================================
ጥቅምት
10/2011 ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣
ኢትዮጵያ
ቀን፡-
11/02/2011 ዓ.ም
ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን
ቅ/ሲኖዶስ
አ/አበባ
===============================
ጉዳዩ፡- በምሥ/ጎጃም
ሃ/ስብከት እየተፈፀመ ያለውን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል በተመለከተ ለዐሥራ ኹለተኛ /12/ ጊዜ አቤቱታ ማቅረብ ይሆናል፡፡
============================
እኛ በምሥ/ጎጃም
ሃ/ስብከት የምንኖር ምእመናን ፣ማኅበረ ካህናት እና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች በሃገረ ስብከታችን እየደረሰ ያለውን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ
በደል አስመልክቶ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ማለትም ለቅ/ሲኖዶስ፣ ለጠ/ቤተ ክህነት፣ ለምሥ/ጎጃም ዞን አስተዳድር፣ ለደ/ማ ከተማ
አስተዳድር እንዲሁም ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተደጋጋሚ ያሳወቅን መሆኑ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን
የሕዝቡ አቤቱታ እና በደል ሳይሰማ እና ሳይደመጥ በመቅረቱ ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የምሥ/ጎጃም ሃገረ
ስብከት ለምሥ/ጎጃም ዞን ብሎም ለአማራ ክልል ከፍተኛ የስጋት ምንጭ በመሆኑ የምሥ/ጎጃም ዞን አስተዳድር ፣ የደ/ማ/ከተማ አስተዳድር
እንዲሁም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለክልላችን የሰላም ስጋት መኾናቸውን በመግለፅ ለኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት እንዲሁም ለቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ ማስገባታቸው ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ
እንዳለ አሁንም በቅ/ሲኖዶስ ተስፋ የማንቆርጥ በመኾናችን የብፁዕ አቡነ ማርቆስን ችግሮች ለዐሥራ ሁለተኛ /12 / ጊዜ እንደሚከተለው
ለማቅረብ ተገደናል፡፡
ቅዱስ አባታችን
ብፁዓን አበው
ሊቃነ ጳጳሳት
ከኹሉም በፊት
የሃገረ ስብከቱን ካህናት እና ምእመናን አቤቱታ ለመስማት በመፍቀዳችሁ በእግዚአብሔር ስም እያመሰገንን በብፁዕ አቡነ ማርቆስ እየደረሰብን
ያለውን ግፍ በዝርዝር እናሳያለን ፡፡
1. የሃይማኖታዊ ችግር
2. አስተዳደራዊ ችግር
3. የፋይናስ ችግር
4. የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አለማስከበር ብሎም መጣስ
5. የሰላም ስጋት
1.ሃይማኖታዊ
ችግር፡-
ምሥራቅ ጎጃም
በመጽሐፍም በቃልም መናፍቃንን ያሳፈሩ የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ ምንጭ
ማለትም የእነ ቅዱስ ወሰማዕት አቡነ ቴዎፍሎስ፤ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ አራት ዓይና ጎሹ እና የእነ
ክቡር ዶክተር ሐዲስ አለማየሁ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መገኛ የሆነችውን
ሀገረስብከት ብጹዕ አባታችን አቡነ ማርቆስ ግን ብዙ ሃይማኖታዊ ግድፈቶችን በየጊዜው የተናገሩ ሲሆን ለአብነት ያክል፡-
ሀ. ማንኛውም
ሰው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውጪ ቢሆንም በክርስቶስ ስም ከተጠመቀ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ሲመጣ ዳግም ጥምቀት ስለሚሆንበት
አይጠመቅም ብለው ታላቁ የቤተ ክርስቲያንን መጽሐፍ በፍትሐ ነገሥት ላይ የተጻፈውን “ለዘተጠምቀ እም አላውያን ያጠምቅዎ ዳግመ”
ትርጉሙም ከአላውያን ወገን የተጠመቀ ቢኖር ዳግም ያጥምቁት “ለዘተወልደ እም ጳውላኒ ዳግመ ያጥምቅዎ ፤ ከሳምሳጢ ጳውሎስ ከአርዮስ
ከንስጥሮስ ወገን የተጠመቁ ቢኖሩ ይጠመቁ” እያለ መጽሐፍ እየተናገረ ይህ ልክ አይደለም በሚል መልኩ ያጠመቁ ካህናትን ዳግም ጥምቀት
ታጠምቃላችሁ እያሉ እያወገዙ መገኘታቸው፡፡
ለ. በእርሳቸው
ትውልድ ቦታ በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ውስጥ በምትገኝ ምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምና በመምህር ገብረ መድኅን እንዳለው ስም የታተመውን ‘’ወልደ አብ’’ የሚባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቃውንት
ጉባኤ ካስመረመረ በኋላ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን መጽሐፍነት ለይቶና በዚህ መጽሐፉ
በታተመበት አካባቢ ሥልጠና እንዲሰጥ ቢወስንም አቡነ ማርቆስ ግን በግልባጩ በዚህ ገዳም ያሉትን ሰዎች ስማቸውን በየመድረኩ እየጠሩ
ማሞገስና የቅዱስ ሲኖዶስንም ውሳኔ ከምንም አለመቁጠርና ማንም መጽሐፍትን ሊያነብ ቢወድ ከዚሁ ገዳም ሄዶ ያንብ በማለት የተወገዘውን
መጻሕፍ መጋበዝና ማስተዋወቅ ፤ ይኸው ‘’ወልደ አብ’’ የተባለው መጽሐፍ የተወገዘው በስህተት ነው የሚል ቡድን አቋቁመው ውሳኔውን
ለማስቀልበስ በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው፤
ሐ. አቡነ
ማርቆስ በዓመታዊ በዓላት ይኹን በአንዳንድ ቦታዎች በሚያስተምሩበት ወቅት ተዋሕዶ የሚለውን ቃል ካለመጥራታቸው በተጨማሪ ሃይማኖታዊ
ግድፈቶችን መናገራቸው፤ ለአብነትም ያህል
‘’ሰኔ ጎልጎታ ልብ ወለድ ነው’’ በዚህ የተጸለየ ጸሎት ጫካ ውስጥ የተዘራ
ዘር ማለት ነው ፤
‘’ተዝካር ሟርት ነው’’
ድጓ ተምረህ ሰው ልትሆን -----እያሉ ማስተማራቸውና ሕዝበ ክርስቲያኑን ግራ
ማጋባታቸው፤
ብጹእነታቸው ነገረ ቅዱሳንን በተመለከተ ግራ የሚያጋባ አቋም ያላቸው ሲሆን
በአንድ ወቅት ሰባክያነ ወንጌልን በመሰብሰብ እሙሐይ አባሆይ እያላችሁ
አትስበኩ በማለት ትእዛዝ መሰል መልእክት ማስተላለፋቸው
ኪዳንንና ቅዳሴን በማይነካ ሁኔታ በዐቢይ ጾም ጊዜ ሰንበት ት/ቤቶች ተሰባስበው
የሚጸልዩትን ጸሎት ማስቆምና ጸሎቱን አድርሰው ወደ ቅዳሴ ለማስቀደስ የሚገባው ሰንበት ተማሪ ተስፋ ቆርጦ ከቤቱ እንዲቀር ማድረግ
መ. ተሐድሶ
የሚባለውን የቤተ ክርስቲያን ጠላት የሆኑትን አቅፈውና ተንከባክበው መያዝ ለዚህም ማሳያ በሀገረ ስብከታችን ከመምሪያው አስከ አጥቢያ
ቤተ ክርስቲያን በግልጽም ይሁን በድብቅ ተሰግስገው መገኘታቸውና እንዲሁም
የሰላም እጦት ምክንያት መሆናቸው
2. የፋይናንስና
አስተዳደር ችግር
አቡነ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሊባርኩ ወደ ገጠር ቤተ ክርስቲያን በሚሄዱበት
ጊዜ ለጧፍ ፣ ለእጣን እንዲሁም ለማስቀደሻ ፍሬ ግብርና አልባሳት ያጣች ቤተ ክርስቲያን ብጹእነታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ሄደው የሚጠይቁት
ገንዘብ ከፍተኛ መሆንና ይህም ያለምንም ሕጋዊ ደረሰኝና አሰራር ውጭ መውሰዳቸው፡፡
ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ ለመብላት የቁጥጥርና የሒሳብ ሹም መደቦችን የሚያስይዙት
በሙያ ብቃት ሳይሆን በቤተሰብ ከዚያም ከራቀ ለሆድ አደሮች በመስጠት ሕጋዊ ሌብነትን መፈጸም፤
ከሕዝብ ጋር በመሆን አንዳንድ ፕሮጀክት እንድንሰራ ተስማምተን እርሳቸውም ኮሚቴ
አቋቋመው ሥራውን ለመጀመር ጠቀም ያለ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ ገንዘቡን ለማባከንና ለመበዝበዝ ጠንካራ የኮሚቴ አባላትን ያለ ምንም
ጥፋትና ግምገማ ከኮሚቴው ማባረር ብሎም ኮሚቴውን ማፈራረስና ለምዝበራ የሚመች ኮሚቴ ማቋቋም፤
ለምሳሌ፡- የሀገረ ስብከቱ ህንጻ አሰሪ ኮሚቴና የባሕረ ጥምቀቱ ኮሚቴ ለዚህ ማሳያዎች
ናቸው፡፡
3. አስተዳደራዊ
ችግር፡-
3.1 የአቡነ ማርቆስ ጠባይ በራሱ ከአንድ አባት የማይጠበቅ ከመሆኑም በላይ ምንም
እንኳን ሀገረ ስብከታቸው ባይቀመጡም አንዳንድ ቀን ይመጡና ዐውደምህረት በሚቆሙበት ሰዓት ታላቁን የጎጃም ሕዝብ ማዋረድና እንደ
ሰው አለመቁጠር ለምሳሌ የጎጃም ሕዝብ ምንም አያመጣም ትንኝ ነው ፣ ብዙ ሊቃውት የወለዱትን አናቶችንና እህቶችን ወደ መድረክ ያወጡና
‘’አንቺ የባሏ እዳ’’ በማለት በሕዝበ ክርስቲያኑ ፊት ማዋረድና ባልና ሚስት እንዲጠራጠሩ ማድረግና በበዓሉ ምክንያት የተሰበሰበውን
ሕዝበ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዳይሰማ ጊዜ ማባከን ፣ ሌላውን ስድብና ንቀት ለጉባኤው
ስለማይመጥን ትተነዋል፡፡
3.2 አቡነ ማርቆስ ፈታኝ የሆነ ችግር ሲመጣና የአጿማት ጊዜያት ሲገቡ ወይም ሲያዙ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተቀራርቦ ችግርን ከመፍታትና ጾም ጸሎት ከመያዝ ይልቅ
ለጉብኝትም ይሁን ገንዘብ ለመሰብሰብ ወደ አሜሪካ ሄዶ ሦስት አራት ወር መቆየት የተለመደ ተግባራቸው ከመሆኑም በላይ በመጡ ሰዓት
ደግሞ ችግሩን ተቋቁመው ከሕዝቡ ጋር ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሰላም ሲወጡ ሲወርዱ የቆዩትን የሀገረ ስብከቱ አገልጋዮችም ሆነ
ወረድ ብለውም ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ጀምሮ አስከ አቃቢት ድረስ ማፈናቀል፤ ለዚህም ማሳያ
ሀ. የቤተሰብ
ቅጥር፡-
የሀገረ ስብከታችን
ሥራ አስኪያጅ አስተዳድር ጉባኤውን በመያዝ ሕዝበ ክርስቲያኑ በጠየቃቸውና
ሕገ ቤተ ክርስቲያን በጠበቀ ሁኔታ ቦታውን በእውቀትም ሆነ በሥነ ምግባር የማይመጥኑ አገልጋዮችን ዝቅ አድሮጎ እንዲመድቡና በአንጻሩ
ደግሞ የእውቀት ምንጭ የሆኑትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በቦታው እንዲተኩ አንዲሁም በቤተሰብ የተያዘችውን ሀገረ ስብከት ነጻ
እንዲያወጧት በመጠየቁና ይህ ካልሆነ ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን በማለቱ የተከበሩ የሀገረ ስብከታችን
ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሀሊ በቃሉ የሕዝበ ክርስቲያኑን ችግር በማዳመጥና በኋላም የአስተዳደር ጉባኤውን በመሰብሰብና አገልጋዮችንም
የሚመጥናቸውን ቦታ ራሳቸው እንዲያመለክቱ በማድረግ ምንም እንኳን የቀድሞው አመዳደባቸው ትክክል ባይሆንምና የደመወዛቸው መጠን ከፍተኛ
ቢሆንም ደመወዛቸውን እንደያዙ ከአካባቢው ሳይለቁ ወረድ ብለው ተመድበዋል፡፡ ይህን በማድረጉም የአስተዳደር ጉባኤው ሕዝበ ክርስቲየኑን
ከስህተት፤ ቤተክርስቲያንን ደግሞ ከቤተሰባዊ ቅጥር አሰራር ነጻ ወጣች ባንልም ነጻ በመውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ቤተሰባቸው በመነካታቸው
አቡነ ማርቆስ የቁጭት ብቀላ ጀምረዋል፡፡
ለ. ሕገ ወጥ
ማሕተም ማስቀረጽና ሕገ ወጥ እገዳ፡-
ሌላው የሕዝበ
ክርስቲያኑ ጥያቄ የፋይናንስ አስተዳደር ጉዳይ ስለነበር ሊቀ ብርሃናትና የአስተዳደር ጉባኤውም ሀገረ ስብከቱ ኦዲት እንዲደረግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር በመነጋገር ለዚህ በጎ ተግባርም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሦስት ኦዲተሮችን ስለላከ የሚያስመሰግነው
ተግባር ነው፡፡ ክቡር የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅም በዚህ ባልተረጋጋና በለውጥ ዘመን ሀገረ ስብከታችንን ከችግር በመታደጋቸው
ከአስተዳደር ጉባኤው ጋር ምስጋና ሲገባቸው ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከእረፍታቸው መልስ ሕዝቡ ሲረጋጋና ሦስት ወር በሰላም ኑሮውን ሲቀጥል
ሰላም የማያስደስታቸው ብፁዕነታቸው በክቡር ሥራ አስኪያጁ ቀሲስ ከሀሊ በቃሉና በሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አባ ወልደ ትንሣኤ ላይ የሥራ እገዳ ደብዳቤ ጽፈውባቸዋል፡፡ ‘’ብር ላበደረ ጠጠር’’ እንዲሉ በዚያ በጭንቅ ሰዓት ሀገረ ስብከቱን ከጥፋት
ታድገው በመቆየታቸው፤ ሊመሰገኑ ሲገባ ሕገወጥ የእገዳ ደብዳቤ መሰጠቱ
አግባብነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በጣም የሚያስገርመውና ቤተ ክርስቲያንን አንገት የሚያስደፋው ጉዳይ ለእገዳው የተጻፈው ደብዳቤና
ማህተም ሕጋዊነት ሁኔታ ነው፡፡ ይኸውም ሕዝበ ክርስቲያኑ ብጹነታቸው ቢመጡ እርምጃ እንወስዳለን ስላለና ወደ ሀገረ ስብከቱ መምጣት
ሳይችሉ ሲቀሩ የሀገረስብከቱ ሕጋዊና ነባር ማህተም እያለ ኹለተኛ ሕገ ወጥ ማህተም በማስቀረጽ በፕሮቶኮል ተመዝግቦ ያልወጣ ደብዳቤ
ወደ ሃገረ ስብከታችን መላካቸው፡፡
ሐ. ሹም ሽርና
ያልተገባ ዝውውር ፡-
ብጹዕ አቡነ
ማርቆስ የእርሳቸው ቤተሰብ ካልሆነ በቀር ሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተረጋግተውና ከቤተሰብ ጋር እንዳይኖሩ በየሦስት ወሩ መቀያየርና
አንዳንዶቹን ደግሞ ከሥራ ማባረር ለዚህም በዓመት ውስጥ የአንድ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እስከ ሦስትና ከዚያ በላይ ጊዜ መቀያየር
በቂ ማሳያ ነው፡፡
ሐ. የሰበካ
መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትን ማገድ፡-
ሕዝብ የመረጣቸውንና
የሚወዳቸውን እንዲሁም ሥራቸውን አውቀው በጥሩ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን የሚያለሙትንና ሌብነትንና ዘረኝነትን የሚከላከሉትን የሰበካ
መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ከሥራ ማባረርና ሲመች ዘመዳቸውንና ሆድ አደሮችን ማስገባት ካልተቻለም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ያለ ሰበካ
መንፈሳዊ ጉባኤ ማስቀረት፣ ለአብነት ያህልም የገዳመ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ያለ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከዓመት
በላይ መቆየቱን መጥቀስ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
መ. የሰንበት
ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ማሳሰርና ማስደብደብ፡-
የነገዪቱ ቤተ
ክርስቲያን ተተኪ የሆኑትንና ተሐድሶ መናፍቃንን በማስተማር፣ ወደ አባቶቻችንም በመውሰድና በማስመከር እንዲሁም ስውር ሴራቸውን በማጋለጥ
ለቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆኑትን የሰንበት ት/ቤት አባላትን ለእስር ጋብዘዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፌሮ፣ በመቋሚያና
በምንባረክበትና የሰላማችን ምልክት በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደሙ እንደፈሰሰው እንደ
ሊቀ ካህኑ ዘካርያስ የሰንበት ተማሪዎች አንድ ቀን አይደለም ሁለት ሦስት ጊዜ ደማቸው ፈሷል፡፡
4. የቅዱስ
ሲኖዶስን ውሳኔና የጠቅላይ በተ ክህነቱን ትዕዛዝ አለማክበርና አለማስከበር ብሎም መጣስ
ብጹእ አቡነ
ማርቆስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቢሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች አያከብሩም፤ አያስከብሩም፡፡ ለዚህም ማሳያዎች፡-
4.1. በሀገረ
ስብከቱ ጸረ ተሐድሶ ኮሚቴ አለማቋቋም፡-
ቅዱስ ሲኖዶስ
በ2007 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ ተሐድሶ በቤተክርስቲያናችን እያደረሰው ያለውን ግፍና በደል ከተመለከተ በኋላ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት
ጀምሮ አስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ጸረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን እንዲሰራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ ውሳኔ መመሪያ ቢያስተላልፍም
ብጹእ አቡነ ማርቆስ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው ኮሚቴም ሳያቋቁሙ መቅረታቸውና እንዲያውም እርሳቸውን የሚያማክሯቸው
ጨለማን ተገን አድርገው ለጥፋት የተፋጠኑ ስውር ጥቅመኛ የሆኑ በተሐድሶ መናፍቃን የሚጠረጥሩ ግለሰቦች መሆናቸው
4.2 ከአራት
ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጊዜ አቡነ ማርቆስ አንዳንድ ጊዜ ልደት
በ28 ቀን ከተከበረ ግዝረትም በአምስት ጥምቀትም በአስር ቀን መሆን አለበት ይላሉ፤ ስለዚህ በዓሉ በታህሳስ 29 ቀን መከበር አለበት
በማለት የቅዱስ ሲኖዶስን ቀኖና ከመጣሳቸውም በላይ ለእርስ በእርስ ግጭት አይነተኛ መንስኤ ሆነዋል፤ ይህንም በኅቡእ “ማኅበረ መሲህ”
የሚባል ማኅበር በመመስረት እየተንቀሳቀሱና ሥልጠና በማሰጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በአንድ ሲኖዶስ ውስጥ ‘’በዶግማ አንድ ነን
በቀኖና ግን እንለያያለን’’ እየተባለ ይገኛል፡፡ ጠበቅ ያለ ጥያቄ
ሲቀርብባቸው ደግሞ አንዱን በ28 ሌላውን በ29 ቀን መከበርና መቀደስ አለበት በማለት ከግጭቱም በተጨማሪ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን
ውስጥ በሁለቱም ቀን በዓሉ ይከበራል ይቀደሳል፡፡
4.3 የጠቅላይ
ቤተ ክህነት ትእዛዝ አለመፈጸም፡-
የጠቅላይ ቤተ
ክህነት ትእዛዝ ከሰኔ 4- ሰኔ 6/2010 ዓ.ም ስለ ስብከተ ወንጌል፣ ስለ ሰበካ ጉባኤና ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ስልጠና
እንዲሰጥ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ልኡክ ቢልክም የሰንበት ተማሪዎች ስልጠናውን ከጀመሩ በኋላ ስለ ስብከተ ወንጌል አሰጣጥና ስለመናፍቃን
ጥያቄ በመጠየቃቸው የሰንበት ተማሪዎች ከስልጠናው ተባረዋል፤ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰ/ት/ቤቶች የመምሪያ
ኃላፊው መምህር እንቁባሕርይ በአሉበት መሆኑ ነው፡፡
4.4 የተወገዘን
መጽሐፍ በድብቅም ይሁን በግልጽ አንዲሸጥ መፍቀድ፡-
በጥቅምት
2010 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ጉባኤ ላይ ‘’ወልደ አብ’’ የሚለው መጽሐፍ ተወግዞ እያለና በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ስልጠና
እንዲሰጥ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በብጹዕነታቸው ሀገረ ስብከት ወልደ አብ መወገዙ ስህተት ነው፤ ስለዚህ ‘’ወልደ አብ’’
መወገዙን እናስመልሳለን የሚል የጨለማ ቡድን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤ ለዚህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የብጹነታቸው ድጋፍ መኖሩና
ይህ ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አለመቀበል ነው፤ እያደገ ሲመጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡
5. የሰላም
ስጋት መሆናቸው
5.1 ሕዝበ
ክርስቲያኑን በቡድን መከፋፈል፡-
አቡነ ማርቆስ
ሁለትና ሦስት ወረዳዎችን ማለትም በተወለዱበት አካባቢ ያሉትን አባቶቻችንን፣ እናቶቻችንን፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በመከፋፈልና
ሃይማኖትህን ሊያስክድህ መጣልህ ተነሥ በማለት ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ለአብነትም ያክል በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ጉንደ
ወይን ከተማ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ራሳቸው የቀጠሩትን ሰባኬ ወንጌል ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሄደሃል
ተብሎ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሕዝቡ እንዲወግረው በማይክራፎን ከቀሰቀሱ በኋላ በአንዳንድ አስተዋይ ግለሰቦችና በመንግስት ጥረት መምህሩ
ሊተርፉ ችለዋል፡፡
5.2 የጾም
ሥርዓትና ቀኖናን በማዘበራረቅ፡-
በዘመነ ዮሐንስ
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ታህሳስ 28 ቀን ቢወሰንም በእኛ ሀገረ ስብከት በአንዲት አጥቢያ ቤተ
ክርስቲን ውስጥ በ28ትም በ29ኝም ቀን የሚያከብሩና የሚቀድሱ አጥቢያዎች አሉ፡፡ አሁንም ይህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ለሰላምም
ጠንቅ ስለሆነና ብጹእነታቸውም ሕዝብን ከሕዝብ የሚከፋፍሉበት ስልት ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአጠቃላይ
ብጹእ አቡነ ማርቆስ ለምን ይህን አደረጉ ብለው ሲጠየቁ አንድ ለየዋህን እውነት የመሰለ ነገር ግን ሀሰት የሆነ መደበቂያ ዋሻ አላቸው
ይኸውም ይህን ሁሉ ያደረገኝ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ይላሉ ነገር ግን
ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ ነውና እኛስ ማኅበረ ቅዱሳንን የምናውቃቸው የተዘጋ ቤተ ክርስቲያን ሲያስከፍቱ፣ አብነት
ት/ቤቶችንና መምህራንን ሲደግፉ፣ ጧፍ እጣን ያጡትን አብያተ ክርስቲያናት ሲረዳና ወጣቱ ሃይማኖቱንና ባህሉን እንዳይለቅ ሲያስተማሩ
ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ
ብጹእ አቡነ ማርቆስ ስለእውነት ደፍሮ የሚናገራቸውን የመንግሥት አካላትም ይሁን ነጋዴ ወይም ምእመን ይህ ማኅበረ ቅዱሳን ነው በማለት
ስምና ተቀጽላ ታርጋ ከነግብርአበሮቻቸው ይለጥፉበትና የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍታሉ፤ ሲፈልጉም ኲላዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያንን
በወንዝ ይከፍሉና የሽዋ ማኅበር ነው ይላሉ፡፡ ይህ ስብስብ ማኅበረ ቅዱሳን እንዳልሆነ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው የዛሬውን አቤቱታ
አቅራቢ የመነኮሳት፣ የካህናት፣ የሽማግሌዎችና ሰ/ት/ቤቶች ስብጥርን ያየ ዓይን ራሱ ምስክር ነው፡፡
ስለዚህ እኛ
የምንፈልገው፡-
1. ደም ሳይፋስ አቡነ ማርቆስ በዚህ ሲኖዶስ ጉባኤ ከምሥ/ጎጃም ሃ/ስብከት እንዲነሡልን፡፡
2. የተከበሩ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሀሊ በቃሉና የተከበሩ የሀገረ ስብከቱ
ጸሐፊ አባ ወልደ ትንሣኤ በሕገ ወጥ ደብዳቤ የታገዱበት እንዲነሣላቸው፤
በመጨረሻም
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሰላማችንን እየነሱን እና እያበጣበጡን አቤቱታ ስናቀርብ ከሳሼ ማኅበረ ቅዱሳን ነው በማለት ቅ/ሲኖዶስን እንኳ
ሳይቀር ሲያታልሉ የቆዩ ቢሆንም የምሥ/ጎጃም ዞን አስተዳደር፤የደ/ማርቆስ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የደ/ማ ከተማ ፖሊስ ብፁዕ
አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም የሰላም ስጋት መሆናቸውን በአካልም በጽሑፍም ለቅዱስነታቸው፣ ለብፁዕ ሥራ አስኪያጁ እና ለብፁዕ የቅ/ሲኖዶስ
ዋና ፀሃፊ እውነታውን ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡ አሁንም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘመዶቻቸውን ፤ጥቅመኞችን እና እንባረራለን ብለው የፈሩ
ካህናትን ለአቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ይዘው መጥተዋል፡፡
ስለዚህ ቅዱስ
አባታችን፣ ብፁአን አባቶቻችን ይህን ሁሉ አቤቱታ ሰምታችሁ ብፁዕ አቡነ ማርቆስን ከሃ/ስብከታችን የማታነሡልን ከሆነ በማንኛውም
መንገድ ቤተክርስቲያናችንን የመጠበቅ ግዴታ ያለብን በመሆኑ ይህን ተከትሎ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን የምትወስዱ መሆኑን ለመግለፅ
እንወዳለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ግልባጭ፡-
- ለሰላም ሚንስቴር
አዲስ አበባ
- ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
ባህር ዳር
- ለምስ/ጎጃም ዞን መስተዳድር
- ለደ/ማርቆስ ከተማ አስተዳደር
ደ/ማርቆስ