Friday, March 1, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 23



                 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፪።
                  ******
በእንተ ምጽአተ ሰብአ ሰገል።
ምዕራፍ ፪።
                  ******
፩፡  ወተወሊዶ እግዚእ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ በመዋዕለ ሄሮድስ ንጉሥ ናሁ ሰብአ ሰገል መጽኡ እምብሔረ ጽባሕ። ሉቃ ፪፥፯።
                  ******
፩፡ ሄሮድስ ነግሦበት በነበረ ዘመን የይሁዳ ዕፃ በምትሆን በቤተ ልሔም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ ሳለ በተወለደ ጊዜ ከተወለደ በኋላ። ሰብአ ጥበብ ሲል ነው ጥበብ ያላቸው ሰዎች ከወደ ምሥራቅ መጡ። ገል ውስተ አፈ ንጉሥ እንዲል። አንድም መሰግላን ይላል ጥበበኞች ሰዎች ማለት ነው።
(ሐተታ) ቤተ ልሔምን አነሣ ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ብሎ የሚያመጣ ነውና። ሄሮድስን አነሣ ወአዘዘ ይቅትሉ ኵሎ ሕፃናተ ዘቤተ ልሔም ብሎ የሚያመጣ ነውና። አንድም ቤተልሔምን አነሣ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም። ትንቢት ወአንቲኒ ቤተልሔም ተብሎ ተነግሯል። ምሳሌ ካሌብ ምድረ ርስትን ሰልሎ ሲመለስ ኬብሮንን አይቶ መጥቶ ኢያሱን ኬብሮንን ስጠኝ ቀድሞ ሙሴ ሰጥቶኝ ነበር። ከአሥራ ሁለቱ ጉበኞች አንዱ እኔ ነበርኩ ያን ጊዜ ፵ ዘመን ሁኖኝ ነበር። ዛሬም ፹ ዘመን ይሆነኛል ከአንተ ጋራ መውጣት መውረድ ይቻለኛል ገና ከጉልበት ነኝ አለው። እስራኤልን አስመክሮ ሰጠው እሱዋን እጅ አድርጎ አዙባ የምትባል አገባ። ከጠላቶቹ ወገን ነበረችና በሱዋ ስም አልጠራትም። ቀጥሎ ከብታ የምትባል አገባ በከብታ ከብታ ተብላለች። ቀጥሎ ኤፍራታ የምትባል አገባ። በኤፍራታ ኤፍራታ ተብላለች። ከሱዋ ወንድ ልጅ ወለደ በዚያ ወራት እንጀራ እገበ እገባ ብሎት ነበርና ስሙንም ልሔም አለው ኅብስት ማለት ነው። ወአምጽኡ ልሔሞሙ እንዲል ኅብስቶሙ ሲል። በልሔም ቤተ ልሔም ተብላለች። ከብታ ማለት ቤተ ስብሐት ማለት ነው። ቤት የእመቤታችን ስብሐት የጌታችን ምሳሌ ኤፍራታ ማለት ፀዋሪተ ፍሬ ማለት ነው። ፀዋሪት የእመቤታችን ፍሬ የጌታችን ምሳሌ። ቤተ ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ነው። ቤት የእመቤታችን ልሔም የጌታችን ምሳሌ።
ሄሮድስን አነሳ ዘመን ትውልድ የሚቆጠር በንጉሥ ነውና። (ታሪክ) እስክንድር የሚባል ንጉሥ ነበረ እሰክንድርያ የምትባል ሴት አግብቶ አቶሮብሎስን ሕርቃሎስን ይወልዳል በሚሞትበት ጊዜ ለሚስቱ ታናሹን አንግሠሽ ታላቁን ካህን አድርገሽ ኑሪ አላት። አድልቶ አይደለም ታናሹ ሕርቃሎስ ብልህ ነው ሰው ማሳደር ያውቃል ብሎ ነው እንጂ። እንደ ነገራት አድርጋ ስትኖር ሄሮድስ ወልደ ሐንዶፌር የእስራኤልን መንግሥት በማናቸውም ምክንያት ይፈላለገው ነበርና ከታላቁ ከአትሮብሎስ ይልክበታል። ታላቅ ሳለህ ታናሽ አዋቂ ሳለሀ አላዋቂ ያነገሡብሀ በምን ምክንያት ነው? ጦርም አንሶህ እንደሆነ ከኔ ወስደህ እሱን ገድለህ ንገሥ አለው። አሱም እውነት መስሎት ጦር ተቀብሎ መጥቶ ወንድሙን ገድሎ ነገሠ። የሕርቃሎስ አርስጥአሎስ የሚባል ልጅ ነበረው በጥበብም ቢሉ ተዋግቶም ቢሉ ያጐቱን ጆሮውን ቈረጠው። እስራኤል አካሉ የጐደለ አያነግሡም ነበርና መንግሥት በመከከል ሳለ እኅታቸው ማርያ ትባላለች እሱዋን አግብቶ ነገሠ። ምንም እሱ በጥበብ በተንኮል የነገሥኩ ቢመስለው መንግሥት ከቤተ ይሁዳ አልመጣም። ኢይጠፍዕ ምስፍና ወምልክና እምአባሉ ለይሁዳ እስከ አመ ይረክብ ዘጽኑሕ ሎቱ ተብሎ የተነገረው ትንቢት እንደ ተፈጸመ ለማጠየቅ በላዩ ላይ ሰማያዊ ንጉሥ ተወለደ ለማለት ሄሮድስን አነሣው።
እምብሔረ ጽባሕ አለ ብርሃን የሚገኝ ከምሥራቅ ነው። ብርህት ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል። የምሥራቅ ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሪት ሕግ ሰራሁላችሁ ሲል። እኒህስ ምን ይዘው መጥተዋል ቢሉ ሠለስቱ መላእክት ሦስቱን ንዋያት ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ለአዳም ሰጡት። አዳም ንሥኢ ሕፄኪ ብሎ ለሔዋን ሰጣት። ከዚያ ሲወርድ ሲዋረድ ከአባታቸው እጅ ገብቷል። ዥረደሽት የሚባል ፈላስፋ አባት ነበራቸው። በቀትር ጊዜ ከነቅዓ ማይ አጠገብ ሁኖ ፍልስፍና ሲመለከት ድንግል በሰሌዳ ኮከብ ተሥላ ሕጻን ታቅፋ አየ። ፈጥኖ በሰሌዳ ብርት ቀርፆ አኖረው። በሚሞትበት ጊዜ እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ስጡ ብሏቸው ነበርና ያን ሰምተው ይዘው መጥተዋል። አንድም ዘእምዘመዱ ለበለዓም እንጂ ይላቸዋል። በለዓም ኮከብ ይሠርቅ እምያዕቆብ ያለውን ሰምተው ይዘው መጥተዋል። አንድም ትሩፋን ባቢሎን ሳሉ ነገሥተ ተርሴስ ወደሰያት አምኃ ያበውኡ ነገሥተ ሳባ ወዓረብ ጋዳ ያመጽኡ እያሉ ሲጸልዩ ይሰሙ ነበርና ይህን ይዘው መጥተዋል።
አንድም ባሮክ አቴና ወርዶ አሥራ ሦስት ያህል ልሳን ተምሯል ያን ጊዜ ዛሬ የሀገራችሁ ንጉሥ የሚገበረውን ወርቅ ኋላ በሀገራችን ከኛ ወገን ንጉሥ ተወልዶ ይገበረዋል ብሎ ነግሯቸው ነበርና ይህንን ይዘው መጥተዋል። አንድም ዳንኤል መቅደስ ትትሐነጽ እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ወእምዝ ትትመዘበር ያለውን ሰምተው ይዘው መጥተዋል። አንድም ዳንኤልን ምንም እሱን ሰውነቱን ባይወዱት ነገሩን ይቀበሉት ነበርና ዛሬ የናንተ ሀገር ንጉሥ የሚገበረውን ኋላ ከኛ ወገን ንጉሥ ተወልዶ ይገበረዋል ብሎ ነግሯቸው ነበርና ይህን ሰምተው ይዘው መጥተዋል።
ለነዚህስ እንዲገለጽላቸው ያደረገ ስለምን ቢሉ ይሹት ነበርና ለፍቅሩ ይሳሱ ነባርና። ክሕደት በነዚህ ጸንቶ ነበርና። ክሕደትም ወደጸናበት መሄድ ልማድ ነው አሁን በመዋዕለ ስደቱ ክህደት ወደ ጸናባቸው ወደ ግብፅ ሄደ ብሎ እንዲያመጣው በእስራኤል ዘለፋ ለአሕዛብ ተስፋ ለመሆን እኛስ እንኳ አውቀን ስንመጣ እስካሁን ሳያውቁት ኑረው ብለው። አንደም ከመ ይንሣእ ንዋየ አቡሁ እንጂ ይላል ያባቱን ገንዘብ ለመቀበል። አሶር የአክዩ በዕብራውያን ወዕብራውያን የአክዩ በአሦር እንዲል። ነገሥተ ፋርስ ለፀብዕ እንጂ ለፍቅር አይመጣም ነበርና በጌታ ልደት ፍቅር እንደ ተጀመረ ለማጠየቅ
                  ******
፪፡ ወበጽሑ ውስተ ኢየሩሳሌም እንዘ ይብሉ አይቴ ሀሎ ዘተወልደ ንጉሠ አይሁድ።
፪፡ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥወዴት አለ እያሉ ኢየሩሳሌም ደረሱ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
23/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment