Sunday, March 3, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 25



 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፪።
                  ******
፯፡ ወእምዝ ጸውፆሙ ሄሮድስ ለሰብአ ሰገል ጽሚተ።
                  ******
፯፡ ከዚህ በኋላ ሰብአ ሰገልን በቆይታ ጸራቸው። ካህናትን ጠይቆ ባዳራሽ አውጥቶ ሰብአ ሰገልን በእልፍኝ ጠራቸው። አሁን ከእኛ ጠይቆ ይነግራቸዋል እንዳይሉት። አንድም ካህናትን በእልፍኝ አስወጥቶ ሰብአ ሰገልን በአዳራሽ አስጠራቸው። ይኸውም ውዳሴ ከንቱ ሽቶ ነው። እኛስ እንኳ አውቀን ስንመጣ እሱ ከዚህ ሁኖ እስከ ዛሬ ሳይሰማ ኑሯል ይሉኛል ብሎ።
ወተጠየቀ እምኔሆሙ መዋዕሊሁ በዘአስተርአዮሙ ኮከብ። ኮከብ የታየበትን ቀን ጠየቃቸው። አንድም ኮከቡ በታየበት ቀን የጌታን ዘመኑን አውቆ ተረዳው። ይህን ኮከብ ከአያችሁ ምን ያህል ዘመን ሁኖታል አላቸው። ሁለት ዓመት ሁኖታል አሉት። ለካ ያም ብላቴና ሁለት ዓመት ሁኖታል አለ።
                  ******
፰፡ ወፈነዎሙ ኀበ ቤተ ልሔም።
                  ******
፰፡  ቤተ ልሔም ነው ብሎ ሰደዳቸው።
ወይቤሎሙ ሐዊረክሙ ተሰአሉ ጥዩቀ በእንተ ውእቱ ሕፃን ወእምከመ ረከብክምዎ ግብኡ ኀቤየ ወዜንዉኒ።
ሂዳችሁ የብላቴናውን ነገር ጠይቃችሁ ድርሱን ያገኛችሁት እንደሆነ በኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ አላቸው።
ከመ እምጻእ አነሂ ወእስግድ ሎቱ። እኔም መጥቼ እሰግደለት ዘንድ። ለሄሮድሳውያን ጒሕሉት ልማዳቸው ነውና እስግድ ሎቱ አለ እንጂ። እቅትሎ ሲል ነው (ሐተታ) እንዲህማ ከማለት ተቀድሞ ሄዶ አይነግራቸውምን ቢሉ ካህናቱ ዘመዶቹ ናቸውና ልከው ያሸሹብኛል ብሎ። በአንድ ሂዶ አይገድለውም ነበር ቢሉ ሰብአ ሰገል ይገላግሉኛል ብሎ። አይሆንም ያልኋቸው እንደሆነ ዕልፍ ዕልፍ ሠራዊት አስከትለው መጥተዋል አግባ መልስ ብለው ይጻሉኛል ብሎ። አንድም እኛ ብቻ መስሎን የሀገሩም ነገሥታት ያምኑበታልሳ ብለው የሰብአ ሰገል ሃይማኖታቸው እንዲጸናላቸው። መንፈስ ቅዱስ አፉን ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ አናገረው።
ወሰሚዖሙ ሖሩ እምኀበ ንጉሥ።
ቤተ ልሔም ነው ያላቸውን ሰምተው ወተአዚዞሙ ይላል። ወእምከመ ረከብክምዎ ግብኡ ኀቤየ ያላቸውን ሰምተው ንጉሥ ነውና ይበጅ ያድርግ ብለው ሄዱ።
                  ******
፱፤ ወናሁ ኮከብ ዘርእዩ በምሥራቅ ይመርሆሙ እስከ ሶበ አብጽሖሙ ቤተ ልሔም።
                  ******
፱፤ በሥምራቅ ያዩት ኮከብ ቤተ ልሔም እስኪያደርሳቸው ይመራቸው ነበር።
ወቆመ መልዕልተ በዓት ኀበ ሀሎ ሕፃን። ባለበት ቦታ በሰው ቁመት ልክ ዘቅዝቆ ቆመ ። በጣት ጠቅሶ እንደ ማሳየት።
                  ******
፲፤ ወርእዮሙ ኮከበ ተፈሥሑ ዓቢየ ፍሥሐ።
                  ******
፲፤ ኮከቡን አይተው ፈጽመው ደስ አላቸው። ለልማዱ ከሰው ሲደርሱ ይሰወራቸው ከሰው ሲለዩ ይመራቸው ነበር አሁን ቢገለጽላቸው እሱ እንጂ ቢሆን ነው ብለው። አንድም ስንኳን ሁለት ዓመት የሄዱለት ነገር ሁለት ሰዓት የሔዳለት ነገር ሲፈጸም ደስ ያሰኛልና። አንድም እንዲህ መርቶ ከምን ያደርሰን ይሆን። ከባሕር ያጠልቀን ከገደል ይጥለን ከፆር ያደርሰን ይሆን ብለው ነበርና ካሰቡት ቢያደርሳቸው ደስ አላቸው። አንድም የሚቀድመው አለ።
                  ******
፲፩፤ ወበዊዖሙ ውስተ ቤት ረከብዎ ለሕፃን ምስለ ማርያም እሙ
መዝ ፸፩፥፲።
                  ******
፲፩፤ ከቤት ገብተው ብላቴናውን ከእናቱ ጋረ አይተው። ከዚሀ በኋላ ኮከቡን አይተው አምሳያው ሁኖ ቢያገኙት ፈጽሞ ደስ አላቸው። ቤት በዓት ጎል ይላል አብነት። ቤት ቢል ዮሴፍ እንደ ዳስ አድርጎ ጥሎ ነበርና። በዓት ያለ እንደሆነ ኢዮስያስ በጨው ማሸጋ ግምብ ዓሠርቶት ነበርና። ጨውን ሲልሱ እንስሳት እየጋጡ አጐድጉደውት ነበርና። ጎል ያለ እንደሆነ የተመቸ የእንስሳት ማደሪያ ሁኖ ነበርና።
ወወድቁ ወሰገዱ ሎቱ።
ከፈረስ ከሰረገላ ወርደው ሰገዱለት። አንድም መላልሰው ሰገዱለት። (ሐተታ) እንደ ስናሩ ንጉሥ ጃን ተከል ሲደርስ ይሰግዳል። የታዘዘ ብላቴና መጥቶ ተነሥ ብለውሃል ይለዋል። ዳግም አልፎ ይሰግዳል። ተነሥ ብለውሃል ይለዋል እንዲህ እያለ ከዚያ ሲደርስ እጅ ነሥቶ ከዙፋኑ በቀኝ አብሮ ይቀመጥ ነበር።
ወአርኃዉ መዛግብቲሆሙ።
ሣጥናቸውን ከፈቱ። እየራሳቸው ጭነዋል ያሉ እንደሆነ የተመቸ። አንድ ነው ያሉ እንደሆነ ሰደፋ ብዙ ነውና፤ እንደ ሰደፍ ነፍጥ። አንድም ፈትሑ ወአርኃዉ ይላል ሣጥናቸውን ከፈቱ ኮረጅዋቸውን ፈቱ።
ወአብአ ሎቱ አምኃነ ወርቀ ከርቤ ወስኂነ።
ወርቁን ዕጣኑን ከርቤውን ግብር አገቡለት (ሐተታ) ወርቅ አመጡለት ይህን የምንገብራቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፍያን ናቸው አንተ ግን ቀድሞም ያልተተፈጠርህ ነህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። ዕጣን አመጡለት ይህን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። ከርቤ አመጡለት ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ብትሆን በሰውነትህ መራራ ሞትን መቀበል አለብህ ሲሉ።
አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ። ዕጣን ምዑዝ ነው፤ ምዑዘ ባሕርይ ነህ ሲሉ። ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል የተለየውን አንድ ያደርጋል። አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ ሲሉ።
አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው ባንተ ያመኑ ምዕመናን ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። ዕጣን ምዑዝ ነው፤ ባንተ ያመኑ ምዕመናን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። ከርቤ አመጡለት በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና።
አንድም ወርቅ የሰማዕታት ምሳሌ ነው ከመ ወርቅ በእሳት ፈተኖሙ ለሰማዕት እንዲል። ዕጣን የባሕታውያን። ከሩቅ እንዲሸት ባሕታውያንም በተስፋ ይኖራሉ። ከርቤ የምዕመናን በፍቅር አንድ ይሆናሉና።
ወርቅ አመጡለት ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ወርቅ ጽሩይነቱም ግብዝነቱም የሚታወቅ በእሳት ሲፈተን ነው። የሃይማኖትም ጽሩይነቱና ግብዝነቱ የሚታወቅ መከራ ሲቀበሉበት ነውና። ዕጣን የተስፋ ዕጣን ከሩቅ እንዲሸት ተስፋም ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩ ታደርጋለችና። አሚንሰ ትሬሰዮ ለዘኢሀለወ ከመ ዘሀለወ  እንዲል። ከርቤ የፍቅር ያ አንድ እንዲያደርግ ፍቅርም አንድ ታደርጋለችና። ሃይማኖት ፍቅር ተስፋ ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ገበሩለት።
አንድም ወርቅ የመላእክት ዕጣን የደቂቀ አዳም ከርቤ የካልዕ ፍጥረት። ከመ ለስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይስግድ ኵሉ ብርክ ዘውስተ ሰማይ ወዘውስተ ምድር ወዘታሕተ ምድር እንዲል። መላአክት ደቂቀ አዳም ክልዕ ፍጥረት ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ወርቅ ዕጣን ከርቤ አመጡለት።
ይህስ ከወዴት የመጣ ነው ቢሉ ሦስቱ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሩፋኤል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ለአዳም ሰጡት።
                  ******
(ታሪኩን በቀጣይ ክፍል)
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
25/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment