Saturday, March 16, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 37



 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፬።
                  ******
፲፩፡ ወእምዝ ኀደጎ ዲያብሎስ።
                  ******
፲፩፡ ከዚህ በኋላ ተወው እስከ ጊዜሁ ብሎ በሉቃስ ያቀናዋል። በዕለተ ዓርብ በአይሁድ ሥግው ሁኖ እስኪያሰቅለው ድረስ አይመለስበትም። ከዚህም በጎ ልጅ ተወልዶ ለአዳምና ለሔዋን በሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ድል ነሣላቸው። አሁን ዛሬ ደም ያለበት ሰው ጌሻ አስነሥቶ አምባውን ሰብሮ ደመኛውን ገድሎ ደሙን መልሶ ሊሄድ የቀሩት ከዛፍ ከገደል ተጠግተው የሆነስ ሆነ አንተ ማነህ እንወቅህ ባሉት ጊዜ የዘመዶቼ የእገሌ የእገሌ ደም የማይቀርብኝ እኔ እገሌ ነኝ ብሎ እንዲል። ጌታም የአባቴ የአዳም የእናቱ የሔዋን ደም የማይቀርብኝ ሲል በሦስቱ አርእስተ ኃጣውዕ ድል ነሣላቸው።
ስቱ አርእሳተ ኃጣውዕ ስስት ትዕቢት ፍቅረ ንዋይ ናቸው። ስስት ያልሰጡትን መሻት ነው። ትዕቢት አምላክ እሆናለሁ ማለት ነው። ፍቅረ ንዋይ በቃኝ አለማለት ነው። በዚህ ሁሉ ድል ነሥቶታል። ዛቲ ስፍጠት እንተ ረሰየቶ ለአዳም ይትመየጥ ውስተ መሬት ወሶበ በጽሐ ኀበ አምላኪየ ወሀቤ ሲሳይ ለኵሉ ገብዓ ሰይጣን ተኃፊሮ ወተመዊዖ እንዲል።
አንድም ድል መንሳቱ ለአዳምና ለሔዋን ብቻ አይደለም ለሁሉም ድል ነሥቶላቸዋል የመነኮሳትም ፆራቸው ስስት ነው በሹት ጊዜ አያገኙትምና በትኅርምት ኑዋሮች ናቸው በቦታቸው ከገዳም በስስት ቢመጣበት በትእግሥት ድል ነሥቶላቸዋል። የካህናት ፆራቸው ትዕቢት ነው አእምሯችን ረቂቅ ማዕርጋችን ምጡቅ እያሉ ይታበያሉ። በቦታቸውም በቤተ መቅደስ በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና ድል ነሥቶላቸዋል። የነገሥታት ፆራቸው ፍቅረ ንዋይ ነው ቤታቸውን ከፍ ካለ ቦታ ሠርተው ያለፈ ያገደመውን የወጣ የወረደውን እያዩ የዚህ ሁሉ እንጅ ኑሮው በኛ ነው እያሉ ገንዘብ ይሰበስባሉ ቦታቸው በተራራ ነው። በተራራ በፍቅረ ንዋይ ቢመጣበት በጸሊዓ ንዋይ ድል ነሥቶላቸዋል።
ከዚህ በኋላ ኃጢአት ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ሁናለች ከሥሩ የተነቀለ ዛፍ እንዳይለመልም እንዳያብብ እንዳያፈራ ኃጢአትም በፍዳ የማታሲዝ ሆናለች። ዛሬ የተያዙ አሉሳ ቢሉ እሊህማ አዋጅ አፍራሾች ናቸው። ንጉሥ ይዘምታል ድል ነሥቶ ሲመለስ ከመንገድ የወጣህ ወታደር ብሎ አዋጅ ይነግራል በደለኛ ወታደር ገንዘብ ሲዘርፍ ከመንደር ገብቶ ቢሞት ንጉሥ ድል አልነሣም ይባላልን። እኒህስ አዋጅፍራሾች ናቸው።
ወናሁ መጽኡ መላእክት ይትለአክዎ
አርባ ቀን በትሕርምት ኖሯልና መላአክት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዘው መጡ። አንድም ድል ነሥቷልና ለከ ኃይል ለከ ጽንዕ እያሉ እያመሠገኑ ቀረቡ። እንደ ዓቢይ ንጉሥ አንደ ንዑስ ንጉሥ ተሳልፈው ሰንብተዋል። ከዚህ በኋላ ሠራዊታችን ለምን ያልቃል አንድ ላንድ እንገናኝ ብለው ተገናኙ። ዓቢይ ንጉሥ ንዑስ ንጉሥን ገደለው። የዓቢይ ንጉሥ ሠራዊት ደስ ብሏቸው እየዘፈኑ ቀርበዋል። የንዑስ ንጉሥ ሠራዊት እያዘኑ እየፈሩ ሽሽተዋል።
እኒህም ድል ነሥቶላቸዋልና። መጡ አለ። ድል ከነሣ በኋላ መምጣታቸውስ ስለምን ቢሉ አስቀድመው መጥተው ቢሆን መላእክትን ይዞ ድል ነሣኝ እንጂ ብቻውንማ ቢሆን መች ድል ይነሣኝ ነበር ባለ ነበርና እንዲህ እንዳይል።
አንድም እናንተም ድል ብትነሱ ይገለጽላችኋል ለማለት። እንዳንድ ባሕታዊ ሰይጣን መጥቶ ንጉሥ ይጠራሃል አለው። አልብየ ንጉሥ ዘእንበለ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አለው። ይህ ደፋር በዓለም እያለ ንጉሥ የለም ይላል ብሎ በያዘው በሎታ ቀጥቅጦት ሄዷል። ከዚህ በኋላ መልአከ ዑቃቢው ተገለጸለት ማነህ አለው እኔ መልአከ ዑቃቢህ ነኝ አለው። እንኪያ አስካሁን ወዴት ኖረሃል አለው አሁንም ድል ብትነሣ ነው አንጂ ድል ባትነሣ አልገለጽልህም ነበር ብሎታል።
                  ******
፲፪፡ መከመ ነበረ አግዚእ ኢየሱስ በቅፍርናሆም። ወሰሚዖ እግዚእ ኢየሱስ ከመ አኀዝዎ ለዮሐንስ ተግኅሠ ውስተ ገሊላ። ማር ፩፥፲፬።
                  ******
፲፪፡ ከመ አኃዝዎ ከመ ተግኅሠ ይላል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐንስን እንዳጋዙት ዮሐንስ እንደተጋዘ በሰማ ጊዜ ገሊላ ገባ። መከራ በመጣባችሁ ጊዜ ሽሹ ለማለት አብነት ለመሆን።
                  ******
፲፫፡ ወኃደጋ ለናዝሬት ወመጺኦ ኀደረ ቅፍርናሆም እንተ መንገለ ባሕር።
                  ******
፲፫፡ ናዝሬትን ትቶ በባሕር አጠገብ ባለች በቅፍርናሆም ሲያስተምር ኖረ። ውስተ አድባረ ዛብሎን ወንፍታሌም። የዛብሎን የንፍታሌም ዕፃ በምትሆን።
                  ******
፲፬፡ ከመ ይትፈጸም ዘተብህለ በኢሳይያስ ነቢይ።
                  ******
፲፬፡ በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል የተነገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ኖረ።
                  ******
፲፭፡ እንዘ ይብል ምድረ ዛብሎን ወምድረ ንፍታሌም። ኢሳ ፱፥፩፡፡
                  ******

፲፭፡ በዛብሎን በንፍታሌም ዕፃ ያሉ ፍኖተ ባሕር። በባሕር አጠገብ ያሉ ጰራልዩ ወጰራልያስ። ጠጠር ገጠር።
ማዕዶተ ሐይቀ ዮርዳኖስ። በዮርዳኖስ ወደብ ማዶ በአንጻረ ሊባኖስ ያሉ። ገሊላ ዘአሕዛብ የአሕዛብ ክፍል ፅፃ በምትሆን በገሊላ ያሉ።
(ሐተታ) ዘሕዝብ አለና ከዚያ ሲለይ ዘአሕዛብ አለ፤ ሰሎሞን ቤተ መቅደስን በሠራ ጊዜ ወአርድአ ኪራም በዕፀወ ቄድሮስ ወጳውቂና እንዲል ጥድ ዘግባ እየጠረበ አግዞታል። ሀያ ያህል ቀላል ቀላል አህጉር ሰጠው እስመ ኢንደማሁ ይላል ደስ ባያሰኙት ወዳጄ በኔና ባንተ ዘንድ ይህ ምን ቁም ነገር ነው አለው። የመልክተኛ ማደሪያ ይሁንህ ብዬ ነው አለው ከዚህ በኋላ አሕዛብ እንደ ባለጉልት፤ እስራኤል እንደ ባለርስት ሁነው የሚኖሩ ሁነዋልና ገሊላ ዘአሕዛብ አለ።
አንድም ፈርዖን አሕዛብን ወግቶ ለልጁ ለሰሎሞን ሚስት ሰጥቷት ነበርና ገሊላ ዘአሕዛብ አለ።
                  ******
፲፮፡ ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ርእየ ብርሃነ ዓቢየ።
፲፮፡ በጨለማ ላሉ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
07/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment