Tuesday, March 12, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 33

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፫።     
                  ******
በእንተ ጥምቀተ እግዚእ ኢየሱስ፡፡
፲፫፡ ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምዮሐንስ፡፡ ማር፩፥፱፡፡
                  ******
፲፫፡ ለጌታ ሠላሳ ሲመላው ለዮሐንስ መንፈቅ ሲተርፈው ያን ጊዜ ጌታ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
አንድም ሰው ሰብስቦ በማያጠምቅበት ጊዜ መጣ። አብ በደመና ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ ሲመሰክር መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ከራሱ ላይ ሲቀመጥ አንድነት ሦስትነት ይታወቃልና። ያን ጊዜ ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ አለ።
(ሐተታ) ምነው ባሪያ ወደ ጌታው ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደ ባሪያ ይሄዳልን። ባሪያ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጅ ጌታ በባሪያው እጅ ይጠመቃልን ቢሉ ጌታ መምጣቱ ለትሕትና ነው እንጅ ለልዕልና አይደለምና፡፡
አንድም ለአብነትነት ጌታ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ቢሆን ዛሬ ነገሥታት መኳንንት መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበርና። ሂዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመሆን።
ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም። ትንቢት ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብዓ ድኅሬሁ፤ ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ ተብሎ ተነግሯል፡፡
ምሳሌም ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ ነው ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል ከታች ወርዶ ይገናኛል፡፡ ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ እንደሆነ የሰው ሁሉ ነቁ አንድ አዳም ነው። ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አሕዛብ በቁልፈት ተለያይተዋል፡፡ ከታች ወርዶ በወደብ እንዲገናኝ ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ በጥምቀት አንድ ሁነዋልና።
አንድም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ክሎዶጎሞርን ድል ነሥቶ ሲመለስ ደስ ቢለው በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርእየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ አለ፡፡ እሱንስ አታየውም ምሳሌውን ታያለህና ሑር ዕድዎ ለዝንቱ ዮርዳኖስ፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግረሀ ሂድ አለው፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሄድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዓ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ አብርሃም የምዕመናን ዮርዳኖስ የጥምቀት መልከ ጼዴቅ የቀሳውስት ኅብስተ በረከት ጽዋእ አኰቴት የሥጋው የደሙ፡፡
አንድም ኢዮብ ከዚህ ተጠምቆ ከደዌው ድኑዋል ኢዮብ የአዳም ከነሕፃናቱ፤ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ፡፡
አንድም እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ ምዕመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ገብተዋልና።
ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ገነት ዐርጓል ምዕመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው።
አንድም የኤልሳዕ ደቀ መዛሙርት ጸበበነ ማኅደር ንዑ ንግዝም ዕፀ ወንሕንፅ ከልዓ ማኅደረ ብለው ሄዱ። እሱም መምህረ ትሕትና ነውና አብሯቸው ሄደ፤ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ሲቆርጥ ምሳሩ ከዛቢያው ወልቆ ከባሕር ገባበት፤ ዝኒ ኅቡይ እግዚእየ ጌታዬ ጥንቱን የተውሶ ያውም ጠፋ ተጨርሶ አለ፡፡ የገባበትን አሳየኝ አለው አሳየው ቅርፍተ ዕፅ ቀርፎ አመሳቅሎ ቢመታው መዝቀጥ የማይቻለው ቅርፍተ ፅፅ ዘቅጦ መዝቀጥ የሚገባውን ብረት ይዞት ወጥቷል፡፡ እንደዚህም ሁሉ ሞት የማይገባው መለኮት ሙቶ ሞት የሚገባው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ፡፡
ጥምቀቱንም ሽቶ አላደረገውም። አኮ ፈቂዶ ለተጠምቆ አላ ከመ የሀበነ ሱታፌ ንጽሕ እንዲል በመጠመቁም ጸጋ ያገኘበት አይደለም አኮ ዘረከበ ጸጋ በተጠምቆቱ አላ ከመ ያብርህ መካናተ ወያኀይል ማያተ ለእለ ሀለዎሙ ይጠመቁ ውስቴታ እንዲል፡፡ ዮርዳኖስን ብርህት ማሕፀን ለማድረግ ለጥምቀት ኃይል ለመስጠት ነው እንጂ።
አንድም ዮርዳኖስ በበጋ የማይጐድል በክረምት የማይተርፍ ማዕከላዊ ውሀ ነው የጌታም ጥምቀቱ እኛም ከመጥቀም በላይ እሱን ከመጥቀም በታች ነውና።
ዳግመኛ በባሕረ ጥብርያዶስ ላደ የሚሄድ ውሀ ነው ዐባይ በጣና ላደ አንዲሄድ የጌታም ጥምቀት ከኛ ጥምቀት በላይ ነውና።
አንድም ብዙ ንዑሳን አንቅዕት ይገቡበታል፤ እሱ ያበረታቸዋል እንጂ እነሱ አያበረቱትም የጌታም ጥምቀት ለኛ ጥምቀት ኃይል ጽንዕ ይሆናል እንጂ የኛ ጥምቀት ለጌታ ጥምቀት ኃይል ጽንዕ አይሆንምና፡፡
አንድም ንዕማን ከዚህ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል ንዕማን የአዳም ከነሕፃናቱ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ። ኢዮብ ንዕማን ጌታ የተጠመቁበት ወደቡ አንድ ነው።
ትንቢቱን አውቆ አናግሯል ምሳሌውንም እንጂ አውቶ አስመስሏል። ምሥጢሩ እንደምነው ቢሉ ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ በአዳምና በሔዋን ሥቃይ አጸናባቸው ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ብትሰጡኝ ባቀለልሁላችሁ ነበር አላቸው። አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብለው ጽፈው ሰጡት፣ መጻፉስ የለም ይሁንብን ማለታቸውን መናገር ነው እንጂ እሱ በሁለት ዕብነ ሩካም ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎታል፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል። በሲኦል የጣለውን በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶላቸው ወጥቷል።
                  ******
፲፬፡ ወዮሐንስሰ ዓበዮ እንዘ ይብል አንሰ እፈቅድ እምኀቤከ እጠመቅ።
                  ******
፲፬፡ ዮሐንስ ግን ባሪያ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ፤ ጌታ በበባሪያው እጅ ይጠመቃልን ብሎ አይሆንም አለው። .
ወአንተኑ ትመጽእ ኀቤየ።
ባሪያ ወደ ጌታው ይሄዳል እንጂ ጌታ ወደ ባሪያው ይሄዳልን አለው፤ እናቱ ምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ እንዲህ አለ።
                  ******
፲፭፡ ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ኅድግ ምዕረሰ።
                  ******
፲፭፡ ጌታ መለሰ አንድ ጊዜስ ተው አለው፡፡
(ሐተታ) አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ፤ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ፤ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ የለበትምና።
እስመ ከመዝ ተድላ ውእቱ ለነ ይህ ለኛ ተድላችን ነውና፡፡
(ሐተታ) ራሱን ከዮሐንስ አግብቶ አንተም መጥምቀ መለኮት ተብለህ ክብርህ ይነገራልና፤ እኔም በባሪያው እጅ ተጠመቀ ተብሎ ትሕትናዬ ይነገራልና ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ።
ትንቢተ ነቢያትን ልንፈጽም ይገባናልና ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታ እንዲጠመቅ ትንቢ ተነግሯልና።
አንድም እስመ ከመዝ ተድላ ለነ ራሱን ከምእመናን አግብቶ ይህ ለእኛ ተድላችን ነውና እናንተም ብትጠመቁ ይወርድላችኋል ለማለት። ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ጽድቀ። ጽድቀ ተሰብኦን ልንፈጽም ይገባናልና።
አንድም ራሱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አንድ አድርጎ ደህ ለእኛ ተድላችን ነውና አለ። አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ ሲመሰክር መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ከራሱ ላይ ሲቀመጥ አንድነት ሦስትነት ይገለጻልና። ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ሉ ጽድቀ። በማኅፀን የጀመርነውን ቸርነት ልንፈጽም ደገባናልና።
ወእምዝ ኀደጎ፡፡ ከዚህ በኋላ ተወው።
(ሐተታ) እንዲያው አይተወውም ስመ አብ ብከ ወስመ ወልድ ለሊከ ወስመ መንፈስ ቅዱስ ህልው ውስቴትከ ባዕደ አጠምቅ በስምከ ወበስመ መኑ አጠምቅ ኪያከ አለው። ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነአንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ ብለህ አጥምቀኝ አለው። ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ባሕር ወርደዋል።
                  ******
፲፯፡ ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ። ሉቃ ፫፥፳፩-፳፪፡፡
፲፯፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውሃው ወጣ፡፡
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
03/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment