Monday, March 4, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 26



 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፪።
(ቊጥር ፲፩ ስል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አመጣጥ የሚናገረው ቀጣዩ ክፍል።)
                  ******
… ይህስ ከወዴት የመጣ ነው ቢሉ ሦስቱ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሩፋኤል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ለአዳም ሰጡት።
አዳም ንሥኢ ሕጼኪ ብሎ ለሔዋን ሰጣት ሔዋን ለሴት ሰጠችው ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ ከኖኅ ደርሱአል። ኖኅ ከመርከብ ሲገባ ይዞት ገብቷል ሲወጣም ይዞት ወጥቷል በሚሞትበት ጊዜ ሴምን ልጁን ከወንድምህ ከካም ወገን ደግ ልጅ ይወለዳልና ካባት ከናቱ አሰናብተህ ወርቁን ዕጣኑን ከርቤውን አጽመ አበውን አስጠብቀው ሥርዓት ሥራበት ብሎታል። ከአባት ከናቱ አሰናብቶ ወርቁን ዕጣኑን ከርቤውን አሸክሞ ሲሄድ ወንድሞቹ ያፌትና ካም ተከተሉት። እናንተ አልታዘዛችሁም የታዘዝን እኛ ነን ተመለሱ አላቸው ተመለሱ። መልአክ ተገልጾ እየመራቸው ሄዱ ዱዳሌም ሲደርሱ ጐድጓዳ ቦታ አገኙ ዓጽመ አበውን ቀብሮ ሦስቱን ንዋያት ሰጥቶ ሥርዓት ይሠራበታል። ከሴት አትድረስ ዳባ ልበስ ሥጋ አትብላ ጠጅ አትጠጣ ራስክን አትላጭ ጥፍርህን አትቊረጥ በስንዴ በወይን አስታኩት ብሎ። እንዲህ ሁኖ ሲኖር አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ ደስ ቢለው በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርእየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ አለው። እሱንስ አታየውም ምሳሌውን ታያለህና ሑር ዕድዎ ለዮርዳኖስ። ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሂድ አለው።
ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሄድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል። መልክ ጼዴቅ የቀሳውስት አብርሃም የምዕመናን ኅብስት የሥጋው ጽዋዕ የደሙ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ፡፡ በዚህ ጊዜ መልከ ጼዴቅ ወርቁን ዕጣኑን ከርቤውን ለአብርሃም ሰጠው። ከአብርሃም ለይስሐቅ ከይስሐቅ ለያዕቆብ ደርስዋል።
ያዕቆብ ወደ ግብፅ ሲወርድ ይዞት ወርዷል ሲወጣም ይዞት ወጥቷል። ከያዕቆብ ሲወርድ ሲዋረድ ከዕሤይ ደርሰዋል። ከዕሤይ ለዳዊት ከዳዊት ለሰሎሞን ከሰሎሞን ለሮብዓም ደርስዋል። በሮብዓም ጊዜ መንግሥት ከሁለት ተከፈለ። ኢዮርብዓም ወልደ ናባጥ በዐሥሩ ነገድ በሰማርያ። ሮብዓም በሁለቱ ነገድ በኢየሩሳሌም ነገሡ ሁለቱ ቢጣሉ ሱስቀም ንጉሠ ግብፅ ለኢዮርብዓም ረዳት ሁኖ መጥቶ ሮብዓምን ወግቶ ግብፅ ይዞት ወርዷ። ይህም ብቻ አይደለም ሰሎሞን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲገባ ብላቴኖቹ ይዘው የሚከተሉት ሦስት መቶ የወርቅ ጋሻስት መቶ የወርቅ ጦር የወርቅ ሾተል አሠርቶ ነበር ይሀን ሁሉ አውርዶታል።
ከግብጽ ባቢሎን እንደምን ይወርዳል ቢሉ ናቡከደነፆር ፈርዖንን ኒካዑን ገድሎ ሦስት ዓመት ባቢሎን ዘግብፅ አሰኝቶ ሲሄድ ከግብፅ ባቢሎን ይዞት ወርዷል። ከዚያ አግኝተው ይዘው መጥተዋል። ሊረዳውስ መጥቶ አይወስድበትም አሕዛብ የሰው ከብት ናቂዎች ናቸውና ብሎ ሮብዓምን ወግቶ ለኢዮርብዓም ሰጥቶት ይሄዳል። ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ሰማርያ ይዞት ወርዷል። ስልምናሰር ዓሥሩን ነገድ በማረከ ጊዜ ፋርስ ባቢሎን ይዞት ወርድዋል። ከዚያ አግኝተው ይዘው መጥተዋል።
አንድም አሜስያስ በሁለቱ ነገድ በኢየሩሳሌም ዮአስ በዐሥሩ ነገድ በሰማርያ ነገሠ፤ አሜስያስ ንጉሠ ኤዶምያስን ወግቶ ሲመለስ ኃይል ቢሰማው ነዓ ንትረዓይ ገጸ በገጽ ብሎ በዮአስ ላከበት። እሱም እስመሁ ሞዕኮሙ ለኤዶምያስ ተዝኅረኑ ልብከ አቃኒ ዘውስተ ዕፅ ለአከት ኀበ ዕፀወ ቄድሮስ እንዘ ትብል ሀቦ ወለተከ ለወልድየ ወመጽኡ ዓራዊተ ገዳም ወኬድዋ ለዓቃኒ ብሎ ገሥግሦ ሂዶ ገጠመው ድል አድርጎታል በአንቀጸ ኤፍሬም አራት መቶ ክንድ አደባባይ አለ በዚያ አስጎትቶታል ነገሥተ እስራኤል ኃያላን ነን ነገሥተ ይሁዳ ድኩማን ናቸው ሲል። በዚህ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ሰማርያ አውርዶ ቃል። ከሰማርያ ስልምናሶር ዓሥሩን ነገድ በማረከ ጊዜ ፋርስ አውርዶታል። ከዚያ አግኝተው ይዘው መጥተዋል። ይህማ እንዳይሆን ዘእንበለ ያእምር ሕፃን ስምየ አቡሁ ወእሙ ይኔሥእይለ ደማስቆ ወምህርካ ሶርያ ይትካፈል ይላልሳ ቢሉ ወርቁ እንጂ ብዙ ነው ከዚያም ከዚያም ደርሱዋል።
አንድም አሣ በሁለቱ ነገድ በአስ በዓሥሩ ነገድ ነግሠው ሳሉ የአሳ ሬማ የምትባል መውጫ መግቢያ ነበረችው። ባኦስ ሂዶ ቀጸረበት በዚህ አዝኖ ሳለ በዚህን ታዝናለህ ከወልደ አዴር ጋራ ሊወጋህ ተማምሎብሃል አሉት። ኅድግአ ኪዳነ ዘተካየድከ ምስለ በአስ ብሎ ከቤተ እግዚአብሔር ዕቃቤት ከቤተ መንግሥት ዕቃቤት የተገኘውን ወርቅ ጨምሮ ለወልደ አዴር ወልደ ጤዲርማን ወልደ አዚን ወልደ አዛሄል ንጉሠ ሶርያ ይሰድለታል። በዚህ ጊዜ ሶርያ ይወርዳል።
አንድም ኢዮአስ በሁለቱ ነገድ ነግሦ ሳለ አዛሄል ሰባት ያህል አኅጉር ወግቶ መጥቶ ከዳር ሰፍሮ ገብር አለው፡፡ አቱአ አግዚእየ ዘአፆርከኒ እፀውር ብሎ ከቤተ እግዚአብሔር ዕቃቤት ከቤተ መንግሥት ዕቃቤት የተገኘውን ወርቅ ሰዶለታል ሶርያ ይወርዳል። ከሶርያ ፋርስ ባቢሎን እንደምን ይወርዳል ቢሉ ቴልጌልቴልፌልሶር በፋርስ ረዓሶን በሶርያ ፋቁሄ ወልደ ሮሜልዩ በሰማርያ አካዝ በኢየሩሳሌም ነግሠዋል በሶርያና በሰማርያ መካከል ሬማት ዘገለዓድ የምትባል አገር አለች የሶርያው ሲበረታ ወደ ሶርያ የሰማርያው ሲበረታ ወደ ሰማርያ የምትገዛ እንደ ዋግ ያለች ናት ዋግ የትግሬው ሲበረታ ወደ ትግሬ የበጌምድሩ ሲበረታ ወደ በጌምድር ትገዛ እንደ ነበረ። በዚህ ጊዜ በፋቁሄ እጅ ገበረች። እሱም ይህችን አገር ላንተ እሰጥሃለሁ ላባቶቼ ሲገዙ የነበሩ ሁለቱ ነገድ አምጸውብኛልና እነዚያን አስገዛኝ ብሎ ከረዓሶን ላከበት በዚህ ተማምለው ሁለቱ አንድ ሁነው ወደ ኢየሩሳሌም ዘመቱ። ወሶበ ሰምዓ ዝንቱ ዳዊት ደንገፀት ነፍሱ ወነፍሰ ኵሉ ሕዝቡ እንዲል። አካዝ ይህን ሰምቶ ገብርከኒ ወወልድከኒ። በግድ ባሯህ በፈቃድ ልጅህ ነኝና። እርዳኝ ብሎ ከቴልጌልቱልፌልሶር ዘንድ ላከበት እሱም ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብሎ ዘመተ። ሶርያ ሲደርስ ይህች አገር የማናት ብሎ ጠየቀ የረአስን አሉት። እሱ ወዴት ሂዷል አለ አካዝን ሊወጋ ኢየሩሳሌም ሂደል አሉት የአካዝን ብላቴና ጥሩ ብሎ አስጠርቶ ጌታህ እርዳኝ ብሎ የላከብኝ ወዴት ድረስ ነው አለው። ኢየሩሳሌም ድረስ አለው። ልጅ እንጂ ቢሆን የጦር መላ በያውቅ ብሎ ተኩስ ዝረፍ አለ። የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች አንዲሉ። የሰው አገር እንወጋለን ብላችሁ አገራችሁ ተወጋላችሁ አሏቸው። ተመልሰው ገጠሙት ረዓሶን በነፍጥ ተመቶ ከዚያው ሙቷል። ፋቁሄ ተመቶ ካገሩ ይሞታል። በዚህ ጊዜ ቴልጌልቴልፌልዕር ከሶርያ ፋርስ አውርዶታል። ከዚያ አግኝተው ይዘው መጥተዋል አምጥተው ለእመቤታችን ሰጧት። እመቤታችንም ተቀብላ ከፍላ ለነዳያን መጽውታለት ለቅዱስ ጴጥሮስ ሰጥታዋለች። ቅዱስ ጴጥሮስም ከፍሎ ለነዳያን መጽውቶለት ለቀሌምንጦስ ሰጥቶታል ቀሌምንጦስ ከፍሎ ለነዳያን መጽውቶለት ከስምንቱ መጻሕፍት ጋራ በአንቀጸ ሮም ቀብሮታል። እነዚህስ ምን ተነሥተው ምን ጊዜ ደርሰዋል ቢሉ ለልደት ሁለት ዓመት ሲቀረው ተነሥተው የልደት ለት ደርሰዋል ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ ኤጲፋንዮስ ዮም ተወልደ ይላልና። ይህማ እንዳይሆን እመቤታችን ሰብአ ስገልን ሸኝታ አልዋለችም አላደረችም ወዲያው መንገድ ጀመረች ይላል በስምንት ቀን ቤተ ግዝረት መግባት ባርባ ቀን ዕጒለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዞ ቤተ መቅደስ መግባት ይቀር የለም ቢሉ አይቀርም።
ቄሣር በግብር ምክንያት አስጠርቶት ሮም ሁለት ዓመት ኑሮ ይመለሣል ከዚያ በኋላ ነገሩን ያነሳዋል። አንድም መንፈስ ቅዱስ ሁለት ዓመት ነገሩን አዘንግቶት ከዚህ በኋላ ያነሣዋል። አንድም የልደት ዕለት ተነሥተው በሁለት ዓመት ደርሰዋል። ወሠሊጦሙ ግብሮሙ አተዉ ሀገሮሙ ናዝሬተ ይላል። ወዴት አግኝተው ይሰጧታል ቢሉ በአድባረ ሊባኖስ ሳለች ባመት ባመት ለገቢረ በዓል ትወጣ ነበርና ከዚያ አግኝተው ይሰጧታል። ኤጲፋንዮስ ዮም ተወልደ ይላልሳ ቢሉ እንደ ዛሬ ደብተራ ባመት ባመቱ ዮም ተወልደ እንዲል።
ወርቅ ያመጣ የሴም ወገን ነው መንግሥት ከሴ ወገን ነውና። ዕጣን ያመጣ የያፌት ወገን ነው ካህናት ከያፌት ወገን ይበዛሉና። ከርቤ ያመጣ የካም ወገን ነው ምዕመናን ከካም ወገን ይበዛሉና። ወርቅ ያመጣ የኻያ ዓመት ነው መንግሥት ከዚህ በላይ በ፴ ዘመን ይገባል ለማለት። ዕጣን ያመጣ ያርባ ዘመን ነው መንፈሳዊ ሹመት ከዚህ በላይ ባምሳ ዘመን ይገባል ለማለት። ከርቤ ያመጣ የ፷ ዘመን ነው ከዚህ በላይ ሞት ያጠራጥራልና።
ለነዚሀም ለሕፃኑ በአምሳለ ሕፃን፤ ለወሬዛው በአምሳለ ወሬዛ፤ ለአረጋዊው በአምሳለ አረጋዊ ታይቷቸዋል። ወጥተው ሲሄዱ አንዱ መልካም ብላቴና አለ። መልካም ጐልማሳ እንጂ መልካም አረጋዊ እንጂ ተባብለው ተመልሰው ቢገቡ በአምሳለ ሕፃን ለታየው በአምሳለ ወሬዛ፤ በአምሳለ ወሬዛ ለታየው በአምሳለ አረጋዊ፤ በአምላለ አረጋዊ ለታየው በአምሳለ ሕፃን ታይቷቸዋል። ከዚህ በኋላ ወጥተው ነገር እንዳንተ መልካም ብላቴና አለው። እንዳንተ መልካም ጐልማላ እንጂ እንዳንተ መልካም አረጋዊ እንጂ ተባብለዋል። መልአኩ እንደሁላችሁም ነው አትጣሉ አላቸው። ማየትንስ መስማት አያስረዳውም ብለው ተመልሰው ቢገቡ በአምሳለ ሕፃን ለታየው በአምሳለ አረጋዊ በአምሳለ አረጋዊ ለታየው በአምሳለ ወሬዛ በአምሳለ ወሬዛ ለታየው በአምሳለ ሕፃን ታይቷቸው ለሁሉም ሶስት ሶስት መልክ ደርሷቸው ፍጹም አምላክነቱን በዚህ ተረድተው ሂደዋል።
እነዚህስ ክብር አላቸው ቢሉ የላቸውም። ዕድግተ በለዓምን ዕብነ ሆሣዕናን እንዳናገረ የታምራት ነውይህማ እንዳይሆን እመቦ ዘአክበረ ልደተ እግዚአ ይከውን ክብሩ ምስለ ሰብአ ሰገል ይላልሳ ብሎ ክብር ያላቸው ናቸው ይህም ሊታወቅ ወአስነቀቶሙ ኅብስተ ሰገም ይላል እመቤታችን ሐሪፀ ሰገም ስንቅ ሰጥታ ሰደደቻቸው ዕልፍ ዕልፍ ሠራዊት እየተመገበለት ባያልቅ አገራቸው ሲደርሱ ደግን ነገር ከከተማ ይዞ መግባት አይገባም ብለው ከከተማ በአፍአ ትተውት ገቡ። ደርሳችሁ መጣችሁን አሏቸው፤ አዎን አሉ። ምን ምልክት አላችሁ አሏቸው፤ እነሱም ምልክታቸውን እንዲህ ብለው ተናገሩ ሁለት ዓመት የሄድነውን በ፵ ቀን ገባንናቱ ስንቅ ሰጥታን ይህ ሁሉ ሠራዊት እየተመገበው ባያልቅ ክቡር ነገር ነውና ከከተማ ይዞ መግባት አይገባም ብለን በአፍአ ትተነው መጥተናል አሏቸው።
አስኪ አሳዩን አላቸው ቢሄዱ ሲጤስ ሲነድ ተገኝቷል። ከዚህ የተነሣ በእሳት እንጂ አምልኩ ሲለን ነው ብለው እሳት የሚያመልኩ ሁነዋል። ናትናኤል ሀገረ ስብከቱ ከዚያ ነውና። ይኸስ የታምራት ነው ሰማዩን ምድሩን ባሕሩን የብሱን በፈጠረ በእግዚአብሔር እመኑ ብሎ አስተምሮ አሳምኖ አጥምቋቸዋልና ክብር ያላችው ናቸው።
                  ******
፲፪፡ ወነገሮሙ በህልም ከመ ኢይግ ብኡ ኅበ ሄሮድስ።
፲፪፡ በሄሮድስ በኵል አንዳይመለሱ በራእይ ነገራቸው።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
26/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment