Saturday, March 9, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 30


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
                  ******
በእንተ ስብከተ ዮሐንስ።
ምዕራፍ ፫ቱ።
                  ******
፩፡ ወበውእቱ መዋዕል በጽሐ ዮሐንስ መጥምቅ እንዘ ይሰብክ በገዳመ ይሁዳ ዘዮርዳኖስ።
                  ******
፩፡ ከመ ናዝራዊ ይሰመይ ወልድየ ብሎ ነበርና ናዝራዊ በተባለበት ወራት ቦአ ናዝሬተ ብሎ ነበርና ናዝሬት በገባበት ወራት ሐያ አምስቱን ዘመን አንድ ወገን አድርጎ ወበውእቱ መዋዕል አለ በዮሐንስ አርባውን ቀን እንዳንድ ቀን አድርጎ ወአመ ሳኒታ እንዳለ።
አንድም ወተወሊዶ ብሎ ነበርና ሥጋ በሆነበት ወራት። አንድም ለዮሐንስ ሠላሳ ሲመላው ለጌታ መንፈቅ ሲቀረው በዚያ ወራት የዮርዳኖስ አውራጃ በምትሆን በይሁዳ ምድረ በዳ ዮሐንስ መጥምቅ ሲያስተምር ደረሰ።
በገዳም አለ ቦታው ነውና። አንድም በገዳም እንጨት ሰባሪ ውሀ ቀጂ አይታጣምና። አንድም በገዳም ፆር ይቀላል ለወጣንያን አብነት ለመሆን በገዳም ፆር ይጸናል። ለፍጹማንአብነት ለመሆን። አንድም ገዳም የአይሁድ ልቡና ነው። በገዳም እህል ተክል እንዳይገኝ፤ በአይሁድም ልቡና ምግባር ሃይማኖት አይገኝምና። አንድም ኢሳይያስ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም ብሎ የተናገረልኝ እኔ ነኝ ሲል።
                  ******
፪፡ እንዘ ይብል ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት። ማር ፩፥፪። ሉቃ ፫፥፫
                  ******
፪፡ መንግሥተ ሰማያት በልጅነት ልጅነት በሃይማኖት ልትሰጥ ቀርባለችና እመኑ እያለ ሲያስተምር ደረሰ።
                  ******
፫፡ እስመ ዝንቱ ውእቱ ዘተብህለ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም። ኢሳ ፵፥፫። ማር ፩፥፫። ሉቃ ፫፥፬።
                  ******
፫፡ በገዳም የሚያስተምር አዋጅ ነጋሪ ተብሎ በኢሳይያስ ቃል የተነገረለት ይህ ዮሐንስ ነውና። ቃለ አዕዋዲ አዕዋዴ ቃል ይላል ትምርቱን ከዚያም ከዚያም የሚያደርስ ማለት ነው ቃል ዓዋዲ ይላል። ይህንንም ቃል ዘይኬልህ በገዳም ብሎ ሊቁ ወስዶታል።
ወይብል ጺሑአ ፍኖቶ ለእግዚአብሔር። የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ። ወርቱዓ ግበሩ መጽያሕቶ። ጥርጊያውን የቀና አድርጉ እያለ ሲያስተምር ደረሰ።
(ሐተታ) ንጉሥ በመጣ ጊዜ ተራራው ኮረብታው ተንዶ ጐድጓዳው መልቶ ሥሩ ተነቅሎ ደንያጊው ተለቅሞ ለፈረስ ለሠረገላ እንዲመች ተደልድሎ ይቆያልና በዚያ ግሥ ተናገረው። የእግዚአብሔር ማደሪያ ሰውነታችሁን ከኃጢአት ከጣዖት ንጹሕ አድርጉ።
                  ******
፬፡ ወልብሱ ለዮሐንስ ኮነ እምፀጕረ ገመል።
                  ******
፬፡ ዮሐንስማ እንዲህ ብሎ ማስተማሩ ነገሥታት እንጂ ካባ ላንቃ ያልብሱኝ ብሎ ነው ትሉኝ እንደሆነ ይህ ለሥጋውያን ነው። እሱ ግን መንፈሳዊ ነውና ይህን አይሻም። ዮሐንስስ የሚለብሰው የገመል ጠጕር ነበር።
(ሐተታ) ገመል ምን ጠጕር አላትና ቢሉ ከጋማዋ ከጅራቷ ቢፈልጉ አይታጣም ልብሱን ሲል ወምበዴ ይጣላዋል ብላ እናቱ ያንን አሠርታ አልብሳው ነበር። አንድም ገመል በቀለኛ ናት አጥብቆ የመታትን እስከ ፮ እስከ ፯ ዓመት አትዘነጋም ባጥ ብላ ትረግጠዋለች። ስፍራ ሲመቻት ገደል ገፍታ ትጥለዋለች። እሱም ወይወድይዎሙ ውስተ እቶነ እሳት የምትል ሕገ በቀል ወንጌልን አስተምራለሁ ሲል።
አንድም ገመል ሁለት ግብር አላት። የሚበላና የማይበላ እንደ ላምና እንደ በሬ ምንዛኅ ታወጣለች እንደ ፈረስ እንደ በቅሎ ሰኩናዋ ጽፉቅ ነው። እስመ ገመል ጽፉቅ ሰኰናሁ ወያመሰኩዕ እንዲል። እሱም ሕገ አሕዛብ ወሕዝብ ወንጌልን አስተምራለሁ ሲል።
አንድም ገመሎ የሚባል ዕፅ አለ ቆርጠው አድርቀው ከባሕር የጣሉት እንደሆነ ጭረት ይወጣዋል ያነን ታትታ አልብሳዋለች። ለጊዜው ኑሮው በገዳም ነውና ልብሱን ሲል ወምበዴ እንዳይጣላው ነው። ፍጻሜው ግን ለምዕመናን አብነት ለመሆን ተርታ ልብስ ለብሳችሁ አልባሌ መስላችሁ ኑሩ ለማለት።
ወቅናቱ ዘአዲም ውስተ ሐቌሁ ዮሐንስማ እንዲህ ብሎ ማስተማሩ ነገሥታት እንጂ የወርቅ ዝናር ያስታጥቁኝ ብሎ ነው ትሉኝ እንደሆነ። ይህ ለሥጋውያን ነው። እሱ ግን መንፈሳዊ ነውና ይኽን አይሻም። እሱስ ወገቡን የሚታጠቅበት ዓረብ ነበር። ያ ከደመ ነፍስ የተለየ እንደሆነ እሱም ከሥጋዊ ከደማዊ ግብር ልዩ ነኝ ሲል። ይኸን አስቀድሞ ከደመ ነፍስ ይለዩታል ከውሀ ይነክሩታል ኋላ ጠጕሩን ይመልጡታል ያለፉታል ቀለም ያገቡታል ከደመ ነፍስ እንዲለዩት መክሮ አስተምሮ ከሥጋዊ ከደማዊ ግብር ይለያቸዋል። ከውሀ እንደ መንከር ያጠምቃቸዋል ያስተምራቸዋል። አንደ ማልፋት ምግባር ሃይማኖት ያሠራቸዋል። ቀለም እንደ ማግባት ጸጋ ክብር ያሰጣቸዋል። ዮሐንስ ግን እንዲህ ማድረጉ ፍትወት እንስሳዊት በባሕርዩ እያለች በገቢር እንዳላወረዳት ያጠይቃል።
ወሲሳዩ አንበጣ ወመዓረ ገዳም።
ዮሐንስማ እንዲህ ብሎ ማስተማሩ ነገሥታት እንጂ ጣቦ ጋቦ ዶሮ ስቅስቆ ያብሉኝ ብሎ ነው ትሉኝ እንደ ሆነ ይህ ለሥጋውያን ነው። እሱ ግን መንፈሳዊ ነውና ይህን አይሻም። ምግቡም አንቦጣ የሚባል ቅጠል ደቁሶ ጨው ነስንሶ ነበር።
አንድም አንበጣ በልሳነ አቴና ቀምሲስ ይለዋል በኛም ሰበቦት የጋጃማ ይባላል። ወመዓረ ገዳም አለ። የማጓ ማር ይሏል አንድም አንበጣ ይላል በቁሙ አንበጣውን ይበላው ነበር። በዐረቡ እልጀራድ ይላል አንበጣ ሲል።
(ሐተታ) በዘመኑዋ እያሉ እንድታልፍ ለማጠየቅ ኦሪትን አይጠብቋትም ነበር። በ፰ ቀን ግዘሩ የምትለውን ኢያሱ በ፵ ዘመን ገዝሯል። ሶምሶን ከአፈ አንበሳ መዓር አግኝቶ ተመግቧል ከመንሰከ አድግ ውሀ ጠጥቷል። ኤልያስም በአፈ ቋዕ ሥጋ እየመጣለት ይበላ ነበር። ዮሐንስም በቁሙ አንበጣውን ይበላው ነበር። ወመዓረ ገዳም ባለው ወመዓረ ጸደና ይላል የጣዝማ ማር ይህንም ሊቁ አንበጣ ዘይቤ ልዕልና ስብከቱ ይእቲ። መዓር ዘይቤ ጣዕመ ስብከቱ ይእቲ ብሎ ተርጐሞታል።
                  ******
፭፡ ወየሐውሩ ኀቤሁ ኩሎሙ ሰብአ ይሁዳ ወኢየሩሳሌም ወኵሉ አድያሚሃ ለዮርዳኖስ። ማር ፩፥፭።
                  ******
፭፡ በኢየሩሳሌም በይሁዳ በዮርዳኖስ አውራጃ ያሉ ሰዎች ሁሉ ከሱ ዘንድ እየሄዱ።
                  ******
፮፡ ወያጠምቆሙ ለኵሎሙ በፈለገ ዮርዳኖስ እንዘ ይትአመኑ ኃጣውኢሆሙ።
፮፡ ኃጢአታቸውን እየነገሩት በዮርዳኖስ ያጠምቃዋው ነበር።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
30/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment