ጥቅምት ፪/፳፻፲፩ ዓ.ም
ደብረ ማርቆስ፣ ኢትዮጵያ
※※※※※※※※ ※※※※※※※※
በክፍል ፩ ያየናቸውና ሌሎችም ያላየናቸው
ነገሮች ተአምራት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ተአምራት ማንም የሚያደርጋቸው ለማንኛውም የሚደረጉለት አይደሉም፡፡ ሆኖም ግን እነዚህን ተአምራት
የሚያደርጋቸው በሙሉ የተመረጠ ጻድቅ ብቻ ነው ብለን ማሰብ ከጀመርን ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር ቤት ለመውጣት እንገደዳለን፡፡ ስለዚህ በቤቱ ለመጽናት መፍትሔ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ተአምርን (ምልክትን)
አለመሻት ነው፡፡
ተአምርን ለማድረግ አትመኝ ተአምር የሚሠሩትንም ለመመልከት አትሻ፡፡ ምክንያቱም ተአምር የእምነታችን መሠረት
እንዳልሆነ መረዳት ይገባሃልና፡፡ ከሐዋርያት ወገን የነበረው ይሁዳ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ የእርሱ ተአምር ምን እንደነበር
ለማወቅ ካስፈለገህ ደግሞ ሙት ያነሣ እንደነበር ማቴ ፯÷፳፪ ላይ የተጻፈውን አንድምታ ትርጓሜ ተመልከተው፡፡ ተአምርን ማድረግ የመንግሥቱ
ወራሽ እንደማያደርገን አምላካችን በማይታበል ቃሉ ነገሮናል “በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምኽ ትንቢት አልተናገርንምን
በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምኽስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን ይሉኛል የዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እላቸዋለሁ” ይላል
ማቴ ፯÷፳፪-፳፫፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ድንቅ የሚባል እጅህን አፍህ ላይ የሚያስጭን ተአምር ሲሰሩ ብታይ አትደነቅ አትገረም፡፡
እንደዚያ ያለ ድንቅ ተአምር ብታደርግም አትመካ ምክንያቱም መንግሥቱን የሚያወርስህ አምላክ እንጅ የሠራኸው ተአምር አይደለምና፡፡
ድንቅ ተአምር አየሁ እያልክ በዓይንህ ልታያቸው በእጅህ ልትዳስሳቸው ከእነርሳቸው ጋር ፎቶ ልትነሣ ከእግዚአብሔር አብልጠህ ልትመለካታቸው
እነርሱ ተው ያሉህን ልትተው አድርግ ያሉህንም ልታደርግ ትችላለህ፡፡ አንተ በልብህ ውስጥ አንግሠኸቸዋል፡፡ እንደነርሱ ያለ የእግዚአብሔር
ወዳጅ የለም፡፡ እንደእነርሱ ያለ ጸሎተኛ ሰጋጅ መጽዋች የለም፡፡ እንደነርሱ ያለ የፍቅር አባት ሰባኪ አስተማሪ የለም፡፡ አጋንንት
የሚርዱላቸው መናፍስት የሚንቀጠቀጡላቸው እንደነርሱ ያለ ጻድቅ የለም እያልክ ለእነርሱ ያለህን ክብር ትገልጣለህ፡፡ ምናልባትም እነርሱን
የሚሰድብብህን ሰው አንተ ሰይጣን ነህ ልትለውም ትችላለህ፡፡ እነርሱን የምትሳደበው አንተም አጋንንት ስላደረብህ ነው ልትለው ትችላለህ፡፡
እነርሱን ከተሳደብህ እግዚአብሔር ይቀጣሃል ልትለውም ትችላለህ፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ እግዚአብሔር ግን እነዚያን አያውቃቸውም፡፡
አንተ ነህ በግድ እውቅና የሰጠኸቸው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያወዳደርካቸው እንጅ እርሱ የዓለም ፈጣሪ እግዚአብሔር ግን አያውቃቸውም፡፡
አያውቃቸውም ማለት የእርሱ እንዳልሆኑ ያውቃቸዋል ማለት ነው፡፡ ለዚህም በማይታበል ቃሉ ወንጌላችን “በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ
ጌታ ሆይ በስምኽ ትንቢት አልተናገርንምን በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምኽስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን ይሉኛል የዚያን
ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እላቸዋለሁ” ይላል ማቴ ፯÷፳፪-፳፫፡፡ “አላወቅኋችሁም እላቸዋለሁ” አለ እኮ፡፡ ታዲያ እርሱ አላውቃችሁም
ያላቸውን አንተ ማን ሆነህ ነው ከእግዚአብሔር ጋር የምታወዳድራቸው?
ከዚህ እንደምንረዳው ተአምር ከሰይጣንም የሚመጣ እንደሆነ ነው፡፡ በስሙ አጋንንትን ማውጣት እንደ ደቂቀ
አስቂዋ፣ በስሙ ትንቢትን መናገር እንደ በለዓም፣ በስሙ ተአምራትን ማድረግ (ሙት ማንሣት እንደ ይሁዳ) ለመንግሥቱ አያበቃም፡፡
ስለዚህ በፍርድ ቀን አላውቃችሁም እንባላለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ
የእግዚአብሔር የሆነውን የሰይጣን ከሆነው ተአምር ለይተን ማወቅ ስለማንችል በተአምረ ኢየሱስ በተአምረ ማርያም በድርሳኖቻቸው ላይ
ያለውን ተአምረ መላእክት በገድሎቻቸው ላይ ያለውን ተአምረ ቅዱሳን እና ተአምረ ጻድቃን ከተቀበልን ለእኛ እሱ እረፍትን ያስገኘናል፡፡
እኔ እውነተኛ ተአምርን ከሀሰተኛው የመለየት ጸጋ አለኝ፣ ብቃት አለኝ፣ ንጽሕና አለኝ፣ ቅድስና አለኝ፣ ፍጹም ነኝ ወዘተ የምትል
ከሆነ እውነቱን ከሀሰት ለይተህ በዚያ ተጓዝ፡፡ ነገር ግን አንድ በነጭ ሽንኩርት የሚጮኽ ጋኔን አስወጥተውልኛል እያልክ ሻንጣ ተሸካሚ
ሆነህ አትቅር፡፡ አንተ እኮ ከእግዚአብሔር ጋር ኾነህ አልሞከርከውም፡፡ እስኪ ንስሐ ግባ እስኪ ሥጋና ደሙን ተቀበል እስኪ ጸበል
ተጠመቅ እስኪ ሥገድ እስኪ ጸልይ እስኪ ጹም በቃ በዚህ ሁሉ የማይወጣ ጋኔን ካለ ያንጊዜ እግዚአብሔርን ፈትነው፡፡
ዛሬ ላይ ድንቅ ተአምርን የሚያደርግ ጻድቅ የለም ማለቴ አይደለም ነገር ግን የእኛ ብስለት መታየት አለበት፡፡
ከዘመኑ አጥማቂ ነን ባዮች ፈውስን እንሰጣለን እያሉ ገንዘብን ከሚሰበስቡ በስሙ ከሚነግዱ ተኩላዎች ሁሉ ራስን ማራቅ ተገቢ ነው፡፡
ምልክትን የሚሻ ሰው ለመንግሥቱ አይበቃም “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል” ብሏል ጌታችን በማቴ ፲፮÷፬፡፡ ስለዚህ ክፉና
አመንዝራ ትውልድ ተብለን እንዳይፈረድብን ምልክትን አንሻ ተአምርን አንፈልግ፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ተአምራትን በየቀኑ እንደሚያደርግልን
በፍጹም መዘንጋት የለብንም፡፡ እንደእኛ ኃጢአት ሳይሆን እንደ እርሱ ቸርነት ብዙ ነገር ይደረግልናል፡፡ የቅዱሳን የብቃት ጸጋቸው
የነፍሳቸው ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ለልብሳቸው፣ የልብሳቸው ለጥላቸው እየኾነ ድንቅ ነገሮችን አድርገዋል እኮ፡፡ እነርሱ ግን ተአምር
በማድረጋቸው ሰው ቅድስናቸውን እንዳያውቅ ይሸሹ ነበር እንጅ የአጋንንትን ምስክርነት እንጀራ አድርገው ሲኖሩ አላየናቸውም፡፡
ተአምርን የሚሻ ትውልድ ለመጥፋት እያቀደ እንደሆነ መረዳት ይኖርበታል፡፡ “…ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ
እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ” ማቴ ፳፬÷፳፬ ይለናል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን የሰውን ልጅ ሊያስቱበት የሚችሉበትን
ተአምር ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እነሆ ክፉዎች ይነሣሉ፡፡ ከእነዚህ ክፉዎች ራስን መጠበቅ ይገባናል፡፡ ስለዚህ በቤቱ ለመጽናት የምትሻ
ከሆነ ተአምራትን ለማየት ተአምራትንም ለመስራት አትሻ፡፡ መናፍቃንን አስለፍልፈው መለሱ፣ አሕዛብን አስጩኸው መለሱ፣ ብዙ መተቶችን
አባረሩ ወዘተ እያሉ የተመረጡት እንኳ ድንቅ ነገር ተደረገ እያሉ የሚከተሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
የዋሃን ተአምራትን አይተው ተአምር አድራጊውን ሲከተሉ ይውላሉ፡፡ ለምን እንደሚከተሉ ሲጠየቁም የሚመልሱት
የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ተአምራትን ስለሚያደርጉ ነው ብለው ነው፡፡ ሆኖም ግን ተአምራትን ያየ ወይም ያደረገ ሁሉ ለመንግሥቱ
አይበቃም፡፡ ለዚህም ምስክሮቻችን ህዝበ እስራኤላውያን ናቸው፡፡ እነርሱ ባሕረ ኤርትራ ተከፍሎላቸው ተሻግረዋል፡፡ ኋላም መና ከደመና
እየወረደላቸው ሲበሉ ውኃ ከጭንጫ ላይ እየፈለቀላቸው ሲጠጡ ነበር፡፡ ነገር ግን ጣዖት ሲያመልኩ ተመልክተናል፡፡ በነዘር እባብም
ጎን ጎናቸውን ተወግተው እንደሞቱ አይተናል፡፡ የተስፋዪቱንም ምድር ሳያዩ በበረሃ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ ተአምራትን ማየትም ሆነ መሥራት
ለመንግሥቱ የሚያበቃ እንዳልሆነ ልትረዳ ይገባል፡፡ /ኦሪት ዘጸአትን ተመልከት/
በስሙ አጋንንትን አውጥተዋል የሚባሉት አፍን በእጅ ላይ የሚያስጭን ድንቅ ተአምራትን አድርገዋል እየተባሉ
የአጋንንትን ምስክርነት በካሴት እያባዙ የአጋንንት ምስክርነት ሰሚዎች ያደረጉን ሰዎች በመጨረሻው የፍርድ ቀን ላይ አላውቃችሁም
የሚባሉት ናቸው፡፡ ከቤተክርስቲያን ውጭ የሚደረገውን የእብደት ሥራስ እንተወው አሁን አሁን ደግሞ የተያዘው በጸበል ቦታ ተቀምጠው
ከቤተክርስቲያን ግቢ ተቀምጠው ይህን ሰይጣናዊ የምትሐት ተአምራት እያደረጉ ምእመናንን የእነርሱ አምላኪዎች ያደረጉ ብዙዎች ናቸው፡፡
የአንተ ክፍልህ የዚህ ጸበል ነው የሚሉ፣ ባለትዳሮችን የሚያፋቱ፣ ያንተን ስም መጥራት አይቻለንም ያቃጥለናል የሚባልላቸው ሥላሴ፣
ድንግል ማርያም፣ ሚካኤል፣ ገብርኤል ሲሉ ግን የማያቃጥላቸው ራሳቸውን በሰይጣን ምስክርነት ከሥላሴ በላይ ያደረጉ ቤተክርስቲያናችንን
የወንበዴዎች ዋሻ ያደረጉ መተተኞች ብዙዎች ናቸው፡፡ እየሠሩት ያለው ነገር ድራማ ነው፡፡ የትኛው ሰይጣን ነው እውነቱን የሚናገረው?
ሥላሴ ብሎ ሲጠራ ያልተቃጠለ ሰይጣን የአጥማቂውን ስም ለመጥራት ግን የማይችል የሚቃጠለው እንዴት ያለ ትዕቢትና ድፍረት ላይ ኾነው
ነው? ሰይጣንስ እሺ ውሸታም ነውና ስምህ አቃጠለኝ ይበል አጥማቂውና ተመልካቹ እንዴት ይህን ይቀበላል? መረን የለቀቀ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን
የሚዳፈር የአጠማመቅ ሥርዓት ምልክትን የመፈለግ ተአምራትን ለማየት የመጓጓት አባዜ መላ ካልተበጀለት ኹላችንም አመንዝራና ክፉ ትውልድ
ኾነን እንደምንቀር ጥርጥር የለውም፡፡
የክፉነት እና የአመንዝራነት መገለጫው ምልክትን መሻት
ነው፡፡ በዚህ ዘመን በተለይ ወጣቱ ምልክትን ከመሻቱ የተነሣ ለተለያዩ አደጋዎች ሲጋለጥ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔርን ተአምር
አሳየኝ ምልክትን አድርግልኝ እያለ ለራሱ ፈጣሪውን የሚማጸን ክፉ እና አመንዝራ ትውልድ እየተበራከተ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚታረድ
በግ እየተጎተተ ወደ መናፍቃን አዳራሽ እየተነዳ ያለው ምልክትን ማየት ስለሚሻ ነው፡፡ በመናፍቃኑ አዳራሽ ቅዠት የሆነውን የፈውስ
እና የምስክርነት መርኃ ግብር መሳተፍን ይሻል፡፡ በመርኃ ግብሩ መሳተፍ ባይችል እንኳ እነርሱ የሚያደርጉት የፈውስ መርኃ ግብር
እኮ ድንቅ ተአምር ነው ይላል ለራሱ፡፡ ሽባውን ተረተሩ፣ ዕውራንን አበሩ፣ ጎባጣውን አቀኑ፣ ከውስጥ ደዌው ገላገሉ፣ በህክምና አይድንም
የተባለውን በሽታ ፈወሱ ወዘተ እያሉ ለራሳቸው ድንቅ የሚሉትን ተአምራዊ ገቢር ያደንቃሉ መመልከትም ይጀምራሉ፡፡ አንድ ቀንም ራሳቸው
ተአምራቱን ለማረጋገጥ ወደ ምንፍቅናው አዳራሽ ጎራ ይላሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ነው እንግዲህ አብዛኛው ወጣት ለመናፍቃኑ ሰይጣናዊ አሠራር
ሰለባ የሆነው፡፡ አብዛኞች ምልክትን የሚሹ ሰዎች እንደምልክት አድርገው የሚቆጥሩት የፈውስን ድርጊት ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ፈውስ
ምንድን ነው? እስኪ እንመልከተው፡፡
ይቀጥላል
ይቆየን፡፡
※※※※※※※※※※※※※※※※
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ድረ ገጽ፡- http://www.melkamubeyene.blogspot.com
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB
‹‹መጥፎውን ሽሹ መልካሙን ሹ››
ድረ ገጽ፡- http://www.melkamubeyene.blogspot.com
ኢሜይል፡- melkamubeyene60@gmail.com
ፌስቡክ ላይክ ገጽ፡- facebook.com/melkamubeyeneB
No comments:
Post a Comment