Sunday, March 3, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 24




                 ====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ።
ምዕራፍ ፪።
                  ******
፪፡ ወበጽሑ ውስተ ኢየሩሳሌም እንዘ ይብሉ አይቴ ሀሎ ዘተወልደ ንጉሠ አይሁድ።
                  ******
፪፡ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ እያሉ ኢየሩሳሌም ደረሱ። (ሐተታ) ምነው ኮከቡ ይመራቸው አልነበረምን? ቢሉ ከሰው ሲደርሱ ይሰወራቸው ነበርና። ከዚህም ስም ላዕላዊ ስም ማዕከላዊ ስም ታሕታዊ አለ። ስም ላዕላዊ ስም ታሕታዊ አልገለጸላቸውም። ስም ማዕከላዊ ገለጸላቸው እንጂ። ስለ ምን ቢሉ ስም ላዕላዊ ገልጾላቸው። አይቴ ሀሎ አምላኽ ዘተወልደ አይቴ ሀሎ ፈጣሪ ዘተወልደ ብለው ጠይቀው ቢሆን። እኒህ ሞኞች ተላሎች ሰማይና ምድር የማይችሉትን ማን ችሎት ተወለደ ይላሉ? ባሏቸው ነበርና። ይህንማ እንዳይሉ አሕዛብ አይደሉ እስራኤል አይደሉምን የተነገረውን ትንቢት የተቈጠረውን ሱባዔ ያውቁ የለም? ቢሉ። በዚያውስ ላይ እኛ ይልቅ አናውቀውምን? ባሏቸው ነበርና።
ስም ታሕታዊ ገልጾላቸው፤ አይቱ ሀሎ ሕፃን ዘተወልደ ብለው ጠይቀው ቢሆን እነዚህ ሞኞች ተላሎች በአዕላፈ እስራኤል ከተማ እልፍ ሙቶ እልፍ ተወልዶ ያድራል ስንቱን እናውቅላቸዋለን ባሏቸው ነበርና ስም ማዕከላዊ ገለጸላቸው።
እስመ ርኢነ ኮከበ ዚአሁ በምሥራቅ ወመጻእነ ከመ ንስግድ ሎቱ። በተፈጥሮ ገንዘቡ የሚሆን። አንድም አምሳያው የሚሆን ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና። ይኽስ በቁሙ ኮከብ ነውን መልአክን ቢሉ፤ መልአክ ነው። በምን ይታወቃል ቢሉ። ኮከብ በሌሊት እንጂ በመዓልት አይታይም። በመዓልት በመታየቱ። ኮከብ ወደ ምዕራብ ይሄዳል እንጂ ወደ መስዕ አይሄድም ። ወደ መስዕ በመሄዱ። ኮከብ መጥቆ ይሄዳል እንጂ በቆመ ብእሲ ዘቅዝቆ አይሄድም። በቆመ ብእሲ ዘቅዝቆ በመሄዱ። ይኽስ በሌሊት የሚታየውን በመዓልት እንዲታይ ወደ ምዕራብ የሚሄደውን ወደ መስዕ እንዲሄድ መጥቆ የሚሄደውን በቆመ ብእሲ ዘቅዝቆ እንዲሄድ የሚያደርግ እሱ ነው ብሎ በቁሙ ኮከብ ነው። ስለምን በኮከብ መራቸው ቢሉ በለመዱት ለመሳብ ኮከብ ያመልኩ ነበርና ከዚያ ሁሉ ግብፃውያን ላም ያመልኩ ነበር በለመዱት ለመሳብ ላም ሠዉልኝ እንዳላቸው።
                  ******
፫፡ ወሰሚዖ ሄሮድስ ንጉሥ ደንገፀ ወተሀውከ።
                  ******
፫፡ ንጉሥ ያሉትን ሰምቶ ሄሮድስ ደነገጸ አዘነ። ሐተታ ንጉሥማ ከሆነ ንጉሥ ሳይገድል ይነግሣልን ብሎ።
ወኵላ ኢየሩሳሌም ምስሌሁ፤ ተሀውከት ያለበት ነው። ከተማዪቱ ከሱ ጋራ እንደ እሱ ተደረጸች። የንጉሥ ሞት የፀሐይ ዕርበት የሁሉ ነውና።
አንድም ሶስቱ ነገሥታት ማንቱሲማር በዲዳስፋ ሜልኩ ይባላሉ ዕልፍ ዕልፍ ሠራዊት አስከትለው መጥተዋልና። ይኽን በሰማ ጊዜ ደነገጠ አዘነ ሕዝቡም ደነገጡ አዘኑ። ፄዋዌ ተመላልሶባቸው ነበርና። ታምረ ኢየሱስ ሦስት ይላል። ትርጓሜ ወንጌል ፲፪ አለ አይጣላም? ቢሉ አይጣላም። ነገር እንደ ትርጓሜ ወንጌል ነው፤ አሥራ ሁለት ሁነው ተነሥተል፤ ፈለገ ኤፍራጥስ ሲደርሱ ንጉሠ ነገሥቱ ፍርሻቡር ይባላል ዘጠኙን ይዟቸው ተመልሱዋል። በምን ምክንያት ቢሉ ከወደኋላችሁ ጦር ተነሣባችሁ ብለዋቸው።
አንድም ስንቅ አልቆባቸው። አንድም ኢየሩሳሌም ጠባብ ናት ለሰፈር አትበቃም ብለዋቸው ምሥጢሩ ግን ከበረከተ ልደቱ እንዳላሳተፋቸው ያጠይቃል። በደቂቀ ነቢያት ወይትነሥኡ ፯ቱ ኖሎት ወ፰ቱ ሠራዊት ይላልሳ? ቢሉ። ሰባቱ ንጉሠ ነገሥትነት የደረቡ ናቸው፤ አምስቱ ንጉሠ ነገሥትነት ያልደረቡ ናቸውና እንደ አንድ ንጉሠ ነገሥት አድርጎ ሳምኖሙ በማለት ተናገራቸው እንጂ ነገር እንደ ትርጓሜ ወንጌል ነው።
                  ******
፬፡ ወአስተጋብኦሙ ለኵሎሙ ሊቃነ ካህናት ወጸሐፍተ ሕዝብ።
                  ******
፬፡ የሕዝቡን ጸሐፍትና ሊቃነ ካህናትን ሰበሰባቸው። (ሐተታ) ሊቀ ካህናቱማ አንድ አይደለም ቢሉ። ምሉና ዱግ ሁነው ተሹመው ነበርና። አንድም አንዱ ሹም አንዱ የሹም ሽር ነው። ጸሐፍት የሚላቸው ወተሠይሞሙ ለለነገዶሙ እንዲል ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ተወጻጽተው ርስት ከርስት ትውልድ ከትውልድ እንዳይፋለስ የሚጽፉ ናቸው። ይልቁንም ክህነት ከቤተ ሌዊ መንግሥት ከቤተ ይሁዳ እንዳይወጣ የሚጽፉ ናቸው። አንድም ከነገደ ስምዖን ተወልደው ይኽን ሁሉ የሚጽፉ ናቸው። ከኒህ ወግ ታሪክ አይታጣምና ብሎ ሰበሰባቸው።
ወይቤሎሙ በአይቴ ይትወለድ ክርስቶስ። ክርስቶስ ወዴት ይወለዳል? ብሎ ጠየቃቸው።
                  ******
፭፡ ወይቤልዎ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ።
                  ******
፭፡ እንደ ዛሬ ምቀኝነት አልሰፋም ነበርና ቀንተው ይመልሱለታል። የይሁዳ ዕፃ በምትሆን በቤተ ልሔም ነው አሉት።
እስመ ከማሁ ጽሑፍ በነቢይ እንዲህ ያለ ጽሑፍ አለና ነበርና ይላል ወንጌላዊ ከነዋዌው ጠቀሰው። ወበእንቲአክሙ ይጸርፉ አሕዛብ ላዕለ ስመ እግዚአብሔር እንዲል።
                  ******
፮፡ ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ። ሚክ ፭፥፪። ዮሐ ፯፥፵፪።
                  ******
፮፤ የይሁዳ ዕፃ የምትሆኝ አንቺም ቤተ ልሔም የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው አሕጉር ብትበልጭ እንጂ አታንሽም የሚል ጽሑፍ አለና ነበርና ይላል።
እስመ እምኔኪ ይወጽእ ንጉሥ ዘይርእዮሙ ለሕዝብየ እስራኤል። ወገኖቼ እስራኤል ዘሥጋን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ባንቺ ይነግሣልና። (ታሪክ) ነቢዩ ሚክያስ ነው ሌላውን ሲያስተምር ውሎ ወደ ማታ በቤተ ልሔም በኩል አልፎ ሲሄድ ተፈታ ምድረ በዳ ሆና ቋያ በቅሎባት አየ። እንዲህ እንጂ እንደሆንሽ አትቀሪም ንጉሥ ይነግሥብሻል የነጋሪት ድምፅ ይሰማብሻል ድንኳን ይተከልብሻል እስራሌል ደጅ ይጠኑብሻል አሕዛብ ይገብሩብሻል ብሎ ትንቢት ተናግሯል። ይህም አልቀረ ዘሩባቤል ነግሦባታል እስራኤል ደጅ ጠንተውባታል የነጋሪት ድምፅ ተሰምቶባታል አሕዛብ ገብረውባታል ድንኳን ተተክሎባታል። አንድም ወገኖቼ እስራኤል ዘነፍስን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ክርስቶስ ባንች ይወለዳልና። ዘሩባቤል እንደ ነገሠ ጌታ ተወልዶባታል። ድንኳን እንደ ተተከለባት የብርሃን ድንኳን ተተክሉሎባታል። ነጋሪት እንደ ተሰማባት ቅዳሴ መላእክት ተሰምቶባታል። እስራኤል ደጅ እንደ ጠኑ መቶው ነገደ መላእክት ደጅ ጠንተውባታል። አሕዛብ እንደ ገበሩ ሰብአ ሰገል ገብረዋል። አንድም አንቺ የኤፍራታ ልጅ እመቤታችን በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት ብትበልጭ እንጂ አታንሽም ወገኖቼ እስራኤል ዘነፍስን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ ባሕርይ ይወለዳል እምኔኪ ከአንች ይወለዳልና።
                  ******
፯፡ ወእምዝ ጸውፆሙ ሄሮድስ ለሰብአ ሰገል ጽሚተ።
፯፡ ከዚህ በኋላ ሰብአ ሰገልን በቆይታ ጸራቸው።
                  ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
24/06/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment