈው ያን ጊዜ ጌታ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
02/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment