Sunday, March 31, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 51


====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፮።
                  ******
፱፡ አንትሙሰ ሶበ ትጼልዩ ከመዝ በሉ። ሉቃ ፲፩፥፪፡፡
                  ******
፱፡ እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ።
(ሐተታ) አብዝታችሁ አትጸልዩ ብሎ ነበርና አጭር ጸሎት፡፡ ጩኸችሁ አትጸልዩ ብሎ ነበርና የሕሊና ጸሎት፡፡ ቋሚ ለጓሚ ገረድ ደንገጽር ሲቆሙ ሲቀመጡ ሲተኙ ሲነሱ የሚጸልዩት አጭር ጸሎት ሠራልን።
አቡነ ዘበሰማያት።
በሰማይ ያለህ አባታችን። አቡነ በሉኝ አለ አምላክነ እግዚእነ መምህርነ በሉኝ አላለም። ቀድሞ ነቢያት ከግብርናተ ዲያብሎስ እንዳልወጡ ሲያጠይቁ አምላክነ እያሉ ይጸልዩ ነበር። እኛ ግን ከግብርናተ ዲያብሎስ እንዳወጣን ሲያጠይቅ አቡነ በሉኝ አለ፡፡ እግዚእነ መምህርነ በሉኝ አላለም፡፡ ጌታ ሎሌውን መምህር ደቀ መዝሙሩን ቢወደው ያበላዋል ያጠጣዋል የልቡናውንም ምሥጢር ያጫውተዋል እንጂ። ርስቱን አያወርሰውም። ርስቱን ግን የሚያወርስ ለልጁ ነው። እሱ ግን የማታልፍ ርስቱን መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናልና፡፡
አንድም ወበከመ ይምህር አብ ውሉዶ ከማሁ ይምህሮሙ እግዚአብሔር ለአለ ይፈርህዎ እንዲል አባት ለልጁ እንዲራራ ይራራልናልና። ዘበሰማያት አለ ከምድራዊ አባት ሲለይ። ምድራዊ አባት ሲወልድ በግዘፍ ሲያሳድግ በግዘፍ ነው፡፡ ኋላም ኃላፊ ርስቱን ያወርሰዋል ኋላ ሞትን ያስከትልበታል። እሱ ግን ሲወልደን በረቂቅ ሲያሳድገንም በረቂቅ ነው፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናል ኋላም ሐይዉ ከመ መላእክትን ያስከትልልናልና፡፡
አንድም ጌታ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን ስለ ልዕልናው በሰማይ አለ ይባላልና። ዘበአንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት እንዲል፡፡
አንድም ጸሎቱ በሰቂለ ሕሊና ይሁን ሲል እንዲህ አለ።
ይትቀደስ ስምከ።
ስመ ወላዲ ስመ ተወላዲ ስመ ሠራዊ ይለይልን በሉኝ።
አንድም ስምየሰ መሐሪ ወመስተሣህል ያልኸው ይጽናልን በሉኝ።
አንድም መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ስምህን አመስግነው ቅድስናህን ተሳትፈው እንደዲኖሩ። እኛም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለን አመስግነንሀ ቅድስናህን ተሳትፈን እንድንኖር አድርገን በሉኝ አለ።
                  ******
፲፡ ትምጻእ መንግሥትከ፡፡
                  ******
፲፡ መንግሥተ ሰማይ ትምጻልን በሉኝ። ትምጻእ ማለቱ ግን ከወዲያ ያለች ከወዲህ የሌለች ሁና ከወዲያ ወዲህ የምትመጣ፤ ከወዲህ ያለች ከወዲያ የሌለች ሁና ከወዲህ ወዲያ የምትሄድ ሁና አይደለም፡፡ ትገለጽልን በሉኝ ሲል ነው እንጂ። አኮ እምካልእ መካን ዘይመጽእ ለአስተርእዮ ኀቤሆሙ አላ ሀሉ ኅቡዓ ወምሉዓ ማዕከሌሆሙ ወውሣጤሆሙ እንዲል።
አንድም ልጅነት ትሰጠን በሉኝ ሲል ነው። መተርጉምኒ ሰመያ ለትምጻእ መንግሥትከ ሱታፌ መንፈስ እንዲል።
ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ።
መላእክት በሰማይ ሊያመሰግኑህ ፈቃድህ እንደሆነ እኛም እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን በሉኝ።
አንድም ኋላ ሙተን ተነሥተን ልናመሠግንህ ፈቃድህ እንደሆነ ዛሬም በሕ
ይወተ ሥጋ ሳለን እናመሰግንህ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን በሉኝ። ከማሁ ማንሻ፡፡
አንድም መላእክት በሰማይ አመስግነውህ ያው ምስጋናው ምግብ ሆኑዋቸው እንዲኖር።
                  ******
፲፩፡ ከማሁ በምድር ሲሳየነ ዘለለዕለትነ ሀበነ ዮም። ዘፍጥ ፳፰፥፳፡፡ ምሳ ፴፥፰፡፡ ፩፡ጢሞ ፮፥፰፡፡ ማር ይስ ፲፪ ም።
                  ******
፲፩፡ ለእኛም በዚህ ዓለም ሳለን የዕለት ምግባችንን ስጠን በሉኝ። በዚህም መጻሕፍት ተባብረውበታል። ያዕቆብ በኦሪት እምከመ ረከብኩ እክለ ዘእበልዕ ወልብሰ ዘእትኤረዝ ይከውነኒ እግዚአብሔር አምላኪየ ብሏል። ጳውሎስም እምከመ ረከብነ ሲሳየነ ወአራዘነ የአክለነ ብሏል። ሠለስቱ ምዕትም በሕንፃ መነኮሳት ኢትኩን መፍቀሬ ወርቅ ወብሩር ዘእንበለ በአምጣን ዘየአክል ለሕይወትከ ለሲሳይከ ወለአራዝከ በአቅም ብለዋል። ማር ይስሐቅም እመቦ ዘተርፈ እምፍቅደ ዕለትከ ሀቦ ለነዳይ ብሏል። ለፍጹማን የሆነ እንደሆነ በቁሙ የዕለት ምግብ ነው። ለሰብአ ዓለም ግን ያመት ልብስ ያመት ምግብ ዘር አስቀርቶ የቀረውን መስጠት ነው።
አንድም ሥጋህን ደምህን ንስሐን ትምርትን ዓስበ ጸሎታችንን ስጠን ባሉኝ።
                  ******
፲፪፡ ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንሕነኒ ንኅድግ ለዘአበሰ ለነ።
                  ******
፲፪፡ እኛም የበደለንን ይቅር እንል ዘንድ በደላችንን ይቅር በለን በሉኝ። ይህማ ማስተላለክ አይሆንም ቢሉ አይሆንም ሰው ይቅር ማለቱ እኔንም እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል ብሎ ነውና።
አንድም ከአኃው አንዱ ተነሥቶ አብሑኒ ከመ እወስከ አሐደ ቃለ ላዕለ አቡነ ዘበሰማያት አላቸው። አባሕናከ ንብብ አሉት፡፡ ረስየነ ያለበት ነው ብሏል፡፡ ይቅር ማለቱ ቅሉ ያለአንተ ፈቃድ አይሆንም ሲል፡፡
                  ******
፲፫፡ ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት፡፡
                  ******
፲፫፡ አቤቱ ወደ ኃጠአት ወደ ክህደት ወደ መከራ ወደ ገሃነም አታግባን በሉኝ።
አላ አድኅነነ ወባልሃነ አምኵሉ አኩይ።
ከኃጢአት ከክህደት ከመከራ ከገሃነም አድነን እንጂ።
እስመ ዚአከ ይእቲ መንግሥት መንግሥተ ሰማይ ገንዘብህ ናትና፡፡
ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም።
ከሃሊነት ጌትነት ለዘላለሙ ገንዘብህ ናትና።
አሜን፡፡
በእውነት።
                  ******
፲፬፡ እስመ ለእመ ኃደግሙ ለሰብእ አበሳሆሙ የኃድግ ለክሙኒ አበሳክሙ አቡክሙ ሰማያዊ። ሲራክ ፳፰፥፫። ማቴ ፲፰፥፴፭፡፡ ማር ፲፩፥፳፭፡፡
፲፬፡ እናንተ ይቅር ብትሉ ሰማያዊ አባታችሁ የናንተንም ኃጢአት ይቅር ይላችኋልና ይቅር ይላችሁ ዘንድ ይቅር በሉ።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
23/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment