Sunday, March 31, 2019

ወንጌል ቅዱስ ክፍል 50

====================
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል።
ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው።
ምዕራፍ ፮።
                  ******
፬፡ ከመ በኅቡዕ ይኩን ምጽዋትከ፡፡
                   ******
፬፡ ምጽዋትህ በስውር ይሆን ዘንድ።
ወአቡከ ዘይሬእየከ በኅቡዕ የአሥየከ ክሡተ።
ስትመጸውት ተሠውሮ የሚያይህ፤ አንድም ተሠውረህ ስትመጸውት የሚያይህ ሰማያዊ አባትህ ጉባኤውንስ ከሻኸው በጻድቃን በሰማዕታት በመላእክት በኃጥአን በአጋንንት ፊት ገልጾ ዋጋህን ይሰጥሃል።
                  ******
፭፡ ወሶበሂ ትጼልዩ ኢትኩኑ ከመ አሕዛብ።
                  ******
፭፡ ግብዞች አትሁኑ።
እስመ ያፈቅሩ በመኳርብት በውስተ መዓዝነ መራህብት ቀዊመ ወጸልዮ ከመ ያስተርእዩ ለዓይነ ሰብእ።
ሰው ይይልን ሰው ይስማልን ብለው በምኩራብ ባደባባይ ቁሞ መጸለይን ይወዳሉና፡፡ በምኩራብማ መጸለይ እንዲገባ ለማጠየቅ ሙሴን ወንድምህ አሮን ድምፅ ያለው ልብስ ለብሶ ያን እያሰማ ገብቶ ይጸልይ ሕዝቡም እሱን አብነት አድርገው ገብተው ይጸልዩ ብሎት የለምን ቢሉ ከዚያው መካነ ጸሎት መካነ ትምሕርት መካነ ተግሣፅ አለ። እኒህ ግን መካነ ጸሎቱን ትተው በመካነ ተግሣፅ ቁመው ይታያሉና። አማን እብለክሙ ኃጕሉ ዕሤቶሙ።
እንዳለፈው በል፡፡
                  ******
፮፡ ወአንተሰ ሶበ ትጼሊ ባዕ ቢተከ ወእፁ ኆኅተከ ወጸሊ ለአቡከ።
                  ******
፮፡ አንተ ግን በምትጸልይበት ጊዜ ከቤትህ ገብተህ ደጅህን ዘግተህ ወደ ሰማያዊ አባትህ ጸልይ፡፡
አንድም በምትጸልይበት ጊዜ ሕዋሳትሕን ሰብስበህ በሰቂለ ሕሊና በነቂሐ ልቡና ሁነህ ወደ ሰማያዊ አባትህ ወደ እግዚአብሔር አመልክት።
ወአቡከ ዘይሬእየክ በኅቡዕ የዓሥየከ ክሡተ።
ተሰውረህ ስትጸልይ የሚያይህ ሰማያዊ አባትህ ዋጋህን ይሰጥሃል፡፡
                  ******
፯፡ ወእንዘ ትጼልዩ ኢትዘንግዑ ከመ አሕዛብ፡፡
                  ******
፯፡ ስትጸልዩ እንደ አሕዛብ አብዝታችሁ አትጸልዩ። ግብር ዘአልቦ ምጣኔ ገዓር ውእቱ ወለገዓርኒ ይተልዎ ዝንጋኤ እንዲል።
አንድም ጨኸችሁ አትጸልዩ። ኢትክላህ በሕቁ አላ ዘምር በመጠን ከመ ኢይዘንግዑ አኃው እንዲል።
እስመ ይመስሎሙ በአብዝኆ ንባቦሙ ዘይስምዖሙ።
አብዝተው ጩኸው በመጸለያቸው የሚሰማቸው ይመስላቸዋልና።
                  ******
፰፡ ኢትትመሰልዎሙኪ።
                  ******
፰፡ አብነት አታድርጓቸው።
እስመ የአምር አቡክሙ ሰማያዊ መፍቅደክሙ ዘእንበለ ትስአልዎ።
እናንተስ አብዝታችሁ ጩኸችሁ ሳትለምኑት ሰማያዊ አባታችሁ የምትሹትን አውቆ ያደርግላችኋል።
                  ******
፱፡ አንትሙሰ ሶበ ትጼልዩ ከመዝ በሉ። ሉቃ ፲፩፥፪፡፡
፱፡ እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ።
                   ******
ይቆየን፡፡
**************
መልካሙ በየነ
ደብረ ማርቆስ፤ ኢትዮጵያ
22/07/2011 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment